ሁላችንም እንደምንረዳው የምጥ ህመም ከህመሞች ሁሉ የላቀ እጅግ አስጨናቂ ህመም በጣም ከባድ ነው። አንዲት ነፍሰ ጡር ሴት ከመውለዷ በፊት በደቂቃዎች ልዩነት ጠንከር እያለ የሚሄድ የምጥ ህመም ስሜት ይሰማታል። ይህንን የምጥ ህመም እንደምንም ተቋቁማ የሚረዳትን ሰው መጥራት ካልቻለች ደግሞ በእርሷም ሆነ በጽንሱ ላይ ሊደርስ የሚችለው አደጋ እጅግ ከባድ ነው።
ብቻዬን አምጣለሁ፤ ልጄንም እገላገላለሁ፤ ብላ ካሰበች ደግሞ ስህተት ከመስራቷም በላይ ለከፍተኛ የደም መፍሰስ ተጋልጣ በእርሷ በሚወለደው ህጻን ላይም ሞትን የመጥራት ሟርት ይሆንባታል። በመሆኑም ለዚህች በምጥ ለተያዘች ሴት እርዳታ ያስፈልጋታል፤ ህመምን ተቋቁማ አዲሱን ልጇን ትታቅፍ ዘንድ የባለሙያ እርዳታንም በእጅጉ ትሻለች። ይህ ከሆነላት ደግሞ ምጧ ቀሎ ፍልቅልቅ ህጻን የመታቀፍ እድሏ ሰፊ ይሆናል። ተረቱስ የሚለው “ምጡን እርሺው ልጁን አንሺው“ አይደል።
ኢትዮጵያዬ ዛሬ ያለችበት ሁኔታ በምጥ ከተያዘችው እናት ጋር በጣም ተመሳሳይ ነው። በአራቱም ማዕዘን የወጠሯት ጠላቶቿ ምጧን በየደቂቃው አቅሙ ከፍ እንዲል የህመም ስሜቷም ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ እያደረጉ ነው። አሁን ህመሙ በርትቶባታል ልጁም አልወለድ ብሎ እያሰቃያት ቢሆንም የእስከ ዛሬው ጥንካሬዋ እንዳይለያት ብዙ እየታገለች ነው።
በዚህ ጊዜ ከምጡ ስቃይ ገላግሎ ልጇን በእጇ የሚያሳቅፋት አዋላጅ ትፈልጋለች። አሁን እንደማየው ግን ቀድመን የተወለድን ልጆቿ ይህ የህመሟ የምጥ ስቃይዋ የገባን የተረዳንላት አይመስለኝም ፤ እንደውም ምጧ እንዲባባስ ለማድረጉ የእኛው ችላ ባይነት ያለበትም ይመስለኛል።
ኢትዮጵያ ምጥ ከጀመራት ዋል አደር ብላለች፤ ምንም እንኳን እኛ ቀድመን የተወለድን ልጆቿ እንደ ቀልድ ብናልፈውም እሷ ግን ከታመመች ዓመታት ተቆጥረዋል። ያኔ ወንድም ወንድሙን ለተራ ጥቅም ብሎ የገደለ ለት ፣ በእኩይ ተግባር አነሳሾች ምክንያት ሕዝብ በሕዝብ ላይ የተነሳ ለት፣ ብዙ ጸሎትና ምህላ ተደርጎ እንኳን ለራሷ ለዓለም በረከት የሚፈስባቸው ቤተ እምነቶቿ የእኩይ ተግባር ዓላማ ማስፈጸሚያ ሆነው ጥቃት የደረሰባቸው ለት፣ በሺህ ዓመታት ታሪኳ ያከማቸቻቸው ቅርሶች ለጥቃት ሲዳረጉ፣ ዜጎች በአገራቸው ላይ ሰርተው መብላት አቅቷቸው የባዕዳንን ደጅ ሲጠኑ ነበር፤ የኢትዮጵያችን ምጥ የጀመረው። ነገር ግን እኛ ቀድመን የተወለድን ልጆቿ ጆሮም አይንም ስላልሰጠናት እነሆ ዛሬ ላይ ምጧ ተባብሶ የአንድ አገር ዜጎች ለተራ ፖለቲካዊ ትርፍ ብለው እየተገዳደሉ ስደትና መከራ እየበዛ በዛው ምጡም እየበረታ ነው ፤ ታዲያ ማነው አዋላጁ?
