ማርከስ ጋርቬይ ጃማይካዊ የፖለቲካ ተሟጋች፣ ጋዜጠኛና የተዋጣለት ተናጋሪ የነበረ የጥቁር መብት ታጋይ ነው። እ.አ.አ. ነሐሴ 17 ቀን 1887 ዓ.ም ተወልዶ በ1940 በ53 ዓመቱ ይህችን ዓለም ተሰናብቷል፡፡ ጋርቬይ ኮቴው ሳይሰማ መጥቶ የሄደ ሰው አይደለም። በየትኛውም አህጉር የሚገኙ ጥቁሮች በቀለማቸው ኮርተውና ከነጮች እኩል ታይተው ሲኖሩ ማየትን ይናፍቅ ነበር፡፡ ይህን ህልሙን ለማሳካት Universal Negro Improvement Association (UNIA) የተባለ ማህበር መስርቷል፡፡
ጥቁሩ ማኅበረሰብ ከነጭ አገዛዝ ነጻ ይወጣ ዘንድ ለራሱ መስራትን ማወቅና ኅብረቱን አጠንክሮ መፍጠን እንዳለበት አመልክቷል፡፡ ያን ጊዜ ጥቁሩ ማኅበረሰብ በራሱ የሚተማመንና ራሱንም ችሎ የሚያድር ይሆናል ብሎ ያምንም ነበር፡፡ የማህበሩ አባላት በባለቤትነት የሚያስተዳድሯቸው ምግብ ቤቶች፣ የንጽህና አገልግሎት መስጫዎች ፣ ፋብሪካዎችና የኅብረት ባንክ እንዲያቋቁሙ አድርጓል፡፡
ጋርቬይ “በኢኮኖሚ ጠንካራ መሰረት ከሌለን በቀላሉ በነጮች እግር ስር እንወድቃለን” ብሎ ስለሚያምን እ.ኤ.አ በ1919 UNIA በተባለው ማህበሩ አማካኝነት “Black Star Line” በሚል መጠሪያ መርከብ የሚያመርት ኩባንያ አቋቁሟል፡፡ ይህ ኩባንያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሶስት መርከቦች ባለቤት መሆን ችሏል፡፡ እነዚህ የድርጅቱ የንግድ መርከቦች በጥቁር ካፒቴንና የመርከብ ሰራተኞች እንዲዛወሩ አደርጓል። ኩባንያው ከፍተኛ ትርፍ በማስመዝገቡ በሂደት በርካታ ጥቁሮች የማህበሩ አባል እንዲሆኑና ራሳቸውን ከድህነት እንዲያወጡ አስችሏቸዋል፡፡
የጋርቬይ ዋነኛ የንግግር ርዕሰ ጉዳይ ጥቁሩ ማኅበረሰብ በባህሉ፣ በቀለሙና በቋንቋው ሊኮራ ይገባል ከሚል እምነቱ የሚቀዳው፣ በጥቁርነት መኩራት (Black Pride) የሚል ነበር፡፡ የተለያዩ ጋዜጦችን በማሳተም ለጥቁሮች ጭቆናና መከራ ድምጽ በመሆን ሰቆቃቸው እንዲያባራ ታግሏል፡፡
በአያሌ መድረኮች ላይ “ነጻነቷን ጠብቃ የምትኖር ብቸኛዋ የጥቁር አገር” እያለ የኢትዮጵያን ስም ደጋግሞ ጠቅሷል፡፡ ኢትዮጵያ በጣሊያን ስትወረር በለንደን ሶስት ታላላቅ ኮንፍረንሶችን በማዘጋጀት በወቅቱ የብዙዎችን ትኩረት የሳበና ጥቁሮች የሚያደርጉት የነጻነት ትግል እንዲጋጋል ያደረገ ንግግር አድርጓል፡፡
ከአስርት ዓመታት በፊት ስለነጻነቷ የመሰከረላትና ወረራ ሲፈጸምባት የተሟገተላት ኢትዮጵያ መንፈሱን ተላብሳ ለዛሬዎቹ የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎች እምቢኝ እያለች ባለችበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ታጋዩ ጋርቬይ ብዙ ተጠቃሽ ንግግሮች ያሉት፣ በዘመናት የማይደበዝዝ አንጸባራቂ ኮከብ ነው፡፡ ከእነዚህ ንግግሮቹ ጥቂቶቹን ወስጄ ኢትዮጵያን ከከበባት አሁናዊ ሁኔታ እና እየሰጠች ካለችው ምላሽ ጋር በማሰናሰል ልመለከታቸው ወድጃለሁ፡፡
ፕሮፖጋንዳ
“Among some of the organized methods used to control the world is the thing known and called PROPAGANDA. Propaganda has done more to defeat the good intentions of races and nations than even open warfare. Propaganda is a method or medium used by organized peoples to convert others against their will. We of the Negro race are suffering more than any other race in the world from propaganda… propaganda to destroy our hopes, our ambitions and our confidence in self.”
