ሕይወትን አንዳንዶች ሰዎች በግላቸው ዝናን ለማግኘት ወይም ለማደግና ኑሮን ለማሸነፍ የሚቀመጡበት ተመልሰው ተሽከርካሪ ወንበር ነው ይሉታል። ምክንያታቸው ሁሉም ወደ አንድ ስፍራ ወይም ወደ ተለያየ ቦታ ይጓዛልና ነው። አንዳንዶች ደግሞ ከዚህ የተለየ ትርጉም ይሰጡታል። ሕይወት ከሞቱም በኋላ የሚኖርበት ነው በማለት። ለዚህ ደግሞ እንደምክንያትነት የሚያነሱት በሥራችን የሚለካ መሆኑን ነው። መልካም ሥራ ካለን ከመቃብር በላይም ሆነን እንኖራለን፣ ሌላውንም እናኖራለን። መጥፎ ከሠራንም እንዲሁ ለብዙዎች መሰናክል እየሆንን እንቀጥላለን። የትኛው ይበጀናልን እንምረጠው።
በዓለም ውስጥ ካሉ ውድ ነገሮች ሁሉ የላቀ ዋጋ ያለውን ውድ ነገር ከመረጥን ስማችን ብዙውን እየታደገ ዳግም ሕይወትን እንድናጣም እንሆናለን። ምክንያቱም ይህንን የመረጠ አካል ነገውን ሰርቷል፤ ለቤተሰቡም ሆነ ለአገሩ ታሪክ አስቀምጧል። አቅዶት ሳይተገብረው የቀረውን እንኳን ለመሥራት የሚጓጓለት ብዙ ሰውን ያገኛል። ስለዚህም ስኬቱ ከሞተም በኋላ የኖረ ይሆንለታል። ለዚህም ነው ሕይወትን ከሞት በኋላም ማየት የሚፈልግ ካለ ባለ ራዕይ ሰው ይሁን የሚባለው። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ለዛሬ የሕይወት ገፅታ አምድ እንግዳ ያደረግናቸው ጋዜጠኛ ዘውዱ መንግስቴ አንዱ ናቸው።
ሥራዎችን ከአገር ውስጥ የጀመሩ ቢሆንም ሕይወት ወደውጭው መርቷቸው ዲያስፖራ ሆነው መጥተው ነው የተገናኘነው። በእንግሊዝ አገር ‹‹ ሉሲ›› የተሰኘ የሬዲዮ ጣቢያ ከፍተው የሚሰሩና በሙያቸው አገራቸውን የሚያገለግሉ ሲሆኑ፤ በገንዘብና በሌሎች ድጋፎችም እንደማንኛውም ዲያስፖራ ይሳተፋሉ። የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክርቤት እንዲቋቋም ከአደረጉት መካከል ይጠቀሳሉ። ከዚያም ባለፈ የአውሮፓውን ተጠሪነት በመያዝ እያገለገሉ የሚገኙ ናቸው። የውጭ ጫናው ላይ የኢትዮጵያውያን ሚና እንዲታይ በማድረግም ዙሪያ ሙያቸው ጋዜጠኝነት ስለሆነ ብዙ ይለፋሉ። የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው በመሆናቸው ጉዳዩ ትኩራት እንዲያገኝ ከወከሏቸው የምክርቤት አባላት ጋር ጭምር በመነጋገር ትክክለኛው መስመር እንዲመጣ እየተጉ ይገኛሉም።
በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያዊ ከአጋሮቻቸው ጋር በመምጣትም ውዥንብር የፈጠሩ ሃሳቦችን ለማጥራትና እውነታውን ለውጪው ዓለም ለማስረዳት በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሲዘዋወሩና መረጃ ሲይዙም ነበር። በተለይ በህወሓት ሴራና በህዳሴ ግድቡ ዙሪያ የሚነገሩ የተዛቡ ወሬዎችን በአካል ጭምር በመሄድ ማረጋገጥም ችለዋል። አዳዲስ መረጃዎች ሲመጡ ደግሞ ከዲያስፖራ ኤጀንሲ ጋር በየሳምንቱ እንዲገናኙ ከተመረጡ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ በመሆናቸው ለአገራቸው ብዙ አበርክቶ ያደርጋሉ። በእነዚህ የሕይወት ልምዳቸው ውስጥ ያለው ተሞክሯቸው ምን እንደሚመስል ተጨዋውተናልና ለሕይወታችሁ መርህ ይሆኗችሁ ዘንድ የመራረጥናቸውን አቅርበንላቸኋል።
በኩርነት ሲወረስ
