ሴቶች በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊ እና በማህበራዊ መስኩ ከወንዶች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል የተለያዩ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና መርሐ ግብሮች ተዘጋጅተው በሥራ ላይ ሲውሉ ቆይተዋል። ከነዚህ መካከል ለ28 ዓመታት ሲያገለግል የቆየውና አሁንም እያገለገለ የሚገኘው ቤሄራዊ የሴቶች ፖሊሲ ይጠቀሳል። ይህ ፖሊሲ በመጀመሪያ የተቀረጸው አንድም የሴቶችን መብት በኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ መስክ ተቋማዊ ለማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው በእነዚሁ መስኮች ውስጥ የሴቶችን መብት ወደ ፊት ለማራመድ በማለም ነበር። በመሆኑም ፖሊሲው ይህን ዓላማውን ምን ያህል እንዳሣካ ለማወቅ በ2011 ዓ.ም በወርሀ ነሀሴ ፖሊሲውን በመከለስ ማሻሻያ ጥናት ወደ ማድረጉ ሂደት የተገባ እንደነበር ይታወሳል። የክለሳ ማሻሻያ ጥናቱ መደረግ የጀመረው የኢትዮ አውስትራሊያ ምርምር ኢንስቲትዩት በሆነው ኢንክሎቬት ትብብር አማካኝነት ነበር።
ፖሊሲው የተቀረጸው ኢህአዴግ በ1983 ዓ.ም ወርሀ ግንቦት ላይ ወደ ስልጣን በመጣበት የሽግግር መንግስት ወቅት ነበር። ከ1987ቱ ዓ.ም ህገ መንግስትም በአንድ ዓመት ይቀድም ነበር። ይህም ከህገ መንግስቱ የመቅደሙ ጉዳይ ፖሊው የተቀረጸው ምን አልባት በእውኑ ሴቶችን ለመጥቀም ታስቦ ሳይሆን የሽግግር መንግስቱ ከሕዝቡ ከግማሽ በላይ ከሆኑት ሴቶች የቆይታ ጊዜውን ለማራዘም የሚያስችለውን ድጋፍ ለማግኘት እንዲረቀቅ የተደረገ ነው የሚል ትችት ሲቀርብበት ኖሯል። ይሄው የ27 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋ ሥርዓት የሥልጣኑ ዘመን ባበቃበት ወቅት ፈጦ የወጣው እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ዓይነት ራስ ወዳድነቱ እውን ፖሊሲውን ለሴቶች አስቦ ሳይሆን በነሱ ድጋፍ የሥልጣን ዘመኑን ለማራዘም አልሞ ያወጣው መሆኑ ትችቱን አጠናክሮታል። ሴቶች በመብት ጥሰቶች፣ በጾታዊ ጥቃቶችና በተለያዩ ችግሮች ሊጠቁ የሚችሉበትንና የበለጠ ተጎጂ የሚሆኑበትን ጦርነት ከፍቶ የገዛ ሀገሩን መውጋቱም ትችቱ እውነታ የነበረው መሆኑን አረጋግጦታል።
ትችቱ በተለይ በየምርጫ ዘመናቱ ገኖ ሲወሳና ፖሊሲውን ሲያብጠለጥል መቆየቱ የሚዘነጋ አይደለም። ብዙ እንከኖቹም ከዚሁ ጋር ተያይዘው የመነጩ ናቸው የሚልም ትችት ሲሰነዘርበት ነበር። ሆኖም በብዙዎች በራሳቸው በሴቶቹም እንደሚነገርለት ከሀገሪቱ የ1987 ሕገ መንግስት አንድ ዓመት ቀድሞ የተቀረጸው ይሄው የሴቶች ፖሊሲ በወቅቱ መቀረጹ ጠቃሚ ሆኖ ተገኝቷል። በሀገሪቱ ለሴቶች መብት መከበር መንገድ ጠራጊም መሆኑን መካድ አይቻልም። በተለይ ዛሬም ድረስ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት ለማስቆምና የሴቶችን ሁለንተናዊ ደህንነት እንዲጠበቅ ማድረግ ባይሆንለትም ችግሩን ለመቀነስ እና ችግሩ እንደ ችግር እንዲታወቅላቸው ማድረግ በማስቻሉ ረገድ ዓይነተኛ መሣሪያ ሆኖ ሲያገለግል ቆይቷል። ለሴቶች የሕግና የሰብዓዊ መብታቸውንና ነፃነታቸውን ለማስከበርም የበኩሉን መደላድሎች ፈጥሯል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡን ወይዘሮ ማርታ ገዙ እንደሚናገሩት በእርግጥ ሀገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ምንጊዜም ህግ በማውጣትም ሆነ ፖሊሲ በማርቀቅ በየትኛውም ሥርዓት ያሉ መንግሥታት ችግር የለባቸውም። ኢትዮጵያ የተለያየ ስምምነትን ቤሄራዊው የሴቶች ፖሊሲ ከመረቀቁ በፊት ቀድማ የፈረመችበትን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል። ከዚህ ጊዜ ጀምሮም የሴቶችን መብቶች የሚያስጠብቁ በርካታ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና ቤሄራዊ ሕጎችን ያፀደቀችበትን መጥቀሱም አብነት ይሆናል። በ2007 ዓ.ም የወጣው ዘላቂ የልማት ግቦችንም እንዲሁ።