ይህ የጋርቬይ ንግግር ምዕራባውያኑ ዒላማቸው ውስጥ ያስገቡትን አካል በቁጥጥራቸው ስር ለማስገባት አስቀድመው በተደራጀ መንገድ ፕሮፓጋንዳቸውን እንደሚነዙ ይገልጻል፡፡ በዚህም ጦርነት መክፈት ሳያስፈልጋቸው ብዙ ጉዳት ማድረስና ብዙዎችን ከመስመራቸው ማስወጣት እንደሚችሉ በፕሮፖጋንዳ የጥቁሮችን ተስፋ፣ ምኞትና በራስ የመተማመን ስሜት ለማጥፋት የሄዱበትን ርቀትና የተከፈለውን ዋጋ በመጥቀስ ያስረዳል፡፡
ምዕራባውያኑ ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያሉትም ይሄንኑ ነው፡፡ ሲ ኤን ኤን ፣ ሮይተርስ ፣ ኒውዮርክ ታይምስ ፣ አሶሼትድ ፕረስ ፣ ዋሽንግተን ፖስት ፣ ቢቢሲ እና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ሙያዊ መርህን ባልተከተሉ ሀሰተኛ ዘገባዎች የኢትዮጵያን እውነት አዛብተው ለዓለም ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት እንኳን ሲ ኤን ኤን “የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጦር መሳሪያዎችን ወደ ጎረቤት አገር ኤርትራ አጓጉዟል” ሲል መሰረተ ቢስ ክስ በማቅረብ የአየር መንገዱን ስም ለማጠልሸት ትልቅ ቋጥኝ ፈንቅሏል፡፡
አምንስቲ ኢንተርናሽናል፣ ዩ ኤስ ኤይድ እና የተመድ ድርጅቶች አሁንም ኢትዮጵያን በተመለከተ አድሏዊ ሪፖርቶችን እያወጡ ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በቅርቡ ከአልጀዚራ ጋር ባደረጉት ቆይታ አሸባሪውን ቡድን “ጠንካራ ተዋጊ ነው የኢትዮጵያ መንግስት ሊያሸንፈው አይችልም” ሲሉ በማሞካሸት ከድርጅታቸው መርህ ጋር የሚጣረስ አስተያየት እስከመስጠት መድረሳቸው ይታወሳል፡፡ ጉተሬዝ ይህን መሰል አስተያየት ሰጥተው ሲያበቁ፣ በያዝነው ሳምንት የዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) የኢትዮጵያ ኃላፊ ማውሪን አቻንግን እና የሥነ ሕዝብ ጽህፈት ቤት ኃላፊዋ ዴኒያ ጌይልን “የድርጅቱን እሴቶች የማያንጸባርቅ” አስተያየት ሰጥታችኋል በሚል ኒውዮርክ ወደ ሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ተጠርተው አስተዳደራዊ እረፍት እንዲወስዱ አድርገዋል፡፡
ሁለቱ ኃላፊዎች ከኢትዮጵያ የተጠሩት ተመድ ከሽብርተኛው ቡድን ህወሓት ጋር ባለው ግንኙነት ተቋማዊ አድሏዊነትን መከተሉን በግልፅ በመናገራቸው፤ አሸባሪውን ቡድን ቆሻሻ እና ጨካኝ ብለው በመግለጻቸው እና የተመድ የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪዎች አዲስ አበባ የሚገኙ ከፍተኛ የተመድ ኃላፊዎችን በማግለል በድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት ካሉ ኃላፊዎች ጋር በቀጥታ ይገናኛሉ ብለው በመናገራቸው ነው፡፡
የምዕራቡ ዓለም የዜና ምንጮችና በሰብዓዊነት ስም ፖለቲካዊ አጀንዳዎችን ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ የእርዳታ ድርጅቶች ተናበው በተደራጀ መንገድ በሰሩት ፕሮፓጋንዳ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድረው መቃብር አፋፍ ላይ የነበረው አሸባሪው ህወሓት አፈር ልሶ ተነስቶ በአፋርና አማራ ክልሎች ላይ ወረራ በመፈጸም የበርካታ ንጹሐንን ህይወት እንዲቀጥፍ፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እንዲያፈናቅልና መሰረተ ልማቶችን እንዲያወድም አድርገዋል፡፡
አሁን ግን ኢትዮጵያ ነቅታለች፡፡ ልክ እንደ ጋርቬይ የምዕራባውያኑ ፍላጎት ምን እንደ ሆነ ተረድታለች፡፡ እነማን ጀርባቸውን ሰጥተዋት ከጀርባዋ እንደሚወጓትና እነማን በክፉ ጊዜዋ ከጎኗ እንደቆሙ ለይታለች፡፡ እየተደረገባት ባለው ፈርጀ ብዙ ጫና ሳትንበረከክ እውነቷን ለዓለም እያስረዳች፣ በወዳጆቿ ታጅባ የፕሮፖጋንዳውን ወጀብ እየቀዘፈች ከበሽታዋ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመገላገል ወደፊት እየተጓዘች ትገኛለች፡፡
ማዕቀብ
“Some of us seem to accept the fatalist position, the fatalist attitude, that God accorded to us a certain position and condition, and therefore there is no need trying to be otherwise. The moment you accept such an attitude, the moment you accept such an opinion, the moment you harbor such an idea, you hurl an insult at the great God who created you, because you question Him for His love, you question Him for His mercy.”
