ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡ እነሆ ሦስት ዓመታት ተቆጠሩ:: በእኚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ በአዲስ አበባና በሌሎች የክልል ከተሞች ላይ ከኢኮኖሚውና ከሌሎች ልማታዊ እንቅስቃሴዎች ባሻገር በከተማ ማስዋብ ሥራ ላይ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል:: እየተሠሩም ይገኛሉ:: እንደሚታወቀው አብዛኛው የሀገራችን ከተሞች የከተማነትን መስፈርት ያሟሉ ናቸው ብሎ መናገር ይከብዳል:: ከሦስት ዓመት ወዲህ በተሠራው የግንዛቤ ለውጥ ግን በብዙ ከተሞች ላይ ከፍተኛ መሻሻልን እያየን የመጣንበት ሁኔታ አለ:: ያለፉትን ሦስት የለውጥ ዓመታት እንደ ማሳያ በመጠቀም የሀገራችንን የከተሞች አሁናዊ መልክ ማየት ይቻላል::
ለዛሬ ግን ሁሉንም ትቼ የመዲናችንን የአዲስ አበባን የሦስት ዓመት በጎ አሻራዎቿን አስቃኛችኋለሁ:: መዲናችን አዲስ አበባ ከዋና ከተማነት ባለፈ የአፍሪካ መዲናም ጭምር ናት:: በዚህም ሳያበቃ የዓለም የዲፕሎማሲ መቀመጫ፣ የአፍሪካ ህብረት ቢሮ መገኛ እንዲሁም የተለያዩ ዓለም ቀፍና አህጉራዊ ስብሰባዎች የሚካሄዱባት ትልቅ ከተማ ናት:: እንደ መዲናችን የአገልግሎት ስፋትና ዓይነት ግን ዜጎችን የሚመጥን በቂና አስተማማኝ የመዝናኛም ሆነ የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ስፍራዎች በጥራትና በዓይነት የሉንም:: ይሄ ብቻ አይደለም 110 ሚሊዮን የህዝብ ቁጥር ላላትና ከሰባ በመቶ በላይ ወጣት ለሆነባት ሀገር የወጣቱንም ሆነ የአብዛኛውን ማህበረሰብ ፍላጎት ያሟላ ሁሉን አቀፍ የመዝናኛ ስፍራ የላትም::
ይሄ የታያቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ተዐምር በሚመስል ሁኔታ ለዚውም በጥቂት ጊዜ ውስጥ የአዲስ አበባን ገጽታ የሚያጎሉ ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ሀገራት ጎብኚዎች መደነቂያ የሆኑ የተለያዩ የመዝናኛ ስፍራዎችን ሠርተውልናል:: በጣም የሚገርመው ደግሞ እያንዳንዱ ፓርክና የመዝናኛ ስፍራ ኢትዮጵያዊነትን በሚያጎሉ ሀበሻዊ ቁሶች የተሠሩ ከመሆናቸውም በላይ በኢትዮጵያዊ ለዛና ቀለም የተበጁ የአብሮነት ጥግ ማሳያ መሆናቸው ነው:: ይሄም ብቻ አይደለም በእያንዳንዱ የከተማ ገጽ ውስጥ፣ በእያንዳንዱ ፓርክና መዝናኛ ስፍራ ውስጥ የሀገርን ታሪክ የሚናገሩ፣ ጥንታዊና ዘመናዊ ሀገር በቀል ትውፊቶች መኖራቸው ነው::
እኚህ ሦስት ዓመታት ባለቀለም ዓመታት ይመስሉኛል:: የደመቁ፣የፈኩ ፍሬያማ ዓመታት:: በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መሪነት ዘመን ተሻጋሪ የጋራ ታሪኮችን በጋራ ጽፈናል:: በትላንትና በዛሬ ውህድ ቀለም እየነከርን የጻፍናቸው የአብሮነት ገጾች አሉን:: እኚህ ውብ ገጾች ስለ ኢትዮጵያ የሚዘምሩ፣ ስለ ታላቅ ሀገርና ታላቅ ህዝብ የሚናገሩ ናቸው:: ኢኚህ ውብ ገጾች ኢትዮጵያን አንድ አድርገው ያቆሙ፣ ለሀገርና ለህዝብ ክብር የሚጨነቁ ጸዐዳ መልኮች ናቸው::
