የዛሬው የፍረዱኝ አምዳችን በአዲስ ተስፋ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ በሆኑት አቶ ፍቃደ አትክልቲ እና በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ ያስቃኘናል፡፡ በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 አስተዳደር የንግድና ኢንዱስትሪ ልማት አስተዳደር ጽሕፈት ቤት የአዲስ ተስፋ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን አቶ ፍቃደ አትክልቲ የንግድ ፈቃድ የለህም በሚል ከ2006 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም የድርጅታቸውን ሼድ በማሸግ እና ከ2011 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም ደግሞ በድርጅቱ ውስጥ ታሽገው የነበሩ ቁሳቁሶችን ለማስረከብ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የተነሳ የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ እና ቤተሰባቸው እጅግ ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማኅበራዊ እና ስነልቦናዊ ችግር መዳረጋቸውን አቶ ፈቃደ ይናገራሉ ፡፡ «ይህን የተፈጸመብኝን ግፍ እና መከራ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት አይቶ ይፍረደኝ» ሲሉ ለአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል አቤት ብለዋል ፡፡ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ስለጉዳዩ የሚመለከታቸውን አካላት እና የሰነድ ማስረጃዎችን በመመርመር የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመፍረድ ይመቸው ዘንድ ከምርመራው የተገኙ መረጃዎችን እነሆ ብለናል፡፡
እንደ አቶ ፍቃደ ገለጻ እና የሰነድ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት፤ አቶ ፍቃደ አታክልቲ በቀድሞው አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 በአሁኑ ደግሞ በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 ነዋሪ ናቸው።አቶ ፍቃደ በ2004 ዓ.ም በንግድ ምዝገባ ፈቃድ አሰጣጥ አዋጅ ቁጥር 686/2002 አንቀጽ 31 መሰረት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስድስት የቤት ቁጥር 1615 በኮንስትራክሽን ዘርፍ የንግድ ፈቃድ በማውጣት አዲስ ተስፋ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የተባለ ድርጅት ይመሰርታሉ።ድርጅቱም የሥራ አስኪያጁን ቤተሰብ በኢኮኖሚ ከመደገፍ ባለፈ ለበርካታ ሰዎች የስራ እድል የፈጠረ እና በአገሪቱ ያለውን የሥራ አጥነት ቁጥር በመቀነስ ረገድ አገራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ድርጅት ነበር።ማኅበሩ ሥራ ሲጀምር ለሥራ ይጠቀምበት የነበረው የቤት ቁጥር 1615 አቶ ፍቃደ በራሳቸው ሙሉ ወጭ የገነቡት ቢሆንም ቤቱን የገነቡበት ባዶ ቦታ ግን ከአከራዮች በኪራይ የተገኘ ነው ።