መቼም ቢሆን በኩርነት ይወረሳል ተብሎ አይታሰብም። እነአቶ ዘውዱ ቤተሰብ ላይ ግን ይህ ተፈጥሯል። በኩርነት የተጀመረው ከሁለቱም አያታቸው ጀምሮ ነው። ስለዚህም እናታቸውም ሆኑ አባታቸው አለፍ ሲልም ሁለቱ አያታቸው የበኩር ልጅ ናቸው። ከዚያ ይህ በኩርነት እርሳቸው ላይ አረፈ። ወርሰውትም ታናናሾቻቸውን በአደጉበት ልክ መንከባከብ እንዲችሉ ሆኑ። የበኩር ልጅነታቸው ሁሉንም የጠቀመ እንደነበር በእንግዳችን ላይ ታይቷል። ምክንያቱም ሁሉም ያሞላቅቃቸዋል። በዚህም የአያት ልጅ ቅምጥል ብቻ ሳይሆን የእናት ልጅ ቅምጥልም ሆነው ነው ያደጉት።
እንግዳችን የተወለዱት በድሮው አጠራር በባሌው ጠቅላይ ግዛት ገናሌ አውራጃ ዶዶላ ከተማ ሲሆን፤ ብሄር ሳይከፋፍሉ በአካባቢው በብዛት ይኖሩ በነበሩት ኦሮሞና አማራ ባህልና ወግ ነው ያደጉት። ይህ ደግሞ ሁልጊዜ የደስታ ምንጫቸው እንደሆነላቸው ይናገራሉ። በተለይም ከባህሉ ባሻገር ያለው የአባቶች ታሪክን የማሳወቅ ሁኔታ ማንነታቸውን የሰራላቸው እንደሆነ ያስታውሳሉ። በእርግጥ ይህ ነገር የመጣው ራሳቸው ፈልገው ከአባቶች እግር ስር ሳይጠፉ በመማራቸው ነው።
አካባቢው ላይ ልጅነታቸውን ሙሉ ሲያሳልፉ ምንም አይነት ክፍፍልን አያውቁም። በዚህም ባሌን ሲጠሩም ሆነ ሲያስታውሷት የተለየ ስሜት ይሰማቸዋል። ብዙ ትዝታዎችም አዕምሯቸው ውስጥ ያቃጭላሉ። ዛሬ ድረስ የማይረሷቸው ቢደገሙ የሚሏቸው ነገሮችም አሉ። ይህ ደግሞ ከትልቅ ሰው ጋር መዋል ነው። እንደእርሳቸው አባባል፤ ከትልቅ ሰው ጋር መዋል ትልቅ ራዕይ ማለም ነው፤ ነገን ማሰብ ነው፤ የወደፊቱን ማንነትን መተንበይ፤ ራስን ማወቅ ነው። ከምንም በላይ በአገር አለመደራደርና አገርን ከምንም በላይ ማስበለጥን መልመድ ነው። ይህንን ደግሞ ሆኜ አይቸዋለሁም ይላሉ።
የእንግዳችን ውሎ በአብዛኛው ከትልልቅ ሰዎች ጋር መሆኑ ትዝ የሚላቸው ጨዋታ ሳይሆን የእድር፣ የእቁብና የተለያዩ ትልልቅ ሥራዎች ላይ በፀሐፊነት ያገለገሉበት ነው። ምክንያቱም በአካባቢያቸው ብዙዎች ቢማሩም ከጨዋታ የሚለያቸውን አይፈልጉም። ስለዚህም የፅሑፍ ሥራ ሲፈለግ እርሳቸው ናቸው የሚጠሩት። በትምህርት ቤትም ቢሆን በንግግር አዋቂነታቸው እርሳቸው ተፈላጊ ናቸውና ጨዋታ ላይ ብዙም አይደሉም። ከዚያ ይልቅ የጋዜጠኝነቱን ባህሪ የተላበሱበትን ተግባር ይከውናሉ። ይህም በወቅቱ ሚኒሚዲያ የሚባል ነገር ስለሌለ ሬዲዮ አዳምጠውና ጋዜጣ አንብበው ያገኙትን አዲስ ነገር ባንዲራ ከተሰቀለ በኋላ ለተማሪዎቹና ለመምህራን ማጋራት ነው። በዚህም ሁሉም ሰው አንተ ጋዜጠኛ ትሆናለህ ይሏቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
‹‹እኔ መሆን የምፈልገውም ትሆናለህ ሲሉኝ የነበረውን ነው›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ አዳዲስ ነገሮችን በትምህርት ቤትና በቤት ውስጥ እንዲያነቡ መደረጋቸው የማንበብ ክህሎታቸውን እንዳዳበረላቸውና ማንበብ የሚወድ ሰው እንዲሆኑ እንዳገዛቸው ያስረዳሉ። ከምንም በላይ ደግሞ ሁልጊዜ አዲስ ነገር ፈላጊ የመሆንን ምስጢርም ያስተማራቸው ይህ ተግባራቸው እንደነበር አጫውተውናል። ሌላው ባህሪያቸው አስታራቂነታቸው ሲሆን፤ ይህንንም የወረሱት ከትልልቅ ሰዎች ነው። በዚህም ትልልቅ ሰዎችን ሳይቀር ያስታርቁ ነበር። ይህ ባህሪያቸው የተለየ አቅምን ፈጥሮላቸዋል። የመጀመሪያው ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑ እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል። በራስ መተማመናቸውንም የጨመረላቸው ይኸው ሥራቸው ነው።
