ቅድሚያ ስለ ሚሳኤል፤
አገራችን የምትገኘው በጦርነት ውስጥ ነው። የጦር ሜዳው ውሎ ያልፈቀደላቸውና እድል ያላገኙ ዜጎችም በአካል ከጦርነቱ ቀጣና ውጭ የሆኑ ቢመስላቸውም በመንፈሳቸውና በስሜታቸው የባሩድ ሽታ እያጠናቸው መዋሉ የሚካድ አይደለም። የሽታዎቹ መገለጫ በርካታ ስለሆነ በዝርዝር መተንተኑ እጅግም አስፈላጊ መስሎ አልታየንም። የጦርነቱ ውሎ አምሽቶ ውጤቶች ደግሞ እውነትም ይሁኑ ሀሰት ጆሯችንንና ዐይናችንን በቀዳሚነት የሚያጠግቡት በመደበኞቹና በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት መሆኑ በግልጽ የታወቀ ነው።
ተገደን የገባንበት ጦርነት እየተፋፋመ ያለው በዐውደ ውጊያው ቀጣና ውስጥ በሚያፏጩት አረሮች መገለጫነት ብቻ ሳይሆን ከየጓዳችን የሚወነጨፉት ሚሳኤሎችም አሉታዊ ተጽእኗቸውና ውጤታቸው በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ወደ ጉዳታችን ትንተና ዘልቀን ከመጥለቃችን አስቀድሞ ስለ ሚሳኤሎች ምንነትና ባህርያት “በጨዋ ሰው” እውቀትና መረዳት ጥቂት ሃሳቦችን በመፈነጣጠቅ ለማስተዋወቅ እንሞክራለን።
ሚሳኤሎች በዋነኛነት በሁለት ዋና መደቦች ሥር እንደሚቧደኑ ለዋቢነት ያመሳከርናቸው ሰነዶች ያረጋግጡልናል። አንደኛው ምድብ የባሌስቲክ የሚሳኤል ዓይነት ሲሆን ሁለተኛው ምድብ ደግሞ የክሩዝ ሚሳኤል ቤተሰቦች በመባል ይታወቃሉ። የሁለቱ የወል ስምና መታወቂያ ባሌስቲክ ሚሳኤል ነው።
የእነዚህን ሁለት የሚሳኤል ዓይነቶች በቀላሉ ለመረዳት እንዲቻል ቀለል ባሉ ማሳያዎች ባህሪያቸውን እናስተዋውቅ። ባሌስቲክ ሚሳኤል የሮኬት ዓይነት ባህርይ ያለው ነው። ሮኬቱን የሚያስወነጭፈው ኃይል የሚመነጨው በከፍተኛ የእሳት ወላፈን ጉልበት ነው። ይህን መሰሉን የእሳት ነበልባል ሮኬቶች ወደ ሕዋ ሲመጥቁ በቴሌቪዥን መስኮታችን ሳናስተውል የምንቀር አይመስለንም። እንደዚሁም ሁሉ ባሌስቲክ ሚሳኤሎችን አምዘግዝጎ የሚያስወነጭፈው የተለየ ኃይል የተገጠመለትና የአቅሙ ብርታትም ከፍ ያለ ልዩ ማስፈንጠሪያ ነው።
ባሌስቲክ ሚሳኤሎች የሚሸከሟቸው አውዳሚ ተተኳሾች ቦንቦች፣ ኬሚካሎች፣ ባዮሎጂካል ማጥቂያ ዎችና የኒዩኩሌር አረሮች ሊሆኑ ይችላሉ። ሌላው ልዩ መገለጫቸው እንደ ብርድ ልብስ ምድራችንን ቁልቁል የተጫነውን ከባቢ አየር (አትሞስፌር) ጥሰው በመውጣት ከ3000 – 12,000 ኪሎ ሜትር ርቀት በመጓዝ ታርጌታቸውን ማጥቃት መቻላቸው ነው። ይህንን አውዳሚ መሳሪያ የታጠቁት ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሰሜን ኮሪያና ህንድን የመሳሰሉ አገራት ናቸው።
ሰሜን ኮርያና ህንድ ሲቀሩ ሌሎቹ ሦስት ሀገራት በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ ቋሚ አባላት ናቸው። በዚሁ ምክር ቤት ውስጥ እነዚህ ሀገራት “በአወቅሁሽ ናቅሁሽ” መገማመት “ድምጽ እንሰጣለን አንሰጥም” እያሉ “እኛም ቤት እሳት አለ” እስከመባባል የሚደፋፈሩበት ምክንያቱ ይህንን “የቬቶ ፓወር” ጉልበታቸውን በመተማመን ነው።
