በአሸባሪው ሕወሓት ኢ-ሞራላዊ እንቅስቃሴዎች ምክንያት እጅግ መራር መስዋዕትነት እያስከፈሉን ያሉ በርካታ ጉዳዮች አሉ። ከባለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ዓበይት የመንግሥት ለውጦች ከተመዘገቡ ወዲህ ከብልጽግና ጉዟችን ሊያደናቅፉን ያሰቡ ከውስጥም በውጭም የኢትዮጵያ ጠላቶች ተነስተዋል። በእነዚህ ጊዜያት በሕዝብ መራር ትግል የተገኙ መንግሥታዊ ለውጦች የማስቀጠል ጉዳይ ትልቁ ፈተና እንደነበርም የማይካድ ሐቅ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ደግሞ ወራሪው የሕወሓት አሸባሪ ቡድን ከተቀበረበት የሞት ጉድጓድ ለመነሳት በተወሰኑ አካባቢዎች የመፍጨርጨር ሁኔታ ቢያሳይም ሕዝቡ አሁንም በአንድነት በመቆሙ የለውጡ ሂደትና የድሉም ባለቤት እራሱ ሕዝቡ መሆኑን እያሳየው ይገኛል።
ይህ የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ባለቤትነት፣ አሸናፊነትና ተጠቃሚነት ወደ መሬት ወርዶ እውን እየሆነ መጥቷል። ይህ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችል የአስተሳሰብ፣ የአደረጃጀትና የተግባር ሥራ መስራት ይጠበቅብናል። ለዚህም የማይቋረጥ የለውጥ ጎዳና ላይ መሆናችንን ሁሉም ልብ ሊል ይገባል።
በለውጥ ሂደት ላይ ነን ስንል በዚህ ወቅት የውጭና የውስጥ ጠላት ኃይሎች በሚዘሩት የውሸት ትርክትና ዘገባ ሳንበገር እኛው በራሳችን በፈጠርነው የአስተሳሰብ፣ የሞራልና የተቀናጀ ኅብረት ድል የምናደርግበት ወቅት ላይ ነን ማለታችን ነው። የገጠመን ፈተና ከባድና ውስብስብ ቢመስልም እነዚህ የጠላት ኃይሎች ተፈጥሯዊ ሞታቸውን በቅርቡ እንደሚሞቱና የኢትዮጵያ ሕዝቦችም የአሸናፊነትን አክሊል መጎናፀፋቸው የማይቀር መሆኑን ልንገነዘብ ይገባል።
አሁን የሚታየው ግጭት በለውጡ ሂደትና ለውጡን በሚጠሉ መካከል በሚፈጠር ቅራኔ የመጣ ነው። አዲሱ የለውጥ አስተሳሰብ አሮጌውን ያሸንፋል። ለውጡ በብርቱ ትግል የመጣ እንደመሆኑ፣ ለውጡን ለማስቀጠልም ብርቱ ትግል ይጠይቃል። በመሆኑም የለውጡን ጥያቄ ለመመለስ ከመወጋገዝ ይልቅ መተጋገዝ፣ ከመጠላለፍ ይልቅ መተቃቀፍ እንዲሁም ከመከፋፈል ይልቅ መተባበር ይጠይቃል።
ለዚህም ምክንያቱ ዘመኑ እርስ በርስ የምንወነጃጀልበት ሳይሆን በይቅርታና በፍቅር የምንጓዝበት ስለሆነ ነው። የጨለማው ዘመን ምዕራፍ እስከወዲያኛው ተዘግቶ አዲስ የተስፋ ጸዳል እየመጣ ስለሆነም ነው።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ አገራችን በአተገባበሩ ልዩና ተዓማኒነት ያለው ምርጫ ያካሄደችበት፣ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ የመንግሥት ሥርዓት በሕዝብ የባለቤትነት ስሜትና ንቁ ተሳትፎ የተመሰረተበት፣ በሕዝቦች አንድነት የውስጡም ሆነ የውጭው ጠላት እየተመታ ያለበት በመሆኑ የሕዝቦች አሸናፊነት ለአፍታም እንኳን ጥርጣሬ ውስጥ ሊገባ አይገባም። ይህም በመላው የሕዝብ ንቅናቄ በመታጀብ እውን እየሆነ ይገኛል።
በዚህ ትክክለኛ የለውጥ አካሄድ የተቃኘና እውን የሆነ የፖለቲካ ተሞክሮ እንዲዳብርና ትርጉም ባለው ሁኔታ እንዲቀጥል የለውጥ ሂደት ባለቤትነት፣ አሸናፊነትና የውጤቱም ተጠቃሚነት ሕዝቡ ራሱ መሆኑን አምኖ ጠላትን ከሚፋለሙ ወገኖች ጎን በጋራ ሊቆም ይገባል። እርግጥ ነው ምልዓተ ሕዝቡ ለውጡን እንደወለደው ሁሉ ለስኬቱም አጋርነቱን እያሳየ ይገኛል።
ሁላችንም የአሸባሪውን ሕወሓት እኩይ የፖለቲካ ጨዋታ በነቃ፣ በማይናወጥ መርህ ላይ በተመሠረተ እና በተቀናጀ የትግል ስልት መክተን ወደ ፊት መራመድ ይገባናል። በቁሙ የውጭ እርዳታ የሚማፀነውን የሕወሓትን እኩይ የፖለቲካ ባህሪ በመፀየፍ ይህ ትውልድ የተጣለበትን አደራ በተግባር ተወጥቶ ማሳየት አለበት። ይህ ትውልድ ከጥንት አርበኛ አባቶች የተቀበለው አደራ አሁን ከምናየው የሕወሓት እብደትና የሸፍጥ ፖለቲካ ጨዋታ በእጅጉ የተለየ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል።
የሕዝብ የለውጥ ሂደት ባለቤትነትና አሸናፊነት እውን የሚሆነው፣ የተጋረጡብን ፈተናዎች ዘርፈ ብዙና ከባድ ቢሆኑም ይህን መራር እውነት በደፋርነት፣ በወኔ እንደምናሸንፈው አምነንና ተቀብለን በጊዜውና ትርጉም ባለው አኳኋን ከገሰገስን ነው! ያለምንም ጥርጥር ሕዝብ ያሸንፋል! የአሸናፊነቱ በረከትም ለልጅ ልጆቹም ያስተላልፋል። ለዛም ነው የለውጥ ሂደቱ ባለቤትነትና አሸናፊነት የሕዝብ ነው የምንለው።
አዲስ ዘመን ጥቅምት 17 ቀን 2014 ዓ.ም