በ2022 ሞሮኮ በምታስተናግደው የሴቶች አፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ የመጀመሪያ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ከሜዳቸው ውጪ ዩጋንዳን በመግጠም የጀመሩት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) የሁለት ለዜሮ ሽንፈት ገጥሟቸዋል። ሉሲዎቹ ወደ ካምፓላ አቅንተው በሴንት ሜሪ ስቴድየም ከትናንት በስቲያ ባደረጉት ጨዋታ ገና በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ግብ ያስተናገዱ ሲሆን አቻ ለመሆን ያደረጉት ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።
ዩጋንዳዎች ገና በሁለተኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ክልላቸው በአንድ ሁለት የኳስ ቅብብል በመውጣት ከግራ መስመር ሱመያ ኩመንተሪ በረጅሙ ያሻገረችው ኳስ ናቲሻ ናቦሳ የሉሲዎቹን የተከላካይ መስመር ተጫዋቾች መዘናጋት ተጠቅማ የመሪነቱን ግብ አስቆጥራለች። ከጅምሩ ግብ ያስተናገዱት ሉሲዎቹ ቀስ በቀስ የኃይል ሚዛኑን ወደ ራሳቸው በማድረግ ጨዋታውን መቆጣጠር የቻሉ ቢሆንም የግብ እድሎች በመፍጠር ረገድ የተሳካ ውጤት ማምጣት ሳይችሉ ቀርተዋል። በተለይም ግብ አምራቿ የሉሲዎቹ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ሎዛ አበራ፣ እመቤት አዲሱ እና መዲና አወል ከርቀት በተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ የዩጋንዳን የግብ ክልል ለመፈተሽ ሙከራ ከማድረጋቸው ውጪ በተደራጀ ሁኔታ የግብ እድል መፍጠር እንዳልቻሉ ታይቷል።
ግብ ካስቆጠሩ በኋላ በራሳቸው የግብ ክልል ተወስነው የተንቀሳቀሱት ዩጋንዳዎች በአንዳንድ አጋጣሚዎች ወደ ግብ እድልነት ሊለወጡ የሚችሉ
መልካም አጋጣሚዎች ቢያገኙም በአግባቡ መጠቀም ሳይችሉ ቀርተዋል። በሁለተኛው የጨዋታ አጋማሽ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የእንቅስቃሴ የበላይነት ቢይዝም አብዛኛው ቅብብል ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ሲደርስ በቀላሉ መባከኑን ቀጥሎ ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ሳያደርጉ እስከ ሰባኛው ደቂቃ ቆይተዋል። በተቃራኒው ረጃጅም ኳሶች ከመስመር በማሻገር ጨዋታቸውን የገፉበት ዩጋንዳዎች በ74 ኛው ደቂቃከቀኝ መስመር ወደ ኢትዮጵያ የግብ ክልል የተጣለውን ኳስ ፋውዚያ ናጂባ በጥሩ ሁኔታ በግንባሯ ገጭታ በማስቆጠር የግብ ልዩነቱን ወደ ሁለት ከፍ አድርገዋል።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ አስር ደቂቃዎች ሲቀሩት ሰናይት ቦጋለ ወደ ሜዳ ተቀይራ በመግባት የዩጋንዳ የግብ ክልል ተደጋጋሚ ኳስ በማድረስ ጫና ለመፍጠር ቢሞክሩም ኳስ እና ግብ ማገናኘት ሳይችሉ ጨዋታውም በዩጋንዳ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የመልሱ ጨዋታ በቀጣዩ ሳምንት በአዲስ አበባ አበበ ቢቂላ ስቴድየም የሚካሄድ ሲሆን ሉሲዎቹ ከሜዳቸው ውጪ የገጠማቸውን የሁለት ለዜሮ ሽንፈት ቀልብሰው ወደ ቀጣዩ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ ለማለፍ በሜዳቸው ጠንካራና ወሳኝ ፍልሚያ ይጠብቃቸዋል። ከሉሲዎቹና ከዩጋንዳ በደርሶ መልስ ውጤት አሸናፊው ቡድን የኬንያ እና ደቡብ ሱዳን አሸናፊን የሚገጥም ይሆናል።
ሉሲዎቹ ሎዛ አበራን የመሳሰሉ አስደናቂ ተጫዋቾች ስብስብ ይዘው ከዓመታት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ለመመለስ ይህ መልካም አጋጣሚ ሲሆን አሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛውም ይህን ለማሳካት ትልቅ አቅም እንዳላቸው ታምኖባቸዋል። የመልሱ ጨዋታ ግን በአበበ ቢቂላ ስቴድየም በሰው ሰራሽ ሜዳ (artefitial turf ) ላይ እንደመከናወኑ ለሁለቱም ቡድኖች ፍልሚያው ቀላል እንደማይሆን ይጠበቃል።
ሉሲዎቹ በአፍሪካ ዋንጫ ለመጨረሻ ጊዜ የተሳተፉት እኤአ 2004 ላይ ሲሆን በዚያ ተሳትፏቸው በታሪክ ትልቁ የሆነውን የአራተኛነት ደረጃ ይዘው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል። የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ እኤአ ከ1991 አንስቶ መካሄድ የጀመረ ሲሆን እኤአ እስከ 1998 ድረስ እንዳሁኑ በሁለት ዓመት አንዴ አይካሄድም ነበር። ናይጄሪያ በዚህ ውድድር እጅግ ስኬታማዋ አገር ስትሆን ካለፉት ሁለት ውድድሮች ውጪ አስር ጊዜ ቻምፒዮን በመሆን የሚስተካከላት የለም። ያለፉትን ሁለት ውድድሮች ኢኳቶሪያል ጊኒ ማሸነፍ ችላለች። የሴቶች የአፍሪካ ዋንጫ ከጅምሩ አንስቶ እንደ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ እያገለገለ የሚገኝ ሲሆን ጋና ለመጨረሻ ጊዜ በ2018 አስተናግዳዋለች። ከዚያ በኋላ በኮቪድ- 19 ምክንያት ሳይካሄድ የቀረ ሲሆን በ2022 ሞሮኮ ውድድሩን ለማስተናገድ ዝግጅት እያደረገች ትገኛለች።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2014