የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በፍጥነትና በጥራት አስገንብቶ ለአገልግሎት ማዋል አለመቻል ተደጋግሞ የሚነሳ ችግር ነው፡፡ በተለያዩ ክልሎች በመገንባት ላይ የሚገኙ ስታዲየሞች በእቅድ ከተያዘላቸው የማጠናቀቂያ ጊዜ እጥፍ ቆይተውም መጠናቀቅ አለመቻላቸው የዚህ ችግር አንዱ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ከእነዚህ ስታዲየሞች መካከል አንዱ የባህርዳር ስታዲየም ሲሆን፤ ከሚጠበቀው በታች በሆነ አፈጻጸም ለረጅም ዓመታት ሳይጠናቀቅ ቆይቷል፡፡ የባህርዳር ስታድየም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ በመገንባት ላይ ካሉ ሌሎች ስታዲየሞች አንጻር በተሻለ ደረጃ ላይ በመገኘቱ ዓለምአቀፍ ውድድሮችን ጭምር በገደብ ሲያስተናግድ የቆየ ብቸኛው ስታድየም መሆኑ ይታወቃል፡፡
ይሁን እንጂ የአፍሪካን እግር ኳስ በበላይነት የሚመራው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ስታዲየሙ መሻሻል ይገባቸዋል ተብሎ የተሰጠውን ግብረመልሶች ተቀብሎ ወደ ተግባር ከመግባት አንጻር ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይቷል በሚል እንዲታገድ አድርጓል፡፡ ካፍ በአባል አገራቱ የሚገነቡ ስታዲየሞችን ገምግሞ ለአህጉር አቀፍ ጨዋታዎች ብቁ መሆናቸውን ያረጋግጣል፡፡ በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ እየተገነቡ ያሉ ስታዲየሞችን በባለሙያዎቹ ምልከታ በማድረግ ችግሮቹን መለየቱ የሚታወስ ነው፡፡ ይሁንና በችግሮቹ ላይ መስራትና ለውጥ በማሳየት ረገድ እንቅስቃሴው ደካማ በመሆኑ አገርን ዋጋ ሊያስከፍሉ የሚችሉ እገዳዎችን መቀበል የግድ ሆኗል፡፡
ኢትዮጵያ ለ6ኛ ጊዜ የተካሄደውን ቻን 2020 ለማስተናገድ እድሉን ብታገኝም በዝግጅት ማነስ መቀማቷ የሚታወስ ነው፡፡ በወቅቱ ውድድር የሚካሄድባቸው ስታዲየሞች ብቁ አለመሆናቸውና ሊያሟሉ የሚገባቸው ጉዳዮችም በግልጽ የተመላከቱበት ነበር፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ የባህርዳር ስታዲየም ብቻ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን እንዲያስተናግድ በሂደትም ያልተሟሉ ጉዳዮ ላይ እንዲሰራከካፍ ማሳሰቢያ ደርሶት ነበር፡፡
በእርግጥ በተለያዩ ጊዜያት ክልሎች ስታዲየሞቹን ለማጠናቀቅ የአቅም ውስንነት እንዳለባቸውና በፌዴራል ደረጃ እገዛ እንዲደረግላቸው ጠይቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በተመሳሳይ ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑንና በስታዲየሞቹ ላይ መስራት ካልተቻለ እገዳውን ማስተናገድ የግድ እንደሚሆንም ለሚመለከታቸው አካላት ሲያሳስብ ቆይቷል፡፡ ይሁንና በተባለው መሰረት ባለመሄድ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ውድድሮችን ማስተናገድ እንዳትችል ተከልክላለች፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ በርካታ ጉዳዮች እየተነሱ ሲሆን፤ የአማራ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮም እገዳውን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በዚህም ቢሮው የተላለፈው ውሳኔ ወቅቱን ያላገናዘበ፣ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን ግምት ውስጥ ያላስገባ መሆኑን ጠቁሞ፤ ቀሪ ስራዎቹም በፌዴራል ደረጃ እገዛ የሚያስፈልጋቸው መሆኑን ገልጿል፡፡ ካፍ ለእገዳው በምክንያትነት ካነሳቸው አስተያየቶች መካከል የተጫዋቾች መልበሻ ክፍል ግብዓቶችን ማሟላት፣ የክብር እንግዶች መቀመጫ ስፍራና የጣሪያ ስራ፣ የሚድያ ክፍል ማዘጋጀት፣ የተጠባባቂ ተጫዋቾች መቀመጫ እንዲሁም የመጫወቻ ሜዳው ሳር እንዲቀየር የሰጠው አስተያየት አግባብነት የሌላቸው መሆኑን በቢሮው የስፖርት ፋሲሊቲ ዳይሬክተር አቶ ባንታምላክ ሙላት አብራርተዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም ስታድየሙን ጣራ ማልበስ፣ በምሽት ጨዋታዎችን ማካሄድ የሚያስችል የመብራት ስራ፣ የተመልካቾች መቀመጫ ወንበር እና የሥርዓተ ድምጽ ግብዓቶችን ማሟላት ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ አብራርተዋል፡፡ እነዚህን ግብዓቶች ማሟላት የክልሉ መንግስት አሁን ካለበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ከአቅሙ በላይ ስለሆኑና የፌዴራል መንግስትን ድጋፍ የሚጠይቁ በመሆናቸው በክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አማካኝነት ምክክር እየተደረገ መሆኑንም አስረድተዋል።
የባህርዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ለበርካታ ዓመታትየተለያዩ ኢንተርናሽናል ጨዋታዎችን በማስተናገድ ለአገር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ በመሆኑ ፋይዳው አገራዊ መሆኑን በክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ ካሳ ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ስታዲየሙ አሁን ለገጠመው ችግር መፍትሄ ከፌዴራል መንግስት ድጋፍ እንደሚፈልግ ተናግረዋል።
የክልሉ መንግስት በችግር ውስጥ ሆኖም አቅሙን መሠረት ያደረገ ከፍተኛ በጀት በመመደብ ስታዲየሙን በማስገንባት የወጣቶችን ጥያቄ ለመመለስ ጥረት እያደረገ እንደሚገኘ የተናገሩት የቢሮው ኃላፊ፣ ከተሰጡት የማስተካከያ ነጥቦች መካከል በክልሉ አቅም ሊሸፈኑ የሚችሉትን ለመስራት የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የማስፈጸሚያ እቅድ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም ስታዲየሙ የሚያስፈልጉትን ግብአቶች በማሟላት ዓለም አቀፍ ደረጃውን አሟልቶ ውድድር ወደ ማስተናገድ እንዲመለስ የሁሉንም አካላት ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑ ታውቆ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ከክልሉ መንግሥት ጎን እንዲቆሙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17/2014