የምጣኔ ሀብት ምሁራን እንደሚያስረዱት፣ ኢኮኖሚ ብቻውን የሚቆም አይደለም። ኢኮኖሚ ከማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ጥብቅ ትስስር ያለው ነው። በተለይ ከፖለቲካ ስክነት ጋር ከፍተኛ ቁርኝት አለው። ፖለቲካው ካልተረጋጋ በተለይ በግጭትና በጦርነት ወቅት ኢኮኖሚ በእጅጉ ይረበሻል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በመጥፎነቱ በታሪክ ጥቁር መዝገብ ላይ የሚሰፍር መሆኑ በርካቶች ይስማሙበታል። ቀኑም አሸባሪው ህወሓት አሸባሪ ቡድን ለ20 ዓመታት ነፍሳቸውን ሰጥተው ሲጠብቁት በነበሩ በኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ በተኙበት ጥቃትን በመፈፀም በኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ላይ ጦርነት የከፈተበት በመሆን ይታወሳል።
የእብሪተኛውን ቡድን ድርጊት ተከትሎም ኢትዮጵያ ሳትፈልግ ወደ ጦርነት ለመግባት ተገዳለች። ላለፈው አንድ ዓመት የተካሄደው ጦርነትም ካደረሰው ሰብዓዊ ኪሳራ በተጨማሪ ከፍተኛ ወጪና ጫና እያስከተለ ይገኛል። በተለይም በኢትዮጵያ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ ከባድ ተጽእኖን እያሳደረ መሆኑ ይታመናል።
የፌዴራል መንግስቱ የገባበት ጦርነት ወዶና ፈቅዶ እንዲሁም አስቀድሞ ዝግጅት ያላደረገበትና በጀት ያልተቆረጠለት በመሆኑ ለዓመት ከያዘው በጀት ተጨማሪ የበጀት ድጎማ እንዲፈልግ ሊያደርገው እንደሚችል ሲገልጹ ይደመጣል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድም ባሳለፍነው ሰኔ ወር መጨረሻ ላይ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው የፌደራል መንግስት በትግራይ ክልል የሰብአዊ መብት ስራዎች ድጋፍ ከጦርነቱ በጀት ውጪ 100 ቢሊዮን ብር ወጪ ማውጣቱን መግለፃቸውም የሚታወስ ነው።
ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም. የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሁኔታና አፈጻጸምን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር እዮብ ተካልኝ፣ ‹‹ጦርነቱ ካደረሰው ሰብዓዊ ኪሳራ በተጨማሪ ከፍተኛ ወጪና ጫና በኢኮኖሚው ላይ ማድረሱ ግልጽ ነው። ነገር ግን በዝርዝር ተጠንቶ የጉዳቱ መጠን መታወቅ አለበት። ጦርነቱ በኢኮኖሚው ላይ እያደረሰ ያለውን ጫና ለማሳየት ያህል ባለፈው አንድ ወር ብቻ መንግሥት በጦርነቱ ምክንያት ለፈጠረው ሰብዓዊ እርዳታ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር አውጥቷል›› ብለዋል።
በዚህ ላይ ወታደራዊ ወጪዎች ሲታከሉበት ከባድ የዋጋ ግሽበት ጫና በኢኮኖሚው ላይ እንደፈጠረም ገልጸዋል። መንግስት ሕግ ለማስከበርና የአገሪቱን ሰላም ለመመለስ ሲል ከፍተኛ ሀብት ከሌሎች የኢኮኖሚ ዘርፎች ለማዘዋወር መገደዱንም አክለዋል።
