ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የኢትዮጵያ መንግሥት ለቱሪዝም ዘርፉ ልዩ ትኩረት መስጠቱ የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎች እየወጡ ነው። አገራችን በጥንታዊ የሥልጣኔ መነሻነቷ፣ የሰው ዘር መገኛ “ምድረ ቀደምት” ፣ የታሪክ፣ የልዩ ልዩ ቅርሶችና የውብ የተፈጥሮ መገኛ ከመሆኗ አንፃር በዓለም ላይ እምቅ የቱሪዝም ሀብት ባለፀጋዎች ተርታ ትመደባለች።
ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ ሀብት በጉያዋ ብትይዝም ቀደም ባሉት ግዜያት በሚፈለገው መንገድ “የፕሮሞሽንና የማርኬቲንግ” ሥራ መሠራት ባለመቻሉ፣ የመዳረሻ ልማቶችን የማልማት ውስንነት እና መሰል ችግሮች ተደራርበው የሚፈለገውን ያክል ኢኖሚያዊ ጥቅም ማግኘት አልተቻለም። ከዚያም ዓለፍ ሲል መላው ዓለም “የኛ” የሆነውን፣ የማንነትና የሉዓላዊነታችን መገለጫዎቻችንን በበቂ ሁኔታ ማወቅ እንዳይችል መንስዔ እየሆነ ይገኛል።
ችግሩ በዚህ ብቻ ሳያበቃ “ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለእዳ አይቀበለውም” እንደሚባለው የአገራችን ብሂል በልዩ ልዩ የቱሪዝም መስህቦች (በርቀትም ይሁን በዙሪያችን) የሚገኙትን የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ተመልክተው በራሳቸው ቅርስ፣ ታሪክ ተፈጥሯዊ ስፍራ እንዲማረኩ ለማድረግ የሚሰራው ሥራ እጅግ ደካማ ሆኖ ቆይቷል። ይሄ የሚያመለክተው በዋነኝነት “የኛ” የሆኑት ሃብቶቻችንን እንዳናውቅ ከማድረጉም ባለፈ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎቻቸውን ተረድተን ልዩ ጥበቃና እንክብካቤ ማድረግ እንዳንችል አድርጎናል። ከላይ ካነሳነው መዋቅራዊ ችግርና የግንዛቤ እጥረት አንፃር የቱሪዝም ዘርፉ ለበርካታ አሥርት ዓመታት ተዳክሞ መቆየቱን “መንግሥት በግምገማው” በማረጋገጡ ካለፉት ዓመታት ወዲህ ልዩ ትኩረት መስጠቱን በተለያዩ መንገዶች ይፋ በማድረግ ዓመርቂ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን የሚያሳዩ ተግባራትን እየተመለከትን ነው።
በቅርቡ እንኳን (በሦስቱ ዓመታት የለውጥ ግዜያት) በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና መሪነት በአዲስ አበባ ልዩ ልዩ ስፍራዎች አዲስ የመዳረሻና የቱሪዝም መስህብ ስፍራ ማልማት ሲቻል፤ በልዩ ልዩ ቦታዎች (በኮይሻ፣ ጎርጎራ፣ ወንጪና የመሳሰሉት ደግሞ) እጅግ ትላልቅ የመዳረሻ ልማት ፕሮጀክቶች ይፋ እየሆኑ ነው። ለዚህም የቱሪዝም ሚኒስቴር መሥሪያቤቶችንና ባለድርሻ ተቋማት በድጋሚ የማደራጀት ስራዎችን እየተሠራ መሆኑ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የቱሪዝም ፅንሰ ሃሳብ
አቶ እዝራ ሃይለማሪያም አሁን በቱሪዝም ሚኒስትር ስር የተጠቃለለው “የቱሪዝም ኢትዮጵያ” መሥሪያ ቤት የሕዝብ ግንኙነት ከፍተኛ ባለሙያ ናቸው። እርሳቸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም የቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) ያስቀመጠውን ትርጓሜ ጠቅሰው ፤ ቱሪዝም ጎብኚ ተብለው በተለዩ ሰዎች የሚፈፀም ድርጊት ነው። ጎብኚ በመደበኛነት ከሚኖርበት አካባቢ ተነስቶ ቢያንስ ለአንድ ዓመት ቆይታ በዓልን ማክበር፣ ጊዜን ማሳለፍና መዝናናትን፣ ሥራን፣ ህክምናን፣ ትምህርትን፣ ጨምሮ ለተለያዩ ጉዳዮች ወደሌላ መዳረሻ የሚጓዝ ሰው ማለት ነው” ይላሉ። የቱሪዝም ዘርፍ እሳቤ ይህ ከሆነ የአንድ አገር የቱሪዝም ዘርፍ ገቢ ከላይ ለተጠቀሱት ዓላማዎች ወደዚያ አገር ከሚመጡ ሰዎች የሚገኝ መሆኑንም ይናገራል። ይህ ገቢ ወደዚያ አገር በሚመጡ ቱሪስቶች ወይም ጎብኚዎች ቁጥር ልክና በዚያ አገር በሚኖራቸው የጊዜ ቆይታ እንደሚወሰንም ነው የሚገልፁት። ጎብኚዎች ወደ አንድ አገር እንዲጓዙና በዚያ እንዲቆዩ ማድረግ ግን ቀላል ሥራ አለመሆኑን ያስቀምጣሉ።
