በ3D የቀለም ቅብ ቴክኖሎጂ የተሰራ ዜብራ ወይም የእግረኞች የመንገድ ማቋረጫ በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምእራብ ሸዋ ዞን በቾ ወረዳ ቱሉ ቦሎ ከተማ ስራ ላይ ውሏል።
የ3D ዜብራ ወይም የእግረኞች መንገድ ማቋረጫው ኤርሚያስ ጌታቸው የተባለ ወጣት ነው የሰራው።
ወጣቱ ኤርሚያስ የ3D ዜብራውን ከበቾ ወረዳ ትራፊክ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር በተሳካ ሁኔታ መስራቱም ተነግሯል።
ወጣት ኤርሚያስ ጌታቸው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደተናገረው፥ የ3D ቀለም ቅብ ቴክኖሎጂ ዜብራውን ለመስራት የተነሳሳው ስለ ፈጠራው በአንድ የቴሌቪዥን ዝግጅት ላይ ከተመለከተ በኋላ ነው።
በሙያው ኤሌክትሪሺያን የሆነው ኤርሚያስ፥ ይህ የ3D ቀለም ቅብ ዜብራ ስራ ግን ቀልቡን ይስብና ለመስራት መወሰኑንም ተናግሯል።
በዚህም ስለ ዜብራው ቀለም ቅብ በኢንተርኔት ላይ በማፈላለግ ካወረደ በኋላ ንድፉን በወረቀት ላይ ሰርቶት ከጓደኛው ጋር ተመካክረውም ለወረዳው ትራፊክ ፖሊስ ያቀርባሉ።
ይህንን ስራ በጓገኛው አነሳሽነት ወደ እውን ለመቀየር ወደ ስራ የገባው ኤርሚያስ፥ ቀለም በመግዛትም የ3D ቀለም ቅብ ዜብራውን በቱሉ ቦሎ ከተማ አስፋልት ላይ መስራት ይጀምራል።
በአሁኑ ወቅትም አንድ ስፍራ ላይ የአስፋልቱን ግማች የእግረኛ ማቋረጫ ወይም ዜብራ በ3D ቀለም ቅብ መስራቱን ነው ኤርሚያስ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የተናገረው።
እስከ ነገ ድረስም ቀሪውን የአስፋልቱን ክፍል ቀብቶ እንደሚጨርም አስታውቋል።
የዜብራው መሰራት የትራፊክ አደጋን ከመቀነስ አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ነው ኤርሚያስ የሚናገረው።
በተለይም አሽከርካሪዎች ዜብራው ጋር ሲደርሱ ዜብራው የቆመ ነገር መስሎ ስለሚታይ ዜብራ ላይ ሰው ኖረም አልኖረም ፍጥነታቸውን ቀንሰው ተረጋግተው እንዲያልፉ ያደርጋልም ብሏል።
ኤፍ ቢ ሲ እንደዘገበው 3D ዜብራ ቻይና፣ ህንድ እና ማሌዢያን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት እየተተገበረ ያለና የትራፊክ አደጋን በከፍተኛ መጠን ለመቀነስ የሚጠቅም መሆኑ ይነገርለታል።