አሸባሪው ህወሓት በፍጥረቱ ከስህተቱ ከመማር ይልቅ በስህተቱ የትግራይን ህዝብ ዋጋ እያስከፈለ ዘመኑን ማርዘም የቻለና አሁንም በዚሁ መንገድ ዘመኑን ለማርዘም እየተፍጨረጨረ ያለ ቡድን ነው። ስህተቶቹን በአግባቡ ተመልክቶ ማረም የሚችልበት አጋጣሚዎችና ሁኔታዎች በተመቻቹለት ወቅት ሳይቀር በስህተቶቹ ከመኮፈስ ባለፈ ለመታረም ፍላጎት የሌለው ፍጹም አምባገነን ስብስብ ነው።
ገና ከምስረታው ከትግራይ ህዝብ ማህበራዊ ስነ ልቦና ባፈነገጠ መልኩ የቀረጸው የትግራይ ማኒፌስቶ ከትግሉ ወቅት ማግስት ጀምሮ ለብዙ የትግራይ ልጆች የሴራ ሞት ምክንያት የሆነ ነበር።ይህን ፍጹም ኢትዮጵያ ጠል እና ለትግራይ ህዝብ አዲስ ማንነት ለመፍጠር የተቀረጸ ማኒፌስቶ በመቃወማቸውም ብዙዎች በግልጽም በስውርም ለህልፈት ተዳርገዋል።
ለትግል ወደ በረሀ በገባው የትግራይ ወጣት ግድያ ላይ መሰረቱን የጣለው የሽብር ቡድኑ ህልውና ላለፉት 50 ዓመታት የብዙ የትግራይ ወጣቶችን ፤ ከዛም አልፎ የብዙ ኢትዮጵያውያንን ህይወት ነጥቋል። ዛሬም ተፈጥሯዊ ሞቱን ላለመሞት በሚያደርገው የደመነፍስ መወራጨት የትግራይን ህዝብ እያስከፈለ ያለው ዋጋ ማሰብ ለሚችል ጤነኛ አእምሮ አስጨናቂም ፤ አሳፋሪም ነው።
ቡድኑ ገና ከጅምሩ በሕዝቦች መካከል በሚፈጠር አለመተማመን ላይ ሕልውናውን ለማጽናት በማኒፌስቶው ጭምር ለትግራይ ህዝብ ጠላት በመፍጠር ፣ ጠላት አድርጎ ለፈረጀው ህዝብ የተለያዩ ትርክቶችን በመፍጠር ጠላትነቱ ስጋና ደም እንዲለብስ አድርጓል። በተለይም አዲሱ ትውልድ የትርክቶቹ ሰለባ እንዲሆን ያለ መታከት ሰርቷል፤ ዛሬም እየሰራ ነው።
ከዚህም ባለፈ በሀገሪቱ ለዘመናት ተከባብረውና ተቻችለው በፍቅር በሚኖሩ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች መካከል አለመተማመንና ጥርጣሬን በመዝራት ፤የተከፋፈለች ሀገር ለመፍጠር በስልጣን ላይ በነበረባቸው 27 ዓመታት በተደራጀና በታቀደ መልኩ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። ይህ ሴራው እንዳሰበው ዕድሜውን በፈለገው መልኩ ባያረዝምለትም ሀገርን ያስከፈለው ዋጋ ግን ከፍያለ ነው።
ሕልውናውን ለማስቀጠል በፍጥረት ዘመኑ ሁሉ ሴራና የሴራ ትብታቦችን ትምክህቱ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው ይህ አሸባሪ ቡድን ፤ ዛሬም ከዚህ የውልደት ርግማኑ መውጣት ባለመቻሉ ችግሩ ወደ ትግራይ ህዝብ እየተጋባ ፤ የትግራይ ህዝብ የእርግማኑ ዋነኘ ገፈት ቀማሽ እየሆነ ነው ። በቀደመው ዘመን በነጻነትና በዴሞክራሲ ስም ልጆቹን /ተስፋዎቹን/ በተጨባጭ ተስፋ አልባ ለሆነ ትግል እንደገበረ ሁሉ ፤ዛሬም በግልጽ በፉከራ ለታጀበ ፤ ሲኦልን በሚያስናፍቅ ሀገር የማፍረስ የከፋ ርግማን ልጆቹን እየገበረ ይገኛል።
በብዙ ወከባ በተፈጠረ ግራ መጋባት፤ ግራ መጋባቱ በፈጠረው ስህተት ፤ ስህተቱ በፈጠረው የአስተሳሰብ ዝንፈት የትግራይ ወጣቶች ውድ የሆነውን ህይወታቸውን በተጨባጭ እንጥፍጣፊ ህዝባዊነት ለሌለው ፣ የአምባገነኖችና የዘራፊዎች ስብስብ ለሆነው ለዚሁ አሸባሪ ቡድን ፍጹም በሆነ ግዴለሽነት እየገበሩ ነው።
ቡድኑ ከውልደቱ ጀምሮ በክልሉ የሀገር ሽማግሌዎችም ሆኑ ተደማጭ ግለሰቦች በራሳቸው ነጻ ህሊና በህዝቡ ውስጥ ተሰሚነት እያገኙ እንዳይሄዱ ከሰራቸው ከፍ ያለ ሴራ የተነሳ ይህንን ማህበራዊ አቅም በማምከኑ አዲሱ ትውልድ ከቡድኑ የሴራ ድምጽ ውጪ እንዳይሰማና እንዳይታዘዝ ሆኗል።
ከዚያም በላይ አዲሱ ትውልድ ስለ ሀገሩና ስለራሱም የጠራ ግንዛቤ እንዳይኖረውና እንደ ትውልድ የአባቶቹ ቀጣይ ትውልድ እንዳይሆን ፤ ከዚህ ይልቅ ቡድኑ የፈጠረለትን የተዛባ ማንነት ተሸክሞ ለቡድኑ ህልውና በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ራስን መስዋዕት አድርጎ እንዲያዘጋጅ አድርጎታል።
ይህ ሁሉ የአሸባሪው ህወሓት ትውልድ ተሻጋሪ ሴራ እስካሁን የትግራይን ህዝብ ሆነ በአጠቃላይ የኢትዮጵያን ህዝብ የቱን ያህል ከፍያለ ዋጋ እንዳስከፈለ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ይህ የቡድኑ ሴራ ዛሬ ላይ አድጎ ስለህልውናው ሲል ሀገር እስከ ማፍረስ ደረጃ በሚደርስ እኩይ ተግባር እስከመሰማራት ደርሷል።ይህ ደግሞ ከኢትዮጵያውያን ዘመናት ካስቆጠረ የሀገር ፍቅር መንፈስ አንጻር የቡድኑን ኢትዮጵያዊነት በብዙ መልኩ አጠያያቂ አድርጎታል።
ይህ ቡድን ትናንት በነጻነትና በዴሞክራሲ ስም ዛሬ ደግሞ በትግራይ ህዝብ / ህልውና ስም ተፈጥሯዊ ሞቱን ለመቀልበስ ሀገርን እስከ ማፍረስ የዘለቀ ሴራ ውስጥ ገብቷል። ሴራው በአሁኑ ወቅት ከማንም ይልቅ የትግራይን ሕዝብ በብዙ መልኩ እየጎዳ እንደሆነም የትግራይ ሕዝብ የትናንት ሆነ የዛሬ ህይወት በተጨባጭ የሚመሰክረው ሀቅ ነው ።
የትግራይ ህዝብ ትናንት ልጆቹን ገብሮ ልጆቹንም ሆነ በልጆቹ ተስፋ ያደረገውን ህይወት አጥቷል። ዛሬም ቡድኑ ከትናንት በከፋ ሴራ ሀገር ለማፍረስ በሚያደርገው የተስፋ መቁረጥ መቅበዝበዝ ልጆቹን በመገበር የሚያተርፈው አንዳች ነገር አይኖርም ። ይህ ደግሞ ነገ የታሪክ ተጠያቂ ማድረጉ ስለማይቀር የትግራይ ህዝብ ልጆቼን ለአሸባሪዎች ዕድሜ መቀጠያ አላደርግም ሊል ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 10/2014