ለ2022 የኳታር ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የደቡብ አፍሪካ አቻውን በባህርዳር ስቴድየም ካስተናገደ ከሳምንት በኋላ ኢትዮጵያ ማንኛውንም ዓለም አቀፍ ጨዋታ በሜዳዋ እንዳታካሂድ ካፍ ባለፈው ሳምንት ማገዱ ይታወቃል። ይህንንም ተከትሎ ዋልያዎቹ ከሳምንት በኋላ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጋናን በገለልተኛ ሜዳ ለመግጠም ተገደዋል። በዚህም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጨዋታውን የሚያካሂድበትን አገርና ስቴድየም መርጦ ባለፈው ዓርብ ይፋ አድርጓል። ይህ ጨዋታ በደቡብ አፍሪካ ኦርላዶ ስታዲየም እንዲካሄድ ኢትዮጵያ መምረጧ ታውቋል።
የባሕር ዳር ስታዲየም በካፍ ከታገደ በኋላ ኢትዮጵያ ወንዶች ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታውን ከአገር ውጭ ለማድረግ በመገደዱ፤ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአማራጭነት ኬንያን፣ ዚምባብዌን እና ደቡብ አፍሪካን መርጧል።
ሦስቱም አገራት ይህንን ጨዋታ ለማስተናገድ ፈቃደኝነታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ የዚምባብዌ ስታዲየም የዚምባብዌን እና የኢትዮጵያን ጨዋታ ብቻ እንዲያስተናግድ በገደብ የተፈቀደለት እንጂ ሌላ ጨዋታ ማካሄድ እንደማይችል ካፍ በማረጋገጡ ሳይሳካ ቀርቷል።
ኬንያ ፈቃደኝነቷን የገለጸች ቢሆንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ ዚምባብዌ ለመጨረሻ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታው ማቅናቱ ስለማይቀር፤ በአንድ የአውሮፕላን ጉዞ እና መጠነኛ ወጪ ጨዋታውን በደቡብ አፍሪካ ለማድረግ ወስኗል። በመሆኑም ጨዋታው ፊፋ በሚያስቀምጠው ቀን በደቡብ አፍሪካ ኦርላዶ ስታዲየም ለማድረግ ከደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ተስማምቷል።
የኢትዮጵያ ስቴድየሞች ጨዋታዎችን እንዳያስተናግዱ መታገዳቸው ቀደም ሲልም ሲጠበቅ የነበረ እንጂ ድንገተኛ ውሳኔ እንዳልሆነ ይታወቃል። አዲስ ዘመንም ከወር በፊት ይህ ውሳኔ ሊተላለፍ እንደሚችል ባለሙያዎችን አነጋግሮ ሰፊ ዘገባ ሰርቷል። ያም ሆኖ የስቴድየሞቹ መታገድ በተለይም በዚህ ወቅት መሆኑ ከጉዳቱ ጥቅሙ ሊያመዝን እንደሚችል የተለያዩ የመከራከሪያ ሃሳቦች ይነሳሉ።
በዋናነት ካፍ እገዳውን በዚህ ወቅት መጣሉ ለብሔራዊ ቡድኑ ያለው ጥቅም የጎላና መልካም አጋጣሚ የፈጠረ መሆኑ ይነሳል፡፡ ዋልያዎቹ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የሚያደርጉት ጉዞ ከደቡብ አፍሪካው ጨዋታ ውጤት በኋላ መጨረሻው መታወቁን ተከትሎ ቀሪዎቹን ጨዋታዎች በሜዳው ማድረጉ የሚፈይድለት ነገር የለም። ምናልባት እገዳው ከደቡብ አፍሪካው ጨዋታ ቀደም ብሎ ቢሆንና ዋልያዎቹም በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ተስፋ ቢኖራቸው ከሜዳ ተጠቃሚነት አኳያ ተጎጂ ይሆኑ ነበር። እገዳው ዋልያዎቹ ለአፍሪካ ዋንጫ ከማለፋቸው አስቀድሞ ቢሆንም ምናልባትም ዋልያዎቹ ከስምንት ዓመት በኋላ ለ2022 የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ሲያልፉ በሜዳቸው የሰበሰቡትን ወሳኝ ዘጠኝ ነጥቦች ባላሳኩ ነበር።
ዋልያዎቹ ከሦስት ወራት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳታፊ እንደመሆናቸው አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጠንካራና ተፎካካሪ ቡድን ለመገንባት እቅድ አላቸው። የኢትዮጵያ ስቴድየሞች ዋልያዎቹ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቻቸውን ሳያጠናቅቁ መታገዳቸው አሰልጣኙ ከሜዳቸው ውጪ ቀሪዎቹን ጨዋታዎች እንደ አቋም መለኪያ ወይም የወዳጅነት ጨዋታ ሊጠቀሙ የሚችሉበትን እድል ፈጥሯል።
አሠልጣኝ ውበቱ ቡድናቸውን ለማጠናከር በሜዳቸው በርካታ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ቢያደርጉም ከሜዳቸው ውጪ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ የሚገጥሙ ችግሮችን በዚህ አጋጣሚ ሊቀርፉ ይችላሉ። ይህም ከሜዳቸው ውጪ የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ ያለውን ውጣ ውረድና ተጨማሪ ወጪ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎቹ ማካካስ እንዲቻል እድል የሚፈጥር ይሆናል።
በሌላ መልኩ የስቴድየሞቹ መታገድ ኢትዮጵያ በየክልሉ እየገነባቻቸው የምትገኘውን ስቴድየሞች ጥራትና ወደ ኋላ ያስቀሯትን ችግሮች እንድትፈትሽ መልካም አጋጣሚ እንደፈጠርም ታምኖበታል። ክልሎችም ይሁኑ የፌዴራል መንግሥቱ እያስገነቡ የሚገኙትና በከፊል የተጠናቀቁት ስቴድየሞች ግንብ ከማቆምና ‹‹ዓለም አቀፍ ስቴድየም›› ብሎ ከመሰየም በዘለለ በርካታ መሟላት ያለባቸው ጉዳዮች እንዳሉም ትምህርት የሚሰጥ ነው።
በተለይም እየተገነቡ የሚገኙት ስቴድየሞች ሁለገብና የኦሊምፒክ መስፈርቶችን የሚያሟሉ ነው ብሎ በርካታ ገንዘብ ከማፍሰስ ባለፈ እግር ኳስ የሚፈልገውን የመጫወቻ ሜዳ ብቻ ጥራቱን ጠብቆ ባነሰ ወጪ እንዲገነባ ማድረግ ሌላኛው አማራጭ እንደሚሆንም አስተያየቶች ይሰነዘራሉ። እየተገነቡ የሚገኙት ስቴድየሞችም ቢሆኑ በርካታ ገንዘብ የወጣባቸው እንደመሆኑ ትልቁን ነገር ሰርቶ ለጥቃቅን ነገሮች ትኩረት አለመስጠት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍልም የካፍ እገዳ አስተማሪ ነው።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2014