ዛሬ አገር ስላቆሙ ሻካራ እጆችና አገር ለማፍረስ ስለሚተጉ ለስላሳ እጆች እናወራለን። ከምታውቁት ውጪ የምነግራችሁ አንዳች እውነት ግን የለኝም።የረሳችሁትን በማስታወስ ለአገር እንድትተጉ ላነሳሳችሁ እሞክራለሁ። የረሳችሁት እውነት ግን ምንድነው? የረሳችሁት እውነት ኢትዮጵያዊነትን ነው። ብዙዎቻችን ብዙ ነገር ስናውቅ የሁሉ ነገር ጅማሬ የሆነችንን አገራችንን ግን አናውቃትም።
በብዙ ዲግሪና ማዕረግ ተከበን ስለአገራችን ትላንት የምናውቀው የሚጠበቅብንን ያህል አይደለም። አገሩን ያላወቀ፣ ታሪኳን ያልመረመረ ትውልድ በምንም ነገር ቢሞላ ጎደሎ መሆኑ የማይቀር ነው። በዚህም ጎደሎ ነን እያልኩ ነው። ዓለምን ብንዞር፣ ጨረቃ ላይ ብንወጣ እንኳን ኢትዮጵያን ሳናውቅ የሚኖረን እውቀትና ጥበብ አይበጀንም።
ታላቁ ጥበባችን በታላቅ ታሪካችን ውስጥ ነው ያለው። ታላቅ ታሪካችን ደግሞ አገርና ሕዝባችን ነው። የትም ቦታ በምንም ሁኔታ ላይ ብንቆም የተነሳችሁት ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ነው። የትም ቦታ ላይ በምንም ክብርና ማዕረግ ቁሙ መጀመሪያችሁ የጥቁርነት ሞገሳችሁ ነው።
ሀበሻዊነትን ረስታችሁ የሚኖራችሁ ልዕልና የለም። ዛሬ ላይ አገራችን ኢትዮጵያ አገርና ሰውነት ባልገባቸው የአሸባሪ ህወሓት ቡድኖች ብዙ መከራን እያስተናገደች ትገኛለች። ያለፉት አስራ ሁለት ወራት ለኢትዮጵያ የምጥ ወራቶች ነበሩ። አንዳንዶች አድምቀው ሲስሏት እንደ ህወሓት ያሉ ቡድኖች ደግሞ ያደበዝዟታል። አንዳንዶች ሲሞቱላት አንዳንዶች ደግሞ ይገሏታል። የረሳንው ታሪክ ይሄ ነው..ከእጇ በልተን ወጪት ሰባሪ መሆናችን። ከጉያዋ አድገን ጡት ነካሽ መሆናችን ነው ።
ኢትዮጵያ አገራችን የሻካራ እጆች አብራክ ናት። ብዙ ታሪካችን፣ ብዙ ገድላችን በእኚህ ወያባ እጆች በኩል የመጡ ናቸው ። ዛሬ ላይ ግን ሌላ ናት። ብዕር የጨበጡ፣ እውቀት የቀሰሙ ፀዓዳ እጆች የሻካራ እጆችን ውለታ በልተው ሊያፈርሷት ትግል ላይ ናቸው። ዛሬ ከትላንት የተሻለ ነው። እውቀታችንንና ቴክኖሎጂውን ተጠቅመን የተሻለች ልናደርጋት ሲገባን እስከ ሲኦል ድረስ ሄደውም ቢሆን ሊያፈርሷት የሚዝቱ መኖራቸው የዘወትር አግራሞቴ ነው።
በዚህ ሥልጡን ዘመን ላይ በሀሳብ ተሟግቶ አገር መለወጥ እንጂ አገር ለማፍረስ ጫካ መግባት ምን ሊባል እንደሚችል እናንተ ስም ስጡት። ሻካራ እጆች ያጸኗት አገር በምንም ሁኔታ በለስላሳ እጆች አትፈርስም። የኢትዮጵያ ጠላቶች ይሄን እንዲያውቁ እፈልጋለሁ። ለስላሳ እጆቻችን በሥራ ሻክረው የአባቶቻችንን አይነት አገር እስኪፈጥሩ ድረስ መትጋት ከሁላችንም የሚጠበቅ አደራ ነው።