በእናትና በአባታቸው ሥር ያሉ ቤተሰባቸውን መመዝገብ የጀመሩትም የመፃፍ ፍላጎታቸው በማየሉ ነው። እንዲያውም አያቶቻቸውን ትልቅም ሆነው በማግኘታቸው አሁን ከስድስት መቶ በላይ የዘር ግንዳቸውን ለማወቅ እንደቻሉበትም አጫውተውናል። ይህ ደግሞ በቅርበት የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህልን፣ ኢትዮጵያዊነትን ለማስፋትና ትውልድ ቀረፃ ላይ ለመስራት ሰፊ እድልም እንደሰጣቸው ገልጸውልናል።
አቶ ዘውዱ ቤተሰባቸውን በፍላጎት እንጂ ተገደው አግዘው አያውቁም። ምክንያቱም በኑሮ የተሻሉ አርሶአደርና ሰራተኞች ናቸው። ስለዚህም ከብት የሚጠበቀውም ሆነ እርሻ የሚታረሰው በቅጥር ነው። ይህ ደግሞ እርሳቸው ጫና እንዳይፈጠርባቸው አድርጓል። ይሁን እንጂ የመጀመሪያ ልጅ በመሆናቸው ታናናሾቻቸውን ማስጠናትና መቆጣጠር የእርሳቸው ኃላፊነት ነበር። ከዚያ ባሻገር መላላክና በማንኛውም ሁኔታ አስፈላጊ ሆኖ ካገኙት የማይሳተፉበት ሥራም አልነበረም።
ፍትህን የተማሩትና ለሕግ ትምህርት ልዩ ፍቅር እንዲያድርባቸው ከአደረጉት አፈንጉስ ደባልቄ አበጀ ከተባሉት የእናታቸው አባት ሲሆን፤ እርሳቸው የጃንሆይ የዘውድ ምክርቤት ፕሬዚዳንት ናቸው። በዚህም በጨቅላ አዕምሯቸው ኖረውት እንዲያድጉ አድርገዋቸዋል። ከአደጉም በኋላ ለመማራቸው መንስኤው እርሳቸው እንደሆኑ አውግተውናል።
ፍላጎትና ተማሪነት
አቶ ዘውዱ የትምህርት ሀሁን የጀመሩት በዚያው በተወለዱበት አካባቢ ዶዶላ ላይ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቱ መካነ ኢየሱስ ይባላል። እስከ ስድስተኛ ክፍልም ተከታትለውበታል። የትምህርት ቤቱ መምህራን በብዛት የውጭ ዜጎች ነበሩና በብዙ መልኩ ጥራት ያለው ትምህርት እንዲማሩ አግዘዋቸዋል። በእርግጥ ኢትዮጵያውያኑም ቢሆኑ በወቅቱ በብዙ መስፈርት ተመርጠው የሚገቡ ስለነበሩ ከአርአያነት ባለፈ በማስተማር ብቃታቸውም ከሁሉም የተለዩ ናቸው። ይህ ደግሞ እንደ እነዘውዱ አይነት ተማሪዎችን በግብረገብነትና በአገር ወዳድነት ከማሳደግም በላይ የተሻሉ ተማሪ እንዲሆኑ መሰረት ጥሎላቸዋል።
ከሰባተኛ ጀምሮ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ትምህርታቸውን በዶዶላ መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርትቤት የተማሩት ባለታሪካችን፤ በትምህርታቸው ጎበዝ የሚባሉ ቢሆኑም የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው ግን በዲፕሎማ እንጂ በዲግሪ ለመማር የሚያበቃቸው አልነበረም። በዚህም በባሌ ቀርተው ባሌ ጎባ የጤና ረዳትነት ትምህርትን በዲፕሎማ እንዲከታተሉ ሆነዋል። ከዚያም ለብሔራዊ ውትድርና ተመልምለው በመሄዳቸው የተለያዩ ወታደራዊ ስልጠናዎችን ወሰዱ። የውትድርና ግዳጃቸውን ሲጨርሱ ደግሞ በግብርና ሜካናይዜሽን ኮርፖሬሽን ውስጥ የአስተዳደር ሰራተኛ ሆነው እየሠሩ መማር ጀመሩ።
