አገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ የሰው ድንበር ተሻግራ ወረራ የፈጸመችበት ምንም ታሪክ የላትም። ይልቁኑ ከውስጥ በባንዳነት ከውጭ የተፈጥሮ ሀብቷ ያስጎመጃቸው ጠላቶቿ በተደጋጋሚ ሉኣላዊነቷንና ህልውናዋን ለመዳፈር መሞከራቸው ደጋግሞ የተስተዋለ ሐቅ ነው።
ከውጭ ጣልያን፣ ሶማሌ ግብፅ፣ ሱዳን፣ ኤርትራና ሶማሊያ በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ተዳፍረውና ድንበሯን ገፍተው ያደረጉት ወረራ በጀግኖች ኢትዮጵያውያን አኩሪ ተጋድሎና መስዋዕትነት ድል ተደርጎ ሰንደቋ በነፃነት፣ በክብርና በኩራት ዛሬም ድረስ እየተውለበለበ ይገኛል።
ዓድዋ፣ ካራማራ፣ መተማ ወዘተ ኢትዮጵያውያን በነፃነት ተጋድሎ ወራሪዎችን መክተው ድል ካስመዘገቡባቸው ታሪካዊ ሥፍራዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በእነዚህና መሰል የተጋድሎ ቦታዎች ኢትዮጵያውያን የብሄር፣ የሃይማኖት፣ የባህልና የቋንቋ ወዘተ ልዩነት ሳይገድባቸው ለውድ አገራቸው በአንድነት ተጋድለው፤ ደማቸውን አፍስሰውና መተኪያ የሌላት ውድ ህይወታቸውን ሰውተው ነፃነታችንን አስጠብቀው ዛሬ ላይ ደርሰናል።
በረጅም ዘመን ታሪኳ የአገራችንን ነጻነትና የህዝቦቿን ህልውና የተፈታተነው የውጭ ወረራ ብቻ አልነበረም፤ ይልቁኑ ከማሕጸኗ በተወለዱና ፍሬዋን በተቋደሱ ከሃዲ ልጆቿም በርካታ ፈተናዎች አጋጥሟታል። የውጭ ወራሪዎች የኢትዮጵያን ሉኣላዊነት በተዳፈሩባቸው ጊዜያት በባንዳነት ተሰልፈው ምሰጢር የሸጡ፤ እንደ ይሁዳ ወገኖቻቸውን አሳልፈው ለጠላት የሰጡና ከወራሪ ጋር ተሰልፈው እናት አገራቸውን የወጉ ከሃዲዎች መጨረሻቸው ባያምርም አገራችንንና ህዝቦቿን ውድ ዋጋ አስከፍለዋል።
እነዚህ ከሃዲዎች የፈጸሙት የአገር ክህደት ኃጢያት አገራችንን ድል ከማስመዝገብ ሊያግዳት አልቻለም፤ ለዚህ ደግሞ ዋናው ምክንያት ለአገራቸው ፍጹም የታመኑ፣ ቁስና ነዋይን ከአገር ሉዓላዊነት ጋር የማያነጻጽሩ፣ ከግልና ከቤተሰባቸው ሕይወት በላይ አገራቸውን ያስቀደሙ በርካታ ዜጎች ባለቤት በመሆኗ ነው።
በዘመናት ታሪኳ ከውስጥ ጠላት ያላጣችው አገራችን ኢትዮጵያ ዛሬ ደግሞ አገር ለመበተን አልሞ የተነሳና በገባበት ቦታ ሁሉ ጭፍጨፋና ግፍ መለያው የሆነ ሕወሓት የተባለ አሸባሪ የውስጥ ጠላት ገጥሟታል። ከውልደቱ ጀምሮ ሴራ፣ ግፍ፣ ተንኮልና ጭፍጨፋ መለያው የሆነው ይህ አጥፊ ኃይል በምስኪን የኢትዮጵያ ውድ ልጆች የሕይወት መስዋዕትነት ሰልጣን በተቆናጠጠባቸው 27 ዓመታት ሳይቀር በርካታ ኢትዮጵያውንን ገድሏል፤ አገር ዘርፏል፤ በጆሮ ለመስማት የሚዘገንን አስከፊ ግፍም በኢትዮጵያውያን ላይ ፈጽሟል።
አሸባሪው ሕወሓት ከፍጥረቱ አንስቶ በአሰቃቂ ሁኔታ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ከኋላው በመውጋት አሰቃቂ ተግባር እስከፈጸመበት ጊዜ ድረስ የእናት ጡት ነካሽ ሆኖ ቆይቷል። ሀገርን ለማፍረስ ህዝብን ለመጨረስ ከውጭ ጠላቶች ጋር ሆኖ ታሪክ የማይረሳው ተግባር በመፈጸምም ላይ ነው።
ቡድኑ ሀገርን ለጠላት አሳልፎ መስጠት ብቻም ሳይሆን በመንግሥታዊ አገዛዝነት በቆየባቸው 27 ዓመታት ሀገር በኢኮኖሚ እንዳታድግና ህዝቡም ተጠቃሚ እንዳይሆን በአንድ ቡድን የበላይነት ሁሉንም ጠቅልሎ ኪሱን ሲያደልብና ሀብትና ንብረት ሲያሸሽና በውጭ ሲያከማች ቆይቷል።
ይሄም አልበቃ ብሎ አሁን ደግሞ ‹‹እኛ ካልዘረፍን ሀገር እናፈርሳለን” በሚል እብሪትና ትዕቢት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ሰላም ለማደፍረስ በመሥራት ላይ ነው። በተለይም በአፋርና በአማራ ክልልና ህዝብ ላይ በከፈተው ወረራና ጦርነት የበርካታ ንፁሐን ዜጎች ሕይወት ተቀጥፏል። ሀብት ንብረት ወድሟል። ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት ተቃጥለዋል። ልጆች ያለወላጅ አዛውንቶች ያለ ጧሪ ቀርተዋል። ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉና ለተለያዩ ችግሮች የተዳረጉም በጣም ብዙ ናቸው።
ይሄው አሸባሪ ቡድን በማይካድራ፣ ጋሊኮማ፣ ድበረ ታቦር፣ ጭና፣ ጭፍራ፣ ውጫሌና ውርጌሳ በከባድ መሳሪያ ንፁሐንን ከመጨፍጨፍ አንስቶ እጅግ አረመኔያዊ በሆነ መንገድ ቤት ዘግቶና ጋዝ አርከፍክፎ እስከማቃጠል የደረሰ በዜጎች ላይ የግፍ ግፍ ፈጽሟል፤ አሁንም በመፈጸም ላይ ይገኛል። ቡድኑ ለተወሰነ ጊዜ ተቆጣጥሯቸው በቆዩ አካባቢዎች ሁሉ እጅግ አረመኔያዊ የግፍ ተግባር መፈጸም የተለመደ ባህሪው ሆኗል።
ከላይ በተለያዩ ማስረጃዎች የተመለከትነው እውነታ የእናት ጡት ነካሽና አጥፊ የሆነው አሸባሪው ሕወሓት ታሪኩ ሁሉ አዳፋ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። ከዚህም በኋላ ለዚህ የሽብር ኃይል ጊዜ መስጠት አገርን አደጋ ላይ መጣልና የዜጎችን ሰቆቃና ስቃይ መጨመር በመሆኑ ከነአዳፋ ታሪኩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ ወቅቱ የሚጠይቀው ግዴታ ነው፤ለዚህ ደግሞ ሁላችንም በአንድነት ልንነሳ ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 14 ቀን 2014 ዓ.ም