አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ባለፉት ስድስት ወራት ለ2 ሺ 360 የአዲስ፣ ማስፋፊያና ልዩ ልዩ ፕሮጀክቶች ለሚሰማሩ የውጭ ባለሀብቶች ፍቃድ መስጠቱን አስታወቀ፡፡
የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ መኮንን ኃይሉ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት በግማሽ ዓመቱ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ እያደገ መጥቷል፡፡ ኮሚሽኑ በዚህ ጊዜ ውስጥ ለ1ሺ 446 የውጭ ባለሀብቶችን ተቀብሎ ተገቢውን የኢንቨስትመንት መረጃ ለመስጠት አቅዶ 1ሺ 882 የሚሆኑትን በማስተናገድ የእቅዱን 160 ከመቶ በላይ ማከናወኑን አስረድተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ላይ በመሳተፍ በተደረገው ኢንቨስትመንቱን የማስተዋወቅ ሥራ አበረታች ውጤት እንደተገኝ ጠቁመዋል፡፡
በ2000 ዓ.ም በኢትዮጵያ የነበረው የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ካፒታል መጠን 215 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን በ2010 ዓ.ም መዳረሻ 3 ነጥብ 75 ቢሊየን ዶላር መድረሱን የገለፁት አቶ መኮንን እስከ አሁንም 5400 የሚደርሱ የውጭ ኩባንያዎች በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስት ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ከቅርብ ወራት ወዲህ ከተለያዩ የዓለማችን ሀገሮች ጋር የፈጠሩት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትና በሀገሪቱ እየተሻሻለ የመጣውን መረጋጋት ተከትሎ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ዘርፉ ከአሁን ቀደም ከነበረው በበለጠ መነቃቃት እንደተፈጠረበት ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ መኮንን ገለፃ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው እንደ ኤግል ሂልስ እና ቮልስ ዋገንን የመሳሰሉት ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ኢንቨስት በማድረግ ላይ እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
እነዚህ ትላልቅ ኩባንያዎች በአንድ ሀገር ላይ ኢንቨስት ከማድረጋቸው በፊት የሚያጠኑት የኢንቨስትመንቱን አዋጭነትና የሀገሪቱን የጸጥታ ሁኔታ እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያንም ተመራጭ ያደረጋት ለኢንቨስትመንት ያላት አዋጭነትና የጸጥታዋ ሁኔታ አስተማማኝ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ይህም በመሆኑ የቮልስ ዋገን ኩባንያ ከሰሀራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ከናይጄሪያና ጋና ቀጥሎ ኢትዮጵያን ሶስተኛ ምርጫው አድርጓታል ፡፡
ቀደም ሲል በውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ተሳትፏቸው የጎላው የቻይና፣ የህንድና የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ባለሀብቶች እንደነበሩ የጠቀሱት አቶ መኮንን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተደረገው የማስተዋወቅ ሥራ የአውሮፓ ባለሀብቶች ቻይናዊያንን በመከተል በሁለተኛ ደረጃ ኢንቨስት በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባት ለውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንቱ ማደግ አስተዋጽዖ ካበረከቱ ጉዳዮች አንዱ ነው ያሉት አቶ መኮንን በቅርቡ ተገንብተው ሥራ የጀመሩት እንደ አዳማና ቦሌ ለሚ የመሳሰሉት ኢንዱስትሪያል ፓርኮችም ሥራ መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡ የአዳማ ኢንዱስትሪ ፓርክ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ማምረት ተሸጋግሮ አሁን ያመረተውን ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ላይ እንዳለ ተናግረዋል፡፡
በቅርብ ግዜ ወደ ሀገራችን እየገቡ ያሉ ካምፓኒዎች ለበርካታ ተጨማሪ ዜጎች የሥራ ዕድል እያበረከቱ እንዳሉ የገለጹት ዳይሬክተሩ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ሀገሪቱ የውጭ ምንዛሬ እጥረት እንዳይገጥማትም የሚኖረው አስተዋጽኦ ትልቅ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በኢያሱ መሰለ