ለወላጆቻቸው የመጀመሪያ ልጅ ናቸው። ወላጅ አባታቸው በ1969ኙ የሶማሌ ጦርነት በመሞታቸው የተወለዱት ሐረር ቢሆንም ያደጉት ኩባ ነው። ለመጀመሪያ ጊዜ ሥራ የጀመሩት አፋር ክልል ሲሆን የሰሜን ምስራቅ የእንስሳት ሀብት ልማት ፕሮጀክት ውስጥ የእንስሳት ጤና ዘርፍ ኃላፊ ሆነው ነው።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ካደረጋቸው የሕዝብ ውክልና ተነስተው በሦስት የፌዴራል መንግስት ተቋማት ተሿሚ ሆነው በሚኒስትር ዴኤታነት አገልግለዋል። ወደ አመራርነት ሲመጡ የገጠሟቸውን ተደራራቢ ኃላፊነቶችን በመወጣት ለመንግስት ሠራተኛው ፐብሊክ ሰርቪስ እንዲመደብ ከማድረግ ጀምሮ በየተቋማቱ በርካታ ስኬቶችን አስመዝግበዋል። ዶክተር ምስራቅ መኮንን ዛሬ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዋና ፀሐፊነት ተመድበው እየሰሩ ይገኛሉ።
እሳቸው እንደነገሩን የመጀመሪያ ትምህርታቸውን የተማሩት ከስድስተኛ ክፍል ጀምሮ የሁለተኛና የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም ኩባ ውስጥ ነው። በመሆኑም ከአምስተኛ ወደ ስድስተኛ ክፍል ሲያልፉ የኪዩባ መንግስት ነፃ የትምህርት ዕድል ሰጣቸው። እናም በ12 ዓመታቸው ቤተሰቦቻቸውን ተለይተው ወደ ኪዩባ ለመሄድ ተገደዱ። ወደ ኪዩባ ሲያቀኑ ከቤት ትምህርት ቤት፤ ከትምህርት ቤት ወደ መኖሪያ ቤት ከመሄድ ውጪ አካባቢያቸውንና ሀገራቸውን እንኳን በውል አያውቁም ነበር። በዛን ጊዜ ቤተሰባቸውን ጥለው ሲሄዱ ታናናሽ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ገሚሶቹ ሰፍር ለሰፈር ድክ ድክ የሚሉ፤ ግማሾቹ ደግሞ በእዝል ያሉ ነበሩ።
በኪዩባ ከስድስተኛ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸው ነበር። ካጠናቀቁ በኋላ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መቀጠል ነበረባቸው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም ከፍተኛ ነጥብ በማምጣታቸው ወደ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት በቁ። የከፍተኛ ትምህርታቸውን በእንስሳት ሕክምና ትምህርት በመከታተልም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ያዙ።
