በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ያለ የኢኮኖሚ ጉዳት ከሚያደርሱ የጤና እክሎች ውስጥ አንዱና ዋነኛው የአከርካሪ አጥንት ጤንነት ችግር መሆኑን በዓለም አቀፍ ደረጃ የተሰሩ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ። 80 ከመቶ የሚሆነው የዓለም ህዝብም በህይወት ዘመኑ ቢያንስ አንድ ጊዜ የአከርካሪ አጥንት ጤና ችግር እንደሚገጥመውም እነዚሁ ጥናቶች ያመለክታሉ። በተለይ ደግሞ የሰዎች የሥራ ሁኔታ ከበድ ያለ እንደሆነ የችግሩ ደረጃ ከፍ እንደሚልም ጥናቶቹ ይጠቁማሉ።
የአከርካሪ አጥንት ጤንነት ለመላው የሰውነት አካል ደህንነት ወሳኝ እንደሆነም በጤና ባለሙያዎች ይነገራል። የአከርካሪ አጥንት ጤንነት መዛባት ለተወሳሰቡ የጤና እክሎች እንደሚዳርግም በባለሙያዎቹ ይገለፃል። ይሁን እንጂ የአከርካሪ አጥንት ጤንነት አስፈላጊነትን ያህል ለጉዳዩ ብዙ ትኩረት ሲሰጠው አይታይም። በኢትዮጵያም ለጤንነት አስፈላጊ ነገር ግን እምብዛም ትኩረት ካላገኙ የጤና ችግሮች ውስጥ የአከርካሪ አጥንት ጤና አንዱ ነው።
ዓለም አቀፍ ቀን እ.ኤ.አ ከ2014 ጀምሮ በየዓመቱ ጥቅምት ስድስት ቀን መከበር የጀመረ ሲሆን ዘንድሮም ለስደስተኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል። በኢትዮጵያም የአከርካሪ አጥንት ጤንነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ትኩረት እያገኘ በመሄዱ በዓሉ በተመሳሳይ ለስድስተኛ ጊዜ ‹‹እንደገና ቀጥ ይበሉ›› በሚል መሪ ቃል ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ከፈርስት ስፓይን ሴንተርና ኦቪድ ኮንስትራክሽን ጋር በመሆን ተከብሯል። በበዓሉ ወቅትም የአከርካሪ አጥንት ጤንነት ላይ የበለጠ ግንዛቤ ለመፍጠር የኦቪድ ኮንስትራክሽን ግንባታ ሳይት ላይ የሚገኙ የግንባታ ሰራተኞች የአከርካሪ አጥንት ጤና ላይ ያተኮረ እንቅስቃሴ እንዲሰሩ ተደርጓል።
የአከርካሪ አጥንት ቀን ከጥቅምት ስድስት ጀምሮ ባሉት ሰባት የተለያዩ ቀኖች በጤና ተቋማት፣ በግንባታ ድርጅቶች፣ በሞተር ድርጅቶች፣ በመንገዶች ባለስልጣን መስሪያ ቤት፣ በትምህርት ቤቶችና የአከርካሪ አጥንት እንክብካቤ በሚመለከታቸው ድርጅቶች ውስጥ እየተከበረም ይገኛል።
የፈርስት ስፓይን ሴንተር ባለቤትና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዶክተር ሰላም አክሊሉ እንደገለፁት፣ የአከርካሪ አጥንት ጤንነት ሲባል የአንድ ሰው መላው ሰውነት ጤንነትን ያጠቃልላል። ይህም የነርቭ ሥርዓት ከአንጎል ጀምሮ በህብለሰረሰርና በአንገት አጥንት በኩል የሚያልፍና ከጎን ያሉት ነርቮችም እጆችን፣ ዝቅ ብሎ ደግሞ የጀርባ አጥንቶች መሀል የሚያልፉ ነርቮች የውስጥ የሰውነት ክፍሎችን በሙሉ ኃይል ይሰጣሉ፤ ያሰራሉ።
በተመሳሳይ ከወገብ ዝቅ ብሎ ያለው ነርቭ ደግሞ የእግሮችን እንቅስቃሴ፣መራመድ፣ መቀመጥ፣ መነሳት የሚያስችሉና ከአከርካሪ አጥንት ጤንነት ጋር የሚያያዙ ናቸው።
እንደ ዶክተር ሰላም ገለፃ በኢትዮጵያ ከአከርካሪ ጤንነት ችግር ጋር በተያያዘ የተጠና ጥናት ባይኖርም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተጠናው ጥናት አኳያ 80 ከመቶ ያህሉ በአዋቂ የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎች በሕይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ የአከርካሪ አጥንት ጤና ችግር እንደሚገጥማቸው ያሳያሉ። እንደውም በጠቅላላው በዓለም አቀፍ ደረጃ 1 ቢሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የአከርካሪ አጥንት ጤና እክል እንዳለበት ጥናቶቹ ያረጋግጣሉ። ከነዚህ ውስጥ ደግሞ ወደ 65 ከመቶ ያህሉ የወገብ ችግሮች ሲሆኑ 35 ከመቶዎቹ ደግሞ የአንገት ችግር መሆኑን ይጠቁማሉ።
ይህ ዓለም አቀፍ መረጃ ቢሆንም ከኑሮ ዘይቤ ክብደት ጋር በተያያዘና አብዛኛዎቹ ሥራዎችም የሚከናወኑት በጉልበት በመሆኑ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካና ገና በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት የአከርካሪ አጥንት ጤና ችግር ጎልቶ እንደሚታይም ጥናቶቹ ያመለክታሉ።