በተለይ ደግሞ ባለፉት 27 ዓመታት ሥልጣን ላይ የቆየው መንግስት በዚህ በኩል ይጠቀስና ይወደሳል። በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ሕጎችን በማውጣትና ፖሊሲዎችን በማርቀቅ በፍጹም አትታማም። ነገር ግን እነዚህን ጉዳዮች ለማስፈጸም የሚወጡ መመሪያዎች ሙሉ በሙሉ አይተገበሩም። ምን ያህሉ ተተግብረዋል፤ ምን ያህሉስ አልተተገበሩም ብሎ አስተያየት ለመስጠት ቢከብድና ራሱን የቻለ ጥናት ማድረግ ቢያስፈልግም እሳቸው በወረቀት ላይ ተወስነው የሚቀሩ ብቻ ነው የሚመስላቸው። ምን አልባትም ከህገ መንግሥቱ ቀድሞ የወጣው የሴቶች ቤሄራዊ ፖሊሲ ሲረቀቅ የታለመለትን ዓላማ ሙሉ በሙሉ ሊያሳካ ያለመቻሉም ጉዳይ ከትግበራው ተግዳሮቶች ጋር ይሰናሰላል ብለው ያስባሉ።
ወጣት መሪዬም ጀማል ይሄንኑ የወይዘሮ ማርታ ቦጋለን አስተያየት ትጋራለች። የፖሊሲ ትግበራው የተቃና ቢሆን ዓላማውን ሙሉ በሙሉ ለማሳካት አይቸግርም ነበር ባይ ናት። አሁንም ፖሊሲውን በክለሳ ከማሻሻሉ ጎን ለጎን ትግበራው ላይ ትልቅ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባም ትመክራለች። ፖሊሲውን ለማስፈጸም የሚወጡ የተለያዩ ሕጎችና መመሪያዎች መከበርና ተፈፃሚ መሆን እንዳለባቸውም ታሳስባለች። ሴቶች ለዚህ በጥቅሉም የራሳቸው ጉዳይ ለሆነ ሁሉ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚገባቸውም ታመለክታለች። ማናቸውም ፖሊሲዎችና ሕጎች ከወረቀት ላይ በመላቀቅ ወደ መሬት ወርደው ተፈፃሚ እንዲሆኑ ግፊት ማድረግ አለባቸው። እንደ እሷ አስተያየት ከሆነ መላው ዓለም ያለበት ዘመን አሁንም አባታዊነት ጎልቶ የሚንፀባረቅበት እንዲሁም የወንዶች ኃያልነት የሚቀነቀንበት ከመሆኑ አንፃር እኛ ሴቶች ተጨባጭ ለውጥ ልናመጣ አንችልም፣ ሰሚም ላይኖረን ይችላል። ነገር ግን በዚህ ተስፋ መቁረጥ የለብንም፣ ድምጽ ማሰማት በራሱ ትልቅ ዋጋ ያለው ለውጥ እንድናመጣ ያስችለናል ስትል ትጠቁማለች።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሴቶች ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጡ መንገዶችን በሙሉ መጠቀም መቻል አለባቸው። ለምሳሌ፦ በየመስኮቹ በህገ መንግሥቱ የተቀመጠላቸው የልዩ ድጋፍ (አፈርማቲቭ አክሽን) ሳይሸራረፍ ተፈፃሚ እንዲሆን መታገል ይኖርባቸዋል። ለተሳትፏቸው ከወንዶች እኩል መመጣጠን አስፈላጊ የሆኑ አስገዳጅ ኮታዎች እንዲቀመጡ ማድረግም ይጠበቅባቸዋል በማለት ተናግራለች።
አስፈላጊ ከሆነ በትምህርት ገበታም ሆነ በየትኛውም መስክ በተለይ በትልቅና መካከለኛ ሥራ ኃላፊነት ላይ ያሉ ሴቶች በቤት ውስጥ በወንዶች እንዲታገዙ የሚያደርግ መመሪያ እንዲወጣ ማድረግ ሁሉ ሊጠይቃቸው ይችላል። ለምሳሌ፦ መካከለኛ ወይም ትልቅ ኃላፊነት ላይ ያለች አንዲት ሴት የቤት ሰራተኛ ሊኖራት፤ በቤት ውስጥ ሊሰራ የሚገባው ሥራ ሁሉ በሰራተኛዋ ሊከናወን ይችላል። ነገር ግን በቤት ውስጥ የሴቶችን ኃላፊነት የሚጠይቁ ሥራዎች እነዚህ ብቻ አይደሉም። እጅግ ብዙ ናቸው። እንዲህ ይሁን እንዲህ ይደረግ ብሎ መምራቱና አቅጣጫ ማሳየቱና መስጠቱ በራሱ በተግባር ከሚከናወነው የቤት ውስጥ ሥራ በላይ ጊዜ ይወስድና ያደክማል። የቤት ሠራተኛዋ በራስዋ በዚህ መንገድ ካልተመራች በራስዋ ብቻ ሥራውን አትወጣውም።
