ዓለማቀፉን ብዙኃን መገናኛ በተለይ ቢቢሲንና ሲኤንኤንን ለሁለት አሥርት ዓመታት ያህል ተከታትያለሁ። በዚህም ብዙ ብዙ አትርፌያለሁ። የዓለምን ውሎና አዳር ከማወቅ፤የምወደውን የጋዜጠኝነት ሙያ ከማዳበር ባሻገር ስለ ውስብስቡና ተለዋዋጩ የዓለማቀፍ ግንኙነት ትብታብ ትዕምርት እንድቀስም፤በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ በራስ መተማመን ስሜት እንድናገር እንድጽፍ እንድሞግት እንድሰናዘርና እንድተነትን ረድቶኛል።
የእንግሊዘኛ ክህሎቴን እንዳጎለብት አግዞኛል።እንደ ፋሪድ ዘካሪያ ካሉ ጎምቱ ጋዜጠኞች ጋር አስተዋውቆኛል። የምዕራባውያንን የአሜሪካንን የዓለማቀፍ ተቋማትን ነገረ ዓለም መመልከቻ መስኮት ሆኖ አገልግሎኛል። ብዙዎቹን ጋዜጠኞች ከአብሮ አደጎቼ ከቤተሰቦቼና ከጓደኞቼ አንዱ የሆኑ እስኪመስል ስማቸው በአፌ ቦታ አግኝቷል።ጁዲ ሱዋሎ ጁሊያን ማርሻል ስቴቨን ሳካር ሊስ ዱሴት ክርስቲያን አማንፓር ሪቻርድ ኩየስት ብራይን ኩሞ ወልፍ ወዘተረፈ።
በተለይ ቢቢሲ ሱስ ሆኖብኝ እንዳልነበር ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ ግን ተቆራርጠናል ማለት ይቻላል።ቢቢሲን ጨምሮ አልጀዚራ ሲኤንኤን ዋሽንግተን ፖስት ኒውዮርክ ታይምስ ዘ ኢኮኖሚስትና ሌሎች እንደ እጄ መዳፍ ስለማውቀው የሀገሬ እውነት ቆርጠው ቀጥለው በርዘውና ከልሰው ይባስ ብለው በሬ ወለደ አይነት መረጃ ሲነዙ ስመለከት አንቅሬ ለመትፋት ተገድጃለሁ።ትራምፕ “ፌክ ኒውስ፣ ኢነሚ ኦፍ ዘ አሜሪካን ፒፕል”ሲላቸው በንዴት እጦፍ እንዳልነበር ዛሬ እኔ ብሻለሁ።
ሌት ተቀን እንዳልተጣድሁባቸው፤ዛሬ ለራሴ እስኪገርመኝ ድረስ አንድ ጊዜ እንኳ ለመመልከት መቸገር ጀምሬያለሁ።የጋዜጠኝነት ቤተ መቅደስ አእማድ አድርጌ የምቆጥራቸው እውነትነት ተጨባጭነት ሚዛናዊነት ገለልተኝነት ወደ አንጻራዊነት ኮስምነውብኛል።የእኔ እውነት ለእነሱ ምንም እንዳልሆነ ስገነዘብ ወሽመጤ ተቆርጧል። ከጋዜጠኝነት መርህ ይልቅ ሌላ የሚታመኑለት የቆሙለት ስውር ፍላጎት ደባና ሴራ እንዳለ ተረድቻለሁ።
እኤአ አቆጣጠር በ2022 ዓም 100ኛ ዓመቱን የሚያከብረው የእንግሊዙ ቢቢሲ በዓለማቀፉ የሚዲያ መልክዓ ጉልህ አሻራ ማኖር የቻለ ፋና ወጊ ተቋም ነው።ከወጭው 60 በመቶ በመንግሥት ይደጎማል።ከዩናይትድ ኪንግ ደም የውጭ ግንኙነት ፓሊሲ ማስፈጸሚያና ተጽዕኖ መፍጠሪያ መሳሪያዎች(ሶፋት ፓወር)ቀዳሚው ነው።ብሪትሽ ካውንስል ብድርና እርዳታ ከውጭ ግንኙነት መሳሪያዎች ረድፍ ይሰለፋሉ።
ከወግ አጥባቂ ሀገሬዎች ይልቅ ለግራ ዘመሞች በማድላት ይከሰሳል።ከቶሪ ወይም ከኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ ይልቅ ለሌበር ያደላል።ዓለማቀፍ እይታዊ ከምዕራባውያን ከአሜሪካና ከዓለማቀፍ ተቋማት እይታ አንጻር የተቃኘ ነው።በዓለማቀፍ ሽብርተኝነት በሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአየር ንብረት ለውጥ ከሌሎች ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ጋር ከሞላ ጎደል ተቀራራቢ የአርትኦት ፓሊሲ ይከተላል።