እ.አ.አ በ2017 ዓ.ም ሰሜን ኮሪያ ድንገት ሳይታሰብ የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ሺንዞ አቤ አሜሪካን ውስጥ በጉብኝት ላይ እያሉ በሙከራ ስም ባለስቲክ ሚሳኤል አምጥቃ ኃይሏን ለማሳየት የሞከረችበትን ታሪክ እናስታውሳለን። ይህም ብቻ ሳይሆን በተከታታይ ዓመታትም ይህንንው የሙከራ ሰበብ እየደረደረች ዓለምን ስታባንን መኖሯ በነጋ በጠባ የሚተረክላት ገድሏ ነው። ሌሎቹ “ኃያላን” ሀገራትም ብዙ ተጠቃሽ መሰል ታሪኮች አላቸው።
ክሩዝ ሚሳኤልም የራሱ ባህርያት እንዳሉት ከላይ የጥቆማ ያህል ጠቅሰን ማለፋችን ይታወሳል። የክሩዝ ኃይል ከጀት ሞተር ጋር ይመሳሰላል። የጄት ማስወንጨፊያው ከኋላ የሚትጎለጎል እሳት ሳይሆን ብርቱው የራስ በራስ ግፊት ጥበብ እንደሆነው ሁሉ የክሩዝ ሚሳኤል ባህርይም እንዲሁ ነው። በዚህን መሰሉ ስሪታቸው ምክንያት ክሩዝ ሚሳኤሎች ምድራችንን የሸፈነውን አትሞስፌር ጥሰው የመውጣት ብርታት ስለሌላቸው የሚበሩት ከአትሞስፌሩ በታች ዝቅ ብለው ነው።
ከባሌስቲኮቹ ጋር ሲነጻጸሩ በቁጥርም ሆነ በዓይነት በርከት ያሉ ተተኳሽ አረሮችን ባይሸከሙም በተጠመደላቸው አንድ ነጠላ ተተኳሽ ግን ታርጌታቸውን የመምታት ብቃታቸው ከፍ ያለ ነው። ሃይፐር ሶኒክ፣ ሱፐር ሶኒክና ሰብ ሶኒክ የተባሉት ስሪቶች ከረቂቅ እስከ መደበኛ የተወሳሰቡ ናቸው።
የባሌስቲክም ሆነ የክሩዝ ሚሳኤሎች ዝርያዎች ይርቀቁም አይርቀቁም ዞሮ ዞሮ ዋነኛ ግባቸው አውዳሚነት ነው። ከመኪና ላይም ይሁን ከመርከብ ላይ ወይንም በፈለገው አካል ላይ ተተክለው የሚነጣጠሩት ጠላታችን ብለው በፈረጁት በሰው ዘርና በአንጡራ ሀብቱ ላይ ነው። የሰው ልጅ አእምሮ ተጠቦባቸው የተፈለሰፉት እነዚህ ተወንጫፊ የሞት መላክተኞች በጦርነት የበላይነትን መጎናጸፍና የኢኮኖሚን ጡንቻ ማሽመድመድ ዋነኛ ተልዕኳቸው ነው። የባለ ሚሳኤሎች ግብ የመጨረሻና የመጀመሪያ ግብ ይሄው ነው። አገራት “እኔ ነኝ ያለ” እየተባባሉ የፉከራ ቀረርቶ የሚያሰሙትም በዚሁ አውዳሚ ትጥቃቸው በመተማመን ነው።
ከየግል ጓዳችን የሚወነጨፉ ሚሳኤሎች፤
አሸባሪው ሕወሓት አገሪቱን ለማድማትና “ቢሆንለትም ለማፈራረስ” በመቃዠት ካሰለፋቸው ጠብመንጃ ነካሽ ሠራዊቱ ቁጥር ቢበልጥ እንጂ በማያንስ ኃይል በየጓው የመሸጋቸው ሚሳኤሎች የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በማምረት ያሰለጠናቸው ምላሶች ናቸው። ከታጠቀው መሳሪያ ይልቅ ውጤት እያስገኘ የሚፎክረውም በዋነኛነት በእነዚሁ የጥፋት ኃይሎቹ ብቃት ተመክቶ ነው። ይህ እኩይ ቡድን በተተኳሽ አረሮች የብዙ ንጹሐን ዜጎችን ሕይወት ሲቀጥፍ በምላስ አደር ፕሮፓጋንዲስቶቹ አማካይነትም ብዙ የማደናገር ሥራ በመስራት የተሳካለት ይመስላል።
ከዘፍጥረት እስከ ዛሬ የነበረውና ያለው የአሸባሪ ሕወሓት ወሳኝ መሠረታዊ ባህርይ ያገጠጠው ውሸታምነቱ፣ የበሬ ወለደ ትርክቱና ህሊና ቢስነቱ መሆናቸው በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው። ጭካኔና ውሸት መለያው የሆነው ይህ የጥፋት ቡድን “ምን ይሉኝ” ያልፈጠረበት የዲያቢሎስ መንትያ ስለሆነ ከዚህ በላይ እርሱን መግለጽ ብዕርን ማታከት ይሆናል።