ያለፉት ሦስት ዓመታት የተግዳሮታቸውን ያክል ምን ያህል ፍሬ አፍርተው ያለፉ እንደነበሩ ከእኔ ይልቅ እናንተ ምስክር ናችሁ ብዬ አምናለሁ:: ለብዙዎቻችን የማይቻል ነገር የቻልንበት፣ በተለያየ መስክ ላይ ከትላንት በተሻለ የሚታይ ለውጥ የመጣበት ጊዜ ስለመሆኑ አምናለሁ:: እያወራን ያለነው ስለ አዲስ አበባ የሦስት ዓመት ውብ አሻራዎች ነው:: እያወራን ያለነው ያለፉት ሦስት ዓመታት ካስገኙልን በረከቶች ውስጥ አንዱን መርጠን ነው:: ከትላልቅ የልማት ፕሮጀክቶች ጎን ለጎን ስለተሠሩ ትናንሽ የልማት ፈርጦች ነው:: በነዚህ ዓመታት ውስጥ የመንግሥት እጆች ከመሥራት አልቦዘኑም::
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ የመንግሥት ጭንቅላት ከማሰብ አልሰነፈም:: እነዚህ ዓመታት በጥልቅ ማሰብ ያለፉ ናቸው እላለሁ:: ለዚህ ምስክር እንዲሆኑን ደግሞ የአዲስ አበባን አሁናዊ ገጽታ ማየቱ ብቻ በቂ ነው እላለው:: ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ሸገርን የማስዋብ ተግባራቸውን ‹‹ገበታ ለሸገር›› ሲሉ በብዙዎቻችን ልብ ውስጥ የጋራ መነሳሳትን ፈጥረው ነበር:: ይሄ ሀገራዊ መነሳሳት ዛሬም ድረስ ዘልቆ ከአዲስ አበባ ባለፈ በብዙ የክልልና የወረዳ ከተሞች ላይ እየተንጸባረቀ ይገኛል::
አዲስ አበባችን የመጀመሪያ ፓርኳን ያየችው በጠቅላይ ሚኒስትራችን የላቀ መነሳሳት አንድነት ፓርክን ነው:: አንድነት ፓርክ ሲሠራ፣ ተሠርቶም ሲመረቅ ከምርቃቱም በኋላ ለጎብኚዎች ክፍት እስኪሆን ድረስ ብዙ አሉባልታዎች ሲወሩ ነበር:: ያው እንደምታውቁት የማይሠራ ሰው ከወሬ ሌላ ምንም ቁም ነገር የለውም:: ሀገር ወደ ፊት የምትሄደው በውስጣቸው ራዕይና መልካም ሃሳብን በሰነቁ ሰዎች ነው::
አሁን ላይ የአዲስ አበባን ገጽ ከቀየሩ መልካም አሻራዎች ውስጥ አንዱ አንድነት ፓርክ ነው እላለሁ:: አንድነት ፓርክ ከፓርክነቱ በተጨማሪ የኢትዮጵያን ድሮአዊና አሁናዊ ታሪኮችን የያዘ ራሱን የቻለ ሙዚየም ነው:: እኔና እናተ ከነውበታችን፣ ከነቀለማችን፣ ከባህልና ስርዓታችን ጋር በአንድ ስፍራ በአንድነት ፓርክ ውስጥ ታሪክ እያወራን አለን:: ታሪክና ትውፊትን በእንደዚህ ዓይነት ዘመን ተሻጋሪ በጎ ሥራ ለትውልድ ማስቀመጥ እጅግ ብልህነት ነው::
ከዚህ በተጨማሪ አንድነት ፓርክ ቤተመንግሥት ግቢ ውስጥ በመሠራቱ ብቻ ልዩ ያደርገዋል:: ትላትና ከዚያ በፊት ባለው ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ቤተመንግሥት ማለት ምን ዓይነት መልክና ገጽታ እንዳለው ሁላችሁም የምታውቁት ነገር ነው:: እንኳንስ ቤተመንግሥት ግቢ ውስጥ የህዝብ ፓርክ ሊሠራ ቀርቶ፣ እንኳንስ ማንም እየሄደ ሊጎበኘው ቀርቶ በዚያ አካባቢ ማለፍ በራሱ ምን ያክል አስጨናቂ እንደነበር የደረሰበት ነው የሚያውቀው:: ዕድሜ ለሦስት ዓመታት በጎ ለውጦች ቤተ መንግሥት ከመኖሪያነት ባለፈ ምንም እንዳይደለ ለማወቅ ችለናል::
የሦስት ዓመታት ባለቀለም ገጾች ብዙ ናቸው:: ስለ አንድነት ፓርክ አውርተን ሳንጨርስ፣ ተገርመንና ተደንቀን ሳናበቃ ሁላችንንም በአንድ ያስገረመ እንጦጦ ፓርክ ተመረቀ:: እንጦጦ ፓርክ ፓርክ ብቻ አይደለም፤ለዚህ ደግሞ ፓርኩን ሄዳችሁ ያያችሁ ምስክሮች ናችሁ:: እንጦጦ ፓርክ የኢትዮጵያዊነት አለላ መልኮች የተጣመሩበት ስውር ጥበብ ነው እላችኋለው:: የኢትዮጵያዊያን በጎ አሻራ የታየበት የድንቅ ሃሳብ ውጤት ነው እንዲህም እላለሁ:: ፓሪስና ዱባይን፣ አውሮፓንና ኢሲያን የሚስተካከል አንዳንዶች እንደሚሉት ደግሞ የሚያስንቅ ኢትዮጵያዊ መልክ ነው::