በወቅቱ የትግራይ ጦርነት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ መፍጠር የጀመረው ጫና የሚታይና መንግሥት የማይክደው መሆኑን ያመላከቱት ዶክተር እዮብ፣ ጦርነቱ ያስከተለው ወጪና እየፈጠረ ያለው ጫና ቀላል ባይሆንም ኢኮኖሚው የቆመባቸው መሰረቶች እንዳልተሸረሸሩ ይልቁንም የተሻለ አፈጻጸምና ተስፋ ስለመኖሩ ነው አጽእኖት የሰጡት።
የተለያዩ የምጣኔ ሀብት ምሁራን በአንፃሩ፣ ለጦርነቱ ወጪ የሚደረገው ሀብት ለሌላ ኢኮኖሚያዊ ዓላማ ይውል የነበሩ መሆኑንም በመጠቆም ጦርነቱ ዛሬም ሆነ ነገ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እንደሚያቆስለው ሲገልጹ ይሰማል። ከዚህ ባሻገር ከጦርነቱ በኋላ በተለይም ሁለትና ሶስት ዓመታት ሊፈጠሩ የሚችሉ ጫናዎች ከባድ ሊሆኑ እንደሚችሉም ይተነብያሉ።
ለመሆኑ ጦርነት በአንድ አገር አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ ምን አይነት ጫና አለው? የሰሜኑ ጦርነት በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ያለው ጫና ምን ይሆን? በቀጣይስ የኢኮኖሚ ቀውሱን ለመቋቋም በሁሉም ረገድ ምን መደረግ ይኖርበታል? የሚል ጥያቄ በማንሳት የተለያዩምሁራንን አነጋግረናል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ መምህሩ ፍሬዘር ጥላሁን፣ ‹‹መጠኑ ይለያይ እንጂ እንደ ጦርነት ውድ ኢንቨስትመንት የለም። ጦርነት ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅና በግብር ብቻ መወጣት የሚከብድ ጭምር ነው፣ መንግሥታትን ብድር እንዲጠይቁ ከሚያስገድዱ ክስተቶች አንዱና ዋነኛውም ጦርነት ነው›› ይላሉ።
እንደ አቶ ፍሬዘር ገለጻ፣ በጦርነት ወቅት ከሰብአዊ ቀውሱ ባሻገር የአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ይገባል። ከምርት አንጻር ብንመለከተው አንድ አገር ጦርነት ውስጥ ካለ አምራች የሚባለው ሃይል በጦርነት ውስጥ ተሳታፊ ስለሚሆን ምርትና ምርታማነትን ሊቀንስ ይችላል።
ከዚህ ባሻገር የመንግሥት ወጪ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር እና የኑሮ ውድነትን ሊያባብስ እንደሚችል የሚያስገነዝቡት አቶ ፍሬዘር፣ በተለይም ‹‹የመንግሥት ብድር በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል፣ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ላይም ከባድ ተጽእኖ ያስከትላል›› ይላሉ።
በዚህ እሳቤ የሚስማሙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት ዶክተር ብርሃኑ ደኑ፣ መጠኑ ምንም ይሆን ጦርነት በተለይ በአገራት የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት ላይ የሚያስከትለው ጫና በቀላሉ የሚይታይ እንዳልሆነ ያስረዳሉ።
እንደ ዶክተር ብርሃኑ ገለፃም፣ በአንድ አገር ኢንቨስትመንት ለመሳብ ብሎም ኢንቨስተሮችን ለመሳተፍ የሰላም ድባብ ወሳኝ ነው። ኢንቨስተሮች ደግሞ መዋእለ ነዋያቸውን ፈሰስ ከማድረጋቸው አስቀድሞ የሚጠይቁት የአገሪቱን ሰላም መሆን ነው።
