በክብር ኖሮ በክብር መሞትን ብዙዎች ይመኙታል፤ ግን የተመኙትን ኖረው የተመኙትን ዓይነት አሟሟት የሚያገኙት ጥቂቶችና የታደሉቱ ናቸው። ለዚህም ነው ሰዎች በተለይም በዕድሜ ገፋ ያሉ አዛውንቶች በነጋ በጠባ ቁጥር “አሟሟቴን አሳምርልኝ” ሲሉ የሚደመጡት።
ይህ የሚያሳየን ሰዎች በክብር መኖርን የሚሹት በስጋ በሚኖሩበት ዘመናቸው ብቻ ሳይሆን፤ የስጋ ሞትን በሚሞቱበት ወቅትም የኖሩበትን ዘመን ክብርና ዝና በማያጎድፍ ሁኔታ እንዲሆን የጸና ምኞት እንዳላቸው ነው።
በክብር መኖርን በማሰብ ብቻ የሰውነትን ክብር እያጡ፤ በክብር መሞትን እየናፈቁ ሲያልፉ እያየናቸው ያለነው የአሸባሪው ህወሓት ዕድሜ ጠገብ አሸባሪዎች ግን ይህ ምስጢር የገባቸው አይመስልም። ምክንያቱም አሸባሪው ህወሓት እንደ ድርጅት፤ አሸባሪዎቹ ዕድሜ ጠገብ አመራሮቹም እንደ ግለሰብ በክብር መኖርን ያልቻሉና ክብር የራቃቸው መሆኑን ብቻ ሳይሆን፤ በክብር መሞት ቀርቶ ሞት እንኳን ያለ እስከማይመስላቸው ደርሰው ታይተዋልና። ሆኖም ዛሬ ላይ የረሱት ሞት ተፈጥሯዊ ሞታቸውን ሊለግሳቸው ቀርቧል።
እንዴት ከተባለም፣ አሸባሪው ህወሓት እንደ ድርጅት በጥቂት ሰዎች በጫካ ተጠንስሶ ሲወለድ፤ በበታችነት ስሜት ውስጥ ሆኖ የበላይ ለመሆን ሲል በንጹሐን ደም ላይ ተረማምዶ የስልጣን ማማን ለመቆናጠጥ በማለም ነበር። ይሄን ምኞቱንም በአሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን አጋሮቹ ታግዞ ለማሳካት በቃ። ኢትዮጵያንም ለ27 ዓመታት በግፍ አስተዳደረ። ይሁን እንጂ በደም ርካብ የተፈናጠጠው ስልጣን ለኢትዮጵያ የሚመጥን፤ ለኢትዮጵያውያንም የሚበጅ አልነበረም።
በ27 ዓመታት የስልጣን ዘመኑ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ጠልነቱ በተግባር የገለጠባቸውን ተግባራት ፈጸመ። የአገርን አንድነት ለአደጋ፣ የህዝቦችንም አብሮነት ለመከፋፈል ዳረገ። ከህዝብ ይልቅ ራስን፣ ከአገር ይልቅ ቡድንን ከፍ አደረገ። ኢትዮጵያዊነትን አቀጭጮ ብሔርተኝነትን አገነነ። ሆኖም የኢትዮጵያ ታላቅነት፣ የኢትዮጵያዊነትም ገናን ስነልቡና፣ የኢትዮጵያውያን ህብረትና አንድነት መቼም ይሄን ዓይነት ሴራ ስለማይፈቅድ፤ ይህ የሴራና ደም ጠገብ ቡድን በ27 ዓመት ግፉ ምክንያት ከስልጣን መንበሩ በውርደት እንዲራገፍ ሆነ።
