ሁለቱን ከተሞች ከአንድ ሰዓት ያነሰ መንገድ ብቻ ያለያያቸዋል። ማህበራዊና ታሪካዊ ዳራዎች ያጠሉበት የማንቸስተርና ሊቨርፑል ከተሞች እግር ኳስ የዘላለም ተቀናቃኝ አድርጓቸዋል።
የሰሜን ምዕራብ እንግሊዝን የበላይነት ለመቆጣጠር ሁለቱ ከተሞች ፍልሚያ ያደርጉ ነበር። ማንቸስተር በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ትመራለች፤ ሊቨርፑል በወደብ ከተማነት ትንቅንቅ ውስጥ ይገባሉ። ድንገት ግን የማንቸስተር የመርከብ መተላለፊያ መንገድ (ታናል) ተሰራና መርከቦቹ በቀጥታ ሊቨርፑል ከተማን ዘለው እቃዎችን ወደ ማንቸስተር ማጓጓዝ ቻሉ። የሊቨርፑል ነጋዴዎችና ህብረተሰቡ ኑሮው ቀነሰ፤ ሥራ አጦች በረከቱ፤ ቁጣም ተፈጠረ። ያ ክስተት በሁለቱ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ልዩነትን ፈጠረ። ያም የከተማ ተቀናቃኝነት የኢኮኖሚ ሽኩቻ በቀላሉ ወደ እግር ኳስ ሜዳዎች ሰተት ብሎ ገባ። ሁለቱ ክለቦች «የእንግሊዝ ኃያሉ ክለብ እኔ ነኝ» በማለት ዛሬም ድረስ ይቆራቆዛሉ።
ማንቸስተር ዩናይትድና ሊቨርፑል በጋራ 124 ዋንጫዎችን ጥርግርግ አድርገው የመደርደሪያቸው ማድመቂያ አድርገዋል። ሊቨርፑል እ.ኤ.አ ከ1975 እስከ 1990 ድረስ 11 የሊግ ዋንጫዎች የሳመባቸውን ዓመታት በኩራት ያነሳል። ማንቸስተር እ.ኤ.አ ከ1993 እስከ 2013 ፍፁም በነገሰባቸውና 13 የኘሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን ባነሳባቸው ዓመታት በመኩራራት «የእንግሊዝ ኃያሉ ክለብ እኔ ነኝ» ይላል።
ዩናይትድ 20 የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫዎችን ሊቨርፑል 18 ዋንጫዎችን በማንሳት በታሪክ ተከታትለው ይጠራሉ። ዛሬም ድረስ ግን ሁለቱ ክለቦች የማይበርድ ውዝግብ ያደርጋሉ። ቀዩ ትንቅንቅ ድሮም ዘንድሮም ወደ ፊትም ተመሳሳይ ነው።
እግር ኳስ ለሁለት የሰነጠቃቸው ሁለት ከተሞች ጉምቱ አሰልጣኞች ስድብ ያመርቱበታል፤ ገናና ተጫዋቾች ሁሌም ይተናነቁበታል። ኮከቦቻቸው አንጨባበጥም ያሉበት የእግር ኳስ ጦርነት ከሁለቱም አቅጣጫ እሳት በየዘመኑ ይወረወራል።
ጨዋታው የ90 ደቂቃ ብቻ አይደለም። ከዛ የዘለለ ትርጉም ይሸከማል። በተቀናቃኞቻቸው የሞት ክስተት ላይ እንኳን ሹፈትን ለመፍጠር የማይመለሱ ነውጠኛ ደጋፊዎች የሚታዩበት፤ ታሪክም ወቅታዊ ሁኔታም ጋዝ ሆነው የሚያቀጣጥሉት፤ አሰልጣኞችም ተጫዋቾችም ከስሜት የማይፀዱበት፤ ልጅም አዋቂም እኩል ጎራ ከፍለው የሚሻኮቱበት የፖለቲካም የኢኮኖሚም፣ የስፖርት የበላይነት ጥያቄም ያልተለየው የእግር ኳስ ጦርነት። «ቀዩ ትንቅንቅ»።
ሁለቱ ቀያይ ለባሾች አንዱ አንዱን አምርሮ ከመጥላቱ ባሻገር በተራ ጨዋታ መሸናነፍን እንደ ሞት ይቆጥሩታል። ዋንጫ በሌለበት እንኳን ማሸነፋቸው እንደ ዋንጫ ማንሳት ይቆጠርላቸዋል።