ትምህርቱን የጀመሩት ቀን እየሠሩ ማታ በመማር ሲሆን፤ ትምህርቱን የሚከታተሉትም በቅድስተማርያም ዩኒቨርሲቲ በማኔጅመንት ነው። ነገር ግን እስከመጨረሻው አልቀጠሉበትም። ምክንያቱም የልጅነት ህልማቸው የሆነውና የሚወዱት የጋዜጠኝነት ሙያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሊጀመር ምዝገባ እየተደረገ መሆኑን ሰሙ። ህልማቸውን እውን ለማድረግም የጀመሩትን ትምህርት አቋርጠው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀሉ። በወቅቱ የመጀመሪያው የመጀመሪያ ዲግሪ የጋዜጠኝነት ትምህርት ተማሪ ነበሩም። ይህም ቢሆን እንደቀደመው አልቀጠለም። ለዚህ ደግሞ የችግሩ መንስኤ የ1997 ምርጫ ነው።
በምርጫው ለመዘገብ ወደተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ተዘዋውረዋል። እውነታውን ለማሳየትም እየጣሩ ካሉ ጋዜጠኞች መካከል አንዱ ነበሩ። ሆኖም የወቅቱ መንግሥት ይህንን አይፈልግምና ብዙ ማስፈራሪያዎችን ያደርግባቸው ነበር። በሚሰሯቸው የምርመራ ዘገባዎችም ቢሆን ጫናዎች ይበረቱባቸዋል። ስለዚህም ጥገኝነት ጠይቀው ወደ እንግሊዝ አቀኑ። በዚያም ነገሮች ሲስተካከሉላቸው የጋዜጠኝነት ፍቅራቸውን የሚያረኩበትን ትምህርት ጀመሩ። ይህም ቢሆን ብዙ ፈተና እንደነበረበት ያስታውሳሉ። ነገር ግን ከፍቅር በላይ ኃያል የለምና ጫናውንና ችግሩን ተቋቁመው በብሮድካስት የጋዜጠኝነት ትምህርት በ‹‹ሊድስ›› ዩኒቨርሲቲ መማር ችለዋል።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከያዙ በኋላ በቀጥታ ሥራውን መስራት ላይ የተሰማሩት እንግዳችን፤ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን መማር ይፈልጉ ነበር። ሆኖም ያሉበት ሁኔታ ይህንን አልፈቀደላቸውም። የመጀመሪያ ዲግሪያ ቸውን ሲማሩ ጥቁር አፍሪካውያን የተለያዩ ድጋፎች ስለሚደረግላቸው ተጠቃሚ ሆነዋል። ሁለተኛው ግን በራስ ወጪ የሚከወን ስለሆነ በእርሳቸው አቅም የሚቻል አይደለም። ስለዚህም እስካሁን ሳይማሩ ቆይተዋል። ነገር ግን በቅርቡ የሰሙት ነገር ተስፋ ሰጥቷቸዋል።
ይህም በብድር መማር ይቻላል የሚለው ሲሆን፤ ለመማር መዘጋጀታቸውን ነግረውናል። ይህ ሁኔታ ከቀጠለ ሦስተኛ ዲግሪያቸውንም እንደሚቀጥሉ አጫውተውናል።
የዲያስፖራው ሥራ
ሥራን የጀመሩት ለብሔራዊ ውትድርና ተመልምለው በሄዱበት ወቅት ነው። ይህም በመስኖ ማሰልጠኛ ውስጥ ሲሆን፤ ጤና ረዳት ስለሆኑ በሙያቸው ወታደሩን እንዲያገለግሉ ሆነዋል። ከዚሁ ግዳጅ ሳይወጡ ጦር ኃይሎች ሆስፒታል ተዛውረውም መሥራት ችለዋል። ቆይታቸው ሁለት ዓመታት ብቻ ቢሆንም በነበራቸው ጊዜ ግን ብዙ ልምድ ቀስመዋል። በተለይም ሁሉንም የህክምና አይነት ለማየትና ለመሞከር ያስቻላቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።
ግዳጃቸው ሲያልቅ ደግሞ በቀጥታ የግብርና ሜካናይዜሽን ኮርፖሬሽን ወደሚባል ተቋም ነው የተዛወሩት። በዚያም ጋምቤላ ውስጥ በሰፈራ ለሄዱ ሰዎች ህክምና ይሰጡ ነበር። በተለይም የግብርና መካናይዜሽን ሐኪም ተብለው ስለተመደቡ ሥራቸው ከባድ ነበር። ምክንያቱም በቦታው የነበሩት ሐኪሞች ሁለት ብቻ ሲሆኑ፤ የሚያክሙት ግን ከሁለት ሺህ በላይ ሰው ነው። ከሥራ አጋራቸው ብዙ ልምዶችን ቢቀስሙም ከጫናው አንጻር ግን ሥራው ይከብድ እንደነበር አይረሱትም። በተለይም አጋራቸው ወደሌላ ቦታ ሲቀየር እጅግ ውስብስብ ጊዜን አሳልፈዋል። በአጠቃላይ ግን የተማሩበትም የሰሩበትም አምስት ዓመታትን እንዳሳለፉ ይናገራሉ።
