አዲስ አበባ፡- አዲስ አበባ 123ኛውን የአድዋ ድል በዓል በስነ ጹሁፍ፣በእግር ጉዞ፣በፌስቲቫልና ግብር በማብላት በደማቅ ሥነ ሥርዓቶች ልታከብር መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።
ከተማ አስተዳደሩ የባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ ትናንት 123ኛው የአድዋ ድል በዓል አከባበር ዙሪያ ከተባባሪ አዘጋጆች ጋር በመሆን ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የአድዋ የድል ጀግኖች አባቶቻችን ከወራሪዎች ጋር ባደረጉት ተጋድሎ የተገኘ ድል መሆኑን የገለጹት ረዳት ፕሮፌሰሩ ይህን የሁሉም የኢትዮጵያ ህዝቦች ታሪክ ከትውልድ ትውልድ ለማስተላለፍ ዓላማ ባደረገ መልኩ የሚከበር መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ረዳት ፕሮፌሰሩ ገለጻ የአድዋ ድል በዓል ለትውልድ ለማስተላለፍ በሚያስችል መልኩ በአዲስ አበባ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ለማክበር ዝግጅቱ ተጠናቋል። ዛሬ በብሄራዊ ቤተ-መዛግብት የፊልም ፌስቲቫል ይካሄዳል፤ ነገ ዓርብ በዓሉን በተመለከተ የሥነ-ጥበብ ድግስ በጣይቱ ሆቴል ተዘጋጅቷል ብለዋል። በበዓሉ ዋዜማ ምሽት በጊዮርጊስ አደባባይ የተለያዩ ትዕይንቶችም ይካሄዳሉ። በዕለቱም በምኒልክ አደባባይና ሀውልት የአድዋ ሰማዕታትን የማስታወስ እና የማወደስ ሥነ-ሥርዓት ይካሄዳል።
በመቀጠልም በዓሉ ከአጼ ምንልክ አደባባይ እስከ አድዋ ድልድይ የእግር ጉዞ የሚካሄድ ሲሆን ምሽት ላይም አርበኞችን እና የበዓሉ ታዳሚዎችን ግብር የማብላት ሥነ-ሥርዓትም የሚከናወን ይሆናል።
በመጨረሻም የበዓሉ ዕለት ከስምንት ሰዓት ጀምሮ በከተማ አስተዳደሩ አዘጋጅነት የ “ክብር አድዋ ፌስቲቫል!” የሙዚቃ ድግስ በመስቀል አደባባይ ተዘጋጅቷል። የሙዚቃ ድግሱ መግቢያ በነፃ ሲሆን በፌስቲቫሉ ላይ በርካታ የአገራችን የኪነ-ጥበብ ሰዎች የሚሳተፉ ይሆናል። ከተሳታፊዎቹ መካከል ድምጻዊ ሙሀመድ አህመድ፣ቢቲጂ፣ኃይሌ ሩት ፣እሱባለሁ ይገኙበታል።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በጌትነት ምህረቴ