ኢትዮጵያ የብልጽግና ተስፋዋን ማለምለም ስትጀምር በክፉ የተነሱባት የውስጥና የውጭ ጠላቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ፈተና ሆነውባታል፡፡ ከጉያዋ የበቀለውና ለግማሽ ምዕተዓመት ሰቅዞ የያዛት አሸባሪው ህወሓት ዛሬም ከመንገዷ ላይ ቆሞ ከጉያዋ የበቀለ ክፉ አረም ሆኖባታል፡፡ ይህን ምቹ አጋጣሚ ያገኙት የውጭ ጠላቶችም በተለያዩ አጋጣሚዎች እጃቸውን ለማስገባት እንቅልፍ አጥተው ሌት ተቀን እየሰሩ ይገኛሉ፡፡
የአሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን የማጥፋት ውጥን የጀመረው ገና ከምስረታው ጀምሮ ነው፡፡ ላለፉት ሃምሳ ለሚጠጉ ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ እረፍት አልባ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ከመነሻው ጀምሮ በትግራይ ህዝብ ጉያ ውስጥ በመወሸቅ እንደክፉ ጠላት ኢትዮጵያን ሲያደማም ኖሯል፡፡ እነዚህ ኃይሎች በመጀመሪያዎቹ የትግል ዘመናቸው የትግራይን ህዝብ ነፃ እናወጣለን የሚል ሃሳብ ሲያራምዱ ቢቆዩም በኋላ ግን ሃሳባቸውን በመለወጥ መላውን ኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት ሲዘርፉ ኖረዋል፡፡
እነዚህ ቡድኖች እድሜ ዘመናቸውን ሁሉ በትግራይ ሕዝብ ስም ሲምሉና ሲገዘቱ የሚታዩ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በዋናት ለችግርና ለመከራ የሚዳርጉትም ይህንኑ ሕዝብ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በመጀመሪያ ለ17 ዓመታት በነበረው ጦርነት የትግራይ ህዝብ ልጆቹን ሲገብር ኖረ፡፡ ከዚያ በ27 ዓመታት የአገዛዝ ዘመናቸው ደግሞ በስሙ ሲነገድ ኖረ፡፡ በዚህ ወቅት ጥቂት የጁንታው አባላት ዋጋ ያስከፈሉትን ሕዝብ ሙሉ ለሙሉ ረስተው በሌብነት ባህር ውስጥ ተዘፈቁ፡፡
ከዚያ በኋላ ግፋቸው በዝቶ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ተነስቶ ለውጡን ሲያመጣ ደግሞ ዳግም ከትግራይ ሕዝብ ጉያ ተወሸቁ፡፡ ይባስ ብሎም ርዳታ እንዳያገኝና በጦርነት ውስጥ በመማገድ ለሌላ መከራና ስቃይ ዳረጉት፡፡ የሚያሳዝነው ነገር የአሸባሪው ህወሓት አመራሮች የህዝብ መጎዳትና ስቃይ ምናቸውም አይደለም፡፡ ለነሱ ትልቁ ጉዳይ ስልጣን ላይ መውጣትና የአገርን ሀብት መዝረፍ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ሕዝብ አልቆ እነሱ ስልጣን ቢይዙ ለነሱ ደስታ ነው፡፡
በዚህ የተነሳ ባለፈው አንድ ዓመት የትግራይ አርሶአደርና ደሃ እናቶችን ልጆች እያፈኑ ያለመሳሪያ ወደጦርነት በመማገድ ግፍ ፈጽመዋል፡፡ በተለይ በሕዝብ ማእበል ርካሽ ፍላጎታቸውን ማሳካት በሚለው አዲሱ ስልታቸው የአገር መከላከያ ሰራዊት መልካም ሥነምግባርና በዲሲፕሊን የታነጸ ባህርይ ባይላበስ ኖሮ የአሸባሪው ህወሓት አመራሮች አብዛኛውን ሲቪል የትግራይ ሕዘብ ለማስፈጀት አንዳችም ርህራሄ የሌላቸው ስለመሆናቸው በተጨባጭ ታይቷል፡፡
አሸባሪው ህወሓት ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ትልቁ የተካነበት ልምዱና ስልቱ ውሸትን የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ አድርጎ መጠቀም ነው፡፡ ይህ ቡድን ከሚከተለው ርዕዮተዓለም ጀምሮ እንኳንስ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ቀርቶ እታገልለታለሁ ለሚለው ሕዝብም ሆነ ከጦርነት ፊት ለሚያሰልፋቸው አባላቱም በግልጽ የማይናገርና ውስጣዊ ማንነቱና ባህርይው በግልጽ የማይታወቅ መሰሪ ቡድን ነው፡፡ ለዚህ አንድ ማሳያ በትጥቅ ትግል ወቅት አንዴ የሶሻሊዝም ሥርዓት አራማጅ፤ ሌላ ጊዜ ነፃ ገበያ፣ ሌላ ጊዜ መልሶ ደግሞ ነጭ ካፒታሊዝም እያለ የሚ ያምታታ ቡድን እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት የጀመረው አንድ የማጭበርበሪያ መንገድ ደግሞ ድል እያገኘሁ ነው፤ አዲስ አበባ እንገባለን፣ ያኔ ሥልጣን ታገኛላችሁ እያለ በተለይ ህፃናትን በተስፋና በሃሽሽ ስካር ግንባራቸውን ለጥይት እንዲሰጡ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከዚህ አንጻር የትግራይ ወጣቶችና ህጻናትን ለጦርነት ለመማገድ የሚሄድበት መንገድ አንድ ማሳያ ሲሆን ከዚህ ውጭ ደግሞ በጎን በእያንደንዱ ቤት የሰው ኮታ እየጣለ ወጣቶችና ህጻናትን በማስገደድ ወደግንባር በመላክ የሚያስፈጅበት መንገድ ሌላው ማሳያ ነው፡፡ በሌላ ጎኑ ደግሞ ለውጭው ማህበረሰብ መንግሥት ገደለን፣ ፈጀን፣ በረሃብ አለቅን፣ እያለ የድረሱልኝ ጥሪ ሲያስተላልፍ ይውላል፡፡
ይህ የሽብር ቡድን ገደልኩ፣ ማረክሁ፣ የሚለው የወታደር ብዛት ምን ያህል በውሸት የተገነባ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ይህ ጦርነት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ይህ ቡድን ገደልኩና ማረክሁ የሚለው የኢትዮጵያ ሰራዊት ቁጥር ቢደመር በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ነው፡፡
ሰሞኑን ደግሞ ይህ ቡድን በተለይ በወሎ ግንባር በቀሰቀሰው ጦርነት ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮህ እንደሚባለው አንዴ አስጥሉኝ ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ደመሰስኩ የሚሉ የተምታቱ መረጃዎችን ማሰራጨቱን ቀጥሎበታል፡፡ በተለይ ጀግናው የኢትዮጵያ አየር ሃይል ያረሰበትን ኪሳራ ተከትሎ ጩኸቱ በርትቷል፡፡
በሌላ በኩል ይህ ቡድን እንዲጠፋ የማይፈልጉት አሜሪካና ምዕራባውያን ወዳጆቻቸው ቡድኑ ተመታ ሲባል ጩኸታቸው ይጨምራል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ከአስር ጊዜ በላይ የተሰባሰቡት የጸጥታው ምክር ቤትም ሆነ የአውሮፓ ህብረትም በተለያየ መንገድ የሚያደርጉት ጫና ዛሬም ቀጥሏል፡፡ ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ እውነት ይዛ የቆመች በመሆኑና በመርህ ስለምትገዛ ለነዚህ ሃይሎች ደባ አልተንበረከከችም፤ ወደፊትም አትንበረከክም፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረቻቸው ሰፋፊ የልማትና የእድገት ትልሞች መሬት እንዲነኩና የባከነው የልማትና የእድገት ጊዜ እንዲካካስ ሰላም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋነኛው መንገድ ይህንን አገር አተራማሽ የሽብር ቡድን ማጽዳትና በአገራችን አስተማማኝ ሰላምን ማስፈን ነው፡፡ ሰሞኑን የኢትዮጵያ አየር ሃይልና የአገር መከላከያ ሰራዊት ከክልል ሚሊሺያ፣ ልዩ ሃይልና ከህዝብ ጋር በመሆን እያካሄዱ ያለው አሸባሪውን ህወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የመደምሰስ ተግባርም የዚህ አካል ነው፡፡
ኢትዮጵያ ሰላም ያስፈልጋታል፡፡ ኢትዮጵውያንም ብልጽግናን ይሻሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ መንገዱን ማጽዳት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር ነው፡፡ በመሆኑም አሸባሪውን ቡድን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከመንገዳችን ላይ በማጽዳት ፊታችንን ወደልማት ማዞር ለነገ የማይባል የዛሬ የቤት ስራ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ለዚህም በጋራ መቆም ከመቼም ጊዜ በላይ የሚያስፈልግበት ወቅት አሁን ነው!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 16 ቀን 2014 ዓ.ም