ባሉበት የኃላፊነት ቦታ ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ ታዲያ ይሄን የቤት ውስጥ ሥራን የመምራት ድርብ ኃላፊነት ወንዶች እንዲጋሯቸው ማድረግ ይገባል። ማናቸውም የሚረቀቁ ፖሊሲዎችም ሆነ መመሪያዎች የታለመላቸውን ግብ እንዲመቱ በነዚህ መታገዝም አለባቸው። መሪዬም ወደ ዋናው ጉዳያችን ስትመለስ ከሁለት አሥርት ዓመት በላይ ሥራ ላይ የነበረው ቤሄራዊ የሴቶች ፖሊሲ በሥራ ላይ በነበረባቸው ጊዜያት ጥሩ ውጤት አምጥቷል ብላ እንደምታምንም ትናገራለች። ምክንያቱ ባይገባትም የዚህ ፖሊሲ ማሻሻል ሂደቱ መጓተቱን የምትጠቅሰው ወጣቷ ነገር ግን ደግሞ አሁን ያለንበት 21ኛው ክፍለ ዘመን ከደረሰበት አኳያ ሲቃኝ ከተደረሰበት ዘመን ጋር አብረው ሊሄዱ የሚገባቸው ጉዳዮችን ማካተቱ፤ የሚሄዱትን ማጠናከሩ እንዲሁም የማይሄዱትን ማስወገዱ ግድ ስለሚል ፖሊሲው መከለሱ ተገቢ ነው ባይ ነችም።
በማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሣትፎና ንቅናቄ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ስለሺ ታደሰ በበኩላቸው ከ1986 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ ሲሰሠራበት የቆየውን ብሄራዊ የሴቶች ፖሊሲ መከለስ ያስፈለገው ከዓለም አቀፍ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተመጣጠነ እንዲሆን ለማስቻል መሆኑን ይጠቅሳሉ።
‹‹የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ለአንድ ወገን ብቻ የሚተው ተግባር ሳይሆን የሁሉንም ዜጋ ኃላፊነት ይጠይቃል›› የሚሉት ዳይሬክተሩ አቶ ስለሺ፤ በ1986 ፖሊሲው በወቅቱ የነበሩትን ሁኔታዎች መሰረት አድርጎ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ሆኖም የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበና የሴቶችን ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ማዕከል ባደረገ መልኩ በአጠቃላይም የሥርዓተ ፆታ እኩልነትን ባረጋገጠ አግባብ ከነበሩ ክፍተቶችና ስኬታማ ተሞክሮዎች ትምህርት በመውሰድ ፖሊሲው እንደገና መፈተሽና እንደ አዲስ መከለስ አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት ወደ ክለሳ ሊገባ የቻለው ብለዋል። አሁን ከተደረሰበት ነባራዊ ሁኔታ ጋር ተያይዞ በሴቶች የሚነሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ በሚያስችል መልኩ ማሻሻያዎች እየተደረጉበት ነው።
በ1986 በወጣው በዚሁ ፖሊሲ ላይ ሰፊ ዳሰሳ በማድረግ የተለያዩ ምክረ ሃሳቦች የቀረበበትም ሁኔታ አለ። በዚህ ቅድመ ጥናት ሁሉም በአገሪቱ የሚገኙ ክልሎች ተሳትፈውበታል። ከተሳተፉበት መካከል ከ60 ወረዳዎች የተውጣጡ የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚገኙበት ተሳትፎም ተጠቃሽ ነው። ከየክልሉ ቢሮዎችና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትም ጋር ውይይት ተደርጎበታል። የጥናቱ ሂደት ከአንድ ዓመት በላይ የዘለቀ ሲሆን በግኝቱ በፖሊሲው ውስጥ የተለያዩ ክፍተቶች መኖራቸውም ተመላክቷል። ከክፍተቶቹ ዋናውና ቀዳሚው የአቅም ማነስ ክፍተት እንደሆነም ተደርሶበታል። ይህ የአቅም ማነስ ከቴክኒክ ጀምሮ በሰው ኃይል፣ በፋይናንስና በመንግስት ተቋማት ጎልቶ የሚንፀባረቅ እንደሆነ ታውቋል።
በአጠቃላይ የሴቶች ጉዳይ ፖሊሲ ራዕይ የሚያተኩረው አርሶና አርብቶ አደር ሴቶች በግብርናው ልማት ውስጥ ያላቸው ሚና ጎልቶ ማየት፣ ምርታማነታቸውና ተጠቃሚነታቸው እውን መሆን ሲችል፤ ተልዕኮው ደግሞ የሴቶችን እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በመሆኑ፣ የሴቶችን መብትና ጥቅም የሚያስጠብቁ ፖሊሲዎች፣ ደንቦችና ሕጎች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ማስቻል ከመሆኑ አንፃር ፖሊሲውን ማሻሻሉ ተገቢና ወቅታዊ ምላሽ ነው በማለት ጽሑፋችንን ቋጨን።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2014