በኢትዮጵያም የአከርካሪ አጥንት ችግር አሳሳቢ ከሆኑ የጤና ችግሮች ውስጥ አንዱ ሲሆን በተለይ ደግሞ እያደገ የመጣውን የግንባታ ዘርፍ ተከትሎ ከአከርካሪ አጥንት ጋር በተያያዙ የሚያጋጥሙ የጤና እክሎችን በብዛት መስማት እየተለመደ መጥቷል።
ዶክተር ሰላም እንደሚሉት የአከርካሪ አጥንት ችግር በዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ከሚያደርሱት ውስጥ አንዱ በመሆኑና በኢትዮጵያም ተመሳሳይ ተፅእኖ እያሳደረ በመምጣቱ የዘንድሮውን የአከርካሪ አጥንት በዓልን ለየት ያደርገዋል። ልዩ ትኩረትም ተደርጎበታል። ከዚህ በመነሳትም ፈርስት ስፓይን ሴንተር ከኦቪድ ግሩፕ ጋር ለመስራት ተነስቷል።
የማእከሉ ዋነኛ ሥራ የአከርካሪ ጤንነትን መጠበቅ ሆኖ ሳለ የኦቪድ ግሩፕ በግንባታው ዘርፍ የተለየ የሥራ ባህልና ከአከርካሪ አጥንት ጤንነት ጋር በተያያዘ ሥራዎችን ለመስራት ፍላጎት በማሳየቱ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በጋራ ለመስራት ተስማምቷል።
ከአከርካሪ አጥንት ጤንነት ጋር በተያያዘ ሰዎችን በእንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ማስተማርና ግንዛቢያቸውን ማስፋት ካልተቻለ ችግሩ በቀላሉ ሊፈታ አይችልም። ከዚህ አንፃር ከኦቪድ ግሩፕ ጋር የተጀመረው ሥራ በተለይ በግንባታ ሥራዎች አካባቢ ያለውን የሥራ ባህል በመቀየርና የአከርካሪ አጥንት ጤንነት ግንዛቤን በማስፋት ሰራተኞች ራሳቸውን እንዲጠብቁ ከማድረግ አንፃር ጉልህ ሚና ይኖረዋል።
ከሁሉ በላይ ደግሞ የአከርካሪ አጥንት ጤንነት ችግር በትክክል በኢትዮጵያ በጉልህ ከሚታዩ የጤና ችግሮች ውስጥ አንዱ መሆኑን በየደረጃው ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ማሳወቅ፣ ከታች ጀምሮ ግንዛቤ መስጠት ያስፈልጋል። ለዚህም የሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል።
የኦቪድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈፃሚና ስፔሻል ፕሮጀክት ኦፊሰር ኢንጂነር ዝናቡ ተበጀ በበኩላቸው እንደሚሉት ኦቪድ ግሩፕ የግንባታ ሥራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶችን በስሩ አቅፏል። ከ6 ሺህ 500 በላይ የሚሆኑ ሠራተኞችንም ቀጥሮ ያሰራል።
ድርጅቱ የመንግሥትን ዕቅድ በተከተለ መልኩ በቀጣይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ቤቶችን ሲገነባ ብዛት ያላቸውን ሰራተኞች ቀጥሮ እንደሚያሰራ ይጠበቃል። ከዚህ አኳያ በኮንስትራክሽን ዘርፉ ሰራተኞች ከባድ እቃዎችን የሚያነሱ በመሆኑ ለሰራተኞች ደህንነትና የአከርካሪ አጥንት ጤንነት ቅድሚያ ሰጥቶ ይሰራል። ከስፓይን ሴንተር ጋር በአከርካሪ አጥንት ጤንነት ዙሪያ የጀመረው ሥራም የዚሁ አንዱ አካል ነው።
ከዚህ አንፃርም ኦቪድ ግሩፕ የሰራተኞቹን የአከርካሪ አጥንት ጤንነት ለመጠበቅ በማለዳ ለአከርካሪ አጥንት ጤንነት አስፈላጊ የሆኑ የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ያሰራል። ይህንንም የእለት ተእለት ባህል አድርጓል። ድርጅቱ ዋነኛ ሀብቶች ሰራተኞቹ ከመሆናቸው አኳያም በሰራተኞች ጤና፣ ደህንነትና አካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ላይ ይበልጥ አተኩሮ ይሰራል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ገለፃ የግንባታው ዘርፍ በኢትዮጵያ ሃያ ከመቶ ያህሉን ዓመታዊ የተጣራ ምርት የሚይዝ በመሆኑና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰራተኞችን ያቀፈ በመሆኑ ድርጅቱ በሰራተኞች ላይ የሚደርሱ አደጋዎችን ለመቀነስ፣ ሰራተኛው በብዛት ሥራ ቦታው ላይ ውጤታማ ሆኖ እንዲገኝ ለማድረግ እንደ ፈርስት ስፓይን ሴንተር ካሉና በአከርካሪ አጥንት ጤንነት ዙሪያ ከሚሰሩ ተቋማት ጋር በጋራ ይሰራል። ይህም ለድርጅቱም ሆነ ለሠራተኞች ውጤታማነት የራሱን አስተዋፅኦ ያበረክታል። በቀጣይም የግንባታውና አምራች ኢንዱስትሪውም ይህንኑ አርአያ ተከትሎ መሬት የወረደ ሥራ ይሰራል ተብሎ ይጠበቃል።
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2014