አፍሪካዊቷ ግዙፍ አገር ሱዳን እኤአ ከ1989 አንስቶ ለሦስት አስርተ ዓመታት በፕሬዚዳንትነት ያስተዳደሩት ኦማር ሃስን አልበሽር ከሁለት ዓመት በፊት በሕዝባዊ አመጽ ከሥልጣን ከተወገዱ ማግስት አንስቶ አገሪቱ የሰላም አየር መተንፈስ አልሆነላትም።
በተለይ የሽግግር መንግሥቱን በጋራ በሚመሩት ወታደራዊ እና የሲቪል ባለሥልጣናት መካከል የተፈጠሩ አለመግባባቶች‹‹አደገኛ›› የተባለ ፖለቲካዊ ቀውስ አስከትለዋል። ባለፈው መስከረም ወር በጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ መፈንቅለ መንግሥት መሞከር ነገሮችን ከድጡ ወደ ማጡ አሻግሮታል ። ክስተቱም የሽግግር አስተዳደሩን በሚመራው ሉዓላዊ ምክር ቤት አባላት መካከል ከፍተኛ ውጥረትን አንግሶ ቆይታል።
ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልን ነው የሚሉ በርካታ አስተያየት ሰጪዎችም፣በሽግግር ሂደት ላይ ያለው የአገሪቱ መንግሥት በራሱ የመጣው በተመሳሳይ በመፈንቅለ መንግሥት ነውና ከሸፈ የተባለው መፈንቅለ መንግሥት በእርግጥም ስለ መክሸፉ ጥርጣሬ እንዳላቸው ሲገልጹ ተደምጠው ነበር።
የተፈራውም አልቀረ ከትላንት በስቲያ በምስራቅ አፍሪካዊቷ አገር በሁለት ወር ውስጥ ሁለተኛው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተካሂዷል።ትላንት ንጋት ላይ ያልታወቁ ወታደሮች ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላህ ሃምዶክንና በርከት ያሉ የሲቪል አመራሮችን በቁጥጥር ስር አውለዋል።
ከመፈንቅለ መንግሥቱ በኋላ በአገሪቱ ያለው ሁኔታ ከቁጥጥር ውጭ ሆኗል።ወደ ዋና ከተማዋ የሚያስገቡ ዋናዋና መንገዶች በወታደሮች ተዘግተዋል። በዋና ከተማዋ ካርቱም የኢንተርኔት አገልግሎት ተቋርጧል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ታውጅል። ክስተቱም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተለያዩ ተቋማት እና አገራት ውግዘት እያስተናገደ ይገኛል።
የፖለቲካ ተንታኞችም ሆኑ የሱዳንን ፖለቲካን በአይነ ቁራኛ የሚከታተሉ ምዕራባውያን አገሮች ብሎም የተለያዩ መገናኛ ብዙኃንም ሽግግሩ ከታሰበው ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሳይደርስ እንዳይንገራገጭና ቀውሱም ለጎረቤት አገራት እንዳይተርፍ ስጋታቸውን እየገለጹ ናቸው።
በእርግጥም የሱዳን ቀውስ ዳፋው በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በቀጣናው ሰላምና መረጋጋት ላይ ተጽዕኖ አለው። እልባቱ ፈጣን ካልሆነ አደጋው የዚያኑ ያህል እንደሚገዝፍ ለማሰብ የሚከብድ አይሆንም ። በተለይ ሱዳን ውስጥ በየትኛውም መልኩ የሚከሰት አለመረጋጋት ለጎረቤት አገራት መትረፉም አይቀርም።በቀጥታ ተጽዕኖ ከሚደርስባቸው አገራት መካከል ደግሞ ኢትዮጵያን በቀዳሚነት ተጠቃሽ ነች።
ኢትዮጵያና ሱዳን ለዘመናት የዘለቀ የጋራ ግንኙነትን የመሰረቱ፣ በተለያዩ የኢኮኖሚያዊ ፖለቲካዊና ማህበራዊ መስተጋብርና ትስስሮሽ የተዋሃዱ ናቸው። የውስጥ ችግር ያልበገረው ረዥም ዘመናትን ያስቆጠረ ወዳጅነት ያላቸውና 750 ኪሎ ሜትሮች ያህል የጋራ ድንበር የሚጋሩት ጎረቤት ብቻ ሳይሆን ቤተሰብም ጭምር ናቸው።
