በተለይ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን በየትኛውም ስፍራና በማንኛውም ሰብዓዊ ፍጥረት ላይ ጥፋትን በማስከተል ላይ ለሚገኘው ሽብርተኝነት የሚሰጠው ትርጓሜ እንደየሀገሩ የሚለያይ ቢሆንም፤ “ሽብርተኝነት አንድን ዓላማ ለማስፈጸም የሽብሩን ድርጊት የሚያዩትና በሚሰሙት ወገኖች ላይ ተፅዕኖ ለማሳደር ታስቦ የሚደረግ ህገ-ወጥ ተግባር ነው” የሚለው ብያኔ ግን ሁሉንም የዓለማችንን ሀገሮች የሚያስማማ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
ይህንን የዓለም ስጋት የሆነውን ሽብርተኝነትን ከመከላከል አንጻር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስተባበሪነት ጸድቀው ስራ ላይ የዋሉ ከ12 የማያንሱ ስምምነቶች አሉ። በነዚህ ስምምነቶች መሰረትም አንድ ሉዓላዊት አገር በሀገሪቱ ፓርላማ ሽብርተኛ ብላ የሰየመችውን ቡድን፣ ድርጅት አልያም ግለሰብ ውሳኔውን አክብሮ መቀበልና ማውገዝ ከሌሎች አገሮች የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው።
ከዚህ አኳያ እስካሁን ከዓለም ላይ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮት ዓለም አላማን ለማራመድ በማሰብ በመንግስት ላይ ተጽእኖ ለማሳደር፣ ህብረተሰብን ወይም የህብረተሰቡን ክፍል ለማስፈራራት ወይም የአንድን አገር መሰረታዊ ፖለቲካዊ፣ ሕገ- መንግሥታዊ ወይም ማህበራዊ ተቋማትን በኃይል ለማናጋት ወይም ለማፍረስ ሲሰሩ የተስተዋሉ እንደ አልቃይዳ፣ አይ ኤስ አይ ኤስ፣ ታሊባን፣ ቦኮሃራም፣ ሎርድ ሪዝስታንስ አርሚ፣ አልሻባብ ወ.ዘ.ተ የመሳሰሉ የሽብር ቡድኖችን ዓለም በአንድነት ለማጥፋት ሲሰራ ተስተውሏል። በአንድ ድምጽም አውግዟል።
የሽብር ቡድኖችን ራእይ ወይም ተልእኮ ለማሳካት የሚንቀሳቀስ አካላት ብቻ ሳይሆን አርማቸውንና ምልክታቸውን የሚጠቀም ማንኛውም አካል በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ቀርቦ ሲጠየቅና እስከሞት ፍርድ ድረስ ሲሰጥ ተስተውሏል። የትኛውም የዓለም የዜና አውታር የሽብር ቡድኖችን አላማና ተልኮ በአንድ ድምጽ ሲያወግዝ ኗሯል። እያወገዘም ይገኛል።
ነገር ግን ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት ገደማ ኢትዮጵያና ህዝቧቿን በአስከፊ የመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ሲጨቁን የነበረው አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአገሪቱ የመጣውን ፖለቲካ ለውጥ ቀልብሶ ተመልሶ በኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ ላይ ለመቀመጥ አልያም አጥፍቼ ልጥፋ በሚል ስሌት በየሳምንቱ የሞት ድግስ እየደገሰ ባለፉት ሶስት ዓመታት የመንግስት ስራ እሬሳ መቅበር እንዲሆን አድርጓል።
በዚህ የሽብር ቡድን የጥፋት ድግስ አገሪቱ አኬል ዳማ ሆናለች። ታዲያ ሽብርተኝነትን አጥብቀን እንዋጋለን የሚሉት አሜሪካና ምዕራባዊያን እንዲሁም ልሳኖቻቸው የዚህን አሸባሪ ቡድን እኩይ ስራ ተሳስተው እንኳን አንዴም አውግዘው አያውቁም። ይልቁንም በህዝብ የተመረጠው መንግስት ላይ ተጽኖ በመፍጠር ቡድኑን በድርድር ሰበብ ዳግም ከወደቀበት አንስቶ ወንበር ላይ ለማስቀመጥ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ሳይቀር በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ በአስር ጊዜ ተቀምጦ ተወያይቷል።
አሸባሪው የህወሓት ቡድን መንግስት በተደጋጋሚ ያቀረበውን የሰላም ጥሪ እንደፍርሃት በመቁጠር ላለፉት ሦስት ዓመታት በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ሀገራዊ ለውጥ ወደጎን በመተው “ጦርነት ለትግራይ ህዝብ ባህላዊ ጨዋታ ነው” በሚል ለጦርነት እና ግጭት ሲዘጋጅ ቆይቷል። ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት የዝግጅት ምዕራፉ ማጠናቀቂያ ነበር፡፡
