በትኛውም መልኩ ስለፍትሕ የሚደረግ ትግል የቱንም ያህል ዋጋ ያስከፍል፤ የቱንም ያህል ጊዜ ይፍጅ በአሸናፊነት የመጠናቀቁ እውነታ ብዙም ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም። ፍትሐዊነት በራሱ ከፍያለ ሰብዓዊ እሴት በመሆኑ በትግል ወቅትም በራሱ ከፍ ያለ አቅምና ከዚህም በላይ የአሸናፊነት ስነ ልቦና የሚያላብስ ነው።
እብሪትና ከዚህ የሚመነጭ የክፋት መንገድ ደግሞ ማንም ይሂድበት ማን መሰረቱ ከተዛነፈ አስተሳሰብ የሚመነጭ በመሆኑ የቱንም ያህል ከፍ ባለ ሴራና ሴራ ትብታብ ቢዋቀር፤ መዋቅሮቹ ባልተገባ መንገድ የተገነቡ በመሆናቸው ፍጻሜው ሽንፈት እና ውርደት እንደሚሆን ይታመናል። ብዙ ዓለም አቀፍ ታሪኮችም ለዚህ እውነት ዋቢ ተደርገው ሊጠቀሱ ይችላሉ።
ላማሳያም የጀርመን ናዚዎች ፣ የጣሊያን ፋሽስቶች ፣ የጃፓን ሚሊተሪዝም ወዘተን መጥቀስ ይቻላል።እነዚህ ኃይሎች ከተነሱበት የእብሪት አስተሳሰብና አስተሳሰቡ ከወለደው የጭካኔ ተግባራቸው የተነሳ ዓለምን አሸንፈው የእብሪት ተስፋቸውን የተጎናጸፉ ያህል ረጅም መንገድ ተጉዘው ነበር። ይሁንና የአስተሳሰብ መሰረታቸው ጤነኛ ባለመሆኑ ውድቀታቸው ለዓለም መማሪያ ሆኖ አልፏል።
በርግጥ የቡድኖቹ ወቅታዊ ቁመና በብዙዎች ዘንድ ከፍ ያለ ግምት የተሰጠውና በአይነኬነት ሞገስ የገዘፈ ሆኖም ታይቶ ነበር። ስለ ፍትሕ በሚታገሉ ኃይሎች ዘንድ እውነታው የተገላቢጦሽ ሆኖ ከፍ ባለ ጽናትና መስዋእትነት ቡድኖቹ ብቻ ሳይሆኑ አስተሳሰባቸውም ላይመለስ ወደ መቃብር ወርዷል። ይህንንም ተጨባጩ የዓለም ታሪክ በብዙ ጥቁር ቃላቶች ተርኮታል።
እንደ ሀገርም ቢሆን እኛ ኢትዮጵያውያን በብዙ እብሪትና ከዚህ በሚመነጭ ንቀት ተሞልቶ የመጣውን የጣሊያንን ቅኝ ገዥ ኃይል በአድዋ ተራሮች በብዙ መስዋዕትነትና ተጋድሎ አሸንፈን ነጻነታችንን አስጠብቀን መቆየት የቻልነው ጦርነቱ ለኛ ፍትሐዊ በመሆኑ ነው። የተጋድሎውና የድል ስኬቱ መሰረትም ይሄው ፍትሐዊነቱ እንደሆነ ታሪክ የሚዘክረው እውነታ ነው።
ኢትዮጵያውያን ካሏቸው ከፍ ካሉ መንፈሳዊ፤ ከዚህም ከሚቀዱ ማህበራዊ እሴቶች መካከል አንዱ ስለ ፍትሕ ያላቸው አመለካከትና ከዚሁ የሚመነጨው አብዝቶ ፍትህ የመፈለግ መሻታቸው ነው። ከዚህ የተነሳም እብሪትን አብዝተው የሚጠየፉና የሚያወግዙ ህዝቦች ናቸው። እብሪት ውድቀትን እንደምታፈጥንም በታሪኮቻቸው በቂ ግንዛቤ ያዳበሩ ናቸው።
የእብሪተኞችን የእብሪት ተግባር ለመመከት ሲወጡም ፤የእብሪተኞች ውድቀት ተፈጥሯዊ መሆኑን በማመንና ከዚህ በሚመነጭ መንፈሳዊ የተጋድሎ አቅም ባለቤት በመሆን ነው። የአሸናፊነት ስነ -ልቦናንም የሚላበሱት ከዚሁ እውነት በሚቀዳ መንፈስ ነው። ረጅሙ የነጻነት ዘመናቸውም በዚህ እውነት ላይ የቆመና የጸና ነው።
ዛሬም ቢሆን የራሳቸውን እጣ ፈንታ በራሳቸው ለመወሰን እያደረጉት ያለው እልህ አስጨራሽ ትግል የቱንም ያህል ፈታኝ ቢሆን እየሄዱበት ያለው መንገድ ፍትሐዊ በመሆኑ ትግሉ የሚፈልገውን መስዋዕትነት በመክፈል በአሸናፊነት እንደሚያጠናቅቁት የጸና እምነት አላቸው።
ትናንት ለጥቁር ህዝቦች ብርሃን ፈንጣቂ የሆነውን የአድዋን ድል ህያው ታሪክ ለማድረግ ሆ ብለው ሲከቱ ትልቁ አቅማቸው ፍትሀዊነታቸው እንደነበር ሁሉ ፤ዛሬም እንደሀገር በውስጥም በውጪም ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች አሸንፈን ለመሻገር የያዙት ፍትሐዊ መንገድ የድል ብስራት አቅማቸው ነው።
ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የቱንም ያህል ስለፍትሕ ጆሮውን ቢዘጋ፣ አንደበቱን ቢለጉም እና ልቡን ቢያደነድን የፍትሕ አሸናፊነት ለጊዜና ቦታ ያልተገዛ በራሱ የሚቆምና የሚጸና መሆኑ የአሸናፊነት ተስፋቸው መሰረት ነው። ትናንት በዓለም አቀፍ የፍትህ አደባባዮች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ሲያሰሙ አለመሰማታቸው ድላቸውን እንዳላስቀረው እንዲሁ ዛሬም ድላቸውን ሊያስቀር የሚችል አቅም የለውም።
ትናንት ስለ ፍትሕ ያሰሙት ጩኸት ሰሚ ማጣቱ ፣ ዛሬ ስለፍትሕ እየጮሁ በተመሳሳይ ሰሚ ማጣታቸው ስለ ፍትሕ በበለጠ ቁርጠኝነት እንዲሰሩና ስለፍትሕ መክፈል የሚገባቸውን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል የላቀ ዝግጁነት እንዲፈጥሩ ከማድረግ ያለፈ ፋይዳ አይኖረውም!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 15/2014