አንዱ ሌላውን ሲንቅ ጀንበር ጥልቅ ይባላል። ይህ ኢትዮጵያን ካዳከሙ ዋነኛ ምክንያቶች መካከል ተጠቃሹ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁን ያለው ባለሙያ ከእርሱ በፊት በእርሱ መደብ ላይ የነበረውን ባለሙያ ይንቀዋል፡፡ ከቀደመው የሚማረው፣ የሚቀበለውና የሚያስቀጥለውን አይሻም፡፡ የቀደመውም ቀጣዩን ይንቀዋል፤ ምንም እንደማያውቅ ይገምታል፡፡ የሰራቸውንና በሚሰራበት ጊዜ ያጋጠሙትን ችግሮች እንዲሁም ችግሮቹን ያለፈባቸውን መንገዶች ለማሳወቅ አይፈቅድም፡፡ ይህ በባለሙያ ብቻ አይደለም፡፡ በኃላፊዎችም ላይ የሚታይ ትልቅ ክፍተት ነው፡፡
የአሁኑ ባለሙያ እና ኃላፊ ቀድሞ የተሠራውን ለይቶ አውቆ የታቀደውን አረጋግጦ፤ ሥራውን ሲቀጥል፤ ለነገ ጠብ የሚል በረከት ያስቀምጣል፡፡ ነገር ግን ቀድሞ የተሠራውን ለተከታዩ አለማስረከብ፤ የሰሩትንና የተገኘውን መረጃ በሙሉ እንዲሁ አየር ላይ በትኖ ሥራን መልቀቅ ባህል ሆኖ ቆይቷል፡፡ ኃላፊውም ሆነ ባለሙያው ወንበር እና ጠረጴዛውን ትቶ ከመውጣት ውጪ፤ የቀጣዩ ሰው ሥራው የተሳካ እንዲሆን የሰራውንና ያልሰራውን ለይቶ ማስረከብ አልተለመደም፡፡
ሥራን በትኖ ሕዝብን ማገልገል፤ ትውልድን መጥቀምና አገር ማሻገር አይቻልም፡፡ እንዲህ ዓይነት አገርን የሚያዳክሙ ልምዶች ከሥራቸው ተነቅለው መጣል አለባቸው፡፡ ሁሉም የሠራውን ሊለይ ያቀደውን ለተተኪው ሊያሳውቅ ይገባል፡፡ የሥራ ርክክብ ተራ ጉዳይ አይደለም፡፡ በዋናነት አገርን ከሚያዳክሙ አንዳንዴም ለውድቀት ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው እንዲህ ያለውን ለአገርና ለሕዝብ የሚጠቅሙ ተግባራት መዘንጋታቸው ነው፡፡ ይህ ችግር ሆኖ መቆየቱን ማመንና መጋፈጥ ያስፈልጋል፡፡
የትኛውም ደረጃ ላይ የተገኘ ሰው ሥራው ማገልገል ነው፡፡ ሥልጣን እና ሹመትም ለማገልገል ነው፡፡ ስለዚህ ሲያገለግል ከቆየ ሌላ ተተኪ የሕዝብ አገልጋይ ብቅ ሲል፤ የሕዝብ አገልግሎት እንዳይስተጓጎል የሰሩትንና የጀመሩትን በአግባቡ ማስረከብ ግድ ይላል፡፡ ሥራን ማስቀደም፣ ሕዝብን ማስቀደም፣ አገርን ማስቀደም ያስፈልጋል፡፡
ሰላም ቢኖርም የሚሰሩት ሥራዎች ፍሬ ካላፈሩ ብልፅግናን ማረጋገጥ አይቻልም፡፡ ብልፅግናን ለማረጋገጥ ደግሞ ለሕዝብ አለመወገንና ስለራስ ብቻ ከማሰብ መታቀብ ይገባል፡፡ ከሥልጣን ለቅቄያለሁ በሚል ቅራኔና ጥላቻ ውስጥ መግባት ከማንኛውም የሕዝብ አገልጋይ ባለሙያም ሆነ ኃላፊ የሚጠበቅ አይደለም፡፡ ስለዚህ መልካም መልካሙን መስራት ይገባል፡፡
መልካም ሥራ የሥነ ምግባር ዋልታና ማገር ነው። መልካም ሰሪ እውነተኛ የሕዝብ አገልጋይ ነው። እውነተኛ የሕዝብ አገልጋይ ደግሞ ቅን ነው፡፡ ቅን ሰው የሕዝብ አፍቃሪና ታታሪ ሰራተኛ ነው፡፡ ቅን ሰው በሥራ ይጠመዳል፡፡ ነገር ግን በሥራ መጠመድ ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ ጉንዳን ታታሪ ሰራተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን የሰራው ሁሉ በአንድ ኮቴ ተደፍጥጦ ድምጥማጡ ይጠፋል፡፡
ዋነኛው ጉዳይ መስራት ብቻ አይደለም፡፡ መሥራት፣ መብላትና መተኛት ላይ ብቻ መጠመድ ለውጥ አያመጣም፡፡ በሥራ ውስጥ ስለአገርና ስለሕዝብ ስለነገ ማሰብ ትልቅ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሥራው በአንድ ሰው ኮቴ ተደፍጥጦ ድምጥማጡ የሚጠፋ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልድ የሚጠቀም እንዲሆን ከሥራ ርክክብ ጀምሮ በቅጡ መታሰብ አለበት፡፡