“መስጠትን አቅዶ ማልማትንም ይጠይቃል” የሚሉት ከፍተኛ ኤክስፐርቱ፤ መስጠቱ በተፈጥሮ የሚገኝ የሰዎችን ቀልብ የሚማርክና ምርምር የሚጭር የተፈጥሮ ሐብት (የውኃ አካላት፣ ደን፣ የእጽዋትና የእንስሳት ዝርያዎች፤ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጥ)፣ የማኅበረሰቦችን ስብጥርና የእነርሱንም ባህል፣ ወግ፣ ባህላዊና ታሪካዊ ቅርሶች፣ ያጠቃልላል ይላሉ። ጎብኚዎችን ለመሳብና የቆይታ ጊዜያቸውን ለማርዘም መከናወን ያለባቸው የልማት ሥራዎች እንዳሉም ያነሳሉ። እነዚህም የተለያዩ አገራት ዜጎች ለትምህርትና ለሥልጠና አገልግሎት፣ ለምርምር እንዲመጡ ማድረግ የሚያስችሉ ጥራት ያለው አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎችንና የመዝናኛ ተቋማትን፣ ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን ማካሄድ የሚያስችሉ ሁለገብ አዳራሾችን የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች፣ የህክምና አገልግሎት ተቋማትን፣ አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ፣ የመጓጓዣና የመገናኛ መሠረተ ልማቶችን እንደሚያካትት ይናገራሉ።
ምን እየተሠራ ነው?
ከላይ ካነሳነው ዝርዝር ሃሳብ አንጻር በቱሪዝም ሚኒስትር ስር በአዲሱ መዋቅር የተካተተው ቱሪዝም ኢትዮጵያ “መዳረሻዎችን” በማልማትና እንዲሁም የውጪና የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን የመሳብ ተግባር ሲሠራ መቆየቱን ይናገራሉ። መንግሥትም ለዘርፉ ከፍተኛ ትኩረት ከመስጠቱ አንፃር አመርቂ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ይገልፃሉ።
ባለፈው የመስከረም ወር የተከበሩ ሃይማኖታዊና ባህላዊ በዓላትን እንደ ምሳሌ የሚያነሱት ከፍተኛ ኤክስፐርቱ “ወቅቱ የኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝና የፀጥታ ስጋት የተስፋፋበት ነው ብለን እጃችንን አጣጥፈን እንድንቀመጥ ሳያደርገን የመስቀል፣ የኢሬቻንና የአዲስ ዓመት በዓላትን አዲስ አበባ ከተማ ለተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች ከመጡ ለውጪ አገር ዜጎችና ለአገር ውስጥ ጎብኚዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መስህቦችን የማስተዋወቅ ተግባር ስናከናውን ቆይተናል” በማለት አስረድተዋል።
“የቱሪዝም ሚኒስትር መሥሪያቤቶችና ተጠሪ ተቋማት አንዱ ትልቁ ተግባርና ኃላፊነታቸው የኢትዮጵያን የቱሪዝም ሃብቶች የማስተዋወቅ፣ የገፅታ ግንባታ በመሥራት እንዲሁም በዋናነት ኢኮኖሚያዊ ገቢ በማስገባት ለአገር አስተዋፆ ማበርከት ነው” የሚሉት ከፍተኛ ባለሙያው፤ የማይዳሰሱ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ሃብቶችን፣ ቅርሶችንና ልዩ ልዩ ተፈጥሯዊ መዳረሻዎችን የማልማት፣ የማስተዋወቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል።