ይህ ውብ መልክ ደግሞ ዝም ብሎ አልመጣም በሦስት ዓመታት የለውጥ ሂደት ውስጥ የተንጸባረቀ ድንቅ ነጸብራቅ እንጂ:: አሁን ላይ እንጦጦ ፓርክን ለብዙ ነገር እየተጠየቀምንው እንገኛለን:: የከተማችን ቁጥር አንድ መዝናኛ ከመሆኑም በተጨማሪ ሠርግና መሰል የደስታ በዓላትን እናሳልፍበታለን:: ለፊልምና ለተለያዩ ቀረጻዎች እየተጠቀምንበት እንገኛለን:: ለተለያዩ ስብሰባዎች እያገለገለን ያለ ዘመናዊና ታሪካዊ፣ የብዙ ሃሳቦች፣ የብዙ ህልሞች ውብ ስፍራ ነው ብል አጋነንክ አንደማትሉኝ ተስፋ አደርጋለሁ::
የሦስት ዓመት በጎ አሻራችን ወደ ሌላም ይወስደናል:: በአንድነት ፓርክ ጀምረን በእንጦጦ ቀጥለን በወዳጅነት ፓርክ አሰልሰናል:: የወዳጅነት ፓርክ እንደስሙ የድንቅ ኢትዮጵያዊነት መንፈስ ያለበት ቅዱስ ስፍራ ነው:: ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አንድ ሆነው እዚያ ቦታ ላይ አሉ:: በርካታ ብሄር ብሄረሰብ በአንድነትና በወዳጅነት እጅ ለእጅ ተያይዘው አንድ ሃሳብ የሚያስቡበት፣ አንድ ህልም የሚያልሙበት ስፍራ ነው እላለው:: እነኚህ ፓርኮች ከመዝናኛነት ባለፈ የከተማችንን ገጽ በትልቁ የቀየሩ የመልካም እጆች ውጤቶች ናቸው:: በእነዚህ ፓርኮች አማካኝነት ለብዙዎች የሥራ ዕድሎች ተፈጥረዋል:: በእነዚህ ፓርኮች አማካኝነት የይቻላል በጎ መንፈስን በውስጣችን አስርጸናል::
እኚህ ፓርኮች በሦስት ዓመታት የተፈጠሩ የእኔና የእናተ መልኮች ናቸው:: በስተመጨረሻም የጉዳዬ አንደኛ ወዳደረኩትና ይሄንንም ጽሑፍ እንድጽፍ ወዳነሳሳኝ ትልቅ ቁም ነገር ልለፍ:: ከላይ እንዳየንው ያለፉት ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያዊያን የስኬት ዓመታት እንደነበሩ በድፍረት መናገር ይቻላል:: ከአንዳንድ ችግሮቻችን ጋር እየታገልን ጥሩ ነገር በማከናወን ዛሬ ላይ ደርሰናል::
የአዲስ አበባን ገጽታ በትልቁ ከቀየሩ የሦስት ዓመት ትሩፋቶች ውስጥ ባሳለፍንው ዓመት የተመረቀው የመስቀል አደባባይ አንዱና ዋነኛው ነው:: መስቀል አደባባይ የከተማዋ ትልቁ አደባባይ ከመሆኑም ባሻገር ለበርካታ ዓመታት የተለያዩ መንፈሳዊና ዓለማዊ በዓላት ሲካሄዱበት ቆይቷል:: የመስቀል በዓልን ጨምሮ፣ የተለያዩ የህዝብ በኣላት፣ የሙዚቃ ኮንሰርት፣ መንግሥታዊ ዝግጅቶች ከተስተናገዱበት ዝግጅቶች ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው::
ይሄን በዓይነቱ ትልቅ የሆነ አደባባይ መንግሥት ከዘጠኝ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ 2.6 ቢሊዮን ብር በሆነ የገንዘብ ወጪ እጅግ ዘመናዊ በሆነ መልኩ አሠርቶ ለአገልግሎት ክፍት አድርጎታል:: እስከ ማዘጋጃ ቤት ድረስ የሚዘልቀው ይሄው የመስቀል አደባባይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት መንግሥት ለከተማ ውበት ምን ያክል ዋጋ እንደሰጠ የሚያመላክት ጉዳይ እንደሆነ ማየት እንችላለን:: አዲስ አበባ ከተማ እንደ ሀገሪቱ ዋና ከተማነቷ፣ እንደ አፍሪካ መዲናነቷ፣ እንደ ዓለምአቀፍ እውቅናዋ ከዚህም በላይ ማማርና መበልጸግ የሚገባት እንደሆነ ይታመናል::
