የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር ባለስልጣን፤ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች ቀልጣፋና ግልጽ ለማድረግ የሚያግዘው ኢንፎርሜሽ ቴክኖሎጂን መጠቀም መጀመሩን ገለጸ።
የጤናጥበቃ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር አሚር አማን ዛሬ የካቲት 20 ቀን 2011 የባለስልጣኑን አገልግሎቶች ለማዘመን የሚረዳውን ሶፍት ዌሩን በመረቁበት ወቅት እንዳሉት ተገልጋዮች ይህን ሶፍት ዌር በመጠቀም ባሉበት ስፍራ ሆነው የተቋሙን አገልግሎት በቀላሉ መጠቀም እንደሚችሉ ነው።
በዚህ ሶፍት ዌር አማካኝነት የምግብና መድሃኒት ምዝገባና ፍቃድ አሰጣጥ ፣የመድሃኒት ግⶵ ፍቃድ፣ የምግብና መድሃኒት መውጪያና መልቀቅያ ፍቃድ ፣የመድሃኒትና የምግብ የብቃት ማረጋገጪያ ፍቃድ አሰጣጥን ፈጣንና ግልፀኝነት ያለው እንደሚያደርገው ሚኒስተሩ ተናግረዋል።
የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሪክተር ወ/ሮ ሄራን ገርባ በበኩላቸው፣ ከዚህ ቀደም የነበረው አሰራር ወረቀትን መሰረት ያደረገ በመሆኑ ተገልጋዮች ተቋሙ ድረስ መምጣት የግድ ይላቸው እንደነበር አስታውሰው፤ ይህ ደግሞ ለገንዘብ፣ ጊዜና ጉልበት ወጪ እንደሚዳረጉ ገልጸዋል።
ይሁንና አሁን ላይ ተቋሙ ይህን ዘመናዊ ሶፍት ዌርን መጠቀም በመጀመሩ ተገልጋዮች ወደ ተቋም መምጣት ሳያስፈልጋቸው በማንኛውም ኢንተርኔት ባለበት ቦታ ሆነው የሚፈልጉት አገልግሎት በቀላሉ ማግኘት እንደሚችሉ ዋና ዳይሬክተሯ ተናግረዋል።
ማዕረግ ገ/እግኢአብሄር