ሀገራችን መዳፏ ውስጥ የሚገኙና ሊገቡ የተቃረቡ አያሌ የማደግ ተስፋዎች አሏት፡፡ እነዚህን በመጠቀም በእርግጠኝነት መልማትና መበልጸገም ትችላለች፡፡ በሰፊ ህዝባዊ ተቀባይነት አገር መምራት የጀመረው አዲሱ መንግስትም ልማቷን፣ ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ ቃል ገብቶ ስራ ጀምሯል፡፡
ብልጽግናን የማረጋገጥ ተግባር ብዙ የሚጠይቃቸው ጉዳዮች ያሉ ቢሆንም ሰላምና መረጋጋት ዋናው ነው፡፡ ህዝብ በሰላም እጦት አደጋ ላይ ከወደቀ ማልማት አይደለም የለማውንም ያልለማውንም ጠብቆ ማቆየት አይቻልም፡፡ በጥባጭ እያለ ማን ጥሩ ይጠጣል አይደል የሚባለው፡፡
በጥባጭ እያለ ጥሩ እንደማይጠጣ አሸባሪው ህወሓት ካደረሳቸው ጥፋቶች በሚገባ ተገንዝበናል፡፡ ቡድኑ በቀጥታ በራሱም በተላላኪዎቹም እዚህም እዚያም በሸረባቸው ሴራዎችና በፈጸማቸው ጥቃቶች በጠፋው የንጹሃን ህይወት፣ በሰሜን እዝ ላይ በተፈጸመው ክህደት፣ የተናጠል የተኩስ አቁሙን ተከትሎ በአማራ እና አፋር ክልል ላይ በፈጸመው ወረራ ዛሬም ድረስ እየፈጸመ ባለው ጥቃት ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን በእጅጉ እየተጎዱ ናቸው፡፡
ይህ አሸባሪ ቡድን ያልተፈጸመ የክፋት ጥግ የለም፡፡ የማይካድራው ቁስል ሳይጠግ በአማራ ክልል አጋምሳ፣ ጭና፣ ቆቦ፣ በአፋር ክልል ጋሊኮማ በርካታ ንጹሃን ዜጎችን ጨፍጭፏል፤ ይሄው ሰሞኑን ደግሞ በአማራ ክልል በውርጌሳና ውጫሌ እንዲሁም በአፋር ክልል ጭፍራ ተመሳሳይ ጭፍጨፋ ፈጽሟል፡፡ በዚህ አሸባሪ የግፍ ተግባር ህይወታቸው የተመሰቃቀለ ዜጎቻችን ደግሞ የት የለሌ ናቸው፤ ሀብታቸውን ጥሪታቸውን አጥተው መጠለያ ውስጥ የገቡትና እየገቡ ያሉትም ስፍር ቁጥር የላቸውም፡፡
የቡድኑ ታጣቂዎች ሊጥ ሰርቀዋል፤ ከአፍ ነጥቀው በልተዋል ማለት ነው፤ አስገድዶ መደፈሩ በብዛት ተፈጽሟል፤ ከብቶች አርደው በልተዋል፤ ነድተዋል፤ ፍጹም አረመኔያዊ በሆነ ሁኔታም በጥይት ደብድበው ገድለዋል፡፡ በጥንቃቄ መራመድ ያለባቸውና መሸበር የሌለባቸው ነፍሰ ጡሮች ቡድኑን ሲሸሹ በየመንገዱ ቀርተዋል፤ የወላድ ወግ አጥተው በየጫካው በየመንገዱ የወለዱትም በርካታ ናቸው፡፡ ህጻናት በዚህ ለጋ እድሜያቸው የጥይትና የሲቃ ድምጽ እንዲሰሙ ተገደዋል፡፡ አቅመ ደካማ እናቶች ሲሸሹ ተገድለዋል፡፡
ለዓመታት በተደረገ ጥረት በብዙ ሀብት የፈሰሰባቸው የጤና፣ የትምህርት፣ የግብርና የመሳሰሉት ተቋማት ተዘርፈዋል፤ መዘረፍ ያልቻሉትን አውድመዋል፤ ሰነዶች ሳይቀሩ ሆን ተብሎ ወድመዋል፡፡ የአርሶ አደሮችን ቡቃያ የጥፋት መፈንጫቸው አድርገውታል፡፡
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለመፈናቀል ተዳርገዋል፡፡ ይህ አሃዝ ቡድኑ በደቡብ ወሎ ላይ እየፈጸመ ባለው ጥቃት የተነሳ አሁንም እየጨመረ መጥቶ የደሴና ኮምቦልቻ ከተሞች በተፈናቃዮች ተጥለቅልቀዋል፡፡ ቡድኑ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት እዚህ ዘርዝሮ መጨረስ አይቻልም፡፡
መንግስት ቡድኑን ለመደምሰስ የተለያዩ እርምጃዎችን ሲወሰድ ቆይቷል፡፡ በህግ ማስከበር ዘመቻው ማንነቱን በሚገባ አሳይቷል፡፡ ቡድኑም ጥጉን ይዞ ነበር፡፡ በአማራ ክልልና በአፋር ክልል ላይ በፈጸመው ወረራም የንጽሃን ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ ቢያልፍና ንብረት ቢወድምም ከአፋር ክልል ሙሉ ለሙሉ ተቀጥቅጦ ወጥቷል፡፡ ከአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር አካባቢም እንዲሁ ዳግመኛ እንዳያስበው ተደርጎ ተደምስሷል፡፡
አሁን የሰሜን ወሎን የተለያዩ አካባቢዎችን ይዞ ይገኛል፡፡ ወረራውን በማስፋት ወደ ደቡብ ወሎ ለመግባት የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረገ ይገኛል፡፡ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች በሚገኙ ነዋሪዎች ላይ ግፍ መፈጸሙን ቀጥሎበታል፡፡