ከ13 ዓመታት የኪዩባ ቆይታ በኋላ እሳቸው በዚህ መልኩ በቀሰሙት ዕውቀት ወደ ሀገሬ ተመልሼ እናቴንና ወንድምና እህቶቼን እንዲሁም ሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቼን አገለግላለሁ የሚል ዕምነት ነበራቸው። ሆኖም ጓደኞቻቸው ያኔ በሀገሪቱ በነበረው ደስ የማይል ሁኔታ ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ፍላጎት አልነበራቸውም። ወደ ኢትዮጵያ ከመመለስ ይልቅ ወደ አውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም ወደ ሌሎች ሀገሮች መሄድ ይመርጡ ነበር። ነገር ግን ይሄ የጓደኞቻቸው ምርጫ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው ሰፊውን አርብቶ አደር ሕብረተሰብ በሙያቸው የማገልገል ፍላጎታቸውን ፈፅሞ አላስቀየራቸውም።
ጓደኞቻቸው ትተዋቸው ወደ አውሮፓና አሜሪካ ሲሄዱ እሳቸው ቢያዝኑም እነሱ ወደ ሄዱባቸው ሀገራት የመሄድ ፍላጎት ፈፅሞ አልነበራቸውም። ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ሰፊውን አርብቶ አደር ሕብረተሰብ በሙያቸው የማገልገል ሀሳባቸውንም አላስለወጣቸውም። በመሆኑም ከ13 ዓመት የኪዩባ ቆይታ በኋላ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ይዘው ወደ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ተመለሱ።
በተመለሱበት ወቅት ትተዋቸው ሲሄዱ ድክ ድክ ይሉና በጀርባ ታዝለው የነበሩት ወንድምና እህቶቻቸው አግብተው፣ ወልደው፣ ትምህርት ጨርሰው ትልልቅ ሆነው ነው የጠበቋቸው።
‹‹መጥቼ ማህላቸው ስቀላቀል ባእድ ሆንኩባቸው›› ሲሉ በልጅነት ከቤተሰብ ተለይቶ ማደግ የሚፈጥረውን ስሜት ይገልፃሉ። እሳቸውም ቢሆኑ እስከ ተወሰነ ጊዜ እህቶቻቸውና ወንድሞቻቸው ይመስሏቸው የነበሩት ኪዩባ አብረዋቸው የነበሩ ጓደኞቻቸው እንጂ እነዚህ በስጋ የሚዛመዷቸው እንዳልነበሩ ይናገራሉ።
በዚህ መካከል የወርልድ ባንክ ፕሮጀክት በሆነውና የሰሜን ምስራቅ እንስሳት ሀብት ልማት በተሰኘው ዓለም አቀፍ ድርጅት ተቀጠሩ።
ለመጀመሪያ ጊዜም ለቀጠራቸው ድርጅት ለመሥራት ወደ አፋር ክልል ሊሄዱ ሲነሱ ወላጅ እናታቸውም ሆኑ የእናታቸው ጎረቤቶችና ሌሎች ዘመድ አዝማዶች በረሃውን አትችይውም በሚል ተቃወሟቸው። በእርግጥ ቀድሞ ስለገጠር አካባቢም ሆነ ስለበረሃ፣ ስለሀገራቸው ኢትዮጵያ ሁኔታም ቢሆን ምንም ዓይነት ዕውቀት አልነበራቸውም። ነገር ግን የተማርኩት እንስሳቶችን ማከም ነው። እንስሳቶቹ ያሉት ደግሞ ገጠር ውስጥ ነውና መሄድ አለብኝ ብለው በመወሰን ወደ አፋር ክልል ሄዱ። የክልሉን ቢሆን ወጉንም ሆነ ባህሉ ያውቁት እንዳልነበረም ይገልፃሉ። ሆኖም በቀላሉ ሊላመዱት መቻላቸውን ያወሳሉ።