በ9/12/2005 ዓ.ም አዲስ ተስፋ ኮንስትራክሽን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ይባል የነበረው ድርጅት ወደ ፍቃደ እና ትርሲት የብረታ ብረት ሥራ የኅብረት ሽርክና ማህበር ተቀየረ የሚሉት አቶ ፍቃደ ፤ በዚሁ ዓመት ፍቃደ እና ትርሲት የብረታ ብረት ስራ የኅብረት ሽርክና ማኅበር በተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ቁጥር 285/1994 አንቀጽ 16 ወይም አንቀጽ 15 መሰረት በተጨማሪ እሴት ታክስ ቁጥር 6309200816 የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢ እንደነበር ያስረ ዳሉ።
ፍቃደ እና ትርሲት የብረታ ብረት ሥራ የኅብረት ሽርክና ማኅበር በተመሰረተ በአጭር ቀናት ውስጥ አንቱታን ያተረፈ ሥራዎችን ያከናወነ ድርጅት ነው የሚሉት አቶ ፍቃደ ፤ የበላይ ዘለቀ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትን የተማሪዎች ዴስክ ፣ የብርሃን ኢትዮጵያ ትምህርት ቤት ሼልፎችን ፣ አርምቼር ወንበሮች ፣ የመምህራን ወንበሮችን እና ጠረጴዛዎችን ፣ ለመስከረም ትምህርት ቤት ሼልፎችን እና የላይብራሪ ወንበሮች እና ጠረጴዛዎችን ፣ ብሔረ ኢትዮጵያ የመምህራን ወንበሮች እና ጠረጴዛዎች፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ጂ+ 3 የወጣት ማዕከል በር እና መስኮት፣ በአራዳ ክፍለ ከተማ የወረዳ 06 ጂ+ 3 የወጣት ማዕከል በር እና መስኮት፣ የፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ልማት ጽሕፈት ቤት የፓርቲሽን ፣ የአራዳ ክፍለ ከተማ የገቢዎች ቢሮ የወንበሮች ፣ የሴቶች እና ወጣቶች ቢሮ የፓርቲሽን ሥራዎችን በመሥራት የአራዳ ክፍለ ከተማ የመንግሥት ኮንስትራክሽን ዋና የሥራ ሂደት ማኅበሩ የተሰጡትን ሥራዎች ለግንባታው በተሰጣቸው ጊዜ ገደብ እና ዲዛይን መሠረት አጠናቆ በማቅረቡ የመልካም ሥራ አፈጻጸም የእውቅና ደብዳቤ ማግኘታቸውን አቤቱታ አቅራቢው ይናጋራሉ።የሰነድ ማስረጃዎችም ያመለክታሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2005 ዓ.ም መጨረሻ አካባቢ ለአስተዳደራዊ ጉዳዮች እንዲመች በሚል ከአራዳ ክፍለ ከተማ በወረዳ 06 ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ቦታዎች ወደ የካ ክፍለ ከተማ እንዲሸጋሸጉ ተደረገ። በሽግሽጉም በአራዳ ክፍለ ከተማ ይገኝ የነበረው የአቶ ፍቃደ ድርጅት ወደ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 እንዲዘዋወር ተደረገ።የተደረገው የማሸጋሸግ ሥራ አቶ ፍቃደን እና ቤተሰቦቹን እጅግ አስከፊ ለሆነ ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊ እና ስነልቦናዊ ችግር የዳረገ ጥቁር የሕይወት አጋጣሚ እንደሆነ አቶ ፍቃደ ይናገራሉ ።