የህክምናውን ሥራ በመተው በአስተዳደር ዘርፍ ወደዋናው መስሪያ ቤት የተዛወሩት አቶ ዘውዱ፤ ከሥራው ጎን ለጎን የሕግ ትምህርታቸውን ተማሩ። ሲጨርሱም ዳግም ወደ ጋምቤላ እንዲመለሱና የኮሚሽኑ ዳኛም ሆነው ለአራት ዓመታት ሠሩ። ከዚያ ለቀው ደግሞ በክልሉ የዳኛ እጥረት በመኖሩ የተነሳ ወረዳ ፍርድቤት ላይ ዳኛ ሆነው እንዲያገለግሉ ተደረጉ። በዚህም ለስድስት ወር ያህል በቦታው አገለገሉ። ከዚያ የክልሉ የሲቪል ሰርቪስ አስተዳደር ኮሚሽን ፍርድቤት የሚባል ነበርና በዚያ እንዲሰሩ ሆኑ።
ሌላው የሥራ ቦታቸው በፋና ዲሞክራሲያዊ አሳታሚ ድርጅት አማካኝነት የሚታተመው እፎይታ የሚባል መጽሔትና ጋዜጣ ላይ ነበር። የጋዜጠኝነት ሙያቸውን ያዳበሩበት ቦታ እንደነበር ያስታወሳሉ። ምክንያቱም በጋምቤላ ዳኛ ሆነው እየሠሩ ሳለ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወኪል ሆነውም አገልግለዋል። በዚህም የካበተ ልምድ እንዲኖራቸው አድርጓቸዋልም። ከዚያ በተመሳሳይ ኔሽን የሚባል ጋዜጣ ነበርና እዚያ ላይ ሠርተዋልም። እንግዳችን ገቢዎች ሚኒስቴር ወይም የአገር ውስጥ ገቢ ባለስልጣንም ውስጥ የሰራተኞች አስተዳደር በመሆን ለሁለት ዓመታት አገልግለዋል። ከአገር ሲወጡ ደግሞ ጥገኝነት ጠይቀው ስለገቡ መማር የመጀመሪያ ሥራቸው አድርገዋል። ከዚያም ትምህርቱ ሲጠናቀቅ የአገር ውስጥ የሥራ ልምዳቸው ታይቶ ቢቢሲ ላይ መሥራት ጀመሩ። ስድስት ወር ከአገለገሉ በኋላ ደግሞ በሙያው ፈቃድ አውጥተው የራሳቸውን ሥራ ወደመሥራቱ ገቡ። ሉሲ የተሰኘ የሬዲዮ ጣቢያም የከፈቱት ለዚህ ነው።
13 ዓመታትን በሥራው ላይ የደፈኑት አቶ ዘውዱ፤ ከሬዲዮ ጣቢያው በተጨማሪ የቴሌቪዥን ሥራም ጀምረዋል። ይህም ዘውዱ ሾው የሚል ሲሆን፤ ከፋና ብሮድካስት ኮርፖሬሽን የአየር ሰዓት በመግዛት የጀመሩት ነው። ይኸው ሥራ በዩቲውብም የሚያስተላልፉት ነው። በተመሳሳይ የመኪና ማሰልጠኛም ከፍተው ይሠራሉ።
በእንግሊዝ አገር ሪፊውጅ ካውንስል ፣ ሬድ ክሮስና የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሊቀመንበር ሆነውም ሠርተዋል። በተለይም በኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሊቀመንበርነት ለስምንት ዓመት ያህል እንዳገለገሉ ይናገራሉ። በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ዲያስፖራዎች የተግባር ምክርቤት ሲቋቋም ጀምሮ የነበሩና አሁን ላይ የአውሮፓው ተጠሪም ናቸው። በተጨማሪ እንደ ጋዜጠኛ በኢንባሲዎች በኩል ለአገር ይጠቅማሉና ብዙ ሠርተዋል የተባሉት ኢትጵያውያን ሲመረጡ አንዱ በመሆናቸው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር ከሚገኘው ከዲያስፖራ ኤጀንሲ ጋራ ይሠራሉም። ሥራው በየሳምንቱ በድረገጽ እየተገናኙ የሚያከናውኑት ሲሆን፤ እነርሱ የሚፈልጉትን መረጃ ያገኙበታል። ኢትዮጵያ ደግሞ ከዲያስፖራው የምትፈልገውን መልዕክት ታስተላልፍበታለች። ስለሆነም አዳዲስ መረጃዎችን በማግኘትና ለሌላው በማቀበልም አገርን መደገፉ ላይ በስፋት ይሳተፋሉም።
ጋዜጠኝነት በእርሳቸው አንደበት