በመካከለኛው ምስራቅ ዋና መቀመጫውን ያደረገ የመጀመሪያዊ ዓለማቀፍ ቴሌቪዥን ጣቢያ ተደርጎ ይወሳል።በኳታር መንግሥት የተቋቋመውና ዶሃ የከተመው አልጀዚራ።እኤአ በ2006 ዓም ከ15 ዓመታት በፊት የተመሰረተ ብላቴና ነው።በመካከለኛው በሩቅ ምስራቅ በሰሜን አፍሪካና በሙስሊም ሀገራት እንዲሁም በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነት እያገኘ ያለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው።የአሜሪካንና የምዕራባውያንን”እውነትና ንጻሬ”የሚሞግት እንደገና ለመበየንም የማያመነታ ለሱኒ ለፍልስጤም ወገንተኛ የሆነ ግራ ዘመም ቴሌቪዥን ነው።
በግሌ መገኛው(ፕላትፎርሙ) መደበኛ ሚዲያ ቢሆንም ይዘቱ ግን ለማህበራዊ ሚዲያ የሚያደላ ሆኖ ይሰማኛል።ለብቻው መጠናት ያለበት ሚዲያ ነው ብዬም አምናለሁ።በኤምሬቶች የምትገዛ በሸርያ የምትተዳደር ሀገር እንዲህ ያለ ጠንካራ ቴሌቪዥን ማቋቋሟ በልኳ እውቅና ሊሰጠው ይገባል።በዶሃና በለንደንና በሚገኙ ስቱዲዮዎቹ በቅብብልና በተራ የሚሰራጨው አልጀዚራ ፊት ለፊት ፈጦ ባይወጣም ጥበብ በተሞላበት መንገድ የኳታርን ጥቅም ማስከበሩ ሳይታለም የተፈታ ነው።ከቢቢሲና ከሌሎች የምዕራባውያን ሚዲያዎች ባስኮበለላቸው ጋዜጠኞች የተደራጀው አልጀዚራ ከቢቢሲ፣ ከሲኤንኤን ፣ከስካይ ኒውስ የወሰዳቸው ቅርጾችና ይዘቶች ስላሉ አልፎ አልፎ እነሱን እነሱን ቢሸት አይገርምም።
የአሜሪካው ሲኤንኤን እኤአ በ1980 ዓም የ24 ሰዓት ስርጭት የጀመረ ፋና ወጊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው።በባህረ ሰላጤው ጦርነት (እኤአ1990/91)የቀጥታ ዘገባዎቹ ከፍተኛ ዝና በማግኘቱ ከፎክስና ከኤምኤስኤንቢሲ ጋር ለመፎካከር በቅቷል። ከዓለም በ14ኛ ደረጃ የሚገኘው ሲኤንኤን ንብረትነቱ የዋርነርና የኤቲኤንድቲ ሲሆን ከቢቢሲና አልጀዚራ ዓለማቀፍ ትኩረት ይልቅ ለአሜሪካ ጥቅሞች ፍላጎቶችና እሴቶች ያደላል(አሜሪካን ኦሬንትድ) ነው ተብሎ ይታማል።
ይህ አቋሙ ሉላዊነትንና ትልቅ መንግሥት(ቢግ ገቨርንመንት) ጠል በሆነው ቀኝ አክራሪ ጥርስ ከማስነከስ አልፎ በተለይ በትራምፕ ሪፐብሊካንንና ደጋፊዎች በሕዝብ ጠላትነትና በዋሾነት ተፈርጇል።እንደ አብዛኛው ኢትዮጵያዊና ትውልደ ኢትዮጵያዊ የዴሞክራት ደጋፊ ስለነበርሁ የትራምፕን የሲኤንኤን ክስና ፍረጃ ሳልቀበለው ብኖርም በሀገሬ ሲመጣ ግን እውነትም ከማለት አልፌ ደመኛዬ አደረግሁት።
እኛን ብቻ ሳይሆን ሲኤንኤን ይደግፈዋል ተብሎ የሚታማበትን የዴሞክራት ፓርቲ መርጠዋል የሚባሉትን ትውልደ ኢትዮጵያውን ጭምር ከድቷል።በነገራችን ላይ የባይደን አስተዳደር እነዚህ መራጮቹንና ደጋፊዎችን ነው ለአሸባሪው ህወሓት ሲል በጠራራ የከዳው።
40 ዓመት በተሻገረው እድሜው ለዛውም በድህረ ቀዝቃዛው ጦርነት ባልተለመደ ሁኔታ ባለፉት ሦስት ዓመታት ስለኢትዮጵያ ይሄን ያህል ሰፊ አሉታዊ የዜና ሽፋን ሰጥቶ አያውቅም።አሜሪካ እሴቶቼ ብላ የምትመጻደቅባቸውን የዴሞክራሲ አላባውያን ማለትም የሚዲያ ነጻነት የሰብዓዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች በተሻለ ሁኔታ ለመተግበር ጥረት በሚያደርግ የዐቢይ አስተዳደር ላይ መዝመትን ለዛውም በሐሰተኛ መረጃ ለምን ፈለገ ?