በዚህ ግዙፍ የዋና ከተማ አደባባይ ላይ የከተማውን ገጽታ የሚጨምሩ እጅግ ሰፊና ማራኪ የሆኑ እስከ አንድ ሺ አራት መቶ ሃምሳ (1450) የሚደርሱ መኪናዎችን መያዝ የሚችል ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎች ተሠርተዋል:: የተለያዩ ሱቆች፣ መጸዳጃ ቤቶች የተካተቱበትም ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ የከተማዋን ውበት የሚያጎሉ የተለያዩ ስክሪኖችም የተገጠሙለት የአውሮፓ ደረጃ ያለው አደባባይ ነው:: ይህ እንግዲህ ያለፈው ሦስት ኣመታት የፈጠረው የለውጥ ገጽ ነው::
ያለፉት ሦስት ዓመታት ካለምንም ዋዛ ፈዛዛ በሥራ ብቻ ያለፉ እንደሆኑ ከላይ የጠቀስኩላችሁ ሀገራዊ በረከቶቻችን እማኝ ምስክሮቻችን ናቸው:: ከሌሎች ሀገራዊ ጉዳዮቻችን ሳንወጣና ሳንርቅ ሀገር እየለወጥን፣ ልማት እየሠራን በመንግሥት መሪነት በህዝቦች ተሳትፎ የመጡ በረከቶች ናቸው::
ከእነዚህ በተጨማሪ በቀጣይም በገበታ ለሸገር ስም ከዚህ የሚበልጡ ኢትዮጵያዊነትን በላቀ መልኩ የሚገልጹ ሌሎች የመልካም ዓመታት በጎ አሻራዎች እንደሚፈጠሩ ተስፋ አደርጋለሁ:: እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ህዝብ ያለፉት ዓመታት ከፈጠሩልን ይልቅ የሚመጡት ዓመታቶች የሚፈጥሩልን ጸጋዎቻችን ይበልጣሉ ብዬ አምናለሁ:: በብዙ ትችትና ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ለዚያውም በአጭር ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባንና አካባቢዋን በዚህ ልክ ማሳመር ከተቻለ ቀጣዩ ጊዜ ምን እንደሚመስል መገመት አይከብድም::
ያለፉት ሦስት ዓመታት የሀያና የሠላሳ ዓመታትን ያክል ዋጋና እሴት ኖሯቸው ያለፉ ነው የሚመስሉት:: ለብዙዎቻችን እውነት የማይመስሉ ነገሮች ተሠርተው ያየንበት ጊዜ ነው:: ያለፉት ሦስት ዓመታት ቃል በተግባር የታየበት፣ መንግሥት በሥራና በልማት ለህዝብ የታመነበት የበጎ አሻራ ጊዜ ነበር ማለት ይቻላል:: ቃል በተግባር የታየበት፣ የእውነት፣ የጽናትና የይቻላል መንፈስ ተንጸባርቆ ያለፈበት ጊዜ ነበር::
ካለፈው ጊዜ ይልቅ የሚመጣው ጊዜ በይበልጥ ተስፋና ከፍታን የያዘ ነው እላለሁ:: ያለፉት ሦስት ዓመታት በሀገራችን የለውጥ ሂደት ውስጥ የራሳቸውን አዎንታዊ በጎ አሻራ አሳልፈው አልፈዋል:: በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው፣ በማህበራዊ መስተጋብሩ ላይ ይሄ ነው የማይባል በጎ ስምና የማይረሳ ቀለምን ትተው ያለፉ ናቸው:: ይህ ትልቅ እውነት ነገም የበለጠ እውነት ሆኖ እንዲቀጥል ከኢትዮጵያ ጎን መቆም ይገባናል:: አክሱምንና ላሊበላን ያነጹ እጆቻችን ዛሬም ተዐምር መሥራት ይችላሉና ለአዲሷ ሀገራችን አዲስ ሃሳብን እናፍልቅ እያልኩ ላብቃ:: ቸር ሰንበንቱ::
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2014