ቡድኑ እያካሄደ ያለው ወረራ በህዝቡ፣ በመከላከያና ሌሎች የጸጥታ ኃይሎች እየተመከተ ነው፡፡ ህዝቡ ቡድኑ ወደ አካባቢው እንዳይገባ ገብቶም ከሆነ ተረጋግቶ እንዳይቀመጥ እያደረገ ነው፡፡ አይቀጡ እየተቀጣ በወጣባቸው አካባቢዎች ሁሉ የህዝብ ከፍተኛ ተጋድሎ አድርጓል፡፡
ህዝቡ ያደረገው ተጋድሎ ህዝቡ ቡድኑን ለመደምሰስ እየተካሄደ ያለውን ዘመቻ በተለያዩ መንገዶች መደገፉን አሁንም አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ የሰራዊቱ ተልዕኮ ይበልጥ እንዲሳካ ህዝቡ አሁንም አጋርነቱን በላቀ መልኩ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
ህዝቡ ብዙ ሊገነዘባቸው የሚገቡ ጉዳዮች አሉ፡፡ ጦርነቱ ወታደራዊ ብቻ አይደለም፡፡ የፕሮፓጋንዳ ጦርነትም አብሮት አለ። በሰርጎ ገቦችና በተላላኪዎች አማካይነት ህዝቡን ከየከተማውና አካባቢው አሸብሮ ለማስወጣት እየተሞከረ ነው፡፡ በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያዎች የሚካሄደው ዘመቻም ሌላው ነው፡፡ ከተሞች ላይ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ ህዝቡ እንዲሸበር እየተደረገ ነው፡፡
በዚህ የሽብር ድርጊት ተጠልፎ መውደቅ አይገባም፡፡ ተጠልፎ መውደቅ ቡድኑን ለመደምሰስ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ከፍ እንዲል ያደርጋል፤ እስከ አሁን የተገኘውን ፍሬ መጠበቅና ማጣጣምም አያስችልም ፡፡
ጦርነቱን በመሸሽ ወይም ሰዎች እንዲሸበሩ የሚያደርግ ከንቱ ወሬ በማናፋስ ማስቀረት አይቻልም፤ ጦርነት ቢሸሹት ይከተላል፤ መፍትሄው መጋፈጥ ብቻ ነው፡፡ ቡድኑ ጃስ ባለ ቁጥር እየበረገጉ አካባቢን ለቆ መውጣት ብርቱውን ጭምር ይሸበራል፤ ራስንም፣ ህዝብንም ሀገርንም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ስለሆነም መፍትሄው መጋፈጥና መጋፈጥ ብቻ ነው፡፡ አሁን ከሀገር መከላከያና ከሌሎች የጸጥታ ሀይሎች ጋር በመሆን ይህን ቡድን መጋፈጥ ይገባል፡፡
ጦርነቱ ኢኮኖሚያዊ መሆኑንም ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ በሀገር ቤት ህዝቡ በኑሮ ውድነት እንዲማረር እየተደረገ ነው፡፡ ምዕራባውያኑ ለኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ብድርና እርዳታ እያቆሙ ሊያንበረክኩን እየሞከሩ ናቸው፡፡
ጦርነቱ ቡድኑ ብቻውን የሚያካሂደው አይደለም፡፡ የውክልና ነው፡፡ በእዚህ ውስጥ ምዕራባውያኑ መንግስታት ግብጽና ሱዳንም በተለያዩ መልኩ ድጋፍ እያደረጉለት ነው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን ዜጎች ሲጨፈጭፍ፣ ሲያፈናቅል፣ ሀብትና ንብረታቸውን ሲያወድም እነዚህ ኃይሎች የማያወግዙትና ተው የማይሉትም ለዚሁ ነው፡፡ ቡድኑ እያጠፋ አጥፊ ተብላ እየተከሰሰችና ጫና እንዲደርስባት እየተደረገ ያላቸው ኢትዮጵያ መሆኗም ይህን ይጠቁማል፡፡ ይህም ጦርነት የገጠምናቸው በርካታ ኃይሎች መሆናቸውን ያመለክታል፡፡
እናም አሸባሪ ቡድኑ የኢትዮጵያን ጠላቶች ተልእኮ እየፈጸመ ነው፡፡ ስለሆነም እንደ እስከ አሁኑ ሁሉ ኢትዮጵያውያን ይህን ጦርነት በድል ለመወጣት የተጠቀሱትን የጦርነቱ ልዩ ልዩ ገጽታዎች ታሳቢ ያደረገ ግንዛቤ ሊኖር ይገባል፡፡ በህልውና ዘመቻው ይህን የቡድኑን እና የምዕራባውያኑን የአካባቢያችን ባላንጣዎች ዘርፈ ብዙ ሴራና ጥቃት የሚመጥን ምላሸ ለመስጠት ዝግጁነትን ይበልጥ ማጠናከር ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን ጥቅምት 11/2014