‹‹በሕይወቴ ደስተኛ ሆኜ የሰራሁበት አፋር ነው ብዬ አስባለሁ›› ሲሉም ዶክተር ምሥራቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በተማሩበት ሙያ እንዲሰሩ ዕድል የሰጣቸው ቦታ በመሆኑ በእጅጉ ተመችቶና አስደስቷቸው እንደነበርም ይናገራሉ። በተለይ እሳቸው ወደ ሥራው የገቡበት ወቅት የደስታ በሽታ የሚባል ወረርሽኝ ከዓለም ሀገራት በሙሉ ጠፍቶ ኢትዮጵያ ውስጥ አፋርና ሶማሌ ክልሎች ላይ ብቻ የቀረበት ነበር። በመሆኑም በሽታውን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት አፋር ክልል ውስጥ የመጨረሻ ዘመቻ ሲካሄድ ደረሱ። የዘመቻው አካል ሆኑና በታሪካዊው ዘመቻ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ በቁ።
‹‹የዘመቻው አካል በመሆኔ እጅግ ደስተኛ ነበርኩ›› የሚሉት ዶክተር ምሥራቅ ለሁለት ዓመት ተኩል በአፋር ክልል ሲሰሩ መቆየታቸውንም አጫውተውናል።
እንዳወጉን በዚህ ሙያቸው ቀጥሎ ያገለገሉት አማራ ክልል ውስጥ ነው። ክልሉ ያወጣውን እንስሳት ህክምናን ሙያ የተመለከተ ማስታወቂያ አይተው ተወዳደሩ። እንደ አጋጣሚ ሴት ተወዳዳሪ እሳቸው ብቻ ነበሩ። በመሆኑም አወዳዳሪዎቹ ሴት ስለሆነች ቅድሚያ ይሰጣት ቢሉም ከእሳቸው ጋር የሚወዳዳሩት በሙሉ አይቻልም እንደ እኛ ትወዳደር እንጂ በፍፁም ቅድሚያ አይሰጣትም አሉ። ከጅምሩም ቢሆን በብቃታቸው የሚተማመኑትና ‹‹ሴቶች በባሕሪያቸው ተደራራቢ ኃላፊነቶችንም ይዘው መሻገር ይችላሉ›› የሚል ዕምነት ያላቸው ዶክተር ምሥራቅም ከወንዶቹ ጋር እኩል መወዳደር እንጂ በሴትነታቸው ቅድሚያ እንዲሰጣቸው እንደማይፈልጉ ተናገሩ።
እንግዲያው በዕጣ ይሁን ተብሎ ስምምነት ላይ ተደረሰና ዕጣ ሲወጣ ለእሳቸው ደረሳቸው። የደረሳቸው ቦታ ደግሞ በሚያስገርም ሁኔታ ወላጅ እናታቸው የተወለዱበት አማራ ሳይንት የተባለው ቦታ ነበር። የተመደቡበት አካባቢ የእናታቸው እናት (አያታቸው) የሚኖሩበት ነበር።
አያታቸው እሳቸው በሚሰሩበት ቦታ ሲያልፉ ሲያገድሙ ስለሚያይዋቸው ያውቋቸው ነበር። አያታቸው መሆናቸውን ባያውቁም በዚሁ ምክንያት ሰላምታ ሁሉ ነበራቸው። አያትም ቢሆኑ ሰላምታ ይኑራቸው እንጂ የልጃቸው ልጅ ስለመሆናቸው አያውቁም።
ያኔ ስልክ አልነበረም። በመሆኑም ዶክተር ምሥራቅ አያታቸው ያሉበት አካባቢ ተመድበው መሥራት ከጀመሩ በኋላ እናታቸውን የሚያገኝዋቸው ደሴ መጥተው ስልክ ሊደውሉላቸው ከቻሉ ብቻ ነበር። ከጊዜ ብዛት ደሴ መጥተው ለእናታቸው ስልክ በመደወል ዕጣ ደርሷቸው አማራ ሳይንት ውስጥ ተቀጥረው እየሰሩ መሆናቸውን ይነግሯቸዋል።
እናት በበኩላቸው እጅግ በመደሰት የተወለዱበት ቦታ መሆኑንና እናታቸው የሚኖሩትም እዛው መሆኑን ይነግሯቸዋል። የሚኖሩበትን አካባቢ ከእናታቸው ይጠይቁና ሲያፈላልጉ አያታቸው ሰርክ ሲያልፉ ሲያገድሙ የሚያይዋቸው ሴት ሆነው ያገኝዋቸዋል።
