ነገ ከሚደረጉ የጎዳና ላይ የሩጫ ውድድሮች መካከል የአትሌቲክስ ቤተሰቡን ቀልብ በእጅጉ የገዛው የቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶን ነው። በስፔኗ ከተማ የሚካሄደው ይህ ውድድ ከፍተኛውን ትኩረት ሊያገኝ የቻለው በመምና በጎዳና ላይ ውድድሮች በበርካታ ድሎች የደመቁ ኢትዮጵያውያን አትሌቶችን እርስ በርስ በማፋለሙ ነው። የመካከለኛና የረጅም ርቀት የዓለም ከዋክብት አትሌቶች በሚፋለሙበት በዚህ ውድድር በሁለቱም ፆታ አሸናፊውን ከወዲሁ መገመት አዳጋች ቢሆንም የቦታው ክብረወሰን የመሰበር ዕድሉ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል።
የ10ሺ ሜትር ንግስቷ ለተሰንበት ግደይ፣ የመካከለኛ ርቀት ፈርጧ ገንዘቤ ዲባባ፣ በግማሽ ማራቶን ከአንድ ወር በፊት የዓለም ክብረወሰን የሰበረችው የዓለምዘርፍ የኋላው እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የውድድሩ ትኩረት ናቸው። የ10ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን ባለቤት የሆነችው ለተሰንበት ግደይ በርቀቱ የዓለም ክብረወሰን ባለቤቷ ከሆነችው ያለምዘርፍ የኋላው ጋር የሚያደርጉት ፉክክር የውድድሩንም የዓለም ክብረወሰንንም እንዲሰበር ሊያደርግ እንደሚችል ይጠበቃል። ከጥቂት ዓመታት በፊት በመካከለኛ ርቀት አስደናቂ ስኬቶችን ማጣጣም የቻለችው ፈጣኗ ገንዘቤ ዲባባ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ውድድሮች ከአሸናፊት ብትርቅም በዚህ ውድድር የርቀቱ ሁለተኛ ፈጣን ሰዓት ባለቤት በመሆኗ ቀላል ግምት የሚሰጣት አይደለችም።
የ5ና 10ሺ ሜትር የክብረወሰን ባለቤት የሆነችው አትሌት ለተሰንበት ግደይ በ5ሺ ሜትር 14:06.62 የሆነ ሰዓት አላት። የ10ሺ ሜትር የዓለም ክብረወሰን በትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የኔዘርላንድስ አትሌት ሲፈን ሐሰን አማካኝነት ከአትሌት አልማዝ አያና እጅ በወጣ አርባ ስምንት ሰዓት ሳይሞላው አስደናቂዋ አትሌት ለተሰንበት ባለፈው ዓመት መልሳ የግሏ ማድረጓ ይታወሳል። ለተሰንበት በሄንግሎው የኢትዮጵያውያን የኦሊምፒክ ማጣሪያ ውድድር ላይ ይህን ክብረወሰን ለመስበር ያስመዘገበችው 29:01.03 ሰዓት ነበር። በቶኪዮ ኦሊምፒክ የ10ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤቷ ለተሰንበት፤ በ15 ኪሎ ሜትርም 44፡20 በሆነ ሰዓት በመሮጥ የዓለም ክብረወሰን ባለቤት ናት። ብርቱዋ አትሌት በጎዳና ላይ ውድድርም ነገ ብቃቷን እንደምታስመዘግብ ይጠበቃል።
በ1ሺ 500 ሜትር እንዲሁም በ3ሺ ሜትር በይበልጥ የምትታወቀዋና በ5ሺ ሜትር ሯጯ ገንዘቤ ዲባባም የዚህ ውድድር ተጠባቂዋ አትሌት ናት። ፈጣኗ አትሌት በ1ሺ 500 ሜትር እና በ3ሺ ሜትር (3:50.07 እና 8:16.60) ክብረወሰን ባለቤት እንዲሁም በ1ሺ 500 ሜትር የኦሊምፒክ ብር ሜዳሊያ ባለቤት መሆኗ ይታወቃል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውድድሮች ላይ ያልታየችው ገንዘቤ በቫሌንሺያ ግማሽ ማራቶን ያለፈው ዓመት ተሳታፊና አሸናፊ ነበረች። በወቅቱ 1:05:18 በሆነ ሰዓት ርቀቱን በቀዳሚነት ያጠናቀቀችው አትሌቷ በነገው ውድድር ላይም አሸናፊ እንዲሁም የክብረወሰን ባለቤት የመሆን ዕድሏ የሰፋ እንደሚሆን ይጠበቃል።
ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት የዓለምዘርፍ የኋላው ደግሞ ከወር በፊት በዚሁ ርቀት ክብረወሰን በመስበር የበላይነቷን ያስመሰከረች አትሌት ሆናለች። በጎዳና ሯጯ በኢትዮጵያ ታላቁ ሩጫ እንዲሁም በአፍሪካ ቻምፒዮና ላይ ባገኘቻቸው ድሎች ከስፖርት ቤተሰቡ ጋር ተዋውቃለች። በዴልሂ ግማሽ ማራቶን ተከታታይ ተሳትፎዋም አሸናፊ ስትሆን፤ በፖላንዱ የዓለም የግማሽ ማራቶን ቻምፒዮናም ተሳታፊ ነበረች። ከወር በፊት ደግሞ በአንትሪም ኮስት ግማሽ ማራቶን ያሸነፈችበት 1:03:43 የሆነ ሰዓት የዓለም ክብረወሰን ሆኗል። አትሌቷ ርቀቱን ከ1ሰዓት ከ04 ደቂቃ በታች በመሮጥም የመጀመሪያዋ ኢትዮጵያዊት አትሌት ናት። ይህም በዚህ ውድድር የስፍራውን ክብረወሰን አሊያም የራሷን ሰዓት ልታሻሽል ትችላለች የሚል ግምት አግኝታለች።
ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ሰንበሬ ተፈሪም በተመሳሳይ በርቀቱ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ከሚጠቀሱት አትሌቶች መካከል ትገኝበታለች። በወንዶች በኩል ተሳታፊ የሚሆነው ሙክታር እድሪስ ደግሞ ከኬንያዊያን አትሌቶች ጋር ይፋለማል። በ5ሺ ሜትር የሁለት ጊዜ የዓለም ቻምፒዮናው አትሌት በጎዳና ሩጫ ሲሳተፍ ይህ ሁለተኛው ሲሆን፤ በግማሽ ማራቶን ያስመዘገበው ፈጣን ሰዓት ደግሞ 59:04 ነው። ይሁን እንጂ አትሌቱ ከጉዳት ካገገመ በኋላ ለረጅም ጊዜያት በኦሊምፒክ እንዲሁም በሌሎች ውድድሮች ዝግጅት ላይ መቆየቱ በጥሩ አቋም ላይ እንዲገኝ አድርጎታል። በመሆኑም በነገው ውድድር ላይም እንደተለመደው ተፎካካሪዎቹን በአስደናቂ አጨራረሱ አስከትሏቸው እንደሚገባ ይጠበቃል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2014