የአዲስ መንግሥት ምስረታና የኃላፊዎች ሹመትን ተከትሎ የሥራ ርክክብ እየተካሔደ መሆኑ የሚመለክቱ ዘገባዎች ከሰሞኑን እየተዘገቡ ነው፡፡ አዲሱ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና የቀድሞ የትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ጌታሁን መኩሪያ የሥራ ርክክብ አድርገዋል፡፡ የሰላም ሚኒስትሩ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም ከቀድሞ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ጋር የሥራ ርክክብ ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ አቶ በለጠ ሞላ ከቀድሞው ሚኒስትር ዶክተር አብርሃም በላይ ጋር የሥራ ርክክብ ማድረጋቸው ተዘግቧል፡፡ በባህልና ስፖርት ሚኒስትርነት የተሾሙት አቶ ቀጀላ መርዳሳም ከቀድሞው የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ከዶክተር ሂሩት ካሳው ጋር የሥራ ርክክብ አድርገዋል፡፡ እነዚህን ለምሳሌ ያህል ጠቃቀስን እንጂ ሌሎቹም ሚኒስትሮች የሥራ ርክክብ እያደረጉ ነው፡፡
አንድ ባለሥልጣን ኃላፊነት የሚሰጠው ሕዝብን እንዲያገለግል ነው፡፡ በቢሮው ውስጥ ደግሞ የተገልጋይ ውሳኔዎች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ በእንጥልጥል የቀሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ባለስልጣኑ ሥራውን ትቶ ቢሮ ቆልፎ ሲጠፋ ተገልጋይ ምን ያህል ሊጎዳ እንደሚችል አያጠያይቅም። ስለዚህ ተሻሪም ሆነ ተሿሚ የስልጣናቸው መነሻ ሕዝብን ማገልገል መሆኑን ሊረዱት ይገባል፡፡ ተሿሚም በደንብ ለማገልገል ዝቅ ብሎ የተሰራውን ሥራ መቀበል የግድ ነው፡፡ ማንም ቢሆን መሰረቱ ትናንት የተሰራው ነው። ትናንት በተሰራው ላይ እርሱ ደግሞ የአቅሙን ያህል ይጨምራል፡፡ ለነገው ደግሞ በአግባቡ ያስረክባል፡፡
22 የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሚኒስትሮች ሲሾምላቸው፤ ተሿሚዎቹ በአዲስ መልክ ሥራ እንዲጀምሩ አይደለም፡፡ በእርግጥ በአዲስ መልክ መሰራት ያለባቸው ሥራዎች ይኖራሉ። ነገር ግን ባለፉት ዓመታት የተሰሩ ስራዎች፤ የነበሩ ጠንካራ ጎኖችና ክፍተቶች ተለይተው አዲሶቹ ተሿሚዎች ሊያውቋቸው ይገባል፡፡ የቀደሙት ያንን የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ያለበለዚያ አዲሶቹ እንደ አዲስ የነበረውን ሳያውቁ ወደ ሥራ መግባታቸው መዘዙ ብዙ ነው፡፡ የበታች ሠራተኛን ጉልበትና ጊዜን ከማባከን በተጨማሪ የሚያስከትለው ኪሳራም ከፍተኛ ነው፡፡
አንድ ባለስልጣን ሲሾም ከዜሮ ከተነሳ መላው ሠራተኛው ወደ ኋላ መጎተቱ የማይቀር ነው። ምክንያቱም አዲሱ ባለስልጣን የቀደመው የሰራውን ሁሉ በድጋሚ ለመስራት ይገደዳል፡፡ ጠጠር እንደማግኘት ቀላል የነበረውን ሥራ፤ ነዳጅ እንደማግኘት ያከብደውና የባለስልጣኑ የሥልጣን ዘመን እንዲሁ በመዳከር ያለ ውጤት ያልፋል፡፡ የሰራቸው አንዳንድ ሥራዎችና ተሞክረው ውጤት ያልተገኘባቸውን ተግባራት አዲሱ ባለስልጣን ሊሞክረው ይችላል፡፡ ይህ የተቋሙን ሀብት ያባክናል። ስለዚህ እንኳን የተሰራውን ተሞክሮ ያልተሳካውን ማሳወቅ የግድ ነው፡፡
ይህ የሥራ ርክክብ በኃላፊነት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በባለሙያ ደረጃም መለመድ አለበት፡፡ ሁሉም የሰራውን የማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት በሕግ መደንገግ ይኖርበታል፡፡ ያለፈውን የማይጠቅመውን እንደከብት በአፍ የገባውን ብቻ ከማመንዠግ በመውጣት አዲስ ባህል ያስፈልጋል፡፡ ማንም ቢሆን ከየትኛውም ሹመት ቢነሳ፤ የትኛውም ባለሙያ የትኛውንም ተቋም ቢለቅ ሥራውን ማስረከብ ግዴታው ሊሆን ይገባል፡፡ ሰላም!
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ.ም