ዶክተር ምስራቅ ወደ ፖለቲካው መስክ ለመምጣት መነሻ የሆናቸውን አስመልክተው እንዳጫወቱን አማራ ሳይንት ላይ በእንስሳት ህክምና እየሰሩ የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል ይሆናሉ። አባል የሆኑት ስለፓርቲም ሆነ ስለ ፖለቲካ የቀደመ ዕውቀት ኖሯቸው አልነበረም። በሂደት ብቃታቸውንና በእንስሳቱ ሕክምና ዘርፍ ያላቸውን አበርክቶ ያስተዋሉት የአካባቢው ነዋሪዎች የሕዝብ ተወካይ እንደትሆኝልን እንፈልጋለን ስላሏቸው ብቻ ነበር።
ያም ሆነ ይሄ ያኔም የምክር ቤት አባል ለመሆን የትውልድ አካባቢ አስፈላጊና ወሳኝ ነበርና በእናታቸው የትውልድ ቦታ በአማራ ሳይንት ተመልምለውና ተወክለው ነው የምክር ቤት አባል የሆኑት። ቆየት ብለው በዚሁ ሳቢያ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ሆኑ። ከአማራ ሣይንት ወደ አማራ ክልል ምክር ቤት በሚሄዱበት ወቅት አግብተው መንትያ ልጆች ወልደው ነበር።
የልጆች ያውም ደግሞ የመንቶች እናትነቱን ከአዲሱ የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤነት ኃላፊነት ጋር አጣጥሞ መሄድ ይጠይቅ ነበር። ህፃናቱን ማጥባቱ፣ መንከባከቡ፣ ለህፃናቱ ከጨቅላነታቸው ጀምሮ ነፍስ እያወቁ ሲመጡ የእናትነት ፍቅር መስጠቱና ከአጠገባቸው ላለመራቅ ጥረት ማድረጉ ቀላል አልነበረም። እንደዛሬው የወሊድ ፈቃድ ጊዜ ረጅም አለመሆኑ በተለይ በራሱ ልጆቻቸውን የመንከባከቡን ጉዳይ አክብዶባቸው ነበር።
ኃላፊነቱ የተፈቀደላቸውን ጥቂት የወሊድ ቀናት እንኳን ለመጠቀም ጊዜ የማይሰጥ መሆኑ ክብደቱን አባብሶታል። በቢሮ ውስጥ በተለያዩ የአዲሱ አመራርነት ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን እንጂ ይሄን ታሳቢ አለማድረጉ ጫናውን የበለጠ አጽንቶባቸው እንደነበር ያስታውሳሉ። ቢሆንም በሁለቱም ወገን የነበረባቸውን በፈተና የተሞሉ ተደራራቢ ኃላፊነቶች በጽናት በመወጣት ተሻግረው ዛሬ ላሉበት ደረጃ መድረስ ችለዋል።
በዚህ በኩል የባለቤታቸው እገዛ ከፍተኛ እንደነበር ያስታውሳሉ። እገዛው በውስጣቸው ኃላፊነቶቹን የመወጣቱን የቁርጠኝነት ስንቅ እንዲሰንቁ እንደረዳቸውም ይጠቅሳሉ። በራሳቸው የነበራቸው ጥንካሬና ብቃት ቀላል እንዳልሆነም ይናገራሉ። የባለቤታቸውን እገዛ ፈቃደኛ ሆኖ ለመቀበል ያለው አበርክቶ ከፍተኛ ከመሆኑ ባሻገር ኃላፊነቶቹን በስኬት እንዲወጡ እንዳደረጋቸውም አልሸሸጉንም። ዛሬ ላይ ያፈሯቸውን ሁለቱን መንትያ ልጆቻቸውን በስርዓት ኮትኩቶ፣ አንጾና አስተምሮ በማሳደግ በህክምናው ዘርፍ የራሳቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ዶክተሮች ማድረግ አስችሏቸዋል።
