በዓለም አቀፍ ደረጃ የአገራት አቅም እና ህልውና የሚለካው በዋናነት ባላቸው የኢኮኖሚ ጥንካሬ መሆኑ አያከራክርም፡፡ ኢኮኖሚ ሲጠነክር ስራ አጥነት ይቀንሳል። በሽታ ይርቃል፡፡ ድህነት ይጠፋል፡፡ ብልጽግና ይመጣል። በተቃራኒው ኢኮኖሚው ሲዳከም የሕዝብ ህልውናም አብሮ አደጋ ላይ ይወድቃል። ስራ አጥነት ይስፋፋል፡፡ድህነት ይባባሳል፡፡ ስደት ይጧጧፋል፡፡ ረሃብ ይከሰታል። ሰላም ይደፈርሳል፡፡ ነጻነት ይጠፋል፡፡
የበለፀጉ አገራት ለከፍታቸው መነሻ የሆኑ አበይት ምክንያቶችን እንደሚጠቅሱ ሁሉ ኢኮኖሚው ያልሰመ ረላቸውም ለዓመታት ድህነት ውስጥ ለመኖራቸው በርካታ ሰበቦችን ይደረድራሉ፡፡ መልከዓ ምድራዊ አቀማመጣቸው ምቹ አለመሆንና በተፈጥሮ ሃብት አለመታደላቸው ደግሞ ከሰበቦቻቸው መካከል በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡
እንደ ምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ምልከታ ግን እነዚህ አገራት በዕድገት ወደ ኋላ ለመቅረታቸውና ለድህነታቸው በመንስኤነት የሚያቀርቧቸው ምክንያቶች ሚዛን የሚደፉ ሆነው አይገኙም፡፡ በእርግጥ ለግብርና ምቹ በሆነና በበቂ ሁኔታ የተፈጥሮ ሃብት ባለበት አካባቢ የሚኖር ህዝብ ከሌላው የተሻለ የኢኮኖሚ ዕድገት ይኖረዋል፡፡ ይህ ማለት ግን የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ብቻውን ኢኮኖሚን ያሳድጋል ማለትም አይደለም፡፡
‹‹በተፈጥሮ ሀብት መበልፀግ ብቻውን የእድገት ምንጭ ቢሆን ኖሮ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎን የመሳሰሉ አገራት ድሃ ሆነው፣ምንም ዓይነት የተፈጥሮ ሀብት የሌላቸው እንደ እስራኤል ዓይነት ሀገሮች ደግሞ በኢኮኖሚ የላቁ አይሆኑም ነበር›› የሚሉት ምሁራኑ፣ከሁሉ በላይ ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ በተለይም የኢኮኖሚ ዕድገት የተለያዩ ተቋማት የሚፈጥሩት ሁለንተናዊ አቅም ወሳኝ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡
በዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ስመጥር የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት፣ ማርጋሬታ ጂኒክ ሃኑዝ ይሕን እሳቤ ሙሉ በሙሉ ይጋሩታል፡፡ ስለ ተቋማት ሲያስረዱም፣ ‹‹የአንድን አገር ብልፅግና ለመገመት ሌላ ምንም ሳያስፈልግ ተቋማትን ብቻ መመልከት በቂ ነው፣ ‹‹If you want to predict the prosperity of a country, just look at its institutions.›› ይላሉ፡፡
እንደ እርሳቸው ሁሉ ሌሎች ባለሙያዎችም፣‹‹በአሁን ወቅት በኢኮኖሚ የላቁ አገራት የከፍታቸው አብይ ምክንያት ውጤታማና ተጠያቂነት የሰፈነበት ተቋም በመገንባታቸው ነው፣በተለይ ለማደግ የሚታትሩ አፍሪካውያን አገራት ይህን በአግባቡ በመገንዘብ ለተቋማት ፈጠራ ብሎም አቅም መጎልበት ትኩረት መስጠት ቢችሉ በቀላሉ ትሩፋቱን መቋደስ አይቸገሩም ›› ይላሉ፡፡
