አዳማ፡- ‹‹አመራርነት ወንበር ይዞ መቀመጥ ብቻ መሆን የለበትም፤ በሥራ መታየት አለበት››ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ። በአመራር ክፍተት በክልሉ ከዚህ ቀደም የተፈጠሩ ስህተቶች እንዳይደገሙ አመራሩ ለተሻለ ሥራ መንቀሳቀስ እንዳለበት አሳስበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ለማ መገርሳ በአዳማ ከተማ ለሁለት ቀናት በተካሄደው አምስተኛው የጨፌ ኦሮሚያ አራተኛ አመት የሥራ ዘመን ዘጠነኛ መደበኛ ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይ እንደተናገሩት ህዝቡ የክልሉን የልማት ሥራ በማገዝ የኩሉን አስተዋጽኦ ሊያደርግ ይገባል።
ቀደም ሲል በማህበራዊ፣በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ዘርፍ በህዝቡ ዘንድ ይነሱ የነበሩና በአመራር ክፍተት የተፈጠሩ ስህተቶች እንዳይደገሙ አመራሩ ‹‹ምን ውጤት አመጣለሁ›› ብሎ እራሱን በመፈተሽ ለተሻለ ውጤት መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ይህን የማያደርግ ከሆነ ተሸክሞ መሄድ ያስቸግራል ብለዋል።
‹‹አመራርነት ወንበር ይዞ መቀመጥ ብቻ መሆን የለበትም። በሥራ መታየት አለበት። ከሥራ ጋር ቶሎ ተላምዶ ለውጤት መንቀሳቀስ ያስፈልጋል›› ያሉት አቶ ለማ ከአዛዥነት ወጥቶ በተጠያቂነት መስራት ከአመራሩ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል። በክልሉ የሰው ኃይል ፍልሰት አሁን እየተሻሻለ የመጣ ቢሆንም መታየት እንዳለበት ጠቁመዋል።
የክልሉ ህዝብም በአካባቢው በመንግሥትም ሆነ በኢንቨስትመንት የሚሰራውን የልማት ሥራ በመደገፍ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት ብለው በክልሉ የሚገነቡ የትምህርት፣የጤና፣እና ሌሎች የልማት ሥራዎች የኦሮሚያ ናቸው የሚል አስተሳሰብ መኖር እንዳለበትም ገልጸዋል።
‹‹በአንድ በኩል ልማት እየተፈለገ በሌላ በኩል ልማትን የሚያርቅ ሥራ መስራት ለክልሉ ስምም ሆነ ለክልሉ እድገት አይበጅም››ሲሉም ተናግረዋል።
በክልሉ የሚስተዋሉ መፈናቀሎችና የተለያዩ ችግሮች መልሶ ክልሉን እየጎዱ መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባም አስታውቀዋል። ችግሮች ሲከሰቱም የተለየ አጀንዳ ያላቸው ሰዎች መጠቀሚያ እንዳይሆን መጠንቀቅና ማስተዋል እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል። ጨፌው የ290 የወረዳ ዳኞች ሹመትና የህብረት ስራ ረቂቅ አዋጅ አጽቋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በለምለም መንግሥቱ
This blog is a great resource for anyone looking to live a more mindful and intentional life Thank you for providing valuable advice and tips