የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ሲዋቀር የምድር፣ የአየር፣ የባህርና የሳይበር ክፍሎች እንዲኖሩት ተደርጎ ነው። በእነዚህም ዘርፎች ሰራዊቱ ከዘመኑ ጋር የሚሄድ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ተጠቅሞ ራሱን እንዲገነባ፣ በዓላማው ላይ ግልፅነት እንዲኖረውና በውስን ሀብት ውጤታማ እንዲሆን ተደርጎ የተዋቀረ ነው።
የመከላከያ ሰራዊት ግንባታ ዓላማው ሰራዊቱ በፖለቲካ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም የተቃኘ እንዳይሆን፣ ተጠሪነቱ በህዝብ ለተመረጠ ወኪሎች ብቻ መሆን እንዳለበት እና የሚመራውም ህገ መንግስቱን ብቻ መሰረት አድርጎ እንደሆነ ያሳያል። በተጨማሪም የመከላከያ ሰራዊቱ ዋና ተልዕኮ ብሔራዊ አንድነቷ የፀና፣ የሀገረ መንግስቱን ግዛታዊ ሉዓላዊነትና አንድነት እንዲሁም የሕዝብ ደህንነት ከማንኛውም ዓይነት የውስጥና የውጭ ጥቃት መከላከል እንዲችል ተደርጎ ተቀርጿል። ነገር ግን ከባለፉት ሶስት የለውጥ ዓመታት በፊት የነበረው አደረጃጀት በተግባር ሲፈተሽ እነዚህን መርሆዎች በጣሰ መልኩ ለአንድ ፓርቲ ብቻ እንዲያገለግል ተደርጎ ነበር።
ለዚህም ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ከራሱ ከመከላከያ ሰራዊቱ የወጡ እና የህወሓት ዋነኛ ዓላማ አስፈጻሚ የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በጓዶቻቸው ላይ የፈፀሙት አሳፋሪ ተግባር ማሳያ ነው፡፡ በሰሜን ዕዝ ላይ ከተወሰደው አሳፋሪ ድርጊት በኋላ መንግስት በወሰደው ህግን የማስከበር ዘመቻ አሸባሪው ህወሓት በ15 ቀናት ውስጥ አከርካሪው ተሰብሮ፣ ዋና ዋና መሪዎቹ ለሞት እና እስራት ሲበቁ የተረፈው ተበትኖ ወደ ዋሻ መግባቱ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅትም ለሀገር አስጊ በማይሆንበት ደረጃ ላይ ደርሷል። በዚህም የመከላከያ ሰራዊቱ ለሀገር አለኝታና መከታ መሆኑን አስመስክሯል።
ነገር ግን መንግስት ትግራይን የማረጋጋትና የመልሶ ግንባታ ስራ እየሰራ ከቆየ በኋላ የሰብዓዊ ቀውስ እንዳይባባስ፤ ቀጣይ ዓመት የምግብ እጥረት እንዳይከሰት ለአርሶ አደሩ የእርሻ እድል ለመስጠት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በመወሰን ሰራዊቱ ከትግራይ እንዲወጣ አድርጓል፡፡ በአጠቃላይ ለክልሉ የጥሞና ጊዜ በመስጠት ህዝቡ የሚሻለውን አስቦ እንዲወስን እድል ለመክፈት ሲባል መንግስት ተኩስ በማቆም ኃላፊነት የተሞላው የተናጠል ውሳኔ አስተላልፎ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አሸባሪው ህወሓት ህጻናትንና አዛውንቶችን እያሰበሰበ በክልሉ ውስጥ ቀውስ የማባባስ ስራ እየሰራ ጎን ለጎን ደግሞ የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ እያካሄደ፣ ሀብትና ንብረትን እያወደመ፣ በርካቶችን እያፈናቀለ ሀገሪቷ ሰላምና መረጋጋት እንዳይታይባት ለማተራመስ እየጣረ ይገኛል፡፡
በተቃራኒው የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት መንግስት የተኩስ ማቆም ውሳኔ ካስተላለፈ በኋላ ሰራዊቱን እንደገና የማደራጀትና የማብቃት ስትራቴጂ ነድፎ ወደ ስራ መግባቱም ይታወቃል። በዚህም የፕሮፌሽናል ሰራዊት ግንባታ መሰረት ተቋሙ በዘመናዊ ወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ ሙያዊ ብቃቱ የተረጋገጠ ሆኖ ተገንብቷል። ይህም ሃገርና ህዝብ የጣለበትን ኃላፊነት በብቃት መወጣት የሚችል እና የሀገርን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ ቁርጠኛ ሆኖ ሀገሩን ከጠላት መከላከል የሚችል የሰራዊት ቁመና እንዲኖረው ያስቻለ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊት አዲሱ አደረጃጀት ካካተታቸው መሰረታዊ ለውጦች ውስጥ ጥራትን ታሳቢ ያደረገና በቴክኖሎጂ የታገዘ የጦርነት ስልት መጠቀም መከላከያውን ዘመናዊና ውጤታማ ሊያደርገው ችሏል። ሰራዊቱ አቅሙን እንደገና በቴክኖሎጂ የታገዘ ስልጠና መገንባቱ ሀገሪቱ የአሸባሪዎችን ሀገር የማፍረስ ተልዕኮ ለመመከትና የሀገሪቱን መሰረተ ልማት ጥበቃ ይበልጥ ለማጠናከር የተሻለ አቅም ፈጥሮለታል። በተለይ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የሰላም መደፍረስ ተከትሎ ሰራዊቱ በዚህ ደረጃ አቅሙን መገንባት መቻሉ ከተቀመጠው ግብ አንፃርም ይበል የሚያሰኝ ነው። ሰራዊቱ በስነ ልቦና፣ በአካል ብቃት፣ በተኩስ ልምምድ፣ የተለያዩ የጦርነት ስልቶችን በተግባርና በንድፈ ሃሳብ መውሰድ መቻሉ ውጤታማና ብቁ ያደርገዋል።
ይህ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በሰሜን ዕዝ የተቃጣበትን የክህደት ተግባር ቀልብሶ በአጭር ጊዜ የአሸባሪውን ህወሓት ኃይል የደመሰሰ የታሪክ አካል በመሆኑ የአገር ኩራት ነው። በቀጣይም የቀሰሙትን ወታደራዊ ሳይንስ ወደ ተግባር በመቀየር ጁንታውን ጨምሮ ሌሎች ለሀገራችን ሰላምና ደህንነት ጠንቅ የሆኑ አካላትን ለመደምሰስ ቁርጠኛ መሆኑን በተግባር እያሳየ ይገኛል፡፡ በአጠቃላይ ከውጪ ኃይሎች ሊሰነዘር የሚችል ጥቃትን የመመከት እና በሀገር ውስጥም ህገ መንግስቱንና ሀገረ መንግስቱን ሊገዳደሩ የሚሞክሩ እንዲሁም የህዝብን ሉዓላዊነት የሚጥሱ ወራሪዎችን የሚፋለም ብቁ ሰራዊት የመፍጠሩ ሂደት ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ምክንያቱም ሠራዊቱ የሕዝቦችን ሉዓላዊነት እና የሉዓላዊነታቸው መገለጫ የሆነውን ሕገ መንግስታዊ ስርአቱን ከወራሪዎች፣ ከአመጺዎች እና ጉልበትን ከሚጠቀሙ ማናቸውም ኃይሎች መከላከል የመጨረሻው ተልዕኮው ነውና!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 9 ቀን 2014 ዓ.ም