የኒውዮርክ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚ ፕሮፌሰር ቢሩ ፓካሽ ፖል፣‹‹Why Institutions Are so Important for Growth››በሚል ፅሁፋቸው፣ ለአንድ አገር ሁለንተናዊ እድገት በተለይ የተቋማት አቅም ወሳኝ መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ ለዚህ እሳቤአቸውም እኤአ እስከ 1970ዎቹ ማብቂያ ተመሳሳይ የኢኮኖሚ አቅም ላይ የነበሩት አይቮሪኮስትና ሜክሲኮ በዋቢነት ያቀርባሉ፡፡
ፀኃፊው ሁለቱ አገራት የትላንትናው ገጽታቸው ታሪክ ሆኖ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ የዕድገት ደረጃና ገፅታ ላይ የመገኘታቸው ዋነኛው ምክንያት አፍሪካዊቷ አገር የተቋማት አቅምና ሚና በአግባቡ መረዳት ባለመቻሏ መሆኑን ያመላክታሉ፡፡
በሌላ በኩል አንዳንድ የምጣኔ ሃብት ምሁራን፣ለአገራት ሁለንተናዊ እድገት የተቋማት ሚና ወሳኝ መሆኑን የሚስማሙበት ቢሆንም ከዚህ ባሻገር ግን ከተቋማት መካከልም በይበልጥ ወሳኝ የሆኑ መኖራቸውንና እነርሱን በመለየት ትኩረት አድርጎ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም አፅእኖት ይሰጡታል፡፡
ከዚህ አኳያ በአንድ ሃገር ውስጥ ኢኮኖሚዊ እድገትን ለማስተዋወቅና የሕዝብን ሕይወት በመቀየር ረገድ የፋይናንስ፣ የትምህርት፣የፍትህ ብሎም የህዝብ አስተዳደር ተቋማት ከሌሎች በተሻለ የላቀ ሚና እንዳላቸው ይጠቁማሉ፡፡
በሊዝበን ዩኒቨርሲቲ ተባባሪ ኢኮኖሚስት የሆኑት ሊያም ብራንት በአንፃሩ‹‹ ፣Which institutions matter for economic growth? በሚል ጥናታቸው፣ይሕን እሳቤ ውድቅ ያደርጉታል፡፡ ‹‹ፖለቲካዊ፣ ህጋዊና ኢኮኖሚካዊ ብሎም የማህበራዊ ተቋማት ሁለንተናው አቅም የአንድንአገር የኢኮኖሚ እድገት ቢወስንም ከሁሉ ገዝፎ አቅም መፍጠር የሚችለውና ዋነኛው አስፈላጊ ተቋም የትኛው ነው የሚለውን በቀላሉ መግለፅ ይቸግራል››ይላሉ፡፡
አገራቱ ኢኮኖሚያቸውን በላቀ መልኩ ለማሻሻል አፈፃፀማቸውን ለማጎልበት ይረዳል የሚሉትን ተቋማት በፈለጉት መልኩ የማዋቀር ነፃ ፈቃድ ያላቸው መሆኑን የሚጠቁሙት ምሁሩ። ፋይዳቸው የላቁ ተቋማትን መለየት እና ትኩረት ለመሰጠት ከተቸገሩም ብቸኛ አማራጫቸው የሌሎችን በተለይ በኢኮኖሚ እድገት ማማ ላይ የተሰቀሉ አገራትን የተቋማት ልየታና አወቃቀር መቃኘት እንደሚችሉም ያመላክታሉ፡፡
ሁሉም ባለሙያዎች በሚባል መልኩም የተቋማት አቅም የአንድ አገር የኢኮኖሚ መሰረት ስለመሆኑ ያሰምሩበታል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት በአንፃሩ በተለይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያንሰራራ የተሻሉ ሃሳቦችን በማፍለቅ ረገድ በቂ አቅም ፈጥረዋል ለማለት አያስደፍርም፡፡
የተቋማት አቅም ግንባታም በዘመቻ መልክ ያዝ ለቀቅ በሚል መልኩ ካልሆነ በስተቀር መድረሻውን በመወሰን በተጠና እና ወጥ በሆነ መልኩ ሲካሄድም እንደማይስተዋልም የተለያዩ የምጣኔ ሃብት ምሁራን ከሚሰጡት አስተያየት በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል፡፡