ኢትዮጵያ አተርፋለሁ ብላ የምታምነው ሰላማዊ፣ የለማች፣ በጋራ ተጠቃሚነት የምታምንና ጠንካራ የሆነች ሱዳን ስትኖር ነው።ኢትዮጵያ ሱዳን ፈተና በገጠማት ጊዜ ከማንም ቀድማ የምትደርስ፣ መልካም ጎረቤት እንደሆነች በተደጋጋሚ አስመስክራለች።
ሱዳን ወደ እርስ በእርስ ግጭት ባመራችበት ክፉ ጊዜያትም ቢሆን ለሰላም ከኢትዮጵያ ቀድሞ የደረሰ ሌላ አንድም አገር የለም።ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ሠራዊቷን በዳርፉርም ሆነ በአብዬ ከአስርተ ዓመታት በላይ በማሰማራት ለጎረቤቷ ሰላም ቁርጠኛ መሆኗን ያስመሰከረችም አገር ናት።በክፉም ሆነ በመልካም ጊዜ ኢትዮጵያ ለሱዳን ታማኝ ወዳጅ መሆኗን ከዚህም በላይ ብዙ ማስረጃዎችም መጥቀስም አይከብድም።
የዲፕሎማሲና ዓለም አቀፍ ምሁራን እንደሚያስረዱትም፣ በዲፕሎማሲ ጎረቤትን መንካበከብ ራስን መንከባከብ ብሎም ብልህነት ነው።ለራስ ሰላም እና እድገት መሰረት ነው።ይሕን ጠንቆቆ የተረዳው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አመራርም፣ለጎረቤቶቹ ቅድሚያ እንደሚሰጥ ካስመሰከረባቸው ተግባራት መካከል ሱዳን ቀዳሚ ተጠቃሽ ናት።
ኦማር ሃስን አልበሽር ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በሱዳን የተፈጠረው ቀውስ ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ በማድረግ ረገድም ዶክተር ዐቢይ የሚቀድማቸው መሪ አልነበረም። የሚወነጃጀሉትን፣በጥርጣሬ የሚተያዩትን፣ የተከፋፈሉትን የጦርና የፖለቲካ መሪዎች ተጣማሪ የሽግግር መንግሥት እንዲመሠርቱ ለማግባባት ኢትዮጵያ ብዙ ደክማለች።እንደሩቅ ታዛቢ ከመመልከት ይልቅ መሸምገል፣ ማማለዱን አከናውና አሳይታለች።
ይሁንና ነገሮች መልካቸውን ለውጠው ከብዙ ድርድርና ውይይት በኋላ የመሪነት ስልጣን የያዙት ግለሰቦች፣ የትላንት ውለታን በልተዋል።ከአዲስ አበባ ይልቅ ዋሽግተንን፣ ከክፉ ቀን ወዳጆቻቸው ኢትዮጵያ ይበልጥ ግብፅን ሲመርጡም አይተናል።
የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ በመጠቀም ድንበራችንን አልፈውም ገብተዋል። ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ ለማደናቀፍ ከግብፅ ጋር አብረው ዓለምን ሲያስተባብሩና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፊት ሲሞግቱን ቆይተዋል። ኢትዮጵያን ውስጣዊ አለመረጋጋት እንደ እድል የመቁጠራቸው እሳቤም ምን ያህል ትላንትን የረሱ፣ ነገን የማያስቡ ቅርብ ዓላሚ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው።
ይህ ሁሉ ሲሆን ኢትዮጵያ በአንፃሩ ቁጣና ኃይልን አማራጭ ከማድረግ ተቆጥባለች። በተለይ የሽግግር መንግሥቱን በጋራ በሚመሩት ወታደራዊና የሲቪል ባለሥልጣናት መካከል የተፈጠሩ አለመግባባት የሚከሰት ቀውስ እልባት እንዲያገኝ የምትችለውን መፍትሔ ከመጠቆም ባለፈ የሰላም ምኞትን በተደጋጋሚ ስትገልፅም ቆይታለች።
