አዲስ አበባ፦ የገቢዎች ሚኒስቴር ህግ የማስከበር ስራውን አጠናክሮ በመቀጠል በታክስ ማጭበርበርና ስወራ የተሰማሩ 135 ድርጅቶችን በመለየት እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታወቀ። በታክስ ማጭበርበርና ስወራውም 14 ቢሊዮን ብር ገቢ ሳይሆን ቀርቷል።
ሚኒስትሯ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ትናንት በሰጡት መግለጫ ከሁለት ወር በፊት የተጀመረውን የገቢ ንቅናቄ ተከትሎ ተጨባጭ የሆኑ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልፀዋል። በተጓዳኝም ህግ የማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን እና በታክስ ማጭበርበርና ስወራ ላይ ተሰማርተው በኦፕሬሽን ከተለዩት 135 ትላልቅ ድርጅቶች መለየታቸውን አስታውቀዋል።
ከድርጅቶቹ መካከል ኢስት አፍሪካንትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ ማህበር፣ አሰብ ሆቴል፣ ቢ ኤም ኤች አጠቃላይ ንግድና ፋኬኛ ኤሌክትሮኒክስ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል። በድርጅቶቹ በተደረገው የታክስ ኦፕሬሽን ደረሰኝ ሳይቆርጡ ግብይት የፈፀሙ መሆናቸውንም አመልክተዋል።
በታክስ ማጭበርበርና ስወራው 14 ቢሊዮን ብር ገቢ ሳይሆን መቅረቱን የገለፁት ወይዘሮ አዳነች፣ከዚህም ውስጥ 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በጥር ወር ብቻ የተደረገ የታክስ ስወራ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ሚኒስትሯ ገለፃ፣ በተደረገው ኦፕሬሽ 78 ድርጅቶች እጅ ከፍንጅ ሲያዙ፤ በታክስ ምርመራ ኦዲት ደግሞ 57 ድርጅቶች ከፍተኛ የታክስ ማጭበርበርና ስወራ እንደፈፀሙ ማወቅ ተችሏል። በድርጅቶቹ ውስጥ በተለያዩ የስራ መደቦች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ 105 ግለሰቦችም በስራ ላይ እንዳሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘው በህግ ቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል።
የንግድ ትርፍ ላይ ደረሰኝ ካልተቆረጠ ትክክለኛ ሂሳብ ሊያዝና መንግስትም ይህን ያህል ግብር አለኝ ብሎ ሊሰበስብ አይችልም ያሉት ሚኒስትሯ። ከተለዩት 135 ድርጅቶች ውስጥ 70 በመቶዎቹ የዕቃ ምንጮች የሆኑ አከፋፋዮችና አስመጪና ላኪዎች፣ ቀሪዎቹ 30 በመቶዎቹ ደግሞ ዝቅተኛ ግብር ከፋይ የሆኑ ቸርቻሪዎች መሆናቸውን ገልፀዋል።
መስሪያ ቤቱ ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ በታክስ ንቅናቄው የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ የቆየ ሲሆን፤ ከብልሹ አሰራር ጋር በተያያዘም በ96 ሰራተኞቹ ላይ እርምጃ መውሰዱና 26 ሰራተኞቹን ደግሞ ማባረሩ ይታወሳል።
አዲስ ዘመን የካቲት 21/2011
በፍሬህይወት አወቀ