የሚለው ጥያቄ በአእምሮዬ የሚመላለሰው ለዚህ ነው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የተመሠረተባቸው ዋና ዋና አእማድ ዓለማቀፍ ሽብርተኝነት እስራኤል ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ብሔራዊ ጥቅም ናቸው።እነዚህን አእማድ ከኢትዮጵያ አንጻር እንመልከት።ቀደም ባሉት ዓመታት ሀገራችን በጸረ ሽብር ትግሉ የአሜሪካ ግንባር ቀደም አጋር ነበረች። የአልቃይዳ ክፋይ የሆኑትን እስላሚክ ኮርትና አልሻባብን ለመታገል ቀድማ ጦሯን ወደ ሶማሊያ አዝምታ ለቀጣናው(ቤል አል ሜንደብ) ደህንነትና ሰላም የአንበሳውን ድርሻ አበርክታለች።
ምሥራቅ አፍሪካ የዓለማቀፍ ሽብርተኛ መናኸሪያ እንዳይሆን በከፈለችው ዋጋ አልሻባብ በተወሰነ አካባቢ ብቻ እንዲወሰንና የቀጣናው ስጋት እንዳይሆን አድርጋለች።ሆኖም አሁን ዓለማቀፍ ሽብርተኝነት ለአሜሪካ ስጋት ወደማይሆንበት ደረጃ ስለደረሰ የኢትዮጵያን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ዝቅ አድርጋዋለች።ይህን ተከትሎ የግብፅ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ከፍ ብሏል።
ብሔራዊ ጥቅሟና የእስራኤልን ጉዳይ ወደፊት አምጥታዋለች።ነጩ ቤተመንግሥት ዙፋን ላይ የተቀመጠው ዲሞክራት ይሁን ሪፐብሊካን የእስራኤልና የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም አንድም ሁለትም ናቸው።ዘመኑ የሰጥቶ መቀበል ነውና ግብጽ የእስራኤልና የፍልስጤም ጉዳይ ባለበት እንዲረግጥ ስትሰራ አሜሪካና እስራኤል በተለይ በአሜሪካና በአውሮፓ ያሉ ተፅዕኖ ፈጣሪ አይሁዳውያን ለግብጽና ለተላላኪዋ ህወሓት የፓለቲካ የዲፕሎማሲና የፋይናንስ ድጋፍ ያደርጋሉ።ያው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለማድረግ መንገዱ ዝግ ስለሆነባቸው እንጂ ከማድረግ ውደ ኋላ አይሉም ነበር ።
ትውልደ ሱዳናዊዋ ከፍተኛ የሲኤንኤን ዘጋቢ ኒማ ኤልባገር እንኳ በጥቂት ወራት ብቻ ስለኢትዮጵያ ወደ 10 የሚጠጉ ሀሰተኛና የተዛቡ ዜናዎችን ፈብርካለች።እጅግ ከበድ ያሉ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተው በሚተነተኑበትና አይሁድ አሜሪካዊ በሆነው ወልፍ ብሊትዝ በሚመራው”ሲቹየሽን ሩም፣” ሳይቀር ሀገራችን መነጋገሪያ አጀንዳ እስከ መሆን የደረሰችው በዚህ ዓለማቀፋዊ ትብታብ ተጠልፋ ቢሆንም እንደ ኒማ ያሉ ለእውቅናና ለዝና ለቋመጡ ጋዜጠኞች ምቹ ሁኔታ መፍጠሩ አልቀረም።
ቀውስ ባለበት ሀገር ሁሉ ህይወቷን አስይዛ በመገኘት በምትሰራቸው “የምርመራ ዘገባዎች”ከደርዘን በላይ ሽልማቶችን ያጋበሰችው ኒማ በየመን በሱማሊያ በሊቢያ በሱዳን ቦኮሀራም በሚንቀሳቀስበት የናይጀሪያ ግዛት በኮንጎ ወዘተ ዘገባዎችን መስራቷና መሸለሟ ለዝና ለእውቅና ሱስ እንድትወሰድ (ኦብሴስድ)እንድትሆን ሳያደርጋት አልቀረም። በሀገራችን ላይ የሠራቻቸው የተዛቡና ሐሰተኛ መረጃዎች የዚህ አባዜ ምሶች ናቸው።ሆኖም በሀገር ቤትም በውጭም ባሉ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያን የቲዊተርና የተቃውሞ ዘመቻዎች ገመናዋ አደባባይ ተሠጥቷል። ተጋልጧል። ለዚህም ይመስላል ድራሽዋ የጠፋው።እዩኝ እዩኝ ደብቁኝ ያመጣል እንዲሉ።