“ጋርቬይ በዚህ ንግግሩ አንዳንዶቻችን ያለንበትን ሁኔታ እድል ፋንታችን አድርገን በመቀበላችን፣ ዕድሌ ነው ብለን የምናስብ በመሆናችን እና እግዚአብሔር ከአንድ ቦታና ሁኔታ ጋር አስማምቶናል ብለን በማመናችን ሁኔታውን ለመቀየር መሞከር አለመፈለጋችንን ይነግረናል፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አመለካከት፣ አስተያየትና ሀሳብ በተቀበልንበት ቅጽበት ፍቅሩን እና ምህረቱን ጥያቄ ውስጥ በመክተታችን በፈጠረን አምላክ ላይ ስድብ እንዳወረድንበት ይቆጠራል ሲልም ያትታል፡፡”
ድህነትን ዕጣ ፈንታችን ነው ብለን ከተቀበልን ከስንዴ ልመና ልንላቀቅ አንችልም፡፡ አሁን አደጉ የምንላቸው አገራት በአንድ ወቅት ድሆች ነበሩ። በሂደት ዜጎቻቸውን ማበልፀግ በመቻላቸው ሀብታም አገራት ለመሆን በቅተዋል። በዓለም ባንክ መለኪያ መሰረት በቀን ከአንድ ነጥብ ዘጠኝ ዶላር በታች የሚያገኝ ሰው ድሃ ነው። በ1982 ዓ.ም ከተጠቀሰው ገንዘብ በታች ዕለታዊ ገቢ የነበራቸው ሰዎች ቁጥር 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ነበር፡፡
ይህ ቁጥር 2007 ዓ.ም ወደ 735 ሚሊዮን ዝቅ ብሏል። ይህም ድህነት ዕጣ ፋንታ አለመሆኑን ያመለክታል፡፡ አገራት በርትተው ከሰሩ ድህነትን ታሪክ ማድረግ ይችላሉ፡፡ በ2007 ዓ.ም የተደረገ ጥናት ግማሽ ያህሉ የዓለማችን ድሆች በሕንድ፣ ናይጄሪያ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ፣ ባንግላዴሽ እና ኢትዮጵያ እንደሚኖሩ ያሳያል። ከእነዚህ አገራት መካከል ህንድ በአጭር ጊዜ ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የድሆች ዜጎቿን ቁጥር መቀነስ ችላለች፡፡
አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ቀዳሚ አጀንዳው ልመናን ማስቀረት መሆኑን ገልጿል፡፡ ኢትዮጵያ ጠንክራ ሰርታ በምግብ ራሷን ከቻለችና የዜጎቿን ህይወት ትርጉም ባለው ደረጃ ካሻሻለች ከምዕራባውያኑ እግር ስር የምትገኝበት ምክንያት አይኖሩም፡፡ አሜሪካና አጋፋሪዎቿ ጠዋት ማታ ማስፈራሪያ የሚያደርጉት ማዕቀብ ጉልህ ጉዳት አያደርስባትም፡፡
ድል ማድረግ
“ If you haven’t confidence in self, you are twice defeated in the race of life. With confidence, you have won even before you have started.”
