100 አለቃ ከነበሩት እና አዲግራት ካፈራቻቸው አባቷ እና ከሰቆጣ ከተገኙት እናቷ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ሚኤሶ ከተማ ነው የተወለደችው። የቀለም ትምህርቷን በሚኤሶ፣ በደሴ፣ በአዲግራት ከተሞች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተከታትላለች። የዛሬዋ የወቅታዊ እንግዳችን ጋዜጠኛ ፍሬወይኒ ገብረጻዲቅ በ2003 ዓ.ም ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ በጋዜጠኝነትን ተግባቦት በዲግሪ መመረቋን ተከትሎ ላለፉት ስምንት ዓመታት በተለያዩ የሬዲዮ ጣቢያዎች በጋዜጠኝነት አገልግላለች። በርካቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በግልጽ ያመነችበትን ስትደግፍ፤ ሊሻሻል ይገባል የምትላቸው ላይ ከምንይሉኝ እና ከምን ይመጣብኛል ነጻ ሆና ሀሳቧን በማካፈሏ ያውቋታል። ማኅበራዊ ሚዲያን መልዕክት ከማስተላለፍ በተጨማሪ የአገኘችውን ተቀባይነት ለተቸገሩ ወገኖቿ እርዳታ ለማሰባሰብ ተጠቅማበታለች። ስለእርዳታ ማሰባሰብ ሥራዋ፤ በእስር ስላሳለፈችው ጊዜ ስለማኅበራዊ ሚዲያ ተሳትፎና ስለአገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ሀሳቧን አካፍላናለች፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴ ታይዋለሽ? በግልስ በዚህ ሁኔታ ጦርነት ውስጥ መሆናችን ምን ስሜት ፈጥሮብሻል?
ጋዜጠኛ ፍሬወይኒ፡- አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ለመጠየቅ እራሱ ለጠያቂውም ይከብዳል።ምክንያቱም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ስለሆንን አገራችን ያለችበትን ሁኔታ እንረዳለን።ከነገ ዛሬ ደግሞ ምን እንሰማ ምን እናይ ይሆን በማለት ላይ ነው የምንገኘው።አገራችን አስከፊ ሁኔታ ላይ ነው ያለችው።በሁሉም አቅጣጫ የውስጥም የውጭም ጠላት ከመቼውም ጊዜ በላይ ያንዣበበት ብቻ ሳይሆን እያጠቃት ያለችበት ወቅት ላይ ነን።አገራችን ልጆቿ ከውጪ ጠላት ጋር ተባብረው እያጠቋት አስከፊ ሁኔታ ላይ የከተቷት እና ደህንነታችን ስጋት ላይ የወደቀበት ጊዜ ነው። ያ ብቻ ግን ሳይሆን ሁልጊዜ ችግር ያጠነክራል እንደሚባለው፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠላትን ለማጥፋት በጋራ የቆመበት ለቀጣዩ ትውልድ ጥሩ የሆነች ኢትዮጵያን ለማስረከብ አንድ የሆኑበት ነው።
ወደ ጦርነት እንዳንገባ ጦርነት የሚለውን ቃል ሁላ ስንጸየፍ ነበር።ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ትምህርት ይሆነን ዘንድ እግዚአብሄር ሶሪያውያንን ወደአገራችን ልኮልናል፤ አልተማርንባቸውም።በየቦታው በየጎዳናው ላይ ስናገኛቸው ነበረ።ልጆቻቸውን ሚስቶቻቸውን ይዘው።በተለይ አዲስ አበባ በእኛ አገር ከሚገኙ የኔቢጤዎች በላይ ሶሪያውያን ነበር ፈሰው የነበረው።ፈጣሪ ይሄን ሲልክ ለምን ብለን አልጠየቅንም፤እኛ ወደዛ እንዳንሄድ ጠቋሚ ነገሮች ነበሩ።