እንደ ምሁራኑ ገለጻም፣ ተቋማቱ ሌላው ቀርቶ እርስ በእርስ አይነጋገሩም፡፡ አይደጋገፉም፡፡ አንደኛው የሚሰራው ፕሮጀክት ሌላኛው ማወቅ መወያየትና ብሎም ተቀራርቦ መስራት ሲገባው ይሕ ሲሆን ግን አይስተዋልም። ይህም ተቋማት ጠንካራ እንዳይሆኑ ካደረጉ ምክንያቶች ከዋነኞቹ መካከል ይጠቀሳል፡፡ጠንካራ ተቋማት ባለመኖራቸውም ምክንያት ኢትዮጵያ ከዓመት ዓመት ግዙፍ የሚባሉ ኪሳራዎችን ስታስተናግድ ቆይታለች፡፡
‹‹ይሕ አይነት ኡደት መስተካከል ካልቻለ አገር በምትፈልገው ፍጥነት መራመድ አትችልም››የሚሉት የምጣኔ ሃብት ምሁራን፣ ሁለንተናዊ እድገት ለማረጋገጥ ከተፈለገ ተቋማት በመገንባት ሂደት ውጤታማ የሚሆኑበትን መንገድ መፈለግ አቅምና አደረጃጀታቸው ምን ያሕል አዋጭ ብሎም አመቺ ነው? የሚለው በየጊዜው መከታተል የግድ ስለመሆኑ አፅእኖት ይሠጡታል፡፡በተለይም ለወቅታዊና አንገብጋቢ ችግሮች መፍትሄ መስጠት የሚያስችሉ ተቋማዊ ለውጦችን መተግባር የግድ ነው››ይላሉ፡፡
ወሳኝ የሚባሉ ተቋማትን በአግባቡ ማደራጀትና ተደራራቢ ተግባር የሚፈፅሙትን መለየት ብሎም ወደ አንድ ማጠፍ ከተቻለም አለአግባብ ይባክን የነበረ ከፍተኛ መጠን ያለው የህዝብና የአገር ሃብትን ከኪሳራ መታደግ እንደሚቻልም አፅእኖት ይሠጡታል፡፡
ኢትዮጵያ የፈለገችው ለማሳካት እና ያሰበችበት ቦታ ለመድረስ ተቋማዊ ግንባታ ላይ በጣም መስራት ይኖርባታል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አመራርም ይሕ እሳቤ ጠንቅቆ የገባው ይመስላል። የኢትዮጵያን ኢኮኖሚው ለማበልፀግ በሚያግዝ መልኩ ተቋማዊ አቅምን ለማጎልበት የተለያዩ ጥረቶችን አድርጓል፡፡ እያደረገም ይገኛል፡፡ በዚህም መሻሻሎች እየታዩ መምጣታቸውን ምሁራን ይገልጻሉ፡፡
በተለይ ከዚህ ቀደም በሙስና ተተብትበው የነበሩ በአግባቡ ቢሰራባቸው የአገር ካስማ የሆኑ ተቋማትን ከተዝረከረከ አሰራር ማላቀቅ ብሎም ፈር ማስያዝ ተችሏል፡፡ ለዚህም በተለይ የገቢዎችና ጉምሩክ ተቋማት አፈፃፀም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡በቢሮክራሲና በአስተዳደር ቁጥጥር ረገድም ለአሰራር የማይመቹ አንዳንድ ህግጋት እንዲመች ተደርገው ተሻሽለዋል፡፡
የስድስተኛው አገር አቀፍ ምርጫ ውጤትን በማስመልከት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም ባስተላለፉት የእንኳን ደስ አላችሁ! መልእክትም የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን እንዲሆን በቀጣዩ አምስት ዓመት ይበልጥ ትኩረት ከሚሰጣቸው ተግባራትና አራት ማዕዘኖች መካከል አንደኛው የተቋማት ግንባታ መሆኑን አስረግጠዋል፡፡፡
‹‹በጥቂት ግለሰቦችና ነጠላ ተቋማት ላይ ከማተኮር ባለፈ ኢትዮጵያን በጽኑ መሠረት ላይ የሚያቆሙ ጠንካራ ተቋማት ያስፈልጉናል››ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹ዘመን ተሻጋሪ ስርዓት ለማጽናት የሚያስችሉ ገለልተኛና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚያገለግሉ ተቋማትን መገንባት ላይ ትኩረት ይደረጋል። ይህ ማሕቀፍ ከፌዴራል እስከ ክልል የሚገኙ ተቋማትን የሚያካትት ይሆናል››ነው ያሉት፡፡