ልክ የዛሬ ዓመት በጥቅምት ወር በአሸባሪው ህወሓት የትንኮሳ ጦርነት የተነሳ እየተባባሰ የመጣው የኢትዮጵያችን ምጥ እነሆ አንድ ዓመት ሙሉ አዋላጅ ሳይገኝለት ምጡም አቅሙን እያበረታ ዛሬ ላይ ደርሰናል። ቀድመው የተወለዱት ልጆቿ ከየአቅጣጫው አገራቸውን ለማዋለድ ቢተሙም የአሸባሪው ጋሻ ጃግሬዎች አይዞህ ባይነት ብሎም የተለያዩ የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሕብረት ችግሩን በታሰበው መንገድ ለመፍታት ሳያስችል ቀርቷል።
በእኔ እይታ ፖለቲከኞች በሕዝብ ምርጫም ሆነ በሌላ አማራጭ መንበረ ስልጣኑን የሚይዙት ሕዝቤ ያሉትን ኅብረተሰብ ለማገልገል ነው። ይህ ሕዝብ በቃኝ አሁን ደግሞ የሥርዓት እንዲሁም የመሪ ለውጥ እፈልጋለሁ ካለ ድምጹ መሰማት መብቱም መከበር አለበት፤ ነገር ግን እየሆነ ያለው ይህ አይደለም። ዓመታትን በሥልጣን ላይ የቆየው አሸባሪው ህወሓት በአልጠግብ ባይ አመሉ ዛሬም ኢትዮጵያን ምጥ ላይ ጨምሯታል። ህመሟ በርትቶ አደጋ ላይ ሊጥላትም አቅዷል።
ያለፉትን 30 ዓመታት ሕዝብ እንደ ሕዝብ ሳይከበር በአገሩ ጉዳይ ባዕድ ሆኖ የባዕዳንን ፍርፋሪ ጠባቂ ተደርጎ መኖሩ ሳያንስ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ አንገቷን ቀና ልታደርግ ነው፤ እንደ ሕዝብ በአገራችን ተሰብስበን ክፉውንም ደጉንም ተጋርተን ልንኖር ነው ስንል በፍጥረቱ በሁከት ተጸንሶ በሁከት የተወለደውና ያደረው አሸባሪው ህወሓት አገር የማሸበር ስራውን ገፍቶበት፤ ይባስ ጦርነት ከፍቶ እነሆ ዛሬ ብዙዎች እየሞቱ፣ ንብረት እየወደመ ፣ ስደት እየበረከተ ነው።
ከወትሮውም ጠላት የማታጣው አገራችን ዛሬ ላይ በየአቅጣጫው ጣታቸውን እየጠቆሙባት ያሉ በዝተዋል። “ኮሽ ሲል አንወድም” እያሉ በየአገራቱ እጃቸውን የሚያስገቡት ብሎም ሽብርተኛ ብለው አንድን ቡድን ለመፈረጅና እርምጃ ለመውሰድ ለማስወሰድ ጊዜ የማይወስድባቸው ምዕራባውያንና ተቋማቶቻቸው ዛሬ ኢትዮጵያ ላይ እየሆነ ያለውን አይቶ እንዳላየ ከማለፍ ጀምሮ እነሱም የእኩይ ተግባሩ ተባባሪ ሆነው በሚያስተዳድሯቸው መገናኛ ብዙሃኖቻቸው በመለፍለፍ ከአሸባሪዎች ጎራ ተመድበው ፍርደ ገምድል ሆነው ቀጥለዋል።
ለእኛ እንደዚህ መሆን ተጠያቂዎቹ ራሳችን ነን፤ ፖለቲከኞቻችን ለግል ፍላጎታቸውና ለስልጣን ጥማታቸው ብለው ኢትዮጵያዊነታችንን ፍቅር አብሮነታችንን ገድለው ባይከፋፍሉን፤ ጥላቻን ባይዘሩብን ፣ በዘረኝነት ቁጥጥር ስር ባያስገቡን ኖሮ እዚህ ባልደረስን ነበር። ሕዝቡም የቀደመ ኢትዮጵያዊ አብሮነቱ ጥሎ ይሄንን የክፋት መንገድ ባይከተል ፤ ቆም ብሎ ክፉ ደጉን ማስተዋያ ልቦናውን አብርቶ ቢሆን ዛሬ ለመስማት የሚቀፈንን እዚህም እዚያም ተገደሉ፣ ሞቱ ተፈናቀሉ የሚለውን ዜና መስማት የቀን ተቀን ተግባራችን ባልሆነ ነበር።
እንግዲህ አገር እንዲህ እንደአሁን በምጥ ላይ ስትሆን ከእኛ ቀድመን ከተወለድን ልጆቿ ብዙ የሚጠበቅ ነገር አለ። ከምንም በላይ የሚፈለግብን አንድነታችን አብሮነታችን መተሳሰብ ፍቅራችን ብቻ ነው። አንድ ከሆንን እንኳን አሸባሪው ህወሓት የሚፈጽመውን የአልሞት ባይ ተጋዳይነት የሽብር ጥቃት ቀርቶ ሌላም እንመክታለን።
አንድ ከሆንን በስንዴ እርዳታቸው ሊያንበረክኩን የሚፈልጉ ሃያላን አገራትን ዞር በሉ ብለን ለራሳችን እንደማናንስ ማሳየት እንችላለን። አንድ ከሆንን ጠላትን መመከት እንዳለ ሆኖ በተሰማራንበት መስክ ላይ ጠንክረን በመስራት ራሳችንን ችለን ማንነታችንን ለዓለም እናሳያለን፤ በአጠቃላይ አንድ ከሆንን አገራችንን አዋልደን ፍልቅልቅ ልጇን በክንዷ እናሳቅፋታለን። እኛም ታላላቆቹ በአዲሱ ልጅ የመጣውን በረከት ተቋድሰን በብልጽግና ጎዳና እንጓዛለን።
በተቃራኒው እንሆናለን ካልን ግን አገራችን ምጧ ተባብሶ ብቻዋን ለመውለድ በምታደርገው ጥረት መካከል እሷንም አዲሱን ህጻንም እናጣዋለን። ያን ጊዜ ደግሞ ከየአቅጣጫው ሊቀራመቷት ያሰቡት እንደ ጉንዳን ወረው እኛነታችንን ሊበዘብዙ ላቀዱ ሁሉ ምቹ እንሆናለን። እንግዲህ ምርጫው የራሳችን ነው። አበቃሁ።
በእምነት
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2014