የሰሞኑ የአሸበሪው ህወሓትን ያዙኝ ልቀቁኝ ፉከራ በሰማሁት ቁጥር ካለ እቅዴ እያሳቀኝ ይገኛል። በእርግጥ ቡድኑ የሀሰት ወሬ በመንዛት ለጥቁር ፕሮፓጋንዳ የሚሸበርላቸው እስካገኙ ድረስ ምላሳቸውም የማይደከም፤ እነሱም የማይቦዝኑ መሆኑ ጸሀይ የሞቀው እውነት ነው። ችግሩ ይህ አካሄድ እንኳን ለእነሱ የሀሳብ አባቶቻቸው ለሆኑት ነጮቹም ያልሰራ መሆኑ ነው።
ፋሽሽት ኢጣሊያውያን ንጉስ በሌለባት ሀገር በየዱር ገደሉ የሚፋለሟቸውን የኢትዮጵያ የቃል ኪዳን ልጆች ቅስም ለመስበር ከአየር ተስፋ የሚያስቆርጥና የማስፈራሪያ ዛቻ ያዘሉ ጦማሮችን ከመርዝ ቦንቡ በተጓዳኝ ያዝንቡ ነበር። ያኔ የነበረው የኢትዮጵያውያኑ ምላሽ ግን በዘመኑ ወጣቶች ቋንቋ «መስሚያችን ጥጥ ነው» የሚል ነበር።
በዚህም የፋሺስት ጣሊያንን የግዛት ዘመን ማሳጣር ብቻ ሳይሆን ባሳለፋቸው አመታትም እግር ከወርች በማሰር እንደልቡ እንዳይፈነጭ ለማድረግ በቅተዋል። የእነዚህ ድሎች ምስጢር ግን ጀግኖች በወሬ ያለመፈታታቸው ብቻ ሳይሆን በማውራት ብቻ የማይቆሙት የቁርጥ ቀን የኢትዮጵያ ልጆች ወሳኝ ተጋድሎ የታከለበትም መሆኑ ነበር። ለዚህ ደግሞ የእነ ራስ አበበ አረጋይ፤ የእነ ጄነራል ጃጋማ ኬሎ «የበጋው መብረቅ» የእነ ሸዋረገድ ገድሌና የሌሎቹም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አርበኞች ታሪክ ቋሚ ምስክር ነው።
በተመሳሳይ ዛሬ ላይ የነሱን ሀሳብ ገዝተው በባንዳነት በሀገር ላይ የተሰለፈው አሸበሪው ህወሓት የአውሮፓውያንን ሀገር ከፋፋይ አካሄድ ወርሰው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ሀገርን ለመከፋፈል ሲጥሩ ኖረዋል። ቡድኑ በማደናበርና በማደናገር ወሬ እየፈበረከ፤ ከፍ ሲልም ታሪክን ባልተገባ መልኩ እየተረጎመ እኩይ አላማውን ለማሳካት ከምስረታው ጀምሮ ሲውተረተር ኑሯል።
የአሸበሪው ህወሓት አመራሮች በወፈፌ እሳቢያቸው የአላማቸው ጥግ ያደረጉት ኢትዮጵያን የመበታተን ሴራ ነበር። ይህንን መርዝ የተሸከመ አላማቸውም የማታ የማታ ቢከሽፍባቸውም ከጅምሩ አንስቶ ለረጅም አመታት በሀሰት ዜና ማለቂያው ያላማረ ድል ሲያጎናጽፋቸው ቆይቷል።
ገና በጥንስሱ ለውጥ ፈላጊ የነበሩትንና በትግራይና በአማራ ምድር ደርግን ለመዋጋት የከተሙትን ኢድዩና ኢህአፓዎችንም ያስወገዱት ከጥይቱ በተጓዳኝ በትግራይ ህዝብ ዘንድ መጡብህ የሚል የውሸት ዜና በመርጨት ነበር። በአንጻሩ እነዚህና ሌሎች ፓርቲና ግለሰቦችም ስምምነት ባይኖራቸውም ትግራይ ሲከትሙ የነበሩት የአንድ ሀገር ህዝቦች ነን የዚህ ያህል አይከፉብንም በሚል ገራገር እሳቤ ነበር።