በአገራችን እንዲህ አይነት ነገር ሊያስነሱ የሚችሉ ፖለቲካውን ስታይ ግን እኛ አልተማርንባቸውም።ከዛም በተጨማሪ በተለያየ ጊዜ ፖለቲካው እየጦዘ ሲመጣ የህወሓት አመራሮች ለውጡን ተከትሎ መቀላቀል ባለመፈለጋቸው ወደዚህ ሁኔታ ውስጥ እንድንገባ አድርገውናል።ግን እዚህ ሁኔታ ውስጥ የከተቱን እነሱ እንደሚሉት ለትግራይ ሕዝብ በማሰብ አይደለም።‹ሊወሩን ነው፤ ሊገሉን ነው› የሚሉት ለትግራይ ሕዝብ በማሰብ ሳይሆን ለውጡን ተቀላቅለው ቢሰሩ ምናልባት ጥቂት ኢትዮጵያን ሲበዘብዙ የነበሩ የህወሓት ባለሥልጣኖች ሊጠየቁ ይችል ነበር።ግን እነሱ ጥቂቶች እንዳይታሰሩ እና አላግባብ የሰበሰቡት ሀብት ንብረታቸው እንዳይቀማ ጠቅልለው መቀሌ በመግባት ሕዝቡን ‹ሊወሩን ነው፤ እኛን ብቻ ሳይሆን እናንተንም ነው፤› ወደሚል ቅስቀሳና ፕሮፖጋንዳ ነበር የገቡት።የተወሰነው የኅብረተሰብ አካል አምኖአቸው ከጎናቸው ሆኖ ነበር።የሚታይ ነገር ነበር፤ በየጊዜው ትርኢት ያሳዩ ነበር፤ በየጎዳናው ልዩ ኃይል እያሰለጠኑ ለጥቃት መዘጋጀታቸውን ያሳዩ ነበር።ከዚህ ተዉ የሚል ሽማግሌም ሄዷል፤ እነኃይሌ ገብረሥላሴ የሃይማኖት አባቶች የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ከሚል እያለቀሱ ለምነዋል።ይሄን ሁሉ ባለመቀበላቸው አገርን መድፈር ነው ሌላ ምንም ልለው አልችልም።
‹ምንም አያመጡም፤ እኛ አሸናፊ ጀግኖች ነን፤› በሚል እብሪት ህጻናቱንም ወጣቱንም ቀስቅሰውት ስለነበር እና 40 ዓመት ሙሉ ከእኔ እና ከአንቺ እድሜ በላይ በዚህ ፖለቲካ መሪዎች እየተኮተኮተ ያደገ ማኅበረሰብ ስላዘጋጁ በደንብ ዘወሩት እና ለዚህ ሁሉ አደጋ ዳረጉት።ዛሬ ያለበትን ጦርነቱን እንደምናየው ነው።ምናልባትም ከስምንት ወር በፊት መከላከያ መቀሌን ተቆጣጥሮ የተሻለ ለውጥ እናያለን ብለን ጠብቀን ነበር።ዳግም ጦርነት የተጀመረበትን ምክንያት መንግሥት የራሱ የሆነ ግምገማ ይኖረዋል።በእውነቱ እነሱ እንደሚሉት አሸንፈው መንግሥት አቅም አጥቶ፤ ወይንስ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ድክመት ወይስ ሌላ የሚለው የራሱ የሆነ ጥናት የሚፈልግ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡-ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ በርካታ የትግራይ ወጣቶች በጫና ውስጥ ሆነውም ህወሓትን ሲቃወሙ ይታያል፤ ከዚህ አንጻር አሁን ባለው ሁኔታ የትግራይ ሕዝብ በተለይ ወጣቱ ለሽብርተኛው ህወሓት ያለው ምልከታ ምን ይመስላል?
ጋዜጠኛ ፍሬወይኒ፡- እኔ ከስድስት ዓመት በፊት ህወሓትን እደግፍ ነበር።ከዛ በኋላ አንዳንድ ደስ የማይሉኝ ነገሮችን ሳይ ከነሱ የተለየ ሀሳብ መስማት አለመውደዳቸውን እና የነሱን ሀሳብ ብቻ እንድትቀበይ ማድረጋቸው፤ ወደ ግል ሕይወትሽ ሁሉ ሲመጡ እና ጓደኞች ሁሉ ሲመርጡልሽ ምንድነው ይሄ ብለሽ መጠየቅ ትጀምሪያለሽ።ሌሎቹ ሲያነሱ የነበሩትን ጥያቄዎች አንቺም እንድትጠይቂ ትሆኛለሽ።ልክ አይደለህም እንዴት እንደዚህ አይነት ጥያቄ ታነሳለህ ትይው የነበረውን ሁሉ ለካ ልክ ነው ወደሚል ትመጫለሽ።
በምናደርጋቸው ውይይቶች ትግራይ