የሽርክና ማኅበሩ የሥራ ቦታ ከአራዳ ወደ የካ ክፍለ ከተማ መሸጋሸጉን ተከትሎ አዲስ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት መገደዳቸውን የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ይናገራሉ። የሽርክና ማኅበሩ ከየካ ክፍለ ከተማ አዲስ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት በመጀመሪያ ደረጃ ከአራዳ ክፍለ ከተማ አውጥቶት የነበረውን የንግድ ፈቃድ መመለስ ይጠበቅባቸዋል። የንግድ ፈቃዱን ለመመለስ ከሚወስደው ጊዜ በተጨማሪ አዲስ ንግድ ፈቃድ ለማግኘት የተለያዩ ጊዜ የሚጠይቁ ሂደቶች እና አሠራሮች በመኖራቸው ፍቃደ እና ትርሲት የብረታ ብረት ስራ የኅብረት ሽርክና ማኅበር አዲስ የንግድ ፈቃድ ከየካ ክፍለ ከተማ እስከሚሰጣቸው ድረስ ሥራቸውን ሳያቋርጡ መስራት እንዲችሉ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን ድርጅታቸውን ኦዲት እንዲያደርግላቸው ይጠይቃሉ። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሽርክና ማኅበሩን ኦዲት ይደረግልኝ ጥያቄ ተቀብሎ ኦዲት ማድረግ ይጀምራል። ኦዲት እያደረገ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን ለየካ ክፍለ ከተማ ለሽርክና ማኅበሩ አዲስ የንግድ ፈቃድ እንዲሰጠው የሚያስችል መረጃ እንዲጽፍላቸው መጠየቃቸውን አቶ ፍቃደ ይናገራሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን በቁጥር 85570330816 በቀን 29/12/2005 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ፍቃደ እና ትርሲት የብረታ ብረት ሥራ የኅብረት ሽርክና ማኅበር ወደ የካ ክፍለ ከተማ የመሥሪያ ቦታቸው ከመሸጋሸጉ በፊት በአራዳ ከፍለ ከተማ ያወጡት የንግድ ፈቃድ እንደነበር ፤ የንግድ ፈቃዱም እስከ የካቲት 25 ቀን 2006 ዓ.ም እንደሚያገለግል እና ደብዳቤው እስከተጻፈበት ጊዜ ድረስ ሕጋዊ ፈቃድ እንዳላቸው “ለሚመለከተው ሁሉ” የሚል ደብዳቤ የተሰጣቸው መሆኑን አቶ ፍቃደ ያስረዳሉ ።የሰነድ ማስረጃዎችም ይህንኑ ይጠቁማሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ በአራዳ ክፍለ ከተማ የአወጡትን የንግድ ፈቃድ በመመለስ ክሊራንስ እንዲሰጣቸው ለኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን አራዳ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ በቀን 10/12/2005 ዓ.ም መጠየቃቸውን ሰነዶች ያመላክታሉ።የሥራ አስኪያጁን ማመልከቻ ተከትሎ የአራዳ ክፍለ ከተማ ቅርንጫፍ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የንግድ ፈቃዱን መዝጋቱን ከሰነዶች የተገኙ ማስረጃዎች ያሳያሉ።
ለየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ፤ አቶ ፍቃደ ሕጋዊ ግብር ከፋይ እንደሆኑ እና በአዲስ አበባ ገቢዎች እና ጉምሩክ ቢሮ ድርጅታቸው ኦዲት ላይ እንደሚገኝ ለሚመለከተው አካል ሁሉ እስከ ስድስተኛው ወር 2006 ዓ.ም ድረስ ሥራቸውን መሥራት እንደሚችሉ የሚጠቀስ ደብዳቤ ቢጻፍላቸውም በየካ ክፍለ ከተማ የወረዳ 04 የንግድ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት አመራሮች በግብር ኃይል እየተደራጁ ወደ ድርጅቱ መሥሪያ ቤት በመሄድ የድርጅቱን ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃደን የንግድ ፈቃድህን አምጣ እያሉ ያስቸግሯቸው እንደነበር አቶ ፍቃደ ይገልጻሉ ።
