ወጣቷና ባለተሰጥዎዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ለተሰንበት ግደይ በአስደናቂ የዓለም ክብረወሰኖቿ ዓለምን ማስደመም ቀጥላለች። በረጅም ርቀት ንግስቷ ጥሩነሽ ዲባባ ከአስራ ሁለት ዓመታት በላይ ተይዞ የቆየውን የ5ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ከዓመት በፊት ቫሌንሲያ ላይ በመስበር የማይቻል የሚመስለውን ስኬት የተጎናጸፈችው ለተሰንበት የውድድር ዓመቱን ለማመን የሚከብድ ሌላ ክብረወሰን በመስበር ነበር ያጠናቀቀችው። ይህም በሪዮ 2016 ኦሊምፒክ አስደናቂዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት አልማዝ አያና ያሻሻለችው የ10ሺ ሜትር ክብረወሰን በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፋን ሃሰን ባለፈው ዓመት ተሰብሮ አርባ ስምንት ሰዓት ሳይሞላው ለተሰንበት በኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር ሄንግሎ ላይ የግሏ ያደረገችበት ታላቅ ስኬት ነው።
በሁለቱ ታላላቅ የዓለም ክብረወሰኖች ደምቃ ወደ ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ያቀናችው ለተሰንበት በታላቁ የስፖርት መድረክ በ10ሺ ሜትር ኢትዮጵያን ወክላ የጠበቀችውን ወርቅ ማጥለቅ ባትችልም የነሐስ ሜዳሊያ ማሸነፏ ይታወሳል። ይህም ውጤት ከጠበቀችው የወርቅ ሜዳሊያ አኳያ ያስከፋት ነበር።
ለተሰንበት በኦሊምፒክ የጠበቀችው ወርቅ አጥታ ስሜቷ ተጎድቶ ቢያስለቅሳትም ነገም ሌላ ቀን ነውና ባለፉት ጥቂት ወራት ጠንክራ ሰርታ የኦሊምፒክ ቁጭቷን በሌላ ተጨማሪ የዓለም ክብረወሰን ማካካስ ችላለች።
ለተሰንበት ከኦሊምፒኩ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከትናንት በስቲያ በተወዳደረችበት የቫሌንሲያ ግማሽ ማራቶን ውድድር የርቀቱን የዓለም ክብረወሰን በመስበር አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ የሶስት ታላላቅ የዓለም ክብረወሰኖች ንግስት ሆናለች። ለተሰንበት በርቀቱ ገና ለመጀመሪያ ጊዜ ብትወዳደርም የቀድሞውን ክብረወሰን ከአንድ ደቂቃ በላይ በማሻሻል ዓለምን አስደምማለች። ለተሰንበት ርቀቱን 1:02:52 ያጠናቀቀች ሲሆን የቀድሞው ክብረወሰን ባለፈው ሚያዝያ በኬንያዊቷ አትሌት ሩዝ ቺፕጌቲች 1:04:02 በሆነ ሰዓት የተመዘገበ ነበር።
የ23 ዓመቷ ድንቅ ኢትዮጵያዊት አትሌት ባለፈው ዓመት የ5ሺ ሜትር ክብረወሰኑን በጨበጠችበት ቫሌንሲያ ከተማ የግማሽ ማራቶን ክብረወሰን በመድገሟ ‹‹ቫሌንሲያ ትመስገን፣ በመጀመሪያ የግማሽ ማራቶን ውድድሬ የዓለም ክብረወሰን በማሻሻሌ በጣም ተደስቻለሁ›› በማለት ውድድሯን ስትፈጽም ተናግራለች። በመጀመሪያ የዓለም ክብረወሰኗ የዓለም መነጋገሪያ ያደረገቻት ቫሌንሲያም በግማሽ ማራቶን ከ63 ደቂቃ በታች ውድድሯን የፈጸመች በታሪክ የመጀመሪያዋ አትሌት እንድትሆን አድርጋታለች።
ለተሰንበት በወንድ አሯሯጭ ታግዛ ከውድድሩ መጀመሪያ አንስቶ ከሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ያለምዘርፍ የኋላው ጋር ያደረገችው አስደናቂ ፉክክር ለክብረወሰኑ መሰበር ትልቅ ሚና ነበረው። አትሌት ያለምዘርፍ በቅርቡ በሰሜን አየርላንድ ባደረገችው የግማሽ ማራቶን ውድድር ርቀቱን 1:03:44 በሆነ ሰዓት የዓለም ክብረወሰን ብታሻሽልም ያስመዘገበችው ሰዓት እውቅና እንዳልተሰጠው ይታወሳል። ያለምዘርፍ በዚህ እልህ ለሌላ ክብረወሰን ከለተሰንበት ጋር አስደናቂ ፉክክር ብታደርግም እስከመጨረሻ መጓዝ አልቻለችም። ያም ሆኖ 1:03:51 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችበት ሰዓት ቀድሞ በኬንያዊቷ አትሌት ከተመዘገበው የርቀቱ የዓለም ክብረወሰን የተሻለ ሆኖ ተመዝግቧል። በተመሳሳይ ሶስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው ኬንያዊቷ ሼላ ቺፕኪሩይ ያጠናቀቀችበት 1:04:53 ሰዓትም ከቀድሞው ክብረወሰን የተሻለ ፈጣን ሰዓት ሆኗል።
በተመሳሳይ በወንዶች መካከል በተካሄደው ውድድር የሁለት ጊዜ የ5ሺ ሜትር የዓለም ሻምፒዮኑ ኢትዮጵያዊ አትሌት ሙክታር ኢድሪስ ትልቅ ያሸናፊነት ግምት ቢሰጠውም ውድድሩን 58:40 በሆነ ሰዓት ስድስተኛ ሆኖ አጠናቋል። ኬንያውያን በበላይነት ባጠናቀቁበት ውድድር አቤል ኪፕቹምባ 58:03 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ያስመዘገበው ሰዓት በርቀቱ በታሪክ ስድስተኛው ፈጣን አትሌት አድርጎታል። ሌላኛው ኬንያዊ ሮኔክስ ኪፕሩቶ 58:09 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ዳንኤል ማቴኮ 58:26 በሆነ ሰዓት ሶስተኛ ሆኗል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2014