«የኔ ፈተና አንድ ብቻ ነው ፤ሊቨርፑሎችን ሁሌም በሚኩራሩበት ሜዳ መደቆስ፤ ከዛ ቀሪውን እናንተ ትፅፉታላችሁ» በማለት ታላቁ የዩናይትድ አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በአንድ ወቅት ለጋዜጠኞች የሰጡት አስተያየት የክለቦቹን ሽኩቻ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
«እኔ ስለ ሊቨርፑሎች ምን አገባኝ?፤ ደጋፊያቸው፤ ስታዲየማቸው ምናቸውም ደስ አይለኝም፤ እነሱን ስናሸንፍ የሚሰማኝን ደስታ እኔ ብቻ ነኝ የማውቀው» ያለበት የዩናይትዱ ታሪካዊ ተጫዋች ጋሪ ኔቭል ንግግርም የሚዘነጋ አይደለም። የቅርቡ ኮከባቸው ዋይኒ ማርክ ሩኒም ቢሆን «ያደግኩት ሊቨርፑልን እየጠላሁ ነው» ማለቱ እስካሁን ክለቡን ለቆ እንኳን ጥርስ አስነክሶበታል።
ወደ አንፊልድ መንደርም ይህ መሪር ጥላቻ ተመሳሳይ ነው። በአንድ ወቅት ታሪካዊው ኮከባቸው ስቴቭን ጀራርድ ወደ መኖሪያ ቤቱ አንድ የቀረፃ ቡድን ይዞ ሄደ። «እነዚህ የምትመለከቷቸው መለያዎች በርካታ የተቃራኒ ክለብ መለያዎች ሲሆኑ ከጨዋታ በኋላ የተቀያየርኳቸው መለያዎች ናቸው፤ ግን አንድም የዩናይትድ መለያ አታገኙም፤ አንድም የዩናይትድ መለያ ቤቴ አይገባም» ያለበት አጋጣሚ ጥላቻው ከእግር ኳሳዊ ጉዳይ የዘለለ ምክንያት ያለው አስመስሎት ነበር።
ሉዊስ ሱዋሬዝ ፓትሪስ ኤቭራን ያልጨበጠበት፤ ሪዮ ፈርዲናንድና ዳኒ ዌልቤክ ሱዋሬዝን አንተ አትጨብጠንም በማለት አፀፋ የሰጠበት ክስተት የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ተጫዋቾች በቀዩ ትንቅንቅ ስሜታቸውን የሚገልፁበት መንገድ የተለየ ነው። ኳስና መረብ ሲያገናኙ ደስታቸውን ለመግለፅ ሜዳው አይበቃቸውም። ሲበለጡ ሽንፈትን በፀጋ የመቀበል ክህሎታቸው ይከዳቸዋል።
ሁሌም ከሜዳ ውጭ የሚጫወተውን ክለብ ለመደገፍ ትኬት ማግኘት ከባድ ነው። ቀድሞ ትኬት ይጠናቀቃል። በጠላት ድንበር ገብተህ እንደመዘመርና እንደ መቦረቅ ምን የሚያስደስት ነገር አለ የሚሉ ደጋፊዎች ብዙ ናቸው። ኦልድ ትራፎርድን ህልም እውን የሚሆኑበት፤ አንፊልድን የታማኝ ደጋፊዎች ህብረ ድምፅ ሌላ ዓለም የሚያስመስላቸው ያኔ ነው።
በቀዩ ትንቅንቅ በጨዋታ ወቅት በሚፈጠሩ ነገሮች ሁሉ በብስጭት የተገኘ ነገር ሁሉ ይወረወራል። ፈርጉሰን በሊቨርፑል ደጋፊዎች በእንቁላል ተደብድበዋል። በ2011 የታዳጊዎች FA ጨዋታ ተቋርጧል፣ ብዙ ብዙም ነገር ተከስቷል። የሁለቱን ክለቦች የመረረ ጥላቻ የሚያሳይ ሌላም መገለጫ አለ። እ.ኤ.አ በ1964 ፊል ቼዝናል የተባለ ተጫዋች ከዩናይትድ ወደ ሊቨርፑል ከተዛወረ በኋላ ባለፉት ከ55 ዓመታት በላይ በሁለቱ ክለቦች መካከል አንድም የተጫዋቾች ዝውውር በቀጥታ ተፈፅሞ አያውቅም።
በአገራችን ሳይቀር የማይናቅ የደጋፊ ቁጥር ያላቸው እነዚህ ሁለት ኃያል ክለቦች እንደተለመደው ሊፋለሙ በኦልድ ትራፎርድ ዛሬ ቀጠሮ ይዘዋል። ዓለምም ቀዩን ትንቅንቅ ለማየት የዛሬዋን ምሽት በጉጉት ይጠብቃል፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14/2014