በግብረ ኃይል እየተሰባሰቡ የሥራ ቦታቸው ድረስ እየመጡ ከማስቸገር ባለፈ ከየካ ከፍለ ከተማ ቁጥር በሌለው በቀን 12 የሚል ነገር ግን ወሩ በግልጽ የማይታይ እና በተሰረዘ በተደለዘ በ2006 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ የማኅበሩን ሥራ አስኪያጅ “የንግድ ፈቃድ የሌለዎት በመሆኑ በ24 ሰዓት የንግድ ፈቃድ እንዲያወጡ እንገልጻለን” የሚል ደብዳቤ እንደተሰጡ ከአቶ ፍቃደ እና ከሰነዶች ያገኘናቸው ማስረጃዎች ያመላክታሉ ።ይህን ተከትሎ «ከአንድ ሁለት ጊዜ ፤ ከሁለት ሶስት ጊዜ ከግብረ ኃይል ጋር እየተመላለሳችሁ ኦዲቱን ቶሎ ጨርስ ስትሉኝ ከርማችሁ እንዴት አሁን ፍቃድ የለህም ትሉኛላችሁ? » ብለው የወረዳ 04 አመራሮችን መጠየቃቸውን ነገር ግን የወረዳው አመራሮች ለጥያቄአቸው ምንም ማብራሪያ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልነበሩ አቤቱታ አቅራቢው ያስረዳሉ።
ይህን ተከትሎ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተ ዳደር ገቢዎች እና ጉምሩክ ባለስልጣን በቁጥር 85570330816 በቀን 29/12/2005ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ድርጅታቸው በኦዲት ላይ እንዳለ የሚገልጸውን እና ከአራዳ ክፍለ ከተማ ደግሞ የንግድ ፈቃዳቸውን የዘጉበትን(የመለሱበትን) እና ክሊራንስ የወሰዱበትን የሚገልጸውን ደብዳቤ ለየካ ከፍለ ከተማ ለወረዳ 04 ማስገባታቸውን አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ። ሰነዶቹን በየካ ክፍለ ከተማ ለወረዳ 04 በሚያስረክቡበት ወቅት የወረዳ 04 የንግድ አስተዳደር ይህ ፈቃድ እንዳለህ አናውቅም ነበር ብለው እንዳፌዙባቸው አቶ ፍቃደ ይናገራሉ ።
ይህ በእንዲህ እያለ በ17/10/2006 ዓ.ም በየካ ክፍለ ከተማ ፍትሕ ጽህፈት ቤት ማህተም የሥራ ቦታቸው መታሸጉን ከሰነዶች ያገኘናቸው ማስረጃዎች ያመለክታሉ። እንደ አቶ ፍቃደ ገለጻ ፤ እንዳይደርስ የለም የኦዲት መጠናቀቂያ ጊዜ ደረሰ።የኦዲቱ ጊዜ በመጠናቀቁ የንግድ ፈቃድ ለማውጣት በር ተከፈተላቸው ። ሕጋዊ መስመሩን ተከትለው የንግድ ፈቃድ በየካ ከፍለ ከተማ ያወጣሉ። ወረዳው የጠየቃቸውን ንግድ ፈቃድ በመጨረስ የመሥሪያ ቦታቸውን እንዲከፍቱላቸው የወረዳ 04ን ንግድ ቢሮን ይጠይቃሉ ።«ወረዳውም ቤቱን የሚከፍትልህ ክፍለ ከተማው እንጂ እኛ አይደለንም» የሚል ምላሽ እንደሰጧቸው አቤቱታ አቅራቢው ያስረዳሉ ።ይህን ተከትሎ አቤቱታ አቅራቢውም « እናንተ የዘጋችሁትን ቤት ማን ይክፈት ?» ሲሉ እንደጠየቁ እና ወረዳውም የታሸገውን ቤት ሊከፍተው የሚችለው የክፍለ ከተማ ንግድ አስተዳደር ጽሕፈት ቤት እንደሆነ በመጠቆም እንዳሰናበቷቸው ይገልጻሉ።
ወረዳው የሰጣቸውን ጥቆማ ይዘው የመሥሪያ ቦታቸውን ለማስከፈት ወደ ክፍለ ከተማ መሄዳቸውን የሚናገሩት አቶ ፍቃደ ፤ በክፍለ ከተማው ግን ጥያቄአቸውን ሊያስተናግድ የሚችል ሰው ማጣታቸውን ያስረዳሉ።
ጥያቄአቸው ምላሽ ሳያገኝ በመቅረቱ እና የመሥሪያ ቦታቸው ከአንድ አመት በላይ በመዘጋቱ ንብረታቸውም ሆነ የቤተሰባቸው ሕይወት በመሰቃቀሉ እንደገና ወደ ወረዳ 4 አስተዳደር ኃላፊ በመምጣት እየተፈጸመባቸው ያለውን ግፍ አልቅሰው እንደነገሩት ይገልጻሉ። ይህን ተከትሎ የወረዳው አስተዳደር ወደ የካ ክፍለ ከተማ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ይልኳቸዋል። አቤቱታ አቅራቢውም የካ ክፍለ ከተማ ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ፊት በቀረበቡት ወቅት ከኃላፊው ያልጠበቁት ነገር እንደጠበቃቸው ይናገራሉ።የንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊው አቤቱታ አቅራቢውን ፖለቲከኛ እንደሆኑ እና የኢህዴግን መንግሥትን እንደሚቃወሙ ፤ እንዲሁም ክፍለ ከተማው አቤቱታ አቅራቢውን ሽብርተኛ አደርጎ እንደሚቆጥራቸው መነገራቸውን የሚጠቁመት አቶ ፍቃደ ፤ እርሳቸውም በተባለው የፖለቲካ ሥራ ውስጥ እንደሌሉበት እና ኢህአዴግን በሽብርተኝነት ለመጣል የሚባለው ነገር ፈጽሞ እንደማይመለከታቸው ለክፍለ ከተማው ንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊ ማስረዳታቸውን ይገልጻሉ።
ይሁን እንጂ የንግድ እና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊው አቤቱታ አቅራቢውን ኢህአዴግን እንደሚቃወም እና የኢህዴግን መንግሥት ለመጣል ከሽብርተኞች ጋር እንደሚሰሩ እንደተነገራቸው ለአቤቱታ አቅራቢው እንደነገሯቸው አቤቱታ አቅራቢው ያስረዳሉ።አቤቱታ አቅራቢውም በድጋሚ ኃላፊው የተነገራቸው የሐሰት ውንጀላ መሆኑን ጠቁመው ችግራቸውን በአጭር ጊዜ እንዲፈቱላቸው ይጠይቋቸዋል።ኃላፊውም ችግሩን ለመፍታት በሌላ ቀን ተመልሰው እንዲመጡ ይቀጥሯቸዋል።አቤቱታ አቅራቢውም በተቀጠሩበት ቀን የተገኘ ምላሽ የለም ።አሁንም ለሌላ ጊዜ ይቀጥሯቸዋል ምላሽ የለም ።እንዲህ እየሆነ በቀጠሮ ምላሽ ሳያገኙ ለበርካታ ጊዜ መንገላታታቸውን የሚናገሩት አቤቱታ አቅራቢው ፤ በመጨረሻም ምላሽ ለማግኘት ወደ የካ ክፍለ ከተማ ቅሬታ ሰሚ መሄዳቸውን ያስረዳሉ ።
እንደ አቶ ፍቃደ ገለጻ ፤ የክፍለ ከተማው ቅሬታ ሰሚ ስለጉዳዩ ለመረዳት ከአቤቱታ አቅራቢው ጋር የተያያዙ ዶክመንቶችን መመርመር ይጀምራሉ።ነገር ግን አቤቱታ አቅራቢው ከቅሬታ ሰሚው ምላሽ ሳያገኙ የፌደራል አቃቤ ህግ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቦሌ ምድብ ችሎት አቶ ፍቃደን ከሰሰ።የክሱ ጭብጥም በ2002 ዓ.ም በወጣው የንግድ ምዝገባ እና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 አንቀፅ 31/1 እና 60/1 የተመለከተውን በመተላለፍ ተከሳሽ የጸና ስራ ፈቃድ ሳይኖረው ሰኔ 17 ቀን 2006 ዓ.ም ከቀኑ 8፡ 00 ሰዓት በየካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04 ክልል ውስጥ ልዩ ቦታው 6 ኪሎ ያሬድ ሙዚቃ ቤት ጎን በቤት ቁጥር 1615 ውስጥ በመከነ እና ባልታደሰ ንግድ ፈቃድ የብረታ ብረት ስራ ላይ ተሰማርቶ እየሰራ በመገኘቱ በፈጸመው ባልፀና ወይም ባልታደሰ ንግድ ሥራ ፈቃድ መነገድ ወንጀል በሚል በቀን 20/4/2008 ተከሰሱ፡፡
ይህን ተከትሎ አቃቤ ሕጉ በአስቸኳይ በአምስት ቀን ውስጥ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ጠየቀ የሚሉት አቶ ፍቃደ፤ በአምስተኛውም ቀን የካ ፈረንሳይ ጣቢያ ታስረው መቅረባቸውን አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ ።ይህ በእንዲህ እንዳለ አቃቤ ሕጉ አቶ ፍቃደ እንደታሰሩ እንዲቆዩ እና ተጨማሪ መረጃዎችን ለማቅረብ ሰባት ቀን ቀጠሮ እንዲሰጠው መጠየቁን አቤቱታ አቅራቢው ያስረዳሉ ።ነገር ግን ፍርድ ቤቱ የአቃቤ ሕጉን ጥያቄ ውድቅ በማድረግ የአምስት ሺህ ብር በዋስትና ከፍለው ሳይታሰሩ እንዲከራከሩ ወሰነ ።ውሳኔውን ተከትሎ አቶ ፍቃደ አምስት ሺህ ብር አሲዘው ከእስር ይወጣሉ።ነገር ግን የከሰሳቸው አቃቤ ሕግ ምክንያቱ በውል ባልታወቀ ምክንያት የክሱን ጉዳይ በመተው ጸጥ እረጭ ማለቱን አቤቱታ አቅራቢው ይገልጻሉ፡፡