መንግሥት ለዘርፉ ከሰጠው ልዩ ትኩረት አንፃርም ብቅርብ ግዜያት ውስጥ ለውጥ እንደሚታይ እምነታቸውን ገልፀዋል። በተለይ ወቅቱ የኮቪድ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋበት ቢሆንም የዘርፉ ባለሙያዎችና መሥሪያ ቤቶች እጃቸውን አጣጥፈው እንዳልተቀመጡ ገልፀው ይሄን ለማካካስ በስፋት “የአገር ውስጥ ቱሪዝም” እንዲስፋፋና ዜጎች እምቅ የመስህብ ቦታዎችን እንዲጎበኙ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አመልክተዋል።
አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎች
በቱሪዝም ዘርፉ ላይ መዳረሻዎችን ከማልማት እንዲሁም የተለመዱ የመስህብ ቦታዎች ጎብኚዎች እንዲመለከቷቸውና ቆይታ እንዲያደርጉባቸው ከመስራት ባሻገር አዳዲስ የመስህብ ቦታዎችንም የማስተዋወቅ ሥራ ወሳኝነት አለው። ከዚህ አንፃር የመንግሥት መሥሪያቤቶች ብቻ ሳይሆኑ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የተሰማሩ የግል ድርጅቶች፣ አስጎብኚ ማህበራትና ትኩረታቸውን “ቱሪዝም ዘርፍ” ላይ ያደረጉ ልዩ ልዩ ተቋማት ድርሻም ጭምር ነው።
አቶ ቦጋለ አቤ “የዳይነስቲ ኢትዮጵያ የቱር” ሥራ አስኪያጅ ናቸው። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ነገር ግን በውጪ አገር ጎብኚዎችም ሆነ በኢትዮጵያውያን ያልታወቁ (ቱሪስት ያላያቸው) መዳረሻዎችን እንዲተዋወቁ እንደሚሠሩ ይናገራሉ።
“በቅርቡ በኢትዮጵያ ውስጥ ከተፈጠረው የሰላም ችግር አንፃር አብዛኛው የቱሪስት መዳረሻ የሆኑት የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍሎች ጎብኚዎች አይጓዙም” የሚሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ዓለም አቀፍ ጎብኚዎች ወደ አገር ውስጥ መምጣት ባይችሉ እንኳን ከስጋት ነፃ የሆኑ አካባቢዎች ላይ በአዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ዲፕሎማቶች፣ በተለያየ የሥራ ኃላፊነት በዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ የሚሰሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የውጪ ዜጎች ላይ ትኩረት በማድረግ የመስህብ ስፍራዎችን እንዲመለከቱ የማስተዋወቅ ኃላፊነትን ወስደው እንደሚሰሩ ይገልፃሉ። እነዚህ የውጪ አገር ዜጎች በእረፍት ግዜያቸው የሚኖሩበትን አገር ማወቅ፣ የመዝናኛ ስፍራዎች ላይ የመገኘት ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው። ስለዚህ የእነርሱን ፍላጎት ለማሟላት አቅደው በመስራት ላይ መሆናቸውን ይናገራሉ።
“በአገር ውስጥ የሚገኙ የውጪ አገር ዜጎችንና ኢትዮጵያውያን ጎብኚዎችን ከአዲስ አበባ በቅርብ እርቀት ላይ የሚገኙ ሆነው ነገር ግን መስህቦቹ ቢጎበኙ ከሌላው ያልተናነሰ አቅም ያላቸውን ውብ መዳረሻዎች እናስጎበኛለን” የሚሉት ሥራ አስኪያጁ አቶ ቦጋለ፤ እንደተናገሩት በዋናነት የብስክሌት ጉዞ (ባይክ ቱሪዝምን) እያስተዋወቁ ይገኛሉ። ሌላው “ሃይኪንግ” ወይም የእግር ጉዞ እየተባለ የሚታወቅ፣ “ራፍቲንግ” ወይም የጀልባ ላይ ትርኢትን (የግቤ ወንዝን ተከትሎ) የሚደረግ አዲስ የቱሪዝም መስህብ የማስተዋወቅ ሥራዎችም በተጨማሪነት ይከናወናል።ሌላው ባህልን ማስተዋወቅን ጨምሮ የመንደር ጉብኝት በማድረግ ጎብኚዎች አዳዲስ ልምዶችን እንዲያገኙና ረጅም የቆይታ ግዜ እንዲኖራቸውም ድርጅታቸው ይሰራል።