ሲኤንኤን ካሉት ፕሮግራሞች ከጂፒኤስ ቀጥሎ “ሲቹየሽን ሩም”ተወዳጅ ነው።ለዚህ ነው በጣም አንገብጋቢና ወሳኝ ሀገራዊና ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች የሚነሱበት ስለሆነ በኋይታውስ ፕሬዚዳንቱ አንገብጋቢ ጉዳይ ሲገጥማቸው ካቢኔዎቻቸውን በሚሰበሰቡበት የጆን ኤፍ ኬነዲይ አዳራሽ ወይም”ሲቹየሽን ሩም” የተሰየመው።ባራክ ኦባማ በቀጥታ የቢን ላደንን ግድያ የመሩት በዚሁ ክፍል ሆነው ነው።
የኢትዮጵያ ጉዳይ እዚህ ድረስ የጦዘበት ዋናው ምክንያት የእስራኤልን ጥቅም በግብጽ በኩል ለማስከበር በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የተነሳ ግብጽ የህልውናየ ስጋት ሆናለች የምትላትን ኢትዮጵያ አዳክሞ ለማፍረስ ነው።አሸባራ ህወሓት አፈር ልሶ እንዲነሳ የሚደረግለት የፓለቲካ የዲፕሎማሲና የሚዲያ ድጋፍ የዚህ አደገኛ ፕሮጀክት አካል ነው።
ከፍ ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት እንደ ኒማ ኤልባገር ያሉ ጋዜጠኞቹ ይሄን ቀውስ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ለሌላ ዙር እውቅናና ሽልማት መታጫነት ተጠቅመውበታል። ኒማ “በምርመራ ጋዜጠኝነት”ና በሚያስገኘው ሽልማትና እውቅና አቅሏን የሳተች(ኦብሴስድ) የሆነች ጋዜጠኛ ናት እንዳልሁት እውቅናና ዝና እስካስገኘላት ድረስ ህይወቷን ሳይቀር አሲዛ የምትቆምር ቁማርተኛ ናት።
ሰሞነኛው በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ የዘገበችው”የምርመራ ዜና”ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።ቀደም ሲል በተከዜ ወንዝ ላይ ማሰቃየት የተፈጸመባቸው የትግራይ ተወላጆች ተገድለው”ተጥለው” ተገኙ የሚለው ሀሰተኛ ዜናዋም ለእርካሽ ዝና ስትል የምትሔድበትን እርቀት ያሳያል።
ለእሷ ሽልማት እስካስገኘ ድረስ ሀገር ቢፈርስ፤የእርስ በርስ ግጭት ቢቀሰቀስ ደንታዋ አይደለም።ለሽልማት ሱስ፣ሀገር ይፍረስ፤ማለት ይሄ ነው።ሆኖም ከፍ ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት የሲኤንኤንም ሆነ የኒማ ሐሰተኛ ዘገባዎች በውጭ በተለይ በአሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያን ዘንድ ቁጣ በመቀስቀሱ ሲኤንኤን በር ላይ የተቃውሞ ሰልፍ እስከማካሄድ ከመድረሱ ባሻገር በማህበራዊ ሚዲያው በተለይ በቲዊተር ላይ የተደረገ የተቀናጀ ዘመቻ ሲኤንኤንንም ሆነ ኒማን ማስደንገጡና ማሳጣቱ አልቀረም።
ቆም ብለው እንዲያስቡ ሳያደርጋቸው አልቀረም።ይህ የዜጎች የአርበኝነት ትግል ከግዕብታዊነትና ስሜታዊነት ተላቆ በተደራጀና በተጠና አግባብ መመራቱ አበረታች ውጤት እያስገኘ ስለሆነ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት። ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!!
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14 ቀን 2014 ዓ.ም