አበው ሲተርቱ “ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው” ይላሉ። ወሬ፤ በተለይ የተሳሳተና ሆን ተብሎ የተፈበረከ የውሸት ወሬ የሚያደርሰው ጥፋት ብዙ ነው። ይህንን አባባል ደግሞ አሸባሪው ሕወሓት በብዙ መልኩ እየተጠቀመበት ይገኛል። ከአሸባሪው ሕወሓት የወሬ ቋት እየተፈበረኩ የሚለቀቁ የውሸት ፕሮፓጋዳዎች ሰዎች ይታዘቡኛልን አሽቀንጥረው የጣሉ፤ ሰው ምን ይለኛል ከማለት ይልቅ ቆሞ ቀሮች የውስጣዊ ማንነታቸውን የሞራል ውድቀት ለመሸሸግ እየተጋጋጡ መሆናቸውን ያየንበት ነው።
ከዚህ የአሸባሪ ቡድን የሚወጡ ወሬዎች ታዲያ ሁለት መልክ አላቸው። በአንድ በኩል ለሽንፈታቸው ማካካሻ እና ከፊት እያሰለፉ ለሚያስጨርሱት ወጣት የስነልቦና ግንባታ በሚል የሚጠቀሙበት የ “አሸንፈናል፣ ወደፊት እየገፋን ነው፣ ከፈለግን አዲስ አበባ መግባት እንችላለን” የድክመት ማካካሻ ወሬ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ “ሊጨርሱን ነው፣ በረሃብ አልቀናል፣ ከዚህ መዓት አውጡን” የሚል ለውጭ ማህበረሰብ የሚሰማ ጩኸት ነው።
አሸባሪው ሕወሓት አስገራሚ ባህርያት ያሉት ቡድን ነው። የሽብር ብድኑ ጦርነት 90 ከመቶ የውሸት ፕሮፓጋንዳ ነው። የሚጠቁሙት የጦርነት ስልት ደግሞ ከአርባ ዓመት በፊት ሲጠቀምበት የነበረው ያረጀ ያፈጀ እና ዘመኑን ያልዋጀ “ቆረጣ ” እየተባለ የሚጠራውን የጦርነት ስልት ነው። ዛሬም ይሄን የጦርነት ስልት ይዞ አሸነፋለሁ ብሎ የሚንገታገት ኋላቀር ሽፍታ ነው።
ከአረጃ እና ከአፈጀው ቆረጣ ከሚሉት የጦርነት ስልታቸው በተጨማሪ አሁን ላይ በፊት ይጠቀሙት ከነበረው የጦርነት ስልታቸው አንዱ የሆነውን ጥቂት ወጣቶችን ክላሽ በማሲያዝና በጎን አስርገው በማስገባት፤ ሰርገው በገቡባቸው ቦታዎች ደግሞ ጥይት በመተኮስ እና ፎቶ በመነሳት ይህንን አካባቢ ተቆጣጥረናል፤ ይህንን ያህል ማርከናል፣ በሺዎች ገድለናል፣የሚል ፕሮፓጋንዳ እንዲነዛ በማድረግ ሽብር መፍጠር ነው።
ለዚህም በማስረጃነት ሰሞኑን ሲነዙ ከነበረውን ፕሮፓጋዳ ላስታውሳችሁ። አሸባሪው ሕወሓት በሃገር መከላከያ ሠራዊት የተሰነዘረበትን ጥቃት መቋቋም ሲያቅተው ባለሁለት ምላሱ የሽብር ቡድን ፕሮፓጋዳውን በሰፊው ተያይዞታል። ይህ ፕሮፓጋዳ ዓላማ ያደረገው ደግሞ በአንድ በኩል ወደጦርነት የሚማግዱት የትግራይ ህዝብ ነው። ለዚህ ህዝብ የሚቀርብለት ፕሮፓጋንዳ “27 ክፍለ ጦሮችን ደመሰስን፣ አራት ኪሎ እንገባለን፤ ኢትዮጵያን አፍርሰን የራሳችንን መንግሥት እንመሰርታለን” ወዘተ የሚሉ የህልም እንጀራዎች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ ለውጭው ወዳጆቻቸው “አለቅን፣ ማዕከላዊው መንግሥት በረሃብ ሊጨርሰን ነው፤ በአውሮፕላንና በድሮን እየፈጀን ነው፤ ወዘተ” የሚሉ የአድኑን መልዕክት የያዘ ነው።