በመሆኑም ይሄን ጥንድ ኃላፊነቶችን ያለፉበትን ወቅት ተሞክሮ ሴቶች በባሕሪያቸው ተደራራቢ ኃላፊነቶችንም ይዘው መሻገር የሚችሉ መሆኑን እንደሚያሳይም ያወሳሉ። በዚህ መልኩ ጥምር ኃላፊነቶቻቸውን መወጣት የቻሉት ዶክተር ምስራቅ እንዳወጉን የአማራ ክልል ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ በመሆን ለአራት ዓመታት አገልግለዋል። የስራ አፈፃፀማቸው አመርቂ በመሆኑና በአማራ ሳይንት በነበራቸው የሕዝብ ውክልና በምርጫ 97 ከክልል ምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤነት ወደ ዋና አፈ ጉባኤነት አደጉ።
እዚህ ቦታ መሥራት እጅግ ከባድ ነበር። ከሰማይ ወፍ የሚያወርዱ በርካታ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት (ያኔ ተቃዋሚ ፓርቲ) የሚባሉት ምክር ቤቱን በ97ቱ ምርጫ አሸንፈው በመቀላቀላቸው መስመር እያስያዙ ጉባኤ መምራት፣ እንደፊቱ ቀላል አልነበረም። የምክር ቤት ስነስርዓቶች የጉባኤ አካሄዶች እንዳይዛነፉ፣ የአባላት መብቶች እንዲጠበቁ፣ የራሳቸው አቀራረብ ጨዋነትና ስነ ስርዓት የተከተለ እንዲሆን ጥንቃቄ መውሰዱ፣ እራሳቸውን ጨምሮ አስፈፃሚዎችም ሆኑ የክልል ፕሬዚዳንቶች ለአንዳንድ ሀሳቦች የሚሰጡት አፀፋ ምላሽ የሰው ስብዕና ወይም የመናገርና ሌሎች መብቶችን የሚነካ፣ የሚጨፈልቅና ከነዚሁ ጉዳዮች ጋር የሚጣረስ እንዳይሆን ማድረጉ ቀላል የአመራርነት ብቃት የሚጠይቅ እንዳልነበር ያስታውሳሉ።
በተለይ በምክር ቤቱ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት አያያዝን አስመልክተው እንደሚያስታውሱት ሀሳባቸው እንዲደመጥ፣ አንዳንዴም የስብሰባውን ዓላማ መስመር እንዲይዝ በማድረግ በኩል በሚወስዱት የራሳቸው እርምጃ ወይም በሚከተሉት አካሄድ ከገዢው ፓርቲም ሆነ ከተፎካካሪ አባላቱ የሚገጥማቸውን ግብግብ መሰል፤ አንዳንዴም ግጭት የሚፈጥር ተግባቦት አስታርቆና አብርዶ ማለፍ ፈታኝም ነበር። በዚህ ሁኔታ በተለይ የተፎካካሪ ፓርቲ ሀሳብ እንዲደመጥ በማድረግ ለአምስት ዓመታት አገልግያለሁ ብለው ያምናሉ።
እንደ ዶክተር ምሥራቅ የክልሉ ምክር ቤት ቋንቋ አማርኛ ቢሆንም በቋንቋችን መናገር አለብን ብለው የሚመጡ የምክር ቤት አባላት በፈለጉት ቋንቋ በመናገር ልምምድ እንዲያደርጉ በማድረግ በኩል ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ዶክተር ምስራቅ ምክር ቤቱ ደረጃውን የጠበቀ መሰብሰቢያ አዳራሽና ቢሮዎች የሚያስችል ስራ ሰርተውም ነው ወደ ፌዴራል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርጠው ለመምጣት የበቁት።