እንደ አቶ ፍቃደ ገለጻ ፤ የአቃቤ ሕጉ እና የፍርድ ቤቱ ዝምታ ለአንድ ዓመት ያህል ቀጠለ።ነገር ግን የመሥሪያ ቦታቸው የታሸገው አቶ ፈቃደ ፍርድ ቤቱ የያዘው ጉዳይ ምን ላይ እንደደረሰ ይጠይቃሉ።የፍርድ ቤቱም ጉዳይ እንገደና መታየት ጀመረ፡፡በመጨረሻም ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቦሌ ምድብ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 160757 ሲያከራክር ቆይቶ በቀን 02/10/09 ባስተላለፈው ውሳኔ መሠረት ተከሳሽ አቶ ፍቃደ አታክልቲ በነጻ ይሰናበታሉ።ነገር ግን ወረዳው በሠራው ስህተት የአቶ ፍቃደን ድርጅት እና ቤተሰቦቹን ዋጋ ማስከፈሉ ሳያሳፍረው እና ሳያሸማቅቀው በፍርድ ቤት ነጻ የተባሉትን አቤቱታ አቅራቢ የሥራ ቦታቸውን የሚከፍትላቸው ያጣሉ።ቀንን ቀን እየወለደው የመሥሪያ እቃቸውን እንደያዘ በወረዳ 4 የታሸገው ቤት ሳይከፈት 2011ዓ.ም ይደርሳል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአቶ ፍቃደ የመሥሪያ ቦታ የተከራዩት እና በእራሳቸው ወጭ ሼድ የሰሩበት ስለነበር ባዶ ቦታውን ያከራያቸው ሰው ቦታዬን ይልቀቁልኝ ሲል ልደታ ፍርድ ቤት መክሰሳቸውን ሰነዶች ያመለክታሉ ።የልደታ ፍርድ ቤትም አቶ ፍቃደ በተከራዩት ባዶ ቦታ ለማኅበሩ ሥራ ማከናወኛ የገነቡትን ቤት እንዲያፈርሱ እና በመሥሪያ ቦታቸው ውስጥ የሚገኝን ማንኛውንም ንብረት በማንሳት ለአከራይ ቦታቸውን እንዲለቁ ውሳኔ ተላለፈባቸው ። ይህን ውሳኔ ተከትሎ በየካ ከፍለ ከተማ የወረዳ 04 አመራሮች የፍርድ ቤት ውሳኔ ይከበር በማለት የአቶ ፍቃደ ድርጅት ባዶ ቦታን በመከራየት የገነቡትን ቤት አፍርስ ለማለት የቀደማቸው አልነበረም ሲሉ አቶ ፍቃደ ይናገራሉ ።
እንደ አቶ ፍቃደ ገለጻ የቦሌ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በነጻ ቢያሰናብተኝም ፤ የልደታው ፍርድ ቤት ቤቱን እንዳነሳ ውሳኔ ቢያስተላልፍም የታሸገውን ቤት ከፍቶ የእቃ ርክክብ የሚያደርግ ሰው ጠፋ።በተስፋ መቁረጥ ውስጥ ሆነው የሥራ ቦታቸው እንዲከፈትላቸው በተደጋጋሚ ወረዳ 4 ጠይቀው ምላሽ ያጡት አቶ ፍቃደ ለወረዳ 4 ቅሬታ ሰሚ ቦታቸውን ተከፍቶ ወረዳው ንብረታቸውን እንዲያስረክባቸው ይጠይቃሉ። የወረዳው ቅሬታ ሰሚም አቤቱታ አቅራቢው በ2009 ዓ.ም በፍርድ ቤት ውሳኔ ነጻ ተብለው ሳለ ስለምን ንብረታቸውን ማስረከብ ያልተቻለበትን ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ ምክንያት በአምስት ቀናት ውስጥ እንዲያሳውቅ ሲል ለወረዳ 04 ንግድ ጽሕፈት ቤት በቁጥር የካ/ቀአ/0123/2011 በቀን 18/1/2011 ዓ.ም በተጻፈ ደብዳቤ ይጠይቃል።