ከፊት ለፊት በቅጥረኞች ከጀርባው በክሃዲዎች የተወጋው የሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ግን ከ20 ዓመት ያላነሰ ከቀበሮ ጉድጓድ ሳይወጣ የትግራይን ህዝብ ሰላም ጠዋት ማታ ሲጠብቅ የነበረ፤ ከሚሰጠው ከዚህ ግባ የማይባል የወር ደመወዙ ቀንሶ ለትግራይ ህዝብ ውሃና ትምህርት ቤት ሲሰራ የኖረ፤ በጥቅሉ በሃዘንና በደስታ ከትግራይ ህዝብ የማይለይ ነበር።
ነገር ግን “በአጎረስኩኝ እጄን ተነከስኩ” እንዲሉ አበው የሽብር ቡድኑ የሰራዊቱን አባላት ገድሎ በድናቸው ላይ ጨፈረ። ልብሳቸውን አስወልቆ እርቃናቸውን አስኬደ። “ውርደቱ ኩራቱ” የሆነበት ይህ አሸባሪ ቡድን “በሰሜን እዝ ላይ መብረቃዊ ጥቃት ፈጽሚያለሁ” በሚል ለዓለም አስተጋባ። ነገር ግን ይህን የሽብር ቡድኑን እኩይ ተግባር አሜሪካና ምዕራባዊያን ባላየ፤ ባልሰማ አለፉት።
መንግስትም ሳይወድ በግድ ተገዶ ህግን የማስከበር እርምጃ ውስጥ በትግራይ ክልል ሲገባ አሜሪካና ምዕራባዊያን መንጫጫት ጀመሩ። ይሁን እንጂ መንግስት የአገርን ሉዓላዊነት የህዝብን ደህንነት ለማስጠበቅ በትግራይ ክልል ህግን ለማስከበር በገባ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቀንደኛ የቡድኑ አመራሮችን በቁጥጥር ስር አዋለ። እጅ ያልሰጡትንም ደመሰሰ። ቀሪ የጁንታው እርዝራዦች ግን ተራ ሽፍታ ሆነው በየቀበሮ ጉድጓዱ የሽምቅ ውጊያ ውስጥ ሊገቡ ችለዋል።
ክልሉን የመከላከያ ሰራዊት ከተቆጣጠረ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ከወታደራዊ ወጪዎች ውጭ ለተለያዩ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች እና ቀለብ ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ አድርጓል። ይህም ለክልሉ ከሚመደበው ዓመታዊ በጀት በ13 እጥፍ የሚልቅ ነው።
መንግስት ይህን ሁሉ ድጋፍ ለክልሉ ህዝብ ቢያደርግም እጁ አመድ አፋሽ ሆኖበት አንድም ዓለም አቀፍ ተቋም በክልሉ መንግስት የሚያደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ እውቅና የሰጠ የለም። ይልቁንም ችግሮቹን ብቻ እየፈለጉ ሲያናፍሱ ተስተውሏል። መከላከያ ክልሉን ለቆ ይውጣ በሚልም ምዕራባዊያን ሲያላዝኑ ከርመዋል።
የጁንታው እርዝራዦች ከጌቶቻቸው በተሰጣቸው ተልዕኮ መሰረት ህዝብ ውስጥ ተሰግስገው በተራዘመ ጦርነት የአገርን ሉዓላዊነት አደጋ ለመጣል እየሰሩ መሆናቸውን የተረዳው መንግስትም፤ የትግራይ ገበሬ ማሳው ጾም እንዳያድርና የጥፋት ቡድኑ እርዝራዦችም ቆም ብለው እንዲያስቡበት የጽሞና ጊዜ ለመስጠት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ መከላከያው ክልሉን ለቆ እንዲወጣ አድርጓል። ነገር ግን አሜሪካና ተባባሪዎቿ መከላከያ የትግራይ ክልልን ለቆ መውጣት አለበት በሚል ሲያላዝኑ ቢከርሙም መከላከያ ክልሉን ለቆ ሲወጣ ግን አንድም ጥሩ አስተያየት አልሰጡም።
መንግሥት ላለፉት ስምንት ወራት በትግራይ የነበረውን ሕግ የማስከበር እርምጃ አቁሞ በሰብዓዊነት ላይ የተመሰረተ የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ቢያውጅም በአሸባሪው ቡድን ተቀባይነትን አላገኘም። መንግሥት የመከላከያ ኃይሉን ከትግራይ ክልል ካስወጣ በኋላም አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ባወጀው ጦርነትና ወራራ አያሌ ንጹሃን ዜጎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በአስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ይገኛሉ።
ጁንታው ቀደም ሲል በማይካድራ የፈጸመው የዘር ማጽዳት ወንጀል እንደተጠበቀ ሆኖ መንግስት የተኩስ አቁም ካወጀ በኋላ በአማራና በአፋር ክልሎች በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በጋሊኮማ፣ በጭና፣ በአጋምሳ እና በራያ ቆቦ ንጹሃን ዜጎችን በጅምላ ጨፍጭፏል። እንስሳትና እጽዋትን ሳይቀር የረሸነ የዓለማችን የመጀመሪያው የሽብር ቡድን ነው።
የሽብር ቡድኑ በአፋር ክልል በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በንብረትና በሰው ህይወት ላይ ያደረሰው ጉዳት እንደተጠበቀ ሆኖ፤ በአማራ ክልል በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች ብቻ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ንጽሃን ዜጎች ለረሃብ እንዲጋለጡ አድርጓል። በክልሉም 20 ሆስፒታሎች፣ 277 የጤና ኬላዎች 29 አምቡላንሶች እንዲሁም 2 የደም ባንክ በሽብር ቡድኑ ወድሟል። እንዲሁም አሸባሪው የትህነግ ቡድን በአማራ ክልል በፈጸመው ወረራ ከ1 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችን የሚያስተናግዱ ትምህርት ቤቶች ጉዳት አድርሷል ፤ ከ260 በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል፤ 2 ሺህ 511 የሚደርሱ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል ጥቃት ደርሶባቸዋል፡፡
ታዲያ ይህን ሁሉ የሽብር ድርጊት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየፈጸመ የሚገኘውን አሸባሪው የህወሓት ቡድንን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለኢትዮጵያ ህዝብ ስጋት እንዳይሆን አድርጎ አከርካሪውን ለመበጠስ መንግስት እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ዝግጅት ተከትሎ “መንግስት የትግራይ ህዝብን ለማጥፋት ጦርነት አውጇልና የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ይድረስልን ሲል የጁንታው ቃል አቀባይ የአሜሪካ ማዕከላዊ መንግስት የስለላ ድርጅት ንብረት ለሆነው ሮይተርስ ለተሰኘው የዜና ወኪል ከሰሞኑ የድረሱልን ጩኸት አሰምቷል።
ይህም ህወሓት- ህዝብን እያሸበረና እየገደለ ድረሱልኝ “ኡኡ” የሚል ብቸኛው የዓለማችን አሸባሪ ቡድን ያደርገዋል። ከምንም በላይ ግን የሚያሳፍረው አሜሪካና ምዕራባዊያን ሽብርተኝነትን በግልጽ እንደሚዋጉ ሲናገሩ ቢቆዩም ህወሓት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እያደረሰ ያለውን የሽብር ጥቃት በቀጥታም በተዘዋዋሪም ሲደግፉ ተስተውሏል።
የጁንታው አፈቀላጤ የድረሱልንና ተደበደብን ጩኸት ሮይተርስ ቀድሞ ተቀብሎ አስተጋብቷል። ዜና እንዲሰራጭ የተፈለገበት ምክንያቱ ቀደም ሲል በተለያዩ ሙህራን እንደተገለጸው የአሜሪካና የአጋሮቿ ፍላጎት በአፍሪካ ሁለተኛ የህዝብ ቁጥር ያላትን ኢትዮጵያን የመበተን እቅድ መሆኑን በግልጽ ያመላክተናል። በአጠቃላይ ምዕራባዊያን መንግስታት እና ልሳኖቻቸው ተቀናጅተው ዓለም ላይ በሽብር ስራው ተወዳዳሪ ከማይገኝለት ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ቁመዋል።
በዚህ ወቅት በአሜሪካና ምዕራባዊያን የሚደገፍን አሸባሪ ቡድን ብቻዋን እየተፋለመች ያለች ብቸኛ የዓለማችን አገር ካለች ኢትዮጵያ ብቻ ናት። ስለዚህ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ከመቼውም በላይ አንድነቱን በማጠናከር አሸባሪውን ህወሓት ለማጥፋት እያደረገ ያለውን ተጋድሎና ድጋፍ አጠናክሮ በማስቀጠል ጁንታውን ዳግም ላይነሳ በመቅበር ተሻጋሪ ታሪክ በመስራት የሀገሩን ህልውና ማስጠበቅ ይኖርበታል።
በሶሎሞን በየነ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2014