ከዚህ እስከዛ በሻካራ እጆች ተስለናል። የደጋግ ልቦች መብቀያ አውድማ ነን። የአባቶቻችንን መልክ መልካችን ላይ ስለን የሚኖረን ፈረንጅኛ መልክና እውቀት የለም። ትላልቆቹ ፈላስፎች የጥበብ ሁሉ ጥግ ራስን ማወቅ ነው ይላሉ። ራስን ሳያውቁ የተጓዙት ጎዳና ሩቅ አያደርስም። ራስን ረስቶ የሄዱበት ጎዳና ጥግ የለውም እንዲህም ይላሉ።
ጥጋችን ኢትዮጵያ ናት። ክብራችሁ ኢትዮጵያዊነት ነው። መነሻችን ሻካራ እጆች ናቸው። ከዚህ ውጪ አንዳች እውነት የለንም። በሻካራ እጆች የቆነጀን የጽኑ ክንዶች አብራክ ነን። በጥቁርነት የተጻፍን የአዳፋ መዳፎች መልኮች ነን። ማንነታችን ይሄ ነው። ጉዟችንን ከዚህ መጀመር ይጠበቅብናል ።
መግቢያዬ ላይ ምን ረሳን ብዬ ጠይቄ ነበር፤ የረሳነው ራሳችንን ነው። የረሳነው ታሪካችንን ነው። የረሳነው መነሻችንን ነው። ወደ ራሳችሁ በመመለስ ወደ አባቶቻችን ሻካራ እጆች እንመልከት ለማለት እወዳለሁ።
የአባቶቻችን እጆች እውነት ነበሩ። ብዙ ነጻነት፣ ብዙ የአገር ፍቅር ብዙ ርህራሄም የዋጃቸው። እኚህ እጆች ብርቅ እጆች ነበሩ.. እኚህ እጆች ለዓለም ሥልጣኔን ያሳዩ ብርሃናማ እጆች ነበሩ። እኚህ እጆች የዓለም መልኮች ነበሩ። በዘፍጥረት የነበሩ ድህረ ዓለምም የከበሩ ፋና ወጊ አሻራዎች ነበሩ። ወደ ራሳችን እንመለስ። አገር ወደ ሠሩ እጆች እንመልከት ።
ኢትዮጵያ በቀደሙት ዘመናት የታላላቅ ስልጣኔዎች ባለቤትና ዓለምን የፈጠረች ነበረች ። ከታላቅነታችን ወጥተን ወደ ታናሽነት ማሽቆልቆላችን ከምን መነጨ ? ይሄን የቁልቁለት ጉዞ መቼም ይጀምር መቼም አሁን ላይ በእኛ በልጆቿ ልናስቆመው ይገባል።
ለአገራችን መልካም ማሰብ ፣ መልካም ማድረግ የዜግነት ግዴታችን ነው ። ከዚህ እውነታ ጋር መጣላት ሲጀመር እና እንደ አሸባሪው ህወሓት አዕምሮ ሲጎለን ለውይይት ከመቀመጥ ይልቅ ለኃይል ጫካ መግባትን እንመርጣለን ። እንደ ህወሓት ሆድ ብቻ ሲኖረን ከአገርና ሕዝብ ይልቅ ለራሳችን ብቻ ማሰ ብ እንጀምራለን ።
አገራችን ያስተማረችን ከድህነት እንድናወጣት እንጂ ከድጡ ወደ ማጡ እንድንወስዳት አይደለም። በእውቀታችን ለችግሯ መፍትሔ እንድንሰጣት እንጂ በችግሯ ላይ ችግር እንድንሆናት አይደለም። አብዛኞቻችን አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ የገባን አይመስለኝም። ውለታ ከመመለስ ይልቅ ውለታ የምንበላ ሆነናል ። ብድር ከመመለስ ይልቅ ለጥፋት የምንሰናዳ ሞልተናል። የአሸባሪው ህወሓት እውነትም ከዚህ የዘለለ አይደለም። ለሃያ ሰባት ዓመት በአምባገነን ሥርዓት አገር መራ። ከሥልጣን ሲወርድ ለዳግም ጥፋት ጫካ ገባ።