ነገር ግን የወረዳው ቅሬታ ሰሚ የላከውን ደብዳቤ የንግድ ጽሕፈት ቤቱ በአምስት ቀን ውስጥ ምላሽ ባለመስጠቱ የወረዳው ቅሬታ ሰሚ በቁጥር የካ/ቅአ0168/2011 በቀን 1/2/2011ዓ.ም ለሁለተኛ ጊዜ በተጻፈ ደብዳቤ የታሸገውን ቤት ያልከፈቱበትን ምክንያት እንዲያሳውቅ ወረዳውን ጠየቀ።ይህን ተከትሎ የወረዳው ንግድ ጽሕፈት ቤት በሕገወጥ መልኩ ግብር ሳይከፍሉ ሲሰሩ በመያዝዎ ቤትዎ መታሸጉ ይታወቃል።ስለሆነም በ19/2/2011ዓ.ም ቤቱን የምንከፍት መሆኑን እናሳውቃለን ሲል በቁጥር 80368 በቀን 15/2011ዓ.ም የተጻፈ ደብዳቤ ለአቶ ፍቃዱ ይደርሳቸዋል። አቶ ፍቃዱም በዚህ ደብዳቤ እንደተገለጸው እኔ በሕገወጥ መንገድ ስሰራ አልተያዝኩም።ነጻ መሆኔን ፍርድ ቤት አረጋግጧል ።ነገር ግን እናንተ ስለምን ከፍርድ ቤት ውሳኔ በኋላ ለሁለት ዓመት ቤቱን አሽጋችሁ ልታቆዩ ቻላችሁ? ለዚህ ምክንያት እፈልጋለሁ።ምክንያቱም በእናንት ስህተት እኔ እና ቤተሰቤ ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንደቆዩ ማስረዳታቸውን ይገልጻሉ።ይህን ጥያቄ ተከትሎ ወረዳው አቶ ፍቃደ በሌሉበት ቤቱን አፈራርሶ እቃቸውንም ሰባብሮ በአደራ በአራዳ ክፍለ ከተማ እንዲቀመጥ መደረጉን አቤቱታ አቅራቢው ይገልጻሉ ።
አቶ ፍቃደም በድጋሚ “እቃዬን ቆጥራችሁ አስረክቡኝ” ሲሉ ወረዳውን ይጨቃጨቁ ያዙ። ወረዳውም እቃው ከነበረበት ወደ አራዳ ክፍለ ከተማ በአደራ ለማስቀመጥ የተጓጓዘበትን የትራንስፖርት እና የሰራተኛ 6 ሺህ አንድ መቶ ብር ከመንግስት ወጭ ስለተደረገ 6 ሺህ አንድ መቶ ብር ከፍለው እቃውን መውሰድ እንደሚችሉ በቁጥር የካ/ወ4/ፍ/76/2011 በቀን 05/06/2011ዓ.ም ይጠይቃሉ።አቶ ፍቃደም የተጠየቁትን ብር አልከፍልም ማለታቸውን ይናገራሉ።ቀጥሎም በቁጥር የካ/ወ4/ፍ/91/2011ዓ.ም በቀን 20/06/2011 ዓ.ም መንግሥት ለእቃ ማጓጓዣ የከፈለውን ብር 3050 ብር እንዲከፍሉ በወረዳው የፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ይጠየቃሉ።
በመጨረሻም እቃው ተሰባብሮ በ2014 ዓ.ም ተገደው እንደተረከቡ አቤቱታ አቅራቢው ይናገራሉ።ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል የወረዳ አራት ዋና አስተዳዳሪን እና የቀድሞውን የፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎችን አነጋግሯል።
የወረዳ 04 ዋና አስተዳዳሪ ምላሽ
አሁን ላይ በየካ ክፍለከተማ የወረዳ 04 አስተዳዳሪ አቶ አብዱልፈታ ኢስማአለ ይባላሉ። የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል የወረዳውን አስተዳደር “ፍርድ ቤት በ2009 ዓ.ም የወሰነውን ውሳኔ ስለምን እስካሁን ሳትፈጽሙ ቀራችሁ? ምክንያቱ ምንድን ነው ? “ ሲል ጠየቀ ። የወረዳ አስተዳደሩም እርሳቸው ወደ ወረዳው ከመጡ አመት እንደማይሞላቸው እና እሳቸው ከመጡ በኋላ ግን እቃውን ለማስረከብ ብዙ እርቀት መሄዳቸውን ይገልጻሉ።
ይህን ተከተሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ፍርድ ቤት ነጻ ናቸው ብሎ ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ የታሸገውን ቤት አለመክፈት ትክክል አይደለም።ትክክል ካልሆነ ወረዳው ፍርድ ቤት የወሰነውን ውሳኔ አለማስፈጸሙ በሕግ አያስጠይቅም ወይ ? ሲል አዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጠየቀ ።አስተዳዳሪውም በሕግ ያስጠይቃል ።ይህን ያደረጉ ሰዎች ላይ አሰራሩን ተከትለው እና ጉዳዩን አጣርተው በሕግ እንደሚጠየቁ ይናገራሉ።