ከቀናት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 6ኛ ዙር 1ኛ ዓመት 1ኛ ልዩ ስብሰባው የፌዴራል መንግሥት የአስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባርን ለመወሰን የወጣውን አዋጅ በአብላጫ ድምጽ ሲያፀድቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለተቋማዊ ሪፈርም እውን መሆኑን መንገድ መጀመሩን አሳይተዋል፡፡
በዚሁ መድረክ የአስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባርን በሚመለከት የምክር ቤት አባላት የተለያዩ ሀሳቦችን የሰነዘሩ ሲሆን፤በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድና በፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አስፋው ምላሽ ሰጥተውበታል፡፡
በጉባዔው ራዕይንና ግልጽ የሆነ እቅድን ለማከናወን የሚችል የተቋም አደረጃጀት እንደሚያስፈልግ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ ቀደም የነበረው የኢትዮጵያን የተቋም ስሪት በድርጊትና ባላቸው ውቅር በርካታ ችግሮች ይታዩበት እንደነበር ሳያስታውሱ አላለፉም፡፡
የእርሳቸው መንግሥት እንደ ማጣቀሻ ወደ ኋላ ሄዶመንግሥታት የሰሩትን ጥናት ለማየት ሲሞክር በ1974ዓ.ም በደርግ መንግሥት ጊዜ ከተሞከረው መጠነኛ ጥናት ውጭ መዋቅርን በሚመለከት እንደ መንግሥት ሰነድ እንዳልነበር አውስተዋል።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ ይህንኑ ችግር ለመቅረፍና አንድ ተቋም እንዴት ይሰራል? በምን እሳቤስ ይደራጃል? የሚለውን ለመለየት መንግሥት ኮሚቴ በማቋቋም ከስምንት ወር በላይ ጥናት አካሂዷል። ከ11አገራት በላይም ተሞክሮ ለመውሰድ ተሞክሯል።
አሁን በሥራ ላይ ያሉት ተቋማት በሙሉ በሚኒስትር ደረጃ ብቻ ሳይሆን እስከ ታችኛው መዋቅር የኃላፊነት ደረጃ ያሉት ውይይት አድርገውበታል። የይድረስ እንዳይሆን በደንብ እንዲታይ ሰፊ ምክክርና ውይይት ተደርጎበታል። ዋና ፍላጎቱም ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ መሆን አለበት የሚል ነው።
‹‹ተቋም ያሰብነውን ትልም ሊያሳካ የሚችል አወቃቀር ካልተገበርን በቀር አሁን ባለው መንገድ አያዋጣም››ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ ካላት አቅም በላይ በጣም ሰፋፊ የተቋም ግንባታዎች እንደነበሩ ገልጸው፤ በአሁኑ ከሞላ ጎደል ቀደም ሲል በአዋጅ ወይም በደንብ የተቋቋሙ 32 ተቋማት ታጥፈዋል ብለዋል። ይህም ሰባት ቢሊዮን የሚሆን ብር መቆጠብ እንዳስቻለ ነው ያስገነዘቡት፡፡
ተቋማቱ በቁጥር መቀነሳቸው ብቻም ሳይሆን የሚቀራረቡ ስራዎች በአንድ ላይ እንዲሰሩ መደረጋቸውንና ከሚቀራረቡ ስራዎች ባሻገርም በአንድ ጭንቅላት ሊመሩ የሚገባቸውን እሳቤዎች መሰብሰብ መቻሉንም ሳያስገነዝቡ አላለፉም፡፡