‹‹መልካምነት ለራስ ነው እንደሚባለው››ዛሬ ሱዳን በየአቅጣጫው እየነደደች፣ወደ ምድራዊ ገሃነም እየተቀየረች ነው።አሁን ባለው ሁኔታ አገር ሆና የመቀጠሏ ነገር አጠያያቂ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል። ወታደርና ሕዝቡ የለየለት አመፅና ድብልቅልቅ ውስጥ ገብተዋል።በቤጃ ጎሳ የምትመራው የወደብ አገር የሆነችው ምስራቅ ሱዳን እራሴን ገንጥያለሁ እያለችም መሆኑም እየተሰማ ነው።
ሰላማዊ፣ የለማች፣ በጋራ ተጠቃሚነት የምታምንና ጠንካራ የሆነች ሱዳን ስትኖር ሁሉ ረገድ ትርፋማ እንደምትሆን የምታምነው ኢትዮጵያ በአንፃሩ ዛሬም እንደትላንቱ በጎረቤቷ ቀውስ መደሰትን ምርጫዋ አላደረገችም።ጮቤም አልረገጠችም።ይልቁንም ቀውስ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ፍላጎቷ መሆኑን አሳውቃለች።
ውሎ ሲያድርም ሱዳን የዴሞክራሲ ሽግግሯን እንድታ ጠናክር፤ኢኮኖሚዋን መልሳ እንድትገነባ፣ለመላ ሕዝቧ ዘላቂ ሰላምና ልማትን እንድታረጋግጥ ምኞቷ ነው።ለሁሉም ሰላማዊ መፍትሔም እጇን ለመዘርጋት ዝግጁ መሆኗም እርግጥ ነው።
ይሁንና ከሰላም ምኞት እና ትብብር ባለፈ የሱዳን ቀውስ አገራችን ላይ ያልተጠበቀ ተፅእኖ እንዳያመጣ በንቃት መጠበቅ የግድ ይላል።ቀውሱም ከምንጊዜም በላይ በሁሉ ረገድ በሁሉም አቅጣጫ እንድንነቃ የማንቂያ ደውል ሊሆንም ይገባዋል።
በተለይ በካይሮ አምሳያ የተቀረፀ መንግሥትን ሱዳን ላይ ለማዋለድ የሚታትሩ አይዞኝ ባዮችም ከጀርባ ስለመኖራቸው መዘንጋትም አያስፈልግም።እዚህ ላይ የአሜሪካው የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ የጄፍሪ ፌልትማን የተናጠል ምክክርና የግብጽ ፍላጎት ሲጨመርበት ደግሞ ምናልባትም ከሴራው ጀርባ ከባድ ተልእኮ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠርም ትክክለኛነት ይሆናል።
መፈንቅለ መንግሥቱን የመራው የሱዳን ወታደራዊ መሪ የግብፅ ተላላኪውና በኢትዮጵያ ላይ ተደጋጋሚ ወረራ የፈፀመው አብዱልፈታህ አልቡርሃን መሆኑ ደግሞ አይንን ለአፍታም ዞር ማድረግ እንደማይገባ ማስጠንቀቂያን የሚሰጥ ነው።
ከሁሉ በላይ ቀውሱን ተከትሎ ወደ ኢትዮጵያ የሚሰደዱ ሱዳናውያንም ሆነ ሌሎች ስደተኞች ላይ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።አጋጣሚውን በመጠቀም አሸባሪ የሕወሓት ቡድን ሱዳን ውስጥ ያሰለ ጠናቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ጋሻ ጃግሬዎችን ለማስረግ እንደሚተጋም ታሳቢ ማድረግ የግድ ይላል። በመሆኑም በድንበር አካባቢ የሚደረጉ ቁጥጥሩ ይበልጥ ተጠናክረው መቀጠል ይኖርባቸዋል።
ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያን ከታሪካዊ ጠላቶች ሴራ መታደግ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት መሆን አለበት። የኢትዮጵያ እውነተኛ የከፍታ ዘመን እንዲረጋገጥ፣ ሕዝቦቿ በሰላምና በነፃነት የተረጋጋ ሕይወት እንዲመሩ አንድነት በማጠናከር ለህልውና ትግል በጋራ መቆም ያስፈልጋል ።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም