ኢትዮጵያ ወራሪ ኃይሎች ሉዓላዊነቷን በመዳፈር በመዳፋቸው ስር ሊያስገቧት በሞከሩባቸው አጋጣሚዎችም ይሁን በሌሎች ጊዜያትና መስኮች አኩሪ ተግባራትን የፈፀሙ ብዙ ጀግኖችን አፍርታለች። ይሁን እንጂ የእነዚህን ጀግኖች ውለታ ጠንቅቆ የማወቁና በዋጋ የማይተመነውን ትልቅ ውለታቸውን የመዘከሩ ጉዳይ ግን እነዚህን ባለውለታዎቻችንን ‹‹አመድ አፋሽ›› የሚያሰኝ ነው። ለኢትዮጵያ ነፃነት፣ ክብርና እድገት ታላቅ ተግባር ፈፅመው ስማቸውም ስራቸውም ከተዘነጉት ባለውለታዎች መካከል ኢትዮጵያን ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ ለመታደግ በምስራቅ በኩል ሲፋለሙ ሕይወታቸው ያለፈው የምስራቆቹ ፈርጦች ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል እና ደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማዕት ይጠቀሳሉ። ለዛሬ የእነዚህን ባለውለታዎቻችን ታሪክ በአጭሩ እንመለከታለን።
፩. ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል
ደጃዝማች ነሲቡ ትምህርታቸውን የተከታተሉት ከወንድማቸው ወሰኔ ዘአማኑኤል ጋር በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ነው። ይህም በኢትዮጵያ ዘመናዊ ትምህርት ታሪክ ውስጥ ዘመናዊ/የምዕራባውያንን ትምህርት ከቀሰሙ ግንባር ቀደምት ኢትዮጵያውያን (የመጀመሪያው ዙር ምሁራን) መካከል አንዱ ያደርጋቸዋል። ሁለቱም ወንድማማቾች የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ሆነው አገልግለዋል።
ከ1914 ዓ.ም እስከ 1923 ዓ.ም ሰባተኛው የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ የነበሩት ነሲቡ ዘአማኑኤል በቆይታቸው በርካታ ተግባራትን አከናውነዋል። የኮንትሮባንድ ንግድን የሚቆጣጠሩና ግንባራቸው ላይ ‹‹የምስጢር ዘበኛ›› የሚል ጽሑፍ ተለጥፎባቸው የሚሰሩ የምስጢር ዘበኞችን እንዲሁም የአራዳ ዘበኞችን በማቋቋም ይታወቃሉ። ከዚህ በተጨማሪም የከንቲባ ነሲቡ ዘአማኑኤል ዘመን ጸጥታ በማስከበር እንዲሁም ሰልፍ በማሳየት ረገድም ይታወሳል።
ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ እንደፃፉት፣ ከንቲባ ነሲቡ ዘአማኑኤል በርካታ ለውጦችን ያስተዋወቁ ከንቲባ ነበሩ። የከተማ መሬት ምዝገባና ምደባ የተጀመረው በእርሳቸው የአስተዳደር ዘመን ነበር። በበዓላት ቀናት ጥይት መተኮስ እንዲቆም፣ የሞቱ እንስሳት እንዲቀበሩ፣ የመንገድ ግንባታ እንዲስፋፋ፣ ከተማ ውስጥ በተለይም በዋና ዋና መንገዶች አካባቢዎች ቤት ለሚገነቡ ነዋሪዎች ብድር እንዲመቻችላቸው፣ ልዩ ልዩ ውሎችን በሚፈራረሙ ወገኖች መካከል የሚደረጉ ስምምነቶች የማዘጋጃ ቤት/የከተማ አስተዳደር እውቅና እንዲያገኙ እንዲሁም የከተማው ሰላምና ጸጥታ እንዲጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎች የተጀመሩትና የተስፋፉት በእርሳቸው የከንቲባነት ወቅት ነበር። እ.አ.አ በ1929 ዓ.ም በርሊንን ከጎበኙ በኋላ ደግሞ አዲስ አበባ ዘመናዊ የውሃ አቅርቦት የምታገኝበትን የአሰራር ስርዓት ለመፈለግ/ለማጥናት ሞክረዋል። በ1923 ዓ.ም በወቅቱ አጠራር ‹‹ጉራጌና ሶዶ›› የሚባለው አካባቢ ገዢ ሆነው ተሾሙ። ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ ደግሞ የባሌ ግዛት ሹም ሆነው ተሹመዋል።
ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ስትወር ንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የፋሽስትን ወረራ ለመመከት የክተት አዋጅ ካወጁ በኋላ የኢትዮጵያን ጦር በተለያዩ ግንባሮች እንዲመሩ ለጦር አበጋዞቻቸው ስምሪት ሰጡ። በምስራቅ በኩል ወረራ የፈጸመውን ማርሻል ሩዶልፎ ግራዚያኒን ለመመከት ወደ ደቡብ ግንባር የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ቀኝ ደቡብ፣ መሐል ደቡብና ግራ ደቡብ በሚሉ ስያሜዎች በሶስት ምድቦች የተደራጀ ነበር። የቀኙ የደቡብ የጦር ሰራዊት ዋና አዛዥም የወቅቱ የሐረርጌ እንደራሴ የነበሩት ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል ነበሩ። የግራ ደቡብ ምድብ ዋና አዛዡ የወቅቱ የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ዋና ገዢ ራስ ደስታ ዳምጠው ሲሆኑ፤ የወቅቱ የባሌ ገዢ የነበሩት ደጃዝማች በየነ መርዕድ ደግሞ የመሐል ደቡብ ጦር ሰራዊት ዋና አዛዥነቱን ይመሩ ነበር።
በሦስቱም ምድብ አዛዦች ስር ደግሞ ሌሎች የጦር አበጋዞች ሰራዊታቸውን ይዘው ተሰልፈው ነበር። ከእነዚህም መካከል ደጃዝማች ሃብተሚካኤል ይናዱ፣ ደጃዝማች መኮንን እንዳልካቸው፣ ደጃዝማች አበበ ዳምጠው፣ ደጃዝማች አምደሚካኤል ሃብተሥላሴ እና የቆራሄው ጀግና ግራዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማዕት (በኋላ ደጃዝማች) በደጃዝማች ነሲቡ ስር ተሰልፈው ነበር።
በደቡብ ግንባር በኩል ከዘመተው የኢትዮጵያ ጦር መካከል በደጃዝማች ነሲቡ የተመራው የቀኙ የደቡብ ጦር ምድብ በፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ላይ ተደጋጋሚ ድሎችን በማስመዝገብ ቀዳሚ ነበር። በደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል እዝ ስር ቆራሄ ላይ መሽገው የነበሩት ግራዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማዕት የወራሪውን የእግረኛ ጦር በተደጋጋሚ ድል አድርገውታል። በአካባቢው የነበሩት ፊታውራሪ ጓንጉልም በፋሺስት ጦር ላይ ጥቃት ሰንዝረው የጠላትን ጦር በመደምሰስ በርካታ የጦር መሳሪያዎችን መማረክ ችለዋል።
በእግረኛ ጦር ውጊያ ሽንፈት የተከናነበውና በሽንፈቱ የተበሳጨው የፋሺስት ጦር መርዝ ጋዝ ጣይ አውሮፕላኖችን በማሰማራት ኢትዮጵያውያንን በግፍ ጨፈጨፈ። ከብዙ እልህ አስጨራሽና መራራ ፍልሚያ በኋላ በደጃዝማች ነሲቡ ይመራ የነበረው ቀኙ የደቡብ ጦር ተፈታ። ደጃዝማች ነሲቡም የኢትዮጵያን አቤቱታ ለዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) ለማቅረብ ወደ ከንጉሰ ነገሥት ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ ጋር ወደ ውጭ ሄዱ።
ስዊዘርላንድ እንደደረሱም ንጉሰ ነገስቱ ከእየሩሳሌም ጀኔቫ እስከሚደርሱ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ በመንግሥታቱ ማኅበር የኢትዮጵያ ልዑክ መሪ በመሆን አገልግለዋል። የልዑኩ መሪ ሆነው በቆዩበት ጊዜ በማኅበሩ ጉባኤ ላይ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር የሚጠቀመውንና የተከለከለ የመርዝ ጋዝ እንዲያቆም በመማጸን፤ ራሳቸውም በመርዝ ጋዝ እንደተጠቁና ጤናቸውም እንደተቃወሰ የሐኪም ማስረጃ ጭምር በማቅረብ የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በኢትዮጵያ ጦርና ሕዝብ ላይ የተጠቀመው የመርዝ ጋዝ እንዲወገዝና በድጋሚ ከመጠቀም እንዲቆጠብ የሚደነግጉ ሁለት የውሳኔ ረቂቅ ሃሳቦችን አቅርበው እንዲጸድቁ ለማድረግ ቢማጸኑም ውድቅ ተደርገውባቸዋል።
የፋሺስት ኢጣሊያ ጦር በምስራቅ በኩል በነበረው የኢትዮጵያ ጦር ላይ ያዘነበው የመርዝ ጋዝ ደጃዝማች ነሲቡን በክሏቸው ስለነበር፣ በዚሁ የመርዝ ጭስ ምክንያት ታመው፣ ጥቅምት 6 ቀን 1929 ዓ.ም በስደት በነበሩበት ስዊዘርላንድ ሕይወታቸው አልፏል።
፪. ደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማዕት
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም ኢትዮጵያን ስትወር በምስራቅ በኩል ወረራ የፈጸመውን የወራሪውን ጦር ክንፍ ለመመከት ወደ ደቡብ ግንባር የዘመተው የኢትዮጵያ ጦር ቀኝ ደቡብ፣ መሐል ደቡብና ግራ ደቡብ በሚሉ ሶስት ምድቦች የተደራጀ ነበር። የቀኙ የደቡብ የጦር ሰራዊት ዋና አዛዥም ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል ነበሩ። ደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል ከነበሩትና ሰራዊታቸውን ይዘው ከተሰለፉት የጦር አበጋዞች መካከል አንዱ የቆራሄው ጀግና ግራዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማዕት (በኋላ ደጃዝማች) ነበሩ።
በደቡብ ግንባር በኩል ከዘመተው የኢትዮጵያ ጦር መካከል በደጃዝማች ነሲቡ የተመራው የቀኙ የደቡብ ጦር ምድብ በፋሺስት ኢጣሊያ ጦር ላይ ተደጋጋሚ ድሎችን በማስመዝገብ ቀዳሚ እንዲሆን ያስቻሉት ግራዝማች አፈወርቅ ናቸው። በደጃዝማች ነሲቡ ዘአማኑኤል እዝ ስር ቆራሄ ላይ መሽገው የነበሩት ደጃዝማች አፈወርቅ ወልደ ሰማዕት የወራሪውን የእግረኛ ጦር በተደጋጋሚ ድል አድርገውታል።
ስለደጃዝማች አፈወርቅ ታሪክ በስፋት አልተፃፈም። ደራሲና ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ ‹‹የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት›› በሚለው መጽሐፉ የደጃዝማች አፈወርቅ መቀመጫ ወደነበረው ወደ ቆራሄ ሄዶ ከደጃዝማች አፈወርቅ ጋር የተገናኘው ጆርጅ ስቲር የተባለ ጸሐፊ ስለደጃዝማች አፈወርቅ ጽፎታል ብሎ ካሰፈረው ጽሑፍ ጥቂቱን እንመልከት።
‹‹ … አፈወርቅ ጨዋና መልካም አስተዳዳሪ ነው። በኦጋዴን ውስጥ ወታደራዊ ካምፖችን በሚገባ ያደራጀ ነው። የወታደሩ ጤና እንዲጠበቅና ዘመናዊ መገናኛ እንዲኖረውና የኦጋዴን ኑሮ አስደሳች እንዲሆን ያደረገው አፈወርቅ ነው … አፈወርቅ በፎቶ ከሚታዩ ይልቅ በቁመናቸው ሲታዩ የተለዩ ናቸው … ካየኋቸው ሹማምንት ሁሉ አፈወርቅ የተለዩ ናቸው …››
ደጃዝማች አፈወርቅ በአጭር ጊዜ ስላደራጁት የጦር ካምፕም እንዲህ ሲል በአድናቆት ጽፏል።
‹‹ … ያንን ውብ የጦር ካምፕ ጎብኝቻለሁ። በጥሩ ሁኔታ የተዘጋጀ ነው። ለአየር ወረራ መከላከያ የሚሆነው ምሽግ ጠመዝማዛ እየሆነ ተበጅቷል። የጠመንጃዎቹ ግምጃ ቤት፣ ወታደሩን እየሰበሰቡ የሚያነጋግሩበት ቦታ ሁሉ በሚገባ የተዘጋጀ ነው። አንዱ ካሚዮናቸውና ሁለቱ ፈረሶቻቸው ዝግጁ ሆነው ሙላህ (ፀረ-አውሮፕላን አርሊኮን) ካምፕ ውስጥ ቆመዋል። ይህ ሁሉ ዝግጅት የተፈፀመው በሶስት ሳምንት ጊዜ ነው።››
ደጃዝማች አፈወርቅ ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር እንደምትፈልግና ዝግጅት ስታደርግ መቆየቷን ያውቁ ነበር። ጆርጅ ስቲር ስለጉዳዩና ደጃዝማች አፈወርቅ ዘንድ መምጣቱ እንዳስደሰተው ሲገልፅ…
‹‹ … ሁል ጊዜ ፀሐይዋ ልትጠልቅ ስትል ወታደሩ ይሰለፍና አፈወርቅ ባሉበት የኢትዮጵያ ባንዲራ ከተሰቀለበት ይወርዳል። አፈወርቅም የተለመደ ንግግራቸውን ያደርጋሉ። ‹ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ልትወር ተነስታለች። እኔ ሳልሞት ኢትዮጵያ አትወረርም። ከሞትኩ በኋላ ግን የፈለገው ይሆናል። የማውቀው ነገር አይኖርምና ያኔ ግዴለኝም!› ይላሉ። እኔም ብሆን አፍሪካ ውስጥ ከዚህ ጠንካራ ሕዝብ መሐል ለመገኘት ያበቃኝን እግዚአብሔርን አመሠግነዋለሁ … ›› ብሏል።
ደጃዝማች አፈወርቅ አውሮፓውያንን ሁሉ በጥርጣሬ ዓይን ቢመለከቱም፤ ለእንግሊዛዊው ጆርጅ ስቲር ካምፑን እንዲያስጎበኙት በንጉሰ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ ስለታዘዙ እራት አብረው እንዲመገቡ ጋብዘውት ከእራት በኋላ አውሮፓውያንን እንደማያምኑ፤ የእንግሊዝና የዓለም መንግሥታት ማኅበር ሁኔታ እንዳሳሰባቸው አጫውተውት ካምፑን አስጎብኝተውታል።
የኢጣሊያ አውሮፕላኖች አልፎ አልፎ ቦምብ ይጥሉ ስለነበር፤ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከተረፈ ቦንብ የተለያዩ ቁሳቁሶችን እየሠሩ ይጠቀሙበት ነበር። ደጃዝማች አፈወርቅ ስጋ ሲበሉ የሚቆርጡበት ቢለዋ የተሠራው ከቦምቡ አካል ነው። ውሀም ሆነ ጠጅ መጠጫቸው ከቦምቡ አካል የተሰራ ኩባያ ነበር። ስቲርም ‹‹… ‹ይሄ ቦምብ ጩኸቱ ያደነቁራል እንጂ እኛን አይነካንም። እኛም እንዲህ እንዲህ እየሰራን እንጠቀምበታለን› ብለውኛል …›› ብሎ ጽፏል።
በዚህ ዓይነት ሁኔታ ደጃዝማች አፈወርቅ ቆራሔ ላይ ሆነው ከወታደሮቻቸው ጋር በንቃት ሲጠባበቁ ፋሺስቶች ከሌላው ጊዜ ለየት ባለ ሁኔታ ኦጋዴንን በቦምብና በመትረየስ መደብደብ ጀመሩ። የቆራሔ ምሽግ ግን አልበገርም አለ።
ደጃዝማች አፈወርቅም ከፈረሰው ከሙላህ ግቢ ሆነው ኦርሊከናቸውን ይተኩሳሉ። በወቅቱ እዚያው ሆኖ ስለጦርነቱ ሲዘግብ የነበረው ጆርጅ ስቲር ስለ ቆራሔ ምሽግና ስለ አካባቢው ውጊያ እንዲሁም ስለ ደጃዝማች አፈወርቅ አስደናቂ ተጋድሎ ሲጽፍ ‹‹ … በተለይ መስከረም 25 ቀን ቆራሔ ላይ የተጣለው ቦምብ 300 ነበር። አንድ መቶውን የቆጠሩት አፈወርቅ ነበሩ። እነዚህ አንድ መቶ ቦምቦች ዙሪያቸውን ሲወድቁ አፈወርቅ ምንም ሳይደናገጡ በሙሉ ልብ ሆነው የቦንቦቹን ፍንዳታ ይቆጥሩ ነበር። በዚያን እለት አምስት ሰዎች ሲሞቱ 15 ሰዎች ቆሰሉ። ጥቅምት አንድ ቀን በተደረገው ጦርነት የራዲዮ ኦፕሬተራቸው ከጥቂት ሰዎች ጋር ሸሽተው ሊያመልጡ ወጡ። ያን የሸሸ ኦፕሬተር ወድያው ይዘውት ሥራውን እንዲቀጥል አደረጉት …
… ወደ ሙስታሂል አቅጣጫ ዋቢ ሸበሌ ወንዝ አጠገብ ያለው የታፈረ ከተማ ምሽግ በቦምብ ክፉኛ ተደበደበ። በታፈረ ከተማና በቆራሔ መካከል ያለው የሽላቦ ምሽግ ጥቅምት አንድ ቀን በቦምብ በኃይል ተመታ። ኢትዮጵያውያን ወታደሮች በየምሽጋቸው ሁነው አውሮፕላኖቹን ለመምታት ይተኩሳሉ። አፈወርቅ በወታደሮቹ መሐል እየተገኙ ያበረታታሉ። በራድዮ መገናኛም እርዳታ እንዲደርስላቸውና ጦራቸው እንዲጠናከር ይጠይቃሉ። ለጥያቄያቸው ሁሉ ግን መልስ አላገኙም …
… በኢጣሊያ በኩል በአውሮፕላን ድብደባ ከለላ የሚታጀብ እግረኛ ጦር ተላከ። እግረኛው የኢጣሊያ ጦር ታፈረ ከተማንና ሽላቦን አጠቃ። ሙስታሂልና ፌርፌር ያሉትን ምሽጎችንም ያዙ። በእነዚህ ምሽጎች ያሉ ኢትዮጵያውያን በርትተው ተዋግተዋል። በሁለቱም ወገን ከባድ ጉዳት ደርሷል … ቆራሔን አልፎ ያለው የቀብሪደሀር ምሽግ በቦምብ ክፉኛ ተደበደበ። ገርለጎቢ፣ ታፈረ ከተማና ሽላቦ ተያዙ። የአፈወርቅ ሰላዮችም መጥተው ማራናሬ ያለው የውሀ ጉድጓድ መያዙን ነገሯቸው። አፈወርቅ ጥሩ ሰላዮች ነበሯቸው … የኢጣሊያ ወታደሮች ደጃዝማች አፈወርቅ ብዙ መትረየሶች እንዳሏቸው ቢናገሩም ብዙ መስሎ የታያቸው በአፈወርቅ አተኳኮስ ምክንያት ነበር።
ከቆራሔ ምሽግ ዙሪያ በአካባቢው የነበሩትን ምሽጎች ሁሉ የተቆጣጠሩት የፋሺስት ወታደሮች እጅግ በጣም ያስቸገራቸውን የቆራሔን ምሽግ በተጠናከረ ኃይል ሰብረው ለመያዝ ተነሱ። ስንቅና ትጥቅ የተሟላለት የፋሺስት ጦር ጭብጦ በሶና ጭላጭ ውሀ ብቻ ከቀረው የደጃዝማች አፈወርቅ ጦር ጋር ተፋጠጠ። ደጃዝማች አፈወርቅ በየወታደሩ መሐል እየዞሩ ‹‹አብረን እንደበላን አብረን እንሙት እንጂ! … አፈወርቅ እጁን ለጠላት አይሰጥም! አንተም የአፈወርቅ ነህና የተቀደሰ እጅህን ላልተቀደሰ ጠላት አትሰጥም …!›› እያሉ ይናገሩ እንደነበር ስቲር ጽፏል።
‹‹… ጥቅምት 23 ቀን ሃያ አውሮፕላኖች እየተመላለሱ ቆራሄን ክፉኛ በቦምብ ደበደቡ። አፈወርቅ በዚህ ሁሉ ጊዜ ብቸኛ አርሊከናቸውን አውሮፕላኖቹ በየሚመጡበት አቅጣጫ በቅልጥፍና እያዟዟሩ ይተኩሳሉ። በዚህ ፍልሚያ ላይ እያሉ በቦምብ ፍንጣሪ እግራቸውን ተመትተው ክፉኛ ቆሰሉ። ቁስላቸው ከባድ ነበር፤ አፈወርቅ ግን ሃሳባቸው ስለ ቁስላቸው ሳይሆን ስለ ቆራሄ ነበር። 220 ኪሎ ሜትር ከሚርቀው ደገሐቡር የቀይ መስቀል የሕክምና ቡድን እንዳለ አፈወርቅ ያውቃሉ። ግን ቁስላቸውን ለመታከም ወደ ደገሐቡር ቢሄዱ ወታደሩ ሁሉ እንደሚከተላቸው ስለሚያውቁ ‹እምቢ› አሉ። አጠገባቸው የነበሩ ወታደሮች ‹እንግዲያውስ ምሽግ ውስጥ ገብተው ከዚያ ይተኙ› ቢሏቸው፤ አፈወርቅ ግን ‹እሰዋለሁ! እንዲህ ያለውን ነገር አላደርገውም። ከዚሁ ሆኜ እታኮሳለሁ!› አሉ። ወደ ግንባሩ ጦሩ አዛዥ ደጃዝማች ነሲቡ መልዕክተኛ ልከው ክፉኛ መቁሰላቸውንና ቆራሄን ግን ሳይሞቱ እንደማይለቁ አስታወቁ። ቢቻል እርዳታም እንዲመጣ ጠየቁ …
… ጥቅምት 24 ቀን ሌሎች አውሮፕላኖች እየተመላለሱ ቆራሄን በቦምብ ሲደበድቡ አፈወርቅም የቆሰለ እግራቸውን እየጎተቱ አርሊከናቸውን ይተኩሱ ነበር። ጥቅምት 25 የቦምብ ድብደባው ተጠናክሮ ቀጠለ። ይህ ሁሉ ሲሆን ጀግናው አፈወርቅ ከተመቱ ጀምሮ በቁስላቸው በኩል ደማቸው ያለማቋረጥ እየፈሰሰ ነበር … አፈወርቅ ጥቂት ቆይተው ደከሙ። አርሊከናቸው ላይም ድፍት አሉ። እጆቻቸው ዝለው መሬት ላይ ወደቁ። አፈወርቅ አርሊከናቸው ላይ ድፍት ብለው የዛሉ እጆቻቸው መሬት ሲነኩ፤ በቁስላቸው በኩል ሲፈስ የነበረው ደም ቆመ›› በማለት ጆርጅ ስቲር ስለ ጀግናው ደጃዝማች አፈወርቅ አሟሟት ተርኳል።
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2014