ሁለተኛ ዲግሪያቸውን የሰሩት በሊደርሽፕ በመሆኑ በፌዴራል የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ በመሆን አገልግለዋል። በተቋሙ ከሀብት ጋር የሚያያዙ የሰው ኃይል አሰራርና አደረጃጀቶችን በመምራቱም ያለባቸውን ኃላፊነት ተወጥተዋል።
‹‹በአምስት ዓመት ውስጥ የሠራተኛ ደመወዝ ሁለቴ ጨምረናል። ሆኖም ሠራተኛው አልረካም›› በዚህ ሳቢያ ለመንግስት ሠራተኞች ፐብሊክ ሰርቪስ እንዲመደብ የተደረገው በተቋሙ ኃላፊነቴን ተወጥቼበታለሁ ከሚሉት ዋናው መሆኑን ያስታውሳሉ። የዚህ ሀሳብ አካል በመሆኔም ደስተኛ ነኝ ይላሉ።
እንደእሳቸው ሰርቪሱ የተመደበው በጥናት ጭማሪው የሰራተኛውን ደመወዝ መጨመር ተከትሎ ትራንስፖርት፣ የቤት ኪራይ፣ የግብርና ምርቶች፣ የምግብና ሌሎች ፍጆታዎች መጨመራቸውንና ሠራተኛው ተጠቃሚ ሊሆን አለመቻሉን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንም አውግተውናል። በተለይ ቤት ቀለል ባለ ዋጋ ለማግኘት ከከተማ እስከ መውጣት፣ ቤት በመከራየቱ እየደረሰበት ያለውን እንግልትና የሥራ ሰዓት መባከን በማገናዘብ ነበር። ተመልሰው ዶክተሬት ዲግሪያቸውን ወደ ያዙበት ግብርና ሙያ በመምጣትም በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ጤና ዘርፉን በሚኒስትር ዴኤታነት መርተዋል። እንስሳት ዘርፉ ቁጥር እንጂ ጥራት ኖሮት ያልገባበትን ችግር ለመቅረፍ ሀገራችን የእንስሳት ኳረንቲ ኖሯት ወደ ሳውዲ አረቢያ እንድትልክ አድርገዋል።
ዶክተር ምስራቅ እንዳጫወቱን ከለውጥ በኋላ የመጡት ወደ ተወካዮች ምክር ቤት ነው። ከባልደረቦቻቸው ጋር በመሆንም ጽሕፈት ቤቱ በሚያስፈልገው ለውጥ ዙሪያም አምስት ጥናቶችን አጥንተው ወደ ምክር ቤቱ የለውጥ ሥራ ገቡ። ከዚህ ቀደም የነበረው መዋቅር ጽሕፈት ቤቱን ሊያግዝ በማይችል እጅግ በጠበበ ሁኔታ የተደራጀ እንደነበር ያስታውሳሉ። ዳይሬክተሮቹ ጭምር ተሿሚ ነበሩ። መጀመሪያም ይሄ በሲቪል በመተካት እንዲሻሻል አድርገዋል።
በቀጣይ በምክር ቤቱ ሕግ አወጣጥ፣ ከቁጥጥርና ክትትል፣ ከሕዝብ ውክልና ጋር ባሉ ክፍተቶች ዙሪያ ለመሥራት ታስቧል። ወደፊት በአደረጃጀት፣ በአሰራር፣ የሠራተኛውን አቅም በሚያጠናክር በክህሎት ይሰራል። በ1923 የተሰራ ህንፃ ቅርስነቱን በጠበቀ ሁኔታ የማደስ፣ ውበት እንዲኖረው ምክር ቤቱ የራሱ ሎጎ እንዲኖረው የስብሰባ አዳራሹ ዘመናዊ መሣሪያዎች እንዲገጠሙለት፣ ቤተ መጽሐፍቱና ዶክመንቶቹ ወደ ዲጅታል እንዲሆኑ ጥረት ተደርጓል ብለዋል። እኛም ቀሪ ዘመናቸውም የስኬት፣ የብልፅግና እንዲሁም ህዝብን በቅንነት የሚያገለግሉበት የተሳካ ዘመን እንዲሆንላቸው እየተመኘን ተሰናበትን። ሳምንት በዚሁ አምድ የሌላ እንግዳ የህይወት ተሞክሮ ይዘን እንቀርባለን። ቸር እንሰንበት።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2014