አሸበሪው ህወሓት ሌላው ቀርቶ የደርግ ውድቀት እውን በሆነበትና እነሱም አዲስ አበባን በተጠጉበት ወቅት ሳይቀር ህዝቡ እንደማይቀበላቸው በመገመት ኢትዮጵያ ወደለየለት የእርስ በእርስ ጦርነት እንዳትገባ በሰላም አስገቡን የሚል ደብዳቤ በትነው እንደነበር የቅርብ ግዜ ትዝታችን ነው። የሚደንቀው እንታገልልሀለን፤ ነጻ አውጥተን ለዘመናት የተጫነብህን ቀንበር እንሰብርልሀለን ብለው ድረሱልኝ ብሎ በስስት የሚጠብቃቸውን ልጆቹን ሲገብር የኖረው የትግራይ ህዝብም የዚህ ሴራ ሰላባ ከመሆን አለመዳኑ ነው።
«ያዳቆነ ሰይጣን ሳያቀስ አይለቅም» እንዲሉ ሀያ ሰባት አመት የዘገመው የግዛት ዘመናቸውም ተጀምሮ የተጠናቀቀው መላውን ህዝብ በሀሰት በማደናበርና በግጭት ስጋት ውስጥ እንዲኖር በማድረግ ነው። በዘመኑ የእኩይ ሴራቻው ቀዳሚ ማጠንጠኛዎች ደግሞ ስምምነታቸው ጤና የሚነሳቸውን የአማራና የኦሮሞ ህዝብን እሳትና ጭድ ማድረግ ነበር። ለዚህም እያንዳንዷን የታሪክ አጋጣሚ አጣሞ በመተንተን የተዳፈነ ረመጥ ሲያዘጋጁ ኑረዋል።
ይህን አካሄድ ደግሞ ከሶስት ዓመት በፊት ህዝባዊው አመጽ በመላው ሀገሪቱ ተቀጣጥሎ መቀልበስ ወደማይችልበት ደረጃ ሲደርስ እነሱም አጠናክረው ቀጥለውበታል። በተለይም የኦሮሞ ወጣቶች ያላንዳች ፍርሀት መሰዋት ሲጀምሩና ከወደ ጎንደር «የኦሮሞ ደም የኔም ደም ነው» የምትለው ነገር ስትመጣ ወያኔም የመጨረሻውን ደውል ማሰማት ጀመረች።
በየቦታው መጣብህ ነጠቀህ ገደለህ በሚል የሀሰት ዜና ያጠመዷቸውን የነገር ፈንጂዎች ማፈንዳት ጀመሩ። በዚህም ለዘመናት በህብረት በኖሩት ሶማሊያና ኦሮሚያ፤ ኦሮሚያና ጉጂ፤ አፋርና ኤሳ፤ አማራና ቅማንት ንጹሀን ዜጎችን የሴራዎቻቸው ሰለባ በማድረግ በሀገራችን ታሪክ ያልታሰበ ጥቁር ጠባሳን አስቀምጠዋል።
«ለፋሲካ የተዳረች ሁሌ ፋሲካ ይመስላታል» እንዲሉ ስንት ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ሁኔታዎች በተቀየሩበት። የህዝቡ አስተሳሰብና ንቃተ ህሊና በዳበረበትና ነግቶ በጠባ ለውጥ በሚፈልግበትም ዘመን እነሱ አስራ ዘጠኝ ስልሳ ስድስት ላይ በቆመ ጭንቅላት ህዝብን ከህዝብ በማጋጨት ባለ ድል ለመሆን እየተውተረተሩ ይገኛሉ። ለዚህ ደግሞ የዘመኑ ምንጫቻው የማይለይላቸው ያሉባልታ ወሬዎች መፈብረኪያና መባዣ ማህበራዊ ሚዲያዎች ትልቅ ተስፋ የሰጧቸው ይመስላል።
ስለ እውነትም ጥቂት በማይባሉ በሀገር ውስም በውጪም ባሉ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ኢትዮጵያ ካለ ከአሸባሪው ህወሓት የሚል እሳቤም እየተስፋፋ መጥቶ ነበር። መነሻቸውም ሆነ መጨረሻቸው ግን ተስፋ መቁረጥ ነው። ተስፋ ያስቆረጣቸው ደግሞ የለውጡ ስር እየሰደደ መምጣትና በህዝቡም ዘንድ ያለው ተቀባይነት እያየለ መምጣቱ ነው። ይህ ማለት እኛ የለውጡ ተመልካች ከመሆን ወደ ለውጡ ተሳታፊነት ስንሸጋገር የማይቀረውን የወያኔን ግብአተ መሬት እናፋጥናለን ማለት ነው።
ይህም ሆኖ ዛሬም ድረስ በእኔ በኩል ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው እንዲሉ ከእነሱ መለፍለፍ የእኛ መነሻቸውም መድረሻቸውም በማይታወቁ የሀሰት ፕሮፓንዳዎች መደናበር ግራ ይገባኛል። በቡድኑ ድንፋታም ሆነ በአውሮፓውያን ጫና የምትፈረስ ኢትዮጵያ የለችም። እንደ ወያኔ ዛቻ በየተገናኘበት የሚገዳደል ኢትዮጵያዊም አይኖርም።
እነሱና ጥቂት ቡችሎቻቸው እስካሁን የቻሉትን አድርገዋል በቀጣይም አስከመጨረሻ ህቅታቸው መፈራገጣቸውም አይቀርም። በዚህ ሂደት ግን እኛ የመጣውን ችግር ከመጋፈጥ ይልቅ ለእነሱ ማስፈራሪያና ዛቻ ቦታ በመስጠት ቀኑ መንጋቱ ላይቀር የጭንቅ ግዜያችንን ልናረዝም አይገባንም።
የዓለም ታሪክ የከተበው ተደጋጋሚው እውነታ የሚያስገነዝበን ዛሬ አደጉ በለጸጉ የምንላቸው ሀገራት በሙሉ በተለያዩ አታካች ችግሮች ውስጥ ማለፋቸውን ነው። የዓለም ልእለ ሀያላን ሀገራት የሚባሉት አሜሪካ ሩስያና ፈረንሳይ ከዛሬ ማንታቸው ጀርባ ከባድ የደም መስዋዕትነት ከፍለዋል። በቅርቡ ሀይላቸውን አፈርጥመው ሀያላኑን መገዳደር የጀመሩት ሰሜን ኮርያ፤ ኢራንና ቱርክ ለዛሬ የበቁት ከውስጥ ችግሮቻቸው ባለፈ በርካታ ጫናዎችንና ማዕቀቦችን በጽናት መሻገር በመቻላቸው ነው።
ቻይናውና ዛሬ በዓለም አቀፍ መድረክ አንገታቸውን ከፍ አደርገው መሄድም መናገርም ከመጀመራቸው በፊት አስከፊ የሚባል ረሀብ አሳልፈዋል። የዓለም የቴክኖሎጂ የዘመናዊ ጦር ባለቤትና የስለላ ቁንጮ የምትባለው እስራኤል በገናናነቷ ዋዜማ ምድራዊ ገሀነም በሆነው ኦሽዊትዝ ዜጎቿ ዜጎቿን ለፋብሪካ ምርትነት ሰውታለች።
የትኛውም የሰለጠነና ሰላማዊ ሀገር ሀዝብ ግዜ የወሰደ ያሳለፈው ፈተናና የከፈለው መስዋዕትነት አለ። ይህ ክስተት እኛጋ ብቻ የተፈጠረ አይደለም ለማለት እንጂ ሩቅ ሳንሄድ ለዛሬይቷ ኢትዮጵያ የትላንት ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን የከፈሉትን ዓለም የመሰከረው ተጋድሎ ማስታወስ በቂ ነው። በመሆኑም ለማይቀረው ድል የአሸባሪውን ህወሓት ድንፋታ ወደጎን በመተው በቻልነው ሁሉ ልዩነታችንን ወደጎን ጥለን ከመንግስትና ለሀገር ከቆሙት ልናብር ይገባል። ይህም በኢትዮጵያችን ታሪክ ባለቤትና የድል አጥቢያ አርበኛ ከመሆን በመታደግ አንገታችንን ቀና እንድናደርግ ያስችለናል የዛሬው መልእክቴ ነው።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 12/2014