ጋዜጠኝነት የመንግሥት አቅጣጫ ጠቋሚ ብቻ ሳይሆን ፈዋሽ መድኃኒትና መድህን ነው። ማህበረሰቡን ማገልገልም ነው። ከሁሉም በላይ መንግሥትና ሕዝብን እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገናኝ ሙያ ነው። ድሮ ጋዜጠኝነት ባልታወቀበት ወቅት ‹‹ እረኛ ምን አለ›› ተብሎ መንግሥትም ሆነ ማህበረሰቡ አቅጣጫውን ያስተካክላል። አሁን ደግሞ ነገሮች ሲረቁ ሙያው ይህንን ተክቶ እንዲሠራበት ሆኗል። ያው አተገባበሩ እንደ ዓለምና እንደ አገሪቱ ሁኔታ የተለያየ ቢሆንም።
ጋዜጠኝነት እንደሙያ ከተጠቀሙበት አገርን ብቻ ሳይሆን ዓለምን መለወጥና ወደ አንድ መስመር ማስገባት የሚቻልበት ነው። ለአብነትም መንግሥት ከድርጊቱ እንዲቆጠብ፣ ባለስልጣኑ አገሩን በአግባቡ እንዲመራና እንዲያገለግል ያደርጋልም። ከሙያው ፈቀቅ ሲባል ደግሞ ዓለምን ሁሉ ሊያደባልቅ የሚችል ሥራ የሚሠራበትም ነው። በዚህም ብዙ አገራት እንደፈረሱና ችግር ውስጥ እንደገቡ አይተናል። አሁን ኢትዮጵያ ላይ እየተፈጠረ ያለውም የዚህ ማሳያ ነው። ከራስ ጥቅም አንጻር በመተርጎም ዘገባዎችን በውጭ መገናኛ ብዙኃኖች መሠራታቸው ብዙ ድብልቅ ነገሮች በአገሪቱ ላይ እንዲፈጠር አድርገዋል። ይህ ደግሞ መንግሥትንም ሆነ ዲያስፖራውን ብዙ እንዲለፋ እያደረገው ይገኛል። ማህበረሰቡም ቢሆን እንዲሁ ብዙ ዋጋ እየከፈለበት ነው ይላሉ።
እንግዳችን ይህንን እልሀቸውን ለመወጣት በጋዜጠኝነቱ ከልጆቻቸው የጀመረ ሥራ እየሠሩ ይገኛሉ። የመጀመሪያ ልጃቸው የወጣቶች ፕሮግራም፤ ሁለተኛና ሦስተኛ ልጆቻቸው ትንሽ ቢሆኑም የሕጻናት ፕሮግራም እያዘጋጁ አገርን የማስተዋወቅ ሥራ ይሠራሉ። አገርን መውደድ፣ ስለ አገር ማወቅና ያወቁትን መናገር እንዴት እንደሆነም ያስተምራሉ። ምክንያታቸው ደግሞ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን አገርን በራሱ መውደድ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው ከእርሳቸው በላይ የተጠቀመበት ማንም እንደሌለ ያምናሉና ነው። ከውጪው ወጣ ሲሉም በአገራቸው ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ እንደማንኛውም ዲያስፖራ የሚጠበቅባቸውን ያደርጋሉ። ለአብነት ለህዳሴ ግድቡ ቋሚ ድጋፍ ማድረጋቸው፣ የውጭ ጫናውን ሊቀንሱ የሚችሉ የዲያስፖራ እንቅስቃሴዎች እንዲጠናከሩ መሥራታቸው፣ በመገናኛ ብዙኃን ጭምር መግለጫዎችን ከመስጠት እስከ ማስተላለፍ ድረስ የሚደርሱ ሥራዎችን መከወናቸው በዋናነት ይጠቀሳሉ።
‹‹በየአቅጣጫው የአማራው ብሔር ተጨፍጭፎ ሳለ አሸባሪው ህወሓት ግን በቀደመ ማንነቱ መረጃው እንዲዛባና ዓለም ላይ እንዲደርስ ውጪ ባሉ ተላላኪዎቹና ደጋፊዎቹ ያናፍሳል። እንደውም የሞቱት ትግራዊያን ናቸው እስከማለትም ደርሶ ነበር። በዚህም እውነታውን አውቆ የሚደግፍ የውጭ አገር እንዳለ ሁሉ ሳያውቅ የህወሓት ተባባሪም ይፈጠራል፤ ተፈጥሮ እየታየም ነው። ›› የሚሉት ባለታሪካችን፤ ይህ እንዳይሆን ሴራውን ለማክሸፍ የተለያዩ ሥራዎችን እየከወኑ እንዳሉም አጫውተውናል። ከእነዚህ መካከል የመንግሥት አጋርነትን በተለያየ መንገድ ማሳየት፣ መከላከያን መደገፍና የውሸት ፕሮፓጋንዳዎችን ሊያከሽፉ የሚችሉ ሥራዎችን መስራት የሚሉት በዋናነት ይካተታሉ። ለዚህም በመላው ዓለም የሚገኙ የዲያስፖራ ኃላፊዎች በአገር ውስጥ መጥተው እውነታውን እንዲያረጋግጡ ሆነዋል። ይህንን መረጃም ለዓለሙ ማህበረሰብ የሚያሳውቁ ይሆናል ብለዋል። የኢትዮጵያ የዲያስፖራ ሙዚየምን ለመመስረት እየተንቀሳቀሱ እንደሆነ አጫውተውናል።