“ይህ የጋርቬይ ንግግር ተሸናፊ ማንነት በመያዝ ቀድመን እጅ የምንሰጥ ከሆነ በተግባርም ከመሸነፍ ውጭ ሌላ ዕድል እንደሌለን፤ በራሳችን የምንተማመን ከሆነ ግን ትንቅንቁን ከመጀመራችን በፊትም አሸናፊዎች እንደሆንንና ትግላችንን ድል እንደሚከተለው” ይገልጻል፡፡
በፕሮፖጋንዳው ሜዳ በሚደረግብን ዘመቻና በማዕቀብ ማስፈራሪያ በሥነ ልቦና የምንሸነፍ ከሆነ በዲፕሎማሲውም ሆነ በጦር ሜዳው ተሸናፊዎች እንሆናለን፡፡ አዕምሯችን ቀድሞ ከተሸነፈ በቁጥጥሩ ስር ያለው አካላችን አሸናፊ ሊሆን አይችልም፡፡ ጋርቬይ “የሰዎችን አዕምሮ ነጻ ካወጣን በመጨረሻም አካላቸውን ነጻ እናወጣለን፡፡” ይላል፡፡
እኛ ቅኝ ገዢዎችን ድል በመንሳት የባርነት ቀምበር ተጭኗቸው ለነበሩት መላ አፍሪካውያን ብርሃን የፈነጠቁት የአባቶቻችን እና የእናቶቻችን ልጆች ነን። ጋርቬይ “መነሻቸውን፣ ባህላቸውን እና የቀደመ ታሪካቸውን የማያውቁ ሕዝቦች ስር እንደሌለው ዛፍ ናቸው፡፡”ብሏል፡፡ እውነት ነው፡፡ ሥራችን ሌላ አይነት ፍሬ እንድናፈራ አይፈቅድልንም፡፡
ኢትዮጵያ ከሰሞኑ ለአሸባሪው ህወሓት በመወገን ብሔራዊ ደኅንነቴ ላይ ስጋት ደቅነዋል ያለቻቸውን የተመድ ሰባት ኃላፊዎች ከአገር እንዲወጡ ማድረጓ በሉዓላዊነቷ የማትደራደርና በራሷ የምትተማመን አይበገሬ አገር መሆኗን የሚያረጋግጥ ተገቢ እርምጃ ነው።
ጋርቬይ “አሁን አንተ ልትጠፋ የምትችለው በራስህ እንጂ ከውስጥ ወይም ከውጭ አይደለም፡፡ ድል የምታደርገውም ሆነ የምትሸነፈው በራስህ ብቻ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰሃል” ይላል፡፡ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከመንግሥታችን ጎን እስከቆምን ድረስ ድላችን በእጃችን ነው፡፡ የምንሸነፈው አንድ መሆን ካልቻልን ብቻ ነው፡፡
ዛሬ ኢትዮጵያ የጋርቬይ መንፈስ ሰፍሮባታል። የጥቁሮች መብት ታጋዩ ከመቶ ዓመታት በፊት “አፍሪካ ለአፍሪካውያን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ!” ሲል የተናገረውን ኃይለ ቃል መርሆ አድርጋለች፡፡ በዓለም አቀፍ መድረኮች በምታቀነቅነው “ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” የሚል ጠንካራ አቋም ምዕራባውያኑ እጃቸውን እንዲሰበስቡ በማድረግ አፍሪካውያን ለአፍሪካውያን እንዲቆሙ እያደረገች ነው፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ከአሜሪካና የፀጥታው ምክር ቤት መዳፍ ወጥቶ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ብቻ እንዲካሄድ አድርጋለች፡፡ በርካታ የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ አሸባሪውን ቡድን ለማስወገድ እየወሰደች ያለችው እርምጃ የአንድ አገር ውስጣዊ ጉዳይ መሆኑን በመግለጽ ከምዕራባውያኑ በተቃራኒ አቅጣጫ በመቆም ድጋፋቸውን ችረዋታል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በዓለ ሲመት ላይ የተገኙት የአፍሪካ አገራት መሪዎች ባደረጓቸው ንግግሮች ከኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጎን መቆማቸውን የገለጹበት መንገድ ይህን የሚያረጋግጥ ነው፡፡
ከጋርቬይ ንግግሮች አንዱ እንዲህ ይላል “በትጋት ላይ ያሉ ሰዎች የሚመጣው ውጤት አያስፈራቸውም።” አዎ፡፡ ኢትዮጵያ በትጋት የቤት ሥራዋን ከሰራች በመጪው ጊዜ የሚመጣው ውጤት አያሳስባትም፡፡
የትናየት ፈሩ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2014