ከትልቅነት ወደ ትንሽነት መሄድ የሰውነት ግብር አይደለም። እጃችንን ለአገራችን መልካምነት እናሰራ። ልባችንንና መንፈሳችንን ለበጎ ዓላማ እናስገዛ። ኢትዮጵያዊነት ጥልቅ፣ ድንቅ፣ ምጡቅ ማንነት ነው። ከዚህ ማንነት ውስጥ በመውጣችን እድለኛ ትውልዶች መሆናችንን በአግባቡ እናስተውል። በሕይወታችን በብዙ እውነት ልንልቅ እንችላለን ። እንደ ኢትዮጵያና እንደ ኢትዮጵያዊነት ታላቅ እውነት ግን ከየትም ልናገኝ አንችልም ።
ታላቁ እውነታችን በታላቅ ታሪካችን ውስጥ ነው። ራሳችንን እንበርብር ። ታሪክ ስለሌላት አሜሪካ ከማወቅ ታሪክ ስላላት ኢትዮጵያ አገራችሁ ማወቅ ለነገ ማንነታችን ትልቅ አቅም ነው ። ታሪክ ስለሌለው ነጭ ከምንጠይቅ ታሪክ ስላላቸው ቀደምት አያቶቻችሁን እንጠይቅ ። እኔ በግሌ ከሕይወቴ እንዲጠፋ የማልፈልገው አንድ እውነት ኢትዮጵያዊነት ነው።
ኢትዮጵያዊነት አስተሳሰብ ነው። ኢትዮጵያዊነት በትላንትና በዛሬ በነጋችንም ውስጥ በዝቶና ተትረፍርፎ የሚገኝ ፀዓዳ መልክ ነው። ይሄን መልካችንን ነው የዘነጋነው ። ይሄን መልካችንን ነው ያጠየምነው ። ዛሬም ነገም አገር ያቆሙ ሻካራ እጆች ያስፈልጉናል። የአሸባሪው ህወሓት እጆች ለስላሳ እጆች ናቸው። መከራን ያላዩ፣ ከትላንት እስከ ዛሬ በድሎት የኖሩ ግን ደግሞ ፀዓዳ መልክን ላለበሰቻቸው ድሀ አገራቸው ሴራን የሚያሴሩ አዕምሮ ታዛዥ የጥፋት እጆች ናቸው ።
የቡድኑ ልቦች የክፋት ልቦች ናቸው። በውስጣቸው አገርና ሕዝብ የለም። ከትላንት እስከዛሬ ስለራሱ ብቻ ሲያስብ የመጣ፤ ዛሬም ስለራሱ በክፋት ተግባር ላይ የሚገኝ ነው ። እመኑኝ ካለ እኔና እናንተ ኢትዮጵያ ምንም ናት። ካለእኔና እናንተ ሻካራ እጆች እና ቅን ልቦች ወደፊት መራመድ አይቻላቸውም።
ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ከሚያስብላት አንዱ የእኔና የእናንተ ባህል፣ ሥርዓት፣ ወግና ልማድ ነው። ኢትዮጵያን የፈጠራት የእኔና የእናንተ ጉራማይሌ ቋንቋ፣ ጉራማይሌ መልክ ነው። ኢትዮጵያን የፈጠራት የእኔና የእናንተ ትላንትና ነው። ኢትዮጵያ ለእያንዳንዳችን ከአገርነት ባለፈ የእውነት ሰሌዳችን ናት። ኢትዮጵያዊነት የማንነታችን መታወቂያ ቀለማችንም ነው። በዚህ ሰሌዳ እና ቀለም ተምረንና ፊደል ቆጥረናል። በዚህ ሰሌዳ ላይ ተመላልሰን ዛሬን ማየት ችለናል። በዚህ ሰሌዳ ላይ ቆመን ዛሬ እየጻፈ ነው ያለው ታሪክ ግን በሻካራ እጆች የተሰራችውን ኢትዮጵያ በለስላሳ እጆች የማፍረስ አይነት ነው ።
ብዙ ሰው ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ከድህነት ባለፈ የጠቀመኝ የለም ይላል። ብዙ ሰው ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ካገኘሁት ይልቅ ያጣሁት ይበልጣል ይላል። ብዙ ሰው ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ኋላ ቀርነትን ነው ያተረፍኩት ይላል። ይሄ የእውቀት ማነስ የፈጠረው ስህተት ነው እላለሁ። ቆይ ለምን ነው ታላቅ ታሪክ የማይታየን? ለምን ነው ታላቅ ትላንት የተረሳን? ደግሞም ኢትዮጵያ ድሀ ናት ካልን ድሀ ያደረግናት እኔና እናንተ ነን። ሳንሠራና ሳንለፋ ተቀምጠን መብላት እየፈለግን እንዴት ነው ሥልጡን አገር የሚያምረን? የአሜሪካ ሥልጣኔ ከሰማይ የወረደ ወይም ደግሞ በተአምር የተገኘ አይደለም ፤ በሕዝቦቿ ሻካራ እጅ የመጣ እንጂ። ለምን እኔና እናንተ አገራችንን ማሳደግ አቃተን?ለምን ወደ ፊት መራመድ አቃተን? በኢትዮጵያዊነታችን ከመማረር ይልቅ ራሳችንን ይሄን ጥያቄ እንጠይቅ። ለአገራችን ምንም መሆን ተጠያቂዎች እኛ ነን። ኢትዮጵያ አገር የሆነችው እኔና እናንተ ስላለንባት ነው። ብዙዎቻችን ኢትዮጵያ ነፍስ ያላት ነው የሚመስለን። ብዙዎቻችን ሁሉ ነገራችንን ለአገራችን አደራ ሰጥተን ሳንሰራ መብላትን የምንሻ ነን። መንግሥት ቤት ድረስ እያመጣ እንዲቀልበን የምንፈልግም ብዙ አለን። ነገር ግን የአገራችን ድህነትና ብልጽግናዋም በእኛ በኩል የሚመጣ ነው። የአገራችን ገጽ እኛ ነን። ድሀ ያደረጓትም ሥራ ጠል ፀዓዳ እጆቻችን ናቸው። ታሪኳ ከእኛ አስተሳሰብ የሚቀዳ ነው።
በአገራችሁ ላይ ጣታችሁን የምትጠቁሙ መጀመሪያ እኔ ማነኝ? ለአገሬ ምን ሰራሁ ብላችሁ ራሳችሁን ጠይቁ። በሻካራ እጆች ላይ ቆማችሁ አትዘባበቱ። ዛሬን ያየነው በነሱ ነው። ሰው ያደረጉን እነዚያ ቆሻሻ እጆች ናቸው። ዛሬም ነገር ለነዚህ እጆች ዘለዓለማዊ ክብር ይገባል። የሻካራ እጆች ውለታ አለብን። እኔና እናንተ እንዲህ ሆነን የተሳልነው በነዚህ እጆች ነው። እኚህ ሻካራ እጆች የእኔና የእናንተ ጌጦች ናቸው። እኚህ ሻካራ እጆች በእያንዳንዳችን ዛሬ ውስጥ ደምቀው አሉ። እኔና እናንተ ብዙ እውቀት አሉን፣ ብዙ ጥበብ ብዙ ማስተዋል አሉን፣ ሕይወት በብዙ ያስተማረችን እንዲህም ነን ግን ደግሞ በብዙ ስህተት ውስጥ የቆምንም ነን።
እስኪ እንጠይቅ እስካሁን በኖርንበት ልክ ለአገራችን የሚሆን ምን መልካም ሥራ ሠራን? ለትውልዱ የሚሆን ምን አሻራ አሳረፍን? አደራ! ልጅ ነኝ፣ ተማሪ ነኝ፣ ሥራ ፍለጋ ላይ ነኝ፣ ሕይወት አልተመቻቸልኝም እንዳትሉኝ። ብዙዎቻችን ለምንም ነገር ሰበብ የምንፈልግ ነን። በአገር ጉዳይ ሰበብ አያስፈልግም። አገር የጋራ ማዕድ ናት። ለአገር ውለታ መዋል ለራስ ውለታ መዋል ነው።
ለአገር ውለታ መዋል ለሌሎች ውለታ መዋል ነው። ለአገር ውለታ መዋል ለትውልድ ውለታ መዋል ነው። እኛ የተፈጠርነው በትላንት የአባቶቻችን ውለታ ነው። እኛ ዛሬን ያየንው ሻካራ እጆች ውለታ ነው። የእኛስ ውለታ ምንድነው? ለአገራችን፣ ለሕዝባችን፣ ለትውልዱ የምንሰጠው መልካም ነገራችን ምንድነው?