አንድ አገር ጦርነት ውስጥ በምትሆንበት ወቅት በተለይም ኢንቨስትመንት ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ ይፈጠራል። ኢንቨስተሮች ሙሉ እምነት እንዳይኖራቸውና መዋእለ ነዋያቸው ፈሰስ ከማድረግ እንዲታቀቡ ያደርጋል። ምርት ገበያ እንዳይደርስ እንቅፋት ይሆናል። በተለይ አዲስ ኢንቨስትመንት ማግኘት ይበልጥ ከባድ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ውስጥም ቢሆን በአሁኑ ወቅት ነባር ኢንቨስትመንቶች ናቸው እንጂ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ወደ ኋላ እያሉ እንዳሉ የሚጠቁሙት የምጣኔ ሀብት ምሁሩ፣ ጦርነቱም አዳዲስ ኢንቨስትመንቶች ላይ ከፍተኛ ተፅእኖ እንደሚያሳድርም ጥርጥር የላቸውም።
መሰል የኢኮኖሚ ጫናዎችን የሚዘረዝሩ ሌሎች ምሁራንም፣ ኢትዮጵያ በጦርነቱ የሚደርስባት የኢኮኖሚ ቁስል የከፋ እንደሚሆን ይተነብያሉ። አቶ ፍሬዘር በአንፃሩ፣ የኢኮኖሚ ጉዳት መጠኑን ለመረዳት የጦርነቱ ርዝመት እጅግ ወሳኝ መሆኑን ያሰምሩበታል። ከጦርነቱ በኋላ በተለይም ሁለትና ሶስት ወራት ወይንም ዓመታት ሊፈጠሩ የሚችሉ ጫናዎች ግን ቀላል የሚባሉ እንዳልሆኑ አጽንኦት ይሰጡታል።
በተለይ በጦርነቱ ምክንያት የደረሰው የመሰረተልማት ውድመት ከፍተኛ እንደሆነና ውድመቱን ዳግም ወደ ነበረበት ለመመለስ ወይም መልሶ ለመገንባት ከፍተኛ ካፒታል እንደሚጠይቅ ፣ ከፍ ሲልም እንደ አዲስ መነሳትን ሳይቀር ሊጠይቅ እንደሚችልም ያስገነዝባሉ። ይህም ‹‹ኢትዮጵያ ከጦርነቱ መጠናቀቅ በኋላም ወደ ግብርና ወይንም ኢንዱስትሪው ልማት እንዳትሸጋገር ማነቆ መፍጠሩ የማይቀር ነው›› ይላሉ።
በፈረንሳይ ፓሪስ ‹‹school of advanced studies in social sciences Paris –/EHESs/የፒኤች ዲ ተማሪ የሆኑት ጌታነህ ውድነህ ፣‹‹ሰላም እድገትና ልማት ቀጥታ ግንኙነት አላቸው። ኢትዮጵያ ከጦርነቱ አስቀድሞ የኢኮኖሚ እድገትን ስታዝመዘግብ ቆይታለች። የተሻለ ምርታማነት ብሎም የገቢ ምንጭ ነበራት። የዚህም ዋነኛ ምክንያት አገርና ህዝብ ሰላም ስለሆኑ ነው›› ይላሉ።
የሰሜኑ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ግን ነገሮች መልካቸውን መቀየራቸውን የሚጠቁሙት አቶ ጌታነህ፣ ‹‹ጦርነቱ የበላው ኢኮኖሚ በጣም ከፍተኛ ነው፣ አገሪቱ ለጦርነት የምታወጣው ገንዘብም በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ወደ ኢኮኖሚ ጫና የሚሄድ ነው›› ይላሉ።
ጦርነቱ የሚያስከትለውን የኢኮኖሚ ጫና ለማካካስ የተለያዩ የአጭር እና የረጅም ጊዜ መፍትሄዎች እስካልተቀመጡ ድረስ ቀጣዩ ጊዜ ከባድ እንደሚሆን ስጋታቸውን የሚጠቁሙት አቶ ጌታነህ፣ ‹‹ጦርነቱ የኢኮኖሚ አብዮት ይዞ እንዳይመጣ ያስፈራል ፣ አንድ ጊዜ የኢኮኖሚ ቀውስ ከተነሳ ደግሞ ፖለቲካው ሊሸከመው አይችልም፣ በቀላሉ መፍትሄ ሊሰጠው አቅም አይኖረውም›› ይላሉ። በሱዳን የኦማር ሐሰን ኧል በሺርን መንግሥት የገለበጠው ይህ የኢኮኖሚ ቀውስ መሆኑን ያስታውሳሉ።
እስካሁን ባለው ሂደት የኢትዮጵያ ህዝብ ጦርነቱ ያስከተለውን ቀውስ ተቀብሎ በሆደ ሰፊነት እያስታመመ መሆኑን የሚያመላክቱት ምሁሩ፣ ‹‹ይሁንና ጦርነቱ ጊዜ እየወሰደና እየተራዘመ በመጣ ቁጥር ለመንግሥት በጣም አደጋ ነው›› ይላሉ።
ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ አስተያታቸውን የሚያጋሩት ምሁራን ‹‹ጦርነቱ የሚያስከትለውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ተቃቁሞ ለመዝለቅ ብሎም አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ምን ሊደረግ ይገባል››? ለሚለው ጥያቄ የተለያዩ የመፍትሄ ምክረ ሃሳቦችንም ይሠጣሉ።
አቶ ፍሬዘር ‹‹በተለይ ሰላም የሰፈነባቸው ክልሎች ከሁሉ በላይ አምራች የግብርናና የኢንዱስትሪ አካባቢዎች አቅማቸውን አሟጠው መስራት የግድ ይላቸዋል። ምርት ማምረት ሲገባው በጦርነት ምክንያት ያላመረተውን አርሶ አደር የመደገፍ ተጨማሪ ኃላፊነት እንዳለባቸው መረዳት ይገባቸዋል ነው›› ያሉት።
ሰላም የሰፈነባቸው አካባቢዎች ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ሁነኛ ዋስትና መሆን እንደሚጠበቅባቸው ያስገነዘቡት አቶ ፍሬዘር፣ የሚያመርቱት ምርት የአካባቢያቸውን ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን እስከ አገር መመገብ ሊሸጋገር እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ የግድ እንደሚላቸውምአጽእኖት ሰጥተውታል።
ከሁሉ በላይ ‹‹ጦርነት የግጭቶችና አለመግባባቶች መፍቻ የመጀመሪያ አማራጭ መሆን አለበት ብዬ አላምንም›› የሚሉት አቶ ፍሬዘር፣ ሰላምን ማምጣት ወደ የሚቻልበት መንገድ መራመድ ለሁሉም ቀውስ ምላሽ እንደሚሆን ታሳቢ ማድረግ እንደሚያስፈልግም ሳያመላክቱ አላለፉም።
አቶ ጌታነህ በበኩላቸው፣ መንግሥት ይህንን ጦርነት ፈጣን መቋጫ ካላገኘለት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አደጋ እንደሚያመጣና ተሻጋሪ ውጤቱ ደግሞ ወደ ፖለቲካው የሚያልፍ መሆኑን ተገንዝቦ ልዩ ጥንቃቄ መደረግ እንዳለበት ይመክራሉ።
‹‹ ኢኮኖሚው በመታደግ ሂደት በተለይም ትልቁን የአገሪቱ ኢኮኖሚ መሸከም የሚችለው የወጣት ሃይል ታሳቢ ያደረጉ ተግባራትን ማከናወንና ወጣቱን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢኮኖሚው ሁነኛ አካል ማድረግ የግድ ያስፈልጋል ነው›› ያሉት።
የአርሶ አደሩ ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር የተለያ ድጋፎችን ማመቻቸት እንደሚገባና ለአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠት ብሎም ጥያቄያቸውን በፍጥነት መመለስ የግድ ስለመሆኑም አጽእኖት የሰጡት አቶ ጌታነህ፣ ለአምራቾች ከቀረጥ ነፃ እድሎችን መፍጠርን ጨምሮ የተለያዩ ማበረታቻዎችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልም አስምረውበታል።
‹‹ግርግር ለሌባ ይመቻል›› እንደሚባለውም አገር በጦርነት ላይ ስትሆን በተለይም የኢኮኖሚ ጤና በህገወጦች እንደሚታወክ የተለያዩ የምጣኔ ሀብት ምሁራን ይስማሙበታል። ህገወጥነቶች በተለይ የኢኮኖሚ አሻጥር በመጠንም ሆነ በአይነት እንደሚጨምር ይገልፃሉ።