ሙዚየሙ የሚቋቋምበት ምክንያት የኢትዮጵያ ቅርሶች በተለያዩ አገራት በመኖራቸው መሰረታቸው ኢትዮጵያ እንደሆነች ለማሳየት ታስቦ የሚሠራ ነው። ለምሳሌ እንግሊዝ ላይ ያለው ሳንቲም ማንም አገር በብር መገበያየት ሳይጀምር ኢትዮጵያ ስታደርገው እንደቆየች የሚያመለክት ነው። እናም ዋናውን ባይሰጡን እንኳን ኮፒውን በማምጣት መነሻነቷን ለማሳየትና ታሪካችንን ለማቆየት ይሰራል ብለዋል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን የተሰጡ ሽልማቶችንም እንደሚያካትት ተናግረዋል።
እንግዳችን በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያን ዳግም ለልማት እንዲነሱ በማድረጉም ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ምክንያቱም ብዙዎች ቀደም ሲል በነበረው መንግሥት የተለያየ ጫና ምክንያት በልማት እንዳይሳተፉ ሆነዋል። አሁን ግን ብዙ እድሎች ክፍት በመሆናቸው ሀብታቸው ለአገራቸው እንዲውል ለማድረግ በቻሉት ሁሉ እየጣሩ ነው። ለዚህ ግን ለመንግሥት ትልቅ አደራ ይሰጣሉ። ዲያስፖራው ከመንግሥት ጎን ሆኖ በልማት፣ በድጋፍና በእውቀት እንዲደግፍ ከተፈለገ ፕሮክራሲዎች መጥፋት አለባቸው። የኢንቨስትመንት ፖሊሲም መሻሻል አለበት ይላሉ።
አዲሱ መንግሥት በሥራችን ስኬታማ እንድንሆን በውጭ ጉዳይ አካባቢ የሚመደቡና አምባሳደር ተብለው የሚሰየሙ አካላት አገራቸውን ጠንቅቀው የሚያውቁና ዲፕሎማሲውን የሚያሳልጡ መሆን እንዳለባቸው የጠቆሙት አቶ ዘውዱ፤ የእስከዛሬው ውድቀታችን መንስኤው እነዚህ ሥራዎችን ባለመሥራታችን የመጣ ነው። ከሁሉም በላይ ለጎሳዬ የሚል አስተሳሰብን ማስቀረት አለመቻላችንም ነው። እናም ምክንያታዊነት ላይ ሊሠራ እንደሚገባ ይናገራሉ። ዲያስፖራው እኔ አካባቢ ላይ ካልሠራህ ሊባል እንደማይገባውም አበክረው ያስረዳሉ።
መልዕክት
የውጭ መገናኛ ብዙኃን ጥቅም ተኮር እንደሆኑ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል። የኢህአዴግንም የሚያግዙበት መንገድ ብዙ ነበር። ለአብነት ምርጫ 97ን ብቻ ማንሳት ለዚህ በቂ ማስረጃ ነው። ቅንጅት እየመራ ሳለ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘገባቸውን እንዲያቆሙ ተደረገ። የሚዘግቡ ከተገኙ ደግሞ ርምጃ ተወሰደባቸው። በተለይም የግሉ ላይ የነበረው ጫና ቀላል አልነበረም የሚሉት አቶ ዘውዱ፤ ብዙ ሰዎች ለመሞታቸው መንስኤ እንደነበር ያስታውሳሉ። በተለይም በተቃውሞው የረገፈ ወጣት ቀላል እንዳልነበር ያነሳሉ። ነገር ግን ዛሬ ላይ በሆነው ባልሆነው የሚጮኸው የውጭ መገናኛ ብዙኃን ምንም አይነት ሽፋን አልሰጠም ነበር። ታዲያ የትኛው የሰብዓዊ መብት ታጋይነታቸው ነው አሁን የሚያስጮሀቸው ሲባል መልሱ ጥቅም የሚል ይሆናልም ባይ ናቸው።
በዚህ ምርጫ ጊዜ በወቅቱ ሸሽተው ለማምለጥ የሚፈልጉ ሁሉ የሚባሉት ‹‹ ኢትዮጵያ የሰላምና የዲሞክራሲ አገር ነች›› ይባልም ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ኢህአዴግ እነርሱ የሚፈልጉትን ሥራ እየከወነላቸው ስለሆነ ክፍተት መፍጠር አይፈልጉም። በዚህም ትውልዱ እንዲሰቃ ፈርደውበታል። ከዚህ አንጻርም የዛሬ ዘፈናቸው ከጥቅማቸው አንጻር እንጂ ከምንም እንዳልመነጨ መገንዘብ ያስፈልጋል ይላሉ። የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ይህንን ተግባራቸውን የሚያከሽፍ ሥራ ቀድመው በተለያየ ቋንቋ መሥራት አለባቸውም ምክራቸው ነው።