በሌሎች ጸሎት፣ በሌሎች ሻካራ እጆች ቆመናል። የእኛስ ቀን መቼ ነው? እጆቻችን በስራ የሚሻክሩበት፣ ልቦቻችን መልካም ሀሳብ የሚያፈልቁበት ጊዜ መቼ ነው? ዛሬ ወይም ነገ ቢሆንስ? ለመልካም ነገር የሚረፍድ ቀን የለም። በጉብዝናችን ወራት አገራችንን እንጡሯት ። በልባችን ውስጥ ጽኑ የአገር ፍቅር ካለ ዛሬ ነገ ሳንል ውለታ መዋል እንችላለን። ቀና ልብ ካለን በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ሆነን ምርጡን ለአገራችን መስጠት አይከብደንም። አገር ለማገልገል ማደግና ባለጸጋ መሆን አይጠበቅብንም። አገር ለማገልገል መማርና ዲግሪ መጫን ግድ አይልም።
አገር ለማገልገል ሥራ መያዝና ሥልጣን ማግኘት ዐቢይ ጉዳይ አይደለም። እስክናድግ፣ እስክንመረቅ፣ ሕይወት እስኪመቻችልን ሳንጠብቅ አገራችንን ማገልገል ይቻለናል። አስተዋይ ሰው ለመልካም ነገር ጊዜ አያጣም። ልጅ ከሆናችሁ በሥርዓት በማደግ፣ ተማሪ ከሆናችሁ በትምህርታችሁ በመበርታት፣ ወዛደር ከሆናችሁ ደግሞ ሕይወትን ለማሸነፍ በርትቶ በመሥራት አገርን ማገልገል ይቻላል። ወላጅ ከሆናችሁ ለልጆቻችሁ ጥሩ ወላጆች በመሆን፣ ባለሥልጣን ከሆናችሁ አገራችሁንና ሕዝባችሁን በታማኝነት በማገልገል የዜግነት ግዴታን መወጣት ይቻላል።
እርዳታ ከኪስ የሚወጣ የሚመስለን ብዙዎች ነን። እርግጥ ነው ከኪስ በሚወጣ እርዳታ ማገልገል ይቻላል፤ እውነተኛ እርዳታ ግን ከልብ የሚወጣ ነው። ከኪሳችን ከምናወጣው ገንዘብ በላይ ልባችን ውስጥ ባለው መልካምነት አገርና ሕዝብ ማገልገል እንችላለን። አገር ለመርዳት ሕዝብ ለማገልገል ገንዘብ እስኪኖረን አንጠብቅ ። ቀናነት በራሱ እርዳታ ነው። መልካምነት አገልግሎት ነው። ፍቅርና ይቅርታ ከገንዘብ የበለጡ የነፍስ መፈወሻ ክኒኖች ናቸው።
መስጠት ከፈለግን የምንሰጠው ብዙ ነገር አለን። በጉልበት በእውቀት፣ በጎ በማሰብ በብዙ ነገር አሻራችንን ማሳረፍ እንችላለን። በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብትሆንም አገራችንን ለማገልገል ጊዜና ጉልበት አናጣም። ለምሳሌ እኔ ጸሐፊ ነኝ ። ስለ አገሬ መልካም በመጻፍና መልካም በማንበብ አገሬን ማገልገል እችላለሁ።
ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታዬን መወጣት እችላለሁ። እናንተም ባላችሁበት በማንኛውም ሁኔታ ላይ ሆናችሁ አገራችሁን በበጎ ማገልገል ይቻላችኋል። እጃችሁን ለስራ ሳትዘረጉና ልባችሁን ለቀናነት ሳታሰለጥኑ “ሀገሬ ምን አደረገችልኝ?” ማለት ትርጉም የለሽነት ነው ።
ሻካራ እጆች ያቆሟትን አገር ፀዓዳ እጆችን ይዘው በተንኮል የሰከሩ ጭንቅላቶች ሲተቿት እንደመስማት ምን የሚያም ነገር አለ። እኛ አባቶቻችንን ለመውቀስም ሆነ ለመተቸት አቅም የለንም። ከቻልን እንደነሱ በአንድ ቆመን ለልጆቻችን የምትሆን አገር እንሥራ። ከቻልን ከድህነትና ከልመና የሚያወጣንን የለውጥ አብዮት በጋራ እንፍጠር። ከቻልን በአባቶቻችን መንፈስ በዘመናችን ላይ ጀግና እንሁን። ካልቻልን ደግሞ ዝም እንበል።
አበቃሁ ቸር ሰንብቱ።
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16/2014