ይህን እሳቤ የሚደግፉት አቶ ጌታነህም ፣በጦርነት ወቅት አጋጣሚን ለግል ጥቅም የሚፈልጉ ከዓለም አቀፍ ግዙፍ ተቋማት ጀምሮ በመንግሥታትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ የኢኮኖሚ አሻጥር ሊፈጸም እንደሚችል ጠቁመው፣ ይህን እኩይ ዓላማ ለማክሸፍና አደጋውን ለመቀነስም ግልጽ የሆነ አሰራርና የቁጥጥር ሥርዓትን መተግበር በተለይም ህብረተሰቡ ዋነኛ የቁጥጥሩ ተዋናይ ማድረግ እንደሚስፈልግ አጽእኖት ሰጥተውታል።
ዶክተር ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ‹‹ኢትዮጵያ በጦርነቱ የምትከፍለው ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ ጉዳቱ ይበልጥ እንዳይባባስ ህግ የማስከበር ዘመቻውን በወታደራዊ የበላይነት እና ድል ፈጥኖ ማጠናቀቅ ይገባዋል። የህግ ማስከበር ዘመቻው ከተጠናቀቀ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለንተናዊ ሰላምን ለማረጋገጥና ኢኮኖሚው እንዲጠነክር ለማድረግ ወቅታዊ ችግሮችን ለይቶ በማውጣት አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይገባል ነው›› ያሉት።
በምጣኔ ሀብት ምሁራኑ ምክር ሃሳብ እንደተመላከተውም፣ የጦርነቱን የኢኮኖሚ ተጽእኖ ለመቋቋም የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ትኩረት ማድረግ ያለበት የአገሪቱን የማምረት አቅም በከፍተኛ ደረጃ ማቀድና መምራት ነው። ጦርነቱ ለአንዲት አገር ህልውና የሚካሄድ እስከሆነ በክልሎች መካከል የምርትና የአገልግሎት ተደጋጋፊነት ወሳኝ ነው።
ከሁሉ በላይ ኢትዮጵያ በጦርነት ውስጥ የምታሳልፈው ጊዜ በተራዘመ ቁጥር የሚደርሰው ኢኮኖሚያዊ ጉዳትም የዚያን ያህል እየጨመረ ይሄዳል። በመሆኑም ጦርነቱ በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት መቀነስ ይቻል ዘንድ ጦርነቱ በተቻለ ፍጥነት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲጠናቀቅ ስትራቴጂክ ዕቅዶችን ነድፎ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል። መንግሥት እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎች በተቻለ ፍጥነት አጠናቅቆ ወደ መደበኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎችና የልማት ሥራዎች እንዲመለስ ከፍተኛ ርብርብ መደረግ አለበት።
በጦርነት ላይ ያለ መንግሥት የገቢ አቅሙን ለማጠናከር የገቢ ምንጮችን መገምገምና ልዩ ልዩ ዘዴዎችን መቀየስ አለበት። የኢኮኖሚውን መዋቅር እየለወጡ የስራ እድል በመፍጠርና ምርትን በማሳደግ ላይ ትኩረት ከተደረገ ኢትዮጵያ ችግሩን ትወጣዋለች። በተለይ በግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ በአሁኑ ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች የተጀመሩ የበጋና የኩታ ገጠም እርሻዎችን ይበልጥ አጠናክሮ መቀጠልም ያስፈልጋል።
ታምራት ተስፋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2014