ከባሌስቲክም ሆነ ከክሩዝ ሚሳኤል ባልተናነሰ አቅም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ አብዛኛው ዜጋ በእርስ በእርሱ ግንኙነትና በማሕበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲታኮስ የሚውለው በምላስ አረር አማካይነት መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው። በተለይም ከአሸባሪው ጋር እየተደረጉ ያሉትን ፍልሚያዎች አስመልክቶ የትኛውም ዜጋ ቢያንስ ከየጓዳው አንድ የምላስ ሚሳኤል ሳያስወነጭፍ እንደማይውል ውጤቱ ምስክር ነው።
እርግጥ ነው የትኛውም ዜጋ በውስጥና በውጭ ጠላቶች ሀገሩ ስትጠቃና ስትደፈር መንገብገቡና መንተክተኩ ያለ ነው። የሀገር ውድቀት የሕዝቡ ውድቀት መሆኑም የታወቀ ነው። ዜጎች በቁጭት፣ በንዴትና በእልህ ስሜታቸውን መግለጻቸው ተፈጥሯዊ ስለሆነ ሙሉ ለሙሉ ስህተት ነው ለማለት ያዳግታል። ችግሩ የሚፈጠረው ከዚህ እውነታ አፈንግጦ ወጣ በማለት ጠላት ለሚያራግበው ፕሮፓጋንዳ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ግብዓት ለመሆን መፍቀዱ ላይ ነው። ዛሬ ዛሬ የዜና ተንታኝ፣ የመፍትሔ አመንጭ፣ የአገራዊ ጉዳዮች ጠቢብና የወታደራዊ ሙያ ኤክስፐርት “ነኝ” የማይል ዜጋ ይኖራል ተብሎ አይገመትም።
ከእያንዳንዱ ጓዳ የሚወነጨፈው “የአሉ” ሚሳኤል በሀገር ውስጥ ጓዳ የተገደበ ብቻም ሳይሆን “የአገሪቱን ሉዓለዊ አትሞስፌር እየጣሰ” ከውጭ ወደ ውስጥ ከውስጥም ወደ ውጭ ሲተኮስ የሚውለው ያለ ገደብ ነው። ፖለቲካው እንደ ጥጥ ይባዘታል። መሪዎች ያለገደብ ይተቻሉ። የጦርነት ማሸነፊያ ስልቱ ይሄና ያ ነው እየተባለ የሚዥጎደጎደው የውርርድና የትችት ዓይነቶች ቀለማቸውና ዓይነታቸው ብዙ ነው።
እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ እኒህን መሰል አስተያየቶች የሚሰጡት ከቅንነት መንጭተው ብቻም ሳይሆን ሌላ የጥፋት ተልዕኮ ኖሯቸው ጭምር መሆኑ ነው። ስለ አንደበት ምንነት በሚገባ ተብራርቶ የተገለጸው በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ስለሆነ እርሱን ማስታወሱ ይበጃል።
“ምላስም እሳት ናት። እነሆ ትንሽ ምላስ በሰውነታችን ውስጥ አመጽ የተሞላበት ዓለም ናት። ሥጋችንን ትበላዋላች፤ ውስጣዊ ሰውነታችንንም ትጠብሰዋለች፤ ከገሃነምም ይልቅ ታቃጥላለች። የአራዊትና የወፎች፣ የተንቀሳቃሾችና በባሕር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ ለሰው ይገዛል፤ ተገዝቷልም። የሰውን ምላስ ግን መግዛት የሚቻለው የለም። ክፉ፣ የሚገድል መርዝም የተመላች ናት።” (ያዕቆብ 3፡6-8)።