አስገራሚው ነገር ለነዚህ ሰዎች ቁጥር ቀላል ነገር ነው። በአንድ ግንባር 3194፣ በሌላ ግንባር 2691፣ በሌላ እንዚሁኑ ቁጥር እየጠቀሱ ገደልን፣ ፈጀን፣ ይላሉ። እውነት ግን በዚያ ጦርነት መካከል አስከሬን የሚቆጥር ጁንታ መድበው ይሆን፤ ወይስ ሰው ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል ብሎ መጠየቅ አይችልም ከሚል የመደፈን ምልክት ነው? እንዲህ ቁጥር እየጠቀሱ በዚያ ጦርነት መካከል ያንን ያህል የገደሏቸው ሰዎች እንዴት ቆጠሩ የሚል ጥያቄ እደሚነሳ እንኳ ለማገናዘብ ቆም ብሎ የሚያስብ ጭንቅላት እንደሌላቸው መገንዘብ ይቻላል። በርግጥ ጥቂት በነሱ ፕሮፓጋዳ ያበዱ ደጋፊዎቻቸው ውሸትም ቢሆን በሚነገራቸው የድል ዜና ውስጣዊም ባይሆን የውሸት ደስታ ሊጎናፀፉ ይችላሉ። ይህ ግን ዘላቂ ደስታ ሳይሆን ራስን ማታለል ነው።
ሌላኛው ስልታቸው ደግሞ በርካታ የሲቪል ሰዎችን በአብዛኛው ሕፃናት፣ አረጋውንና ሴቶችን ከፊት በማሰለፍ በህዝብ ማዕበል ወደፊት ለመግፋት መሞከር ነው። ይህ በብዙ መልኩ ጊዜ ያለፈበት ኃላፊነት የጎደለው የውጊያ ስልት ነው። በዚህም የቱን ያህል የትግራን ህዝብ በየውጊያ ወረዳው ወጥቶ እንደቀረ በቅርቡ እራሱ የትግራይ ህዝብ የሚያውቀው ይሆናል።
ከፕሮፓጋንዳ ቀጥሎ ያለው የሕወሓት የዘመቻ ሥራ ደግሞ በተገኘው ቀዳዳ ሁሉ ጅምላ ጭፍጨፋ ማካሄድ ነው። ይህ ቡድን በማይካድራ የጀመረውን ጅምላ ጭፍጨፋ ተጠናክሮ በማስቀጠል በጭና፣ በቆቦ፣ በአጋምሳ ፣ በጋሊኮማ እንዲሁም በውጫሌ የዘር ማጥፋት ዘመቻ አካሂዷል። እስከ አምስት የሚሆኑ የአንድ ቤተሰብ አባላትን በመግደል አሰቃቂ ግፍ ፈጽሟል።
ከዚህም አልፈው እንስሳትን ከማረድና ከመዝረፍ በዘለለ በቁማቸው በማቃጠልና በጥይት በመፍጀት ከሰው ልጅ የማይጠበቅ አሳፋሪ ድርጊት ፈጽሟል። የደረሰ ሰብልንም በማሳ ላይ በማበላሸት ህዝብን ለማስራብ ዓላማ አድርጎ አሳፋሪ ድርጊት ፈጽሟል። ሰሞኑን ደግሞ በማጀቴ እንዳየነው በማሳ ላይ ታጭዶ የተከመረ የጤፍ ክምርን በእሳት በማጋየት ማንነቱን አሳይቷል። ይህ ሁሉ ሲሆን ግን እነአሜሪካና ወዳጆቻቸው እውነታውን ለመቀበል የሚያስችል ልብ አልሰጣቸውም።
የፕሮፓጋንዳው ዘመቻ እንደተለመደው በፉከራና በስድብ ታጅቦ የሚቀርብ ነው። በተለይ አሸባሪው ጌታቸው ረዳ በስክሪን ፊት በቀረበ ቁጥር ሁለት ነገሮችን ሳያነሳ ያለፈበት ጊዜ የለም። አንደኛ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ሳይሳደብ፤ ሁለተኛ ደግሞ ከፈለግን አዲስ አበባ እንገባለን ሳይል አያልፍም። ለመሆኑ በዚህ መልኩ ከመሰቃየት እና ዞር ብለው ለዓለም ማህበረሰብ ከመጮህ አዲስ አበባ መግባት ከቻሉ ምን ይጠብቃሉ የሚለው ጥያቄ የብዙዎች ነው። ግን ወሬና ተግባር ለየቅልም አይደል።
የአሸባሪው ሕወሓት አባላት ባህርያት በጣም የሚያስገርሙ ናቸው። ልክ እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል እንዳለችው እንስሳ እነሱ ስልጣን ላይ ካልቆዩ በስሙ የሚነግዱት የትግራይ ህዝብም ሆነ ሳይወዱ እየጠሉ ሲያስተዳድሩት የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ ምናቸውም አይደለም። ይህ ባይሆን ታዲያ ለውጡ እውን ይህንን ያህል ዋጋ እንዲከፍሉ የሚያደርግ ምን ችግር ኖሮበት ይሆን በዚህ መልኩ ህዝቡን ለከፋ ችግር የዳረጉት።
የሕወሓት መሰረታዊ ችግር የስነልቦና ቀውስ ነው። እነዚህ ኃይሎች ለራሳቸው የሰጡት ግምትና ለራሳቸውም ሆነ ለትግራይ ህዝብ ያስታጠቁት የውሸት ማንነት ዛሬ ራሳቸውን በራሳቸው ጠልፎ ሊጥላቸው ደርሷል። እነዚህ ሰዎች እነሱ ብቻ ጀግና፣ እነሱ ብቻ አዋቂ እና ሁሌ አሸናፊ የሚሆኑ እየመሰላቸው እኩል እንሁን ሲባሉ ሞት መስሎ ታያቸው። ለዚህ ነው እኩልነት የበታችነት መስሎ የተናነቃቸው።
በተለይ ሕወሓት ከደርግ ጋር ባደረገው ጦርነት ህዝቡ በወቅቱ በደርግ ካድሬዎች ላይ በነበረው ቅሬታ ምናልባት ለውጥ ቢመጣ ይሻል ይሆናል በሚል ለሕወሓትና አጋሮቹ በሩን ክፍት አድርጎ እድል ሰጥቷቸው ነበር። ይህ እውነታ ግን አንድም ቀን በሕወሓት መንደር ተወርቶ አያውቅም። አምልጧቸው እንኳን ህዝቡ ላደረገላቸው ድጋፍ አመስግነው አያውቁም። ይልቁንም እነሱ ጀግኖች በመሆናቸው አሸንፈው እንደገቡ ሲያወሩ ኖሩ። ይህንንም በከበሮ እያጀቡ ሌላውም ማህበረሰብ እንዲቀበል ለማድረግ ጣሩ። በተለይ የትግራይ ህዝብ እነሱ ጀግኖች እንደሆኑ አምኖ እንዲቀበል በርካታ የስነልቦና ጫና አሳደሩበት፤ ታዲያ አሁን ለውጥ መጥቶ እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ እኩል እንኑር ሲባሉ ያልለመዱትና ለ27 ዓመት ያዳበሩት አጉል ሱስ እንዴት ይልቀቃቸው?
እኔ የሚገርመኝ ግን የነዙት ፕሮፓጋንዳ አይደለም። መቼም እነሱ ከፕሮፓጋንዳም በላይ በተግባር የክፋትን ጥግ ያሳዩን የክፋት ተምሳሌቶች ናቸው። ነገር ግን በእነዚህ ሰዎች የሚነዙ አሉባታዎችና የውሸት ወሬዎችን ተቀብሎ በፌስቡክ የሚያራግቡና አልፎ አልፎም እነሱ የሚናገሩትን እየሰማ እውነት መስሎት የሚታለል የህብረተሰብ ክፍል ነው።
በርግጥ እነዚህ ሰዎች ወሬ መፈብረክ ብቻ ሳይሆን ያንን ወሬ የሚያራግብላቸው የሰው ቻናልም የመፍጠር ክህሎት አዳብረዋል። አንድ ቦታ የተነገረ ወሬ እንደ እቃ ከአንዱ ጫፍ ወደሌላው ጫፍ ለማድረስ የተካኑ የውሸት ፕሮፌሰሮችን ፈጥረዋል። የእነዚህ ሰዎች የወሬ አካሄድ የኮሙኒኬሽን ህግን ጭምር የጣሰ ነው። በኮሙኒኬሽን ህግ አንድ ወሬ ከአንድ ጫፍ ወደሌላው ጫፍ ሲሄድ በተወሰነ መልኩ የቅርፅ አንዳንዴም የመልዕክት መዛባት ይደርስበታል። የነሱ የውሸት ፕሮፓጋንዳ ግን ያለምንም ችግር ቀጥ ብሎ የሚጓዝ በመሆኑ ተጠቅመውበታል።
የወሬ አካሄዳቸው ደግሞ መነሻው እነጌታቸው ረዳ ናቸው። ተቀባዮቹ ደግሞ የዓለምአቀፉ ሚዲያና የራሳቸው የወሬ አመላላሾች ናቸው። ስለዚህ ወሬው አንድ ቦታ ከተፈበረከ በኋላ የወሬ ተቀባዮቹ ፈጥነው ወሬውን በመውሰድ በዚህ አካባቢ እኮ ተቆጥረዋል፤ እዚህ አካባቢ ናቸው፤ እንዲህ እያደረጉ ነው በማለት በማባዣ መሳያዎቻቸው አማካኝነት ወሬውን ያዛምታል። ከዚያ ይህንን ወሬ የነሱ ጋሻጃሬዎች እየሳቁ፤ አንዳንዱ ደግሞ ካለማወቅ ወስዶ ያባዛዋል። እናም አሸባሪው ሕወሓት ከህልውናው በላይ ያለው ወሬው ብቻ ሆኖ ዛሬም አለ።
ፀጉራም ውሻ አለ ሲሉት ይሞታል እንደሚባለው አሸባሪው ሕወሓት አሁን አለ ለማለት ከባድ ነው። ከሱ ይልቅ አንደበቱ አሁንም አለ። ይህ አንደበት የሚዘጋው ደግሞ የሐሰት ፕሮፓጋንዳውን ጭንቅላት መዝጋት ሲቻል ነው። ስለዚህ በውሸት ላይ ለተመሰረተው የቡድኑ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ቦታ ሳንሰጥ ይህንን ቡድን መደምሰስና ፊታችንን ወደልማታችን መመለስ ለቀጣዩ ብልፅግናችን ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው።
ውቤ ከልደታ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14 ቀን 2014 ዓ.ም