በመንግሥት የኃላፊነት ሥራ ውስጥ በቀላሉ ለመግባባት የማይደረስባቸው ጉዳዮች መዋቅርና ምደባ መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሁሉም ሰው ለራሱ ብቁና አስፈላጊ እንዲሁም ከሌሎች የተሻለ መሆኑን ያስባል፤ ነገር ግን መዋቅርና ምደባው በቀላሉ ሊያግባባ እንደማይችል ግንዛቤ መውሰድ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።በቀጣይ እየተማሩና እያሻሻሉ መሄድ ተገቢ እንደሆነም አፅእኖት ሰጥተውታል፡፡
የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ዶክተር ፍጹም አስፋውም፤ የፌዴራል መንግሥት የአስፈፃሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር በአዋጁ ላይ ተዘርዝሮ መቅረቡን ገልጸዋል። አንዳንድ ተቋማት የአስፈጻሚ ባህሪ ቢኖራቸውም በህግ አውጭው ሥር ተጠሪ ሆነው የነበሩ ሲሆን፤ ነገር ግን ከውጤታማነት አኳያ የሠሩትን ሥራ እስከ ጫፍ ድረስ በመመልከት፤ በተለይ ከክስና ከመሳሰሉት ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያለን ክፍተት ለመቅረፍ እንደ ጸረ ሙስናና ሥነ ምግባር ኮሚሽን ያሉት ወደ አስፈጻሚ መምጣታቸውን ለአብነት አንስተዋል፡፡
አንዳንድ የምክር ቤት አባላት አዋጁ ለአስፈጻሚው አካላት ግልጽ ተልእኮን ያነገበ እንዲሁም የአገርን እድገትና ብልጽግና ማረጋገጥ እንደሚችል እምነታቸውን መሆኑን፣የአደረጃጀት መዋቅሩ አስፈላጊና ችግር ፈቺ እንዲሁም ሥራና ባለቤት የሚገናኝበትና በጀት ቆጣቢ እንደሆነ ሲገልጡ ተደምጠዋል፡፡ ይሁንና ይህ ብቻውን ችግር ሊፈታ እንደማይችልና ተገቢ የሆነ ክትትል እንደሚሻም ተጠቁሟል።
በአንጻሩ አዋጁ ለቀጣይ አገራዊ እጣ ፈንታ የተሻለ ተስፋ ሰጭ እንዲሆን ምክረ ሀሳቦችም ቀርቦበታል። በተለይም በርካታ ቁጥር ያላቸው ተቋማት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ተጠሪ መሆናቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ጫና ሊፈጥሩ አይችል የሚል ጥያቄም ተነስቷል፡፡ ሆኖም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእነዚህና መሰል ተግባራት ላይ አተኩረው መስራት ስለሚገባቸው ጫናውን ለመቀነስ በምክር ቤቱ አባላት እገዛ እንደሚያስፈልጋቸውና ክትትሉም የጋራ መሆኑ ተገልጿል። ዓለም አቀፍ አሠራርን የሚጣረሱ አወቃቀሮች ካሉም ታይተው ማስተካከያ እንደሚደረግባቸው ነው የተመላከተው፡፡
የምጣኔ ሃብት ምሁራን እንደሚስማሙበትም፣ በኢኮኖሚ የላቁ አገራት የከፍታቸው አብይ ምክንያት ውጤታማና ተጠያቂነት የሰፈነበት ተቋም መገንባታቸው ነው፣ይሕ እንደመሆኑ ኢትዮጵያ ለተቋማት ፈጠራና ሁለንተናዊ አቅም መጎልበት ትኩረት መስጠቷ ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ ይሑንና የተቋማት ግንባታ ውጤት በአንድ ጀንበር የሚመጣና የሚመዘን አይደለም፡፡ ስራውን ለነገ ሳያሳድሩ ከዛሬ መጀምር ግን ወደሚፈለገው መንገድ የሚያደርስ ወሳኝ እርምጃ ነው፡፡
ታምራት ተስፋዬ አዲስ ዘመን ጥቅምት 9/2014