“በመስህብ ስፍራዎች የመሠረተ ልማት ችግር ቢኖሩ እንኳን እኛ ከምናበረታታው የተራራ ላይና መሰል አስቸጋሪ ስፍራዎች ላይ የሚደረግ የእግርና የጀልባ ላይ ጉዞ አንፃር ብዙም እንደ ፈተና አናየውም” የሚሉት ሥራ አስኪያጁ ሁል ግዜም ቢሆን ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ሲከሰቱ እነዚያን እንደ እድል በመጠቀም በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የመውጫ መንገድ ማበጀት እንደሚገባ ይናገራሉ። ለዚህ ነው አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ማስተዋወቅን ቀዳሚ አጀንዳቸው አድርገው እየተንቀሳቀሱ መሆኑን የሚናገሩት። አሁን ላይ ደግሞ መንግሥት በአዲስ አበባ በመሰል አካባቢዎች እያለማቸው የሚገኙ መስህቦችንም ታሳቢ እንደሚያደርጉ ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀውልናል።
ማጠቃለያ
በርካታ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ አገር ነች። ከ3 ሚሊዮን ዓመታት በላይ እድሜ ያስቆጠረው “የሉሲ” ወይም ድንቅነሽ አፅም መገኛ አገር፤ ኢትዮጵያ የአረቢካ ቡና ዝርያ መገኛም ነች። የዓለማችን ረጅሙ ወንዝ ጥቁር አባይም የሚገኘው በኢትዮጵያ ነው። የኤርታአሌ የእሳተ ገሞራ ሀይቅና የዓለማችን እጅግ ረባዳና ሞቃት ስፍራ ዳሎልም የሚገኙት በኢትዮጵያ ነው። ይህ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያ የንግስት ሳባ አገር ነች፣ የሙሴ ፅላትም በኢትዮጵያ ይገኛል ተብሎ ይታመናል፤ በአክሱም ፅዮን ቤተክርስቲያን። ከእነዚህ ሌላ ለመዝናናት አመቺ የሆኑ በርካታ የስምጥ ሸለቆ ሃይቆችና ፍል ውኃዎች፣ እንዲሁም የዱር እንስሳት ፓርኮችና መጠበቂያዎች ይገኛሉ። እንግዲህ፤ ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊ፤ሰው ሰራሽና ባህላዊ ቅርሶችን በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስና ትምህርት ድርጅት (ዩኔሰኮ) በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚዋ አገር ለመሆን በቅታለች። ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ባህላዊ ቅርሶች የበለፀገች፤ የቱሪስት መስህብ ያላትና እነዚህንም ቅርሶች በዩኔስኮ በማስመዝገብ ከአፍሪካ አገራት ቀዳሚዋ ብትሆንም የአገሪቱ የቱሪዝም ዘርፍ ግን የሚፈለገውን ያህል ወይም የሚገባውን ያህል እንዳላደገ ይነገራል።
ከቅርብ ግዜያት ወዲህ መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉ የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት እንደሆነ በማመን ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በተግባር ሰፋፊ ልማቶችን፣ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ መሆኑን የሚያመላክቱ መረጃዎችን መጥቀስ ይቻላል። ታዲያ ይሄን መልካም አጋጣሚ መጠቀም ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል። በተለይ በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች በቱሪዝም ሆስፒታሊቲ ዘርፍ፣ በፕሮሞሽንና የገበያ ልማት ብሎም በአስጎብኚ ድርጅቶች ውስጥ በቀጥታ ሊሳተፉ ይገባል። የዚህ ድምር ውጤት ደግሞ “ምድረ ቀደምት” አገራችንን ለመላው ዓለም ከፍ አድርጎ ማስተዋወቅ እንዲቻል ከማድረጉም ባለፈ ኢኮኖሚያዊ ትርፉ ለአገር እድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት ጥርጥር አይኖረውም።
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14 ቀን 2014 ዓ.ም