አዲስ አበባ፡- በጋምቤላ ክልል በሚገኙ አምስት የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ‹‹የጦር መሳሪያ የታጠቁ ስደተኞች አሉ›› የሚል መረጃ እንዳለ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ገለጹ።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኡሙድ ኡጁሉ ከአዲስ ዘመን ጋር በአደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፣ አብዛኛው የደቡብ ሱዳን ወንድ ስደተኛ ሠራዊት የነበረ በመሆኑ ትጥቅ ይዘው ገብተዋል የሚል መረጃ ስላለ የፌዴራል መንግስቱ ገብቶ ትጥቅ እንዲያስፈታ ክልሉ መጠየቁን አመልክተዋል።
ክልሉ ከደቡብ ሱዳን ጋር የተያያዘው በመሆኑ በቀላሉ የጦር መሳሪያ የሚገባበት ሁኔታም እንዳለ ጠቅሰው፣ ይህን ስጋት ለመከላከል የፌዴራል ፖሊስ፣ የሀገር መከላከያ፣ የክልሉ ልዩ ኃይልና ፖሊስ በመቀናጀት በተጠንቀቅ ላይ(ስታንድ ባይ) በመሆን ፀጥታ የመጠበቁ ስራ እየተከናወኑ መሆኑን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያን ድንበር አጠቃላይ መጠበቅ አይቻልም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ በደቡብ ሱዳን ያለው አለመረጋጋትም አንድ ችግር ነው። የሙርሌ ማህበረሰብም ከብቶቻቸውን ይዘው ድንበራችንን አልፈው ወደ እኛ ግዛት ይገባሉ ብለዋል።
የሙርሌ ማህበረሰብ ልጆችና ከብቶችን ለመውሰድ ወደ ክልሉ ይመጣሉ ያሉት አቶ ኡሙድ፣ በአጠቃላይ ድንበሩ ክፍት ስለሆነ ክልሉ ሊቆጣጠረው እንደማይችል አመልክተዋል ።
ከዚህ በፊት በሙርሌ የተወሰዱና ያልተመለሱ ህጻናት በመሉ መመለስ አለባቸው። ይህ የመንግስት አቋም ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ከተወሰዱት ህፃናት መካከል ትንሽ በእድሜ የገፉት በዲማ በኩል አድርገው በአለፈው አመት ሰባት ልጆች መመለሳቸው አስታውሰዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በወንድወሰን መኮንን