ሌላው በአእምሯችን አዛዥነት በጣታችን እየጠነቆልን በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የምናስወንጭፋቸው ያልተገቡ አስተያየቶችና የረከሱ ሃሳቦችም ከሚሳኤል እኩል የማፍረስና የማውደም አቅማቸው ከፍ ያለ ነው። ከተግባራዊ እርምጃ ይልቅ በምላስና በሾለ ጣት የምናስወነጭፋቸው ያልታሰበባቸውም ሆኑ ታስቦባቸው የተቀመሙ “የአንደበት ኒኩሌሮች” የሚያደርሱት የከፋ ጥፋት ምን መልክ እንዳለው እለት በእለት የምናስ ተውለው ነው።
መርዝ ከተሞላ አንደበት የሚቀዱት አሉባልታዎች በአገር አስተዳደርና አስተዳዳሪዎች፣ በጦርነት ተፋላሚ ጀግኖችና አዛዦች፣ በኢኮኖሚው ዘርፍ አመንጭዎችና አድራሾች ዘንድ እያሳደሩ ያለውን ተጽእኖ በአሃዝ ከመቁጠርም ሆነ በግምት ከመተንበይ የዘለለ ስፋትና ብዛት እንዳላቸው ከውጤቱ እያስተዋልን ነው።
እንደማናችንም ዜጎች አንድ ነፍስ ያላቸው መሪዎቻ ችንና ፊት ቀደሞች በሚሊዮኖች ነፍሶች የሻከረ አንደበት ሲብጠለጠሉና ሲዋረዱ መዋላቸው ምስክሩ ውሏችን ራሱ ነው። የብዙ አንደበቶች ትችትና ዘለፋም ለሉዓላዊነት የሚዋደቀውን ጀግና ሠራዊት ወኔ እንደሚያቀጥንና ጉልበት እንደሚያዝል አልገባንም ማለት አይቻልም። ይህንን መሰሉ የአፍ እላፊና የሃሜት ማዳመቂያ ማንን እንደሚጠቅም ይታወቃል።
“እከሌ የተባለ ሁነኛ ሰው እንዳረጋገጠልኝ፣ እንዲህና እንዲያ ካለው ምንጭ እንደሰማሁት፣ እከሌ የተባለ የቅርቤ ሰው እነከሌ ከስብሰባ እንደወጡ ሹክ እንዳለኝ፣ እከሌ ከሚባው ተዓማኒ የዜና ምንጭ እንዳረጋገጥኩት ወዘተ.” በሚሉ “የእመኑኝ ባዮች የውሸት ማስረጃዎች” የሚወነጨፉት የምላስ ሚሳኤሎች ሀገራችንን በበርካታ ዘርፎች ክፉኛ እየጎዱ እንዳሉ ምስክር አያስፈልገውም።
“ከሰደበኝ መልሶ የነገረኝ ገደለኝ” እንዲል ብሂሉ “በአሉና በተባባሉ” ወሬ ተጠምዶ በአስተኳሽነት መዋል ሌሎችን ብቻም ሳይሆን ራስን በራስ ከማቁሰልም መትረፍ አይቻልም። ዛሬ ያልተረጋገጡ ሃሜቶችንና ወሬዎችን ማንፈሱና ማበጠሩ ለጠላቶቻችን ሴራ ማዳበሪያ ይሆኑ ካልሆነ በስተቀር ለሕዝብ የሚፈይዱት አንዳችም ቁም ነገር አይኖራቸውም። ያልተረጋገጡ ወሬዎችንና ሃሜቶችን እየሰፈሩና እየቸረቸሩ መዋል ውሎ አድሮ ለህሊና ጸጸትና ለስሜት ስብራት አሳልፎ እንደሚሰጥም ልንገነዘብ ይገባል።
ምላስ አጥንት የላትም፤ አጥንትን ለመስበር ግን ብርቱ አቅም አላት። ባልተገባ የወሬ ሚሳኤል ጥቃት የሚጨቀየው እጃችን ብቻም ሳይሆን ነፍሳችን ጭምር ናት። እውነትን መሠረት ያላደረገና ከገንቢ ሂስ የራቀ ወሬና ሃሜት፣ ስድብና ትችት ክንፍ አቆጥቁጦ በፈጣን በረራ በመምዘግዘግ የሚከንፈውና ታርጌቱን የሚመታው ከሚሳኤል አረር በፈጠነ ቅጽበት መሆኑን አበክረን ልንገነዘብ ይገባል።
መፍትሔው አንድና አንድ ነው። በየጓዳችን የምንጠምደውን ሚሳኤል እናምክንና ለእውነት አንቁም። ባልተረጋገጠ የወሬ ሚሳኤል ተኩስ አደጋ ላይ ወድቀን ሌሎችንም አደጋ ላይ እንዲወድቁ ምክንያት ከመሆንም ራሳችንን እንግዛ። የነገረ ሚሳኤል ማእከላዊ መልዕክት ይሄው ነው። ሰላም ይሁን!
ጌታቸው በለጠ /ዳግላስ ጴጥሮስ)
gechoseni@gmail.com
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2014