«እንደሚታወቀው አቤቱታ አቅራቢው ብዙ ገንዘባቸውን ያፈሰሱበት ንብረታቸው ወረዳ 04 በፈጠረው የሐሰት ክስ ከ2006 ዓ.ም እስከ 2014 ዓ.ም እንዲጉላሉ ተደርጓል ።በዚህም ቤተሰባቸው እና የማኅበሩ ሥራ አስኪያጅ ለከፋ ኢኮኖሚዊ፣ ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ችግር ተዳርገዋል።ለዚህ ጉዳታቸው የሚሆን ካሳ ማን ነው የሚከፍላቸው? » ሲል የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል የወረዳ አራትን አስተዳዳሪ ጠየቀ ።የወረዳ አስተዳዳሩም የካሳ ከፍያው በወረዳው አስተዳደራዊ ውሳኔ ተሰጥቶበት እንዲከፈላቸው ጥረት እንደሚያደርጉ ጠቁመው ፤ በአስተዳደራዊ ውሳኔ መክፈል ካልተቻለ ግን ጉዳዩ በፍርድ ቤት የሚታይ እንደሆነ ገልጸዋል።
የቀድሞው የወረዳው ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ
አቶ አሸብር አባይ ይባላሉ፤ የቀድሞው የወረዳ 04 ፍትሕ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ናቸው ።ከአቶ ፍቃደ ጋር ተያይዞ በእኝህ ሰው እጅ ብዙ ፊርማዎች ተፈርመው ይገኛሉ።ይህን ተከትሎ የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም የፍትሕ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ የነበሩትን አቶ አሸብርን እንዲህ ሲል ጠየቀ ፡- “ ከአቶ ፍቃደ ጋር ተያይዞ በእርስዎ የተፈረሙ ብዙ ሰነዶች አሉ።እነኝህ ሰነዶች ደግሞ አቶ ፍቃደን ለእዚህ ችግር የዳረጉ ናቸው ።ስለዚህ አቶ ፍቃደ እዚህ ለደረሱበት ችግር አንደኛው ተጠያቂ እርስዎ ነዎት፤ እዚህ ላይ ምን ይላሉ?” አቶ አሸብርም በአንተ ፊርማ ሰውየው ብዙ በደል ደርሶባቸዋል ብሎ መጠየቅ ሲጀመር ትክክል አይ ደለም ። እንደዚህ ብለህ ለምን ትጠይቀኛለህ ? እንዲህ ብለህ ለመጠየቅስ ማስረጃ አለህ ብለው የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልን ጠየቁ ።የአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍልም ማስረጃዎች አሉኝ በማለት የሰነድ ማስረጃዎችን አንድ ፣ ሁለት ብሎ እየቆጠረ መስጠት ሲጀምር ዝግጅት ክፍሉ የሚሰጣቸውን ማስረጃዎች እና የድምጽ መቅጃ መሳሪያውን በመወርወር እና አላስፈላጊ ቃላትን በመናገር ምናልባትም ከአንድ የወረዳ ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ይሰራ ከነበረ ሰው የማይጠበቅ ነገር በመናገር ቃለ ምልልሱን አቋርጠው ወጡ። ውድ አንባቢያን፤ እኝህ ሰው ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው እቃውን ላጓጓዝንበት አንድ ጊዜ ስድስት ሺህ በሌላ ጊዜ ደግሞ ሶስት ሺህ ክፈሉ እያሉ ማህተም ሲያደርጉ የነበሩ ሰው ናቸው።
ውድ አንባቢያን፣ ከላይ ያነሳናቸው ሰነዶችና ማስረጃዎች እንደሚያመለክቱት ችግሩ በቀላሉ መፍትሔ ማግኘት የሚችል ሆኖ እያለ በዚህ መልኩ ረጅም ጊዜ መንከባለሉ በአንድ በኩል ግለሰቦችን ለችግር የሚዳርግ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ መንግሥትም ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዳያገኝ ያደርጋል።በመሆኑም እንዲህ አይነት የመልካም አስተዳደር ችግሮች በወቅቱ መፍትሔ ቢያገኙ መልካም ነው እንላለን፡፡
ሙሉቀን ታደገ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም