በኢትዮጵያ እጅግ ተዘውታሪ ከሆኑ ስፖርቶች መካከል የቴኳንዶ ስፖርቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በተለይ ታዳጊና ወጣቶች በእነዚህ ስፖርቶች የሚካፈሉ ሲሆን፤ በየአካባቢውም በርካታ የማሰልጠኛ ማዕከላት ይገኛሉ፡፡ በሀገር አቀፍ የስፖርት አካዳሚዎችና በክልል ፕሮጀክቶችም ውስጥ በተመሳሳይ ታዳጊዎች ከሚሰለጥኑባቸው ስፖርቶች መካከል ይመደባል፡፡
ክረምት ወቅት ደግሞ በልዩ ሁኔታ ወጣቶች ጊዜያቸውን ለማሳለፍ የሚመርጧቸው ስፖርቶች ናቸው። የተዘውታሪነታቸውን ያህል እንደ አትሌትክስ ውጤት ባይመዘገብባቸውና እንደ እግር ኳስም ከፍተኛ ትኩረት አይሰጣቸው እንጂ የተሳታፊዎቹ ቁጥር ግን በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም፡፡
በየአካባቢው በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ከሚሳተፉባቸው የቴኳንዶ ስፖርቶች መካከልም አንዱ ወርልድ ቴኳንዶ ነው፡፡ ተወዳጅ የሆነው ይህ ስፖርት የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚን ጨምሮ በተለያዩ የስፖርት ማሰልጠኛ ማዕከላት ውስጥ ስልጠና የሚሰጥበት ሲሆን፤ በሀገር ውድድሮች ሲዘጋጁ በዓለም አቀፍ ውድድሮችም ተሳትፎ ይደረጋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች እንዲሁም በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች በሚካሄዱ ቻምፒዮናዎች ውጤት መመዝገብ ተችሏል፡፡
በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜም በቅርቡ በተካሄደው የቶኪዮ ኦሊምፒክ በዚህ ስፖርት ተሳትፎ መደረጉ የሚታወስ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ፍሬ በሆነው ሰለሞን ቱፋ ብቸኛ ወካይነት በተደረገው ተሳትፎም በስፖርቱ ያለው ተስፋ በግልጽ ተንጸባርቋል። ሰለሞን በጉዳት ምክንያት ሜዳሊያ ማስመዝገብ ባይችልም ዲፕሎማ በማግኘት በታሪክ የመጀመሪያው ስፖርተኛ ሆኗል፡፡ ይህም በርካታ ታዳጊና ወጣት የስፖርቱ ተዋናዮችን የሚያነቃቃና ለወደፊትም ውጤታማ ለመሆን የሚቻልበትን መንገድ የቀየሰ ነው ሊባል ይችላል፡፡
ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን የባለሙያችን አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ስልጠና አዘጋጅቷል፡፡ ስልጠናው የተዘጋጀውም ፌዴሬሽኑ ከዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ሲሆን፤ የቴኳንዶ ፑምሴ አርት እና የስፕሪንግ ዳኝነት ስልጠና መሆኑን ከኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ይጠቁማል። በዚህ ስልጠና ላይም የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠና ሲሰጥ፤ ከተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ተመርጠው የተውጣጡ 100 ሰልጣኞች ተሳታፊ ይሆናሉ፡፡
ስልጠናውን የሚሰጡት ባለሙያዎችም በስፖርቱ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሱና ዓለም አቀፍ ዕውቅና ያላቸው የውጪ ዜጋ እንዲሁም ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡ የውጪ ዜጋው ግራንድ ማስተር ዳኒል ቫሄ ሲሰኙ በስፖርቱ ሰባተኛ ዳን መድረስ የቻሉ ናቸው፡፡ የወርልድ ቴኳንዶ የአሰልጣኞች አሰልጣኝ የሆኑት ባለሙያው በቶኪዮ ኦሊምፒክ በዳኝነትተሳትፎ ነበራቸው። በስፖርቱ የፑምሴ አሰልጣኝ እና ፑምሴ ዳኛ ከመሆናቸው ባለፈ በዳኝነቱ የዓለም ምርጡና አንደኛ ደረጃ ላይ የደረሱ መሆናቸውንም ፌዴሬሽኑ አሳውቋል፡፡
ኢትዮጵያዊው አሰልጣኝ ደግሞ ስድስተኛ ዳን ላይ የደረሱት ግራንድ ማስተር አዲስ ኡርጌሳ ሲሆኑ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ሀገሩን የወከለው የወርልድ ቴኳንዶ ስፖርተኛ የሰለሞን ቱፋ አሰልጣኝ መሆናቸው ይታወቃል። ግራንድ ማስተር አዲስ በወርልድ ቴኳንዶ የአሰልጣኞች አሰልጣኝ፣ በዓለም አቀፉ ፌዴሬሽን የቴክኒክ አባል እንዲሁም የስፓሪንግ አሰልጣኝና ዳኛ ናቸው፡፡
ፌዴሬሽኑ በበጀት ዓመቱ ሊሰራ ካቀዳቸው ስራዎች መካከል የባለሙያዎችን አቅም መገንባት አንደኛው ሲሆን፤ ይህንን መነሻ በማድረግም በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነውን ዓለም አቀፍ ስልጠና ከውጭ ሀገር በመጡ ከፍተኛ የስልጠና ባለሙያዎች እየሰጠ ይገኛል፡፡ የስልጠናው ተካፋዮችም ትጥቅና ሌሎች ወጪዎችን በራሳቸው ሸፍነው እየሰለጠኑ መሆናቸውም ታውቋል፡፡ ስልጠናው በላፍቶ ሞል እና በ4 ኪሎ ስፖርት ትምህርት ስልጠና ጂምናዚየም ከጥቅምት 5-13/2014 ዓ.ም ድረስ የሚሰጥ መሆኑም ታውቋል፡፡
ይህ ስፖርት የአብዛኛዎቹ የማርሻል አርት ስፖርቶች ምንጭ በሆነችው ኮሪያ መነሻውን ያደረገ ሲሆን፤ ሰዎችን ከአካላዊ እንቅስቃሴው ባሻገር መልካም ስብዕና እንዲላበሱ ያደርጋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማህበር እአአ በ1973 ሲቋቋም በዚህ ወቅት 208 አባል ሀገራትን በስሩ ይይዛል፡፡ የኦሊምፒክ ስፖርት የሆነው ወርልድ ቴኳንዶ እአአ ከ2ሺ ጀምሮ ኮሚቴውን በመቀላቀል ውድድር እየተደረገበት ይገኛል፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2014