የውጭ ጫናው መንስኤ ኢትዮጵያ የጀመረችው የእድገት እንቅስቃሴ አፍሪካን የሚያድን መሆኑ እየታየ መምጣቱ ነው። ይህ ሆነ ማለት ደግሞ የውጭውን ዓለም እርቃኑን ያስቀረዋል። ስለዚህም ከአሁኑ መታገል ግድ ነውና ጠላትን እየደገፉ ለልማት የሚሠራውን መንግሥት እያኮሰሱ መዳረሻውን ማጥፋት ላይ ዘምተዋል። ብዙው ማህበረሰብም ዋጋ እንዲከፍል አድርገዋል። እናም በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ በአገር ውስጥ ያሉት ይህንን ጥላቻ ያነገበ እንቅስቃሴ ለመግታት መጀመሪያ አንድነታቸውን ማጠንከር ይኖርባቸዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ለራሳቸው መብት ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም መብት የሚሟገቱ መሆኑን ሱማሊያ ትመስክር የሚሉት ባለታሪካችን፤ በሱማሊያ ሕግ ማስከበር ላይ የተሰማሩ ዜጎቻችን ሌላ አገር ላይ ሞት ተደግሶላቸው ሰው የተባለ ፍጡርን ሲጠብቁ ይታያሉ። እንደ አሜሪካ አይነቶች ግን አንድም ወታደር ከራሳቸው ውጪ እንዲጎዳ አይፈቅዱም። ለማንም ወታደራቸውን ልከው ጠበቃ አያደርጉም። ታዲያ ሰብዓዊ መብት ታጋይነትን ማን ያስተምር ሲሉ ይጠይቃሉ። መልሰውም እኛ ያለምክንያት የምናደርገው ነገር እንደሌለ መረዳትና ከመከላከያ ጎን ቆሞ አገርን ማዳን የዛሬ ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት እንደሆነም ይመክራሉ።
የእንግሊዞችም ሆነ የአሜሪካኖች ጥላቻ የከፋ እንደሆነ የሚያሳየው በአገራቸው ጭምር ችግሮች ሲፈጠሩ እያዩ ዝም ማለታቸው ነው። ለዚህም ማሳያው ለንደን ላይ የኢትዮጵያ ኢንባሲ ውስጥ ባንዲራው ወርዶ የኦነግ ባንዲራ ሲሰቀል ምንም ማለት አለመቻላቸው ነው። በደህንነት ጉዳይ እንግሊዝን የሚያክል ጥንቁቅ አገር ማንም አልነበረም። ጥፋተኞችን ነጥላ በደቂቃዎች ውስጥ መያዝ ትችል ነበር። ሆኖም መረጃው እያላት ዝምታን መርጣለች። እኛ አገር ላይ ግን በተቃራኒው ነው። በኢንባሲው ሥር እንኳን ማለፍ አይቻልም። ለዚህም ኃላፊነቱን የሚወስደው መንግሥት ነው፤ በደንብ እንዲጠበቅ ያደርጋል። የእነርሱ አገር ላይ ግን ይህ ሲደረግ አይታይም። ይህ ደግሞ የሚያሳየው እነርሱ ለአገራችንም ሆነ ለመንግሥታችን ክብር አለመስጠታቸውን እንደሆነም ያስረዳሉ።
በመጨረሻ ያነሱት ሕገመንግሥቱን ሕዝብ በሚፈልገው መልኩ መቀየርና ሊያሠርው በሚችለው መልኩ ማድረግ እንዳለበት ሲሆን፤ ሕዝቡም ሁልጊዜ መንግሥትን ከመቃረን ሊቆጠብ ይገባል ብለዋል። ምክንያታቸውንም ሲያብራሩ የራሱን ኃላፊነት ሳይወጣ ቁጭ ብሎ እየዋለ መንግሥትን የሚቃወም መኖሩ ነው። በዚያ ላይ መብቱን የሚያስከብር ሰውም አናሳ ነው። ስለዚህም ሕብረተሰቡ መብቱን እያስከበረ ከሥራ ጋር የተዋሀደ ተቃርኖ ማድረግ አለበት። ከግለሰብ እስከ ማሕበረሰብ ድረስ መታገልና ማሳመንን ልምድ ሊያደርግ ይገባል ምክራቸው ነው። ሰላም!!
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14 ቀን 2014 ዓ.ም