የአገር ሉአላዊነትን የማስከበር ተልዕኮ የተሰጠው የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት በዘመናዊ መልኩ ከተደራጀበት ጊዜ አንስቶ የተሰጠውን ሀገራዊ ኃላፊነት በስኬት ለመወጣት ከፍ ያሉ መስዋዕትነቶችን ሲከፍል ቆይቷል፤ አሁንም እየከፈለ ይገኛል። በዚህም የሀገርና ህዝብ ኩራት ምንጭ መሆኑን በተጨባጭ አስመስክሯል።
ባለፉት 50 ዓመታት ሰራዊቱ ለተለያዩ የፖለቲካ አስተሳሰቦች ተገዥ እንዲሆን በመደረጉ፤ የህዝባዊነት መሰረቱን በብዙ የተፈታተነው ሲሆን፤ ይህም ሆኖ ግን የሀገር ሉአላዊነትን በማስጠበቅ በኩል የነበረው አኩሪ ታሪክ ከፍ ያለ እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ።
የሀገርን ህልውና ከጠላት ስጋት ለመታደግ ሆነ ሰላም ለማስከበር ከሀገር ውጪ በተሰጠው ግዳጅ ከፍ ያሉ ገድሎችን በመፈጸም፤ ዓለም ስለ ኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በታሪክ የሚያውቀውን አኩሪ ገድል በተሻለ የግዳጅ አፈጻጸም ማደስ ያስቻሉ ታሪኮችን መስራት የቻለ ነው።
ሠራዊቱ ከለውጡ ማግስት አንስቶ ሕዝባዊነቱን እና ሀገራዊ ተልዕኮውን በተሻለ ቁመና ገለልተኝ ሆኖ መፈጸም እንዲችል የተፈጠረለትን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ህዝባዊነቱን አስተማማኝ የሚያደርጉ ተግባራትን በስፋት ሲተገብር ቆይቷል። ራሱን በወታደራዊ ስነ ምግባር እና እውቀቶች በተሻለ መልኩ ከማነጽ ጀምሮ፤ ግዳጅ የመፈጸም አቅሙን ሁለንተናዊ በሆነ መልኩ እያሳደገ ይገኛል።
ይህ እውነታ አሸባሪው ህወሓት በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በሀገርቱ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን የህልውና ስጋት በ15 ቀናት ውስጥ ስኬታማ በሆነ የግዳጅ አፈጻጸም መቀልበስ ችሏል። በዚህም የቱን ያህል አስተማማኝ ሀገራዊ አቅም እንደሆነ በተጨባጭ አስመስክሯል።
መከላከያ ሰራዊቱ በአንድ በኩል አሻባሪውን ቡድን ከህዝብ ለይቶ ለመምታት የሄደበት መንገድ ፤ከዛም በላይ የትግራይን ህዝብ ከጦርነት አደጋ ለመታደግ የከፈለው ከፍ ያለ ዋጋ ህዝባዊነቱን፤ ከሁሉም በላይ ለዜጎች ያለውን ክብር በተጨባጭ ያስመሰከረበት ነው። ይህም በደሙ የጻፈው የነገ ታሪኩን የሚያደማምቁ ገድሎቹ ናቸው።
የመከላከያ ሠራዊቱ ዛሬም ቢሆን አሸባሪውን ህወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጌዜ በማስወገድ፤ የእብሪት መንገዱ በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ምንም ዓይነት ቦታ እንዳይኖረው በጽናት እየሰራ ይገኛል። በስራውም እያስመዘገበው ያለው ስኬት ከፍያለ ነው። በአንድ በኩል ራሱን እያበቃ በሌላ በኩል ሀገራዊ ስጋቶችን በስከነ መንገድ እየቀለበሰ እየሄደበት ያለው መንገድ ለአስተማማኝ ድል መሰረት እንደሚሆንም ይታመናል።
አሸባሪው ህወሓት መንግስት ሆኖ በቆየባቸው 27 ዓመታት ውስጥ ይከተለው ከነበረው ሀገር ጠል አስተሳሰብ አንጻር ዋናው የአስተሳሰቡ ሰለባ የነበረው የመከላከያ ሰራዊቱ ነበር። የመከላከያ ሰራዊቱ በቡድኑ ሙሉ በሙሉ ከመያዙም ባለፈ ሃገራዊ ቁመናውም በስጋቶች የተሞሉ እንደነበሩ ይታወቃል።
ይህንን ሠራዊት ከቡድኑ ሙሉ በሙሉ ነጻ አድርጎ በስጋት የተሞሉ ሀገራዊ ቁመናውን በማስተካከል የሀገር ኩራት በሚያደርግ የግዳጅ ቁመና ላይ እንዲገኝ ለማድረግ ቀን ከለሌት ያለ እረፍት መስራትን አስፈልጓል። ለዚህ የሚሆን የፖለቲካ ቁርጠኝነትም ጠይቋል።
ከዚህ ጎን ለጎንም ለሀገር ህልውና ስጋት የሆነውን የአሻባሪውን ህወሓት የጥፋት ተልዕኮ ለማምከን በግዳጅ ወረዳዎች ያለ ዕረፍት ከፍ ያሉ ተጋድሎዎችን በመፈጸም የቡድኑ ህልሞች ህልው ሆነው እንዲቀሩ አድርጓል። በዚህም ከህዝብና ከተለያዩ የጸጥታ ሀይሎች ጋር የነበራቸው መናበብ ህዝባዊነቱን በተጨባጭ ያሳየ ሆኗል።
የሽብር ቡድኑ እየተከተለው ካለው አውዳሚ የጦርነት ስትራቴጂ አንጻር፤ መከላከያ ሰራዊቱ በሰከነና ሀገራዊ ጉዳትን በሚቀንስና አሸባሪውን ቡድን በማያዳግም መልኩ ለማስወገድ በሚያስችል መልኩ እየሰራ ነው። ሂደቱም የሁሉንም አካላት ትዕግስትን የሚጠይቅ ነው።
ትዕግስት ከምታፈራው ፍሬ አንጻር የመከላከያ ሰራዊቱን የግዳጅ ተልእኮ አፈጻጸም በአግባቡ በመረዳት ካልተገቡ ትችቶችንና ነቀፋዎች በመታቀብ የመከላከያ ሰራዊቱን የግዳጅ አፈጻጸም ስትራቲጂ ለመከላከያ ሰራዊቱ በመተው ደጀንነታችንን አጠናክረን በመቀጠል የድል ብስራቱን ቀን ማቅረብ ይገባናል። ከዚህ ውጪ የመከላከያ ሰራዊቱ የግዳጅ አፈጻጸም ላይ ያለ እውቀት በደመነፍስ የምንሰጣቸው አስተያየቶች፤ ለአሸባሪው ህወሓት የፕሮፓጋንዳ አቅም ከመሆን ባለፈ የሚያስገኘው ጥቅም እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2014