ቀድሞውንም መልካም ነገር ይዞ ያልተነሳው ይህ ቡድን ታዲያ እሱ የማይመራትና እንዳሻው የማያደርጋት አገር አታስፈልገውምና ሲጠነሰስ የያዘውን ምኞቱን እውን ለማድረግ እና ታላቋን ኢትዮጵያ አፍርሶ ታላቋን ትግራይ ለመገንባት በስፋት ተንቀሳቀሰ። የህልሙን ፍጻሜ ለማየትም የአገር ዋልታ በሆነው የአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ፈጸመ። ይህ የቡድኑን ክፋት ብቻ ሳይሆን የቡድኑን ክፉ ሞት እንዲታይ አደረገ።
በዚህም የፌዴራል መንግሥት ኢትዮጵያውያንን አስተባብሮ በወሰደው ዕርምጃ ቡድኑ ከሞቀ ቤቱ ወደ ዋሻ ወርዶ ወደ ተራ አሸባሪና ሽፍታነት ተቀየረ። አንቱ የተባሉ የቡድኑ አመራሮች እንዳልባሌ በየጉራንጉሩ ተንጠባጥበው አስከሬናቸው ተለቀመ። ገሚሱም በገዛ ሽብርተኛ ጓዶቻቸው እየተቀሉ አንገትና አካላቸው እየተለየ በየቦታው ተጣሉ። ገሚሶቹም ከየዋሻው እየታደኑና ካቴና እጃቸው ላይ እየገባ በፍርድ አደባባይ ቀረቡ። የተቀሩትም ከሰውነት ጎዳና ወጥተው በየጢሻው ተሸሽገው ለማምለጥ ሞከሩ።
ከዚህ ሁሉ በኋላ መንግሥት ለሰብዓዊነት ቅድሚያ ሰጥቶ መከላከያ ሠራዊቱን ከክልሉ ባስወጣ ማግስት፤ ደም የቀመሰ ሆኖባቸው በየቀበሮ ጉድጓዱ ለነፍስ ተሸሽገው የነበሩ ጥቂት ትራፊዎች ዳግም ደም ለማፍሰስ ተሰማሩ። በአማራ እና አፋር ክልሎች ወረራን በመፈጸም ንጹሐንን በጅምላ ጨፈጨፉ፤ ንብረት አውደሙ፤ እንስሳትን ሳይቀር ገደሉ፤ ለሰው ልጅ እና እንስሳት ጥቅም ይሰጣሉ ብለው ያሰቧቸውን እጽዋት ሳይቀር በመጨፍጨፍ አረመኔነታቸውን አሳዩ።
ይህ የክፋቶች ሁሉ ክፋት፣ የአሸባሪዎች ሁሉ አሸባሪነት፣ ከገዳዮች የላቀ የጨፍጫፊነት ተግባራቸው ሲገለጥ ህዝብና መንግሥት በጋራ ቆመው ሊያጠፉት ተነሱ። ይሄን የተገነዘበው አሸባሪው ህወሓትም ታሪክ የደገመበትን ተግባር ወደመፈጸም ገባ። ህልውናውን ለማስጠበቅ ሲልም ቀደም ብሎ ሲነግድበት የነበረውን የትግራይ ህዝብ በጅምላ ወደ ጦርነት መማገድን ዋና ተግባሩ አደረገ። በዚህም ጋሻ አድርጎ ይዞት የነበረውን ህዝብ ወደ እሳት እየማገደ የእሳት ራት እያደረገው ነው።
ይህ ዕርምጃውም የሽብር ቡድኑ የተደበቀበት ጫካ እንዲሳሳና ፀሐይ ላይ እንዲወጣ አደረገው። ይሄም በኢትዮጵያውያን ከሚደርስበት ምት ባለፈ፤ በራሱ ጊዜ ተፈጥሯዊ ሞቱን ጠቅልሎ እንዲሞት መንገድ የከፈተ ሆነ። እናም አሸባሪው ህወሓት በቅርቡ ተፈጥሯዊ ሞቱን ይሞታል። የዛኔ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ድላቸውን እያጣጠሙ ወደ ብልጽግና ማማቸው በከፍታ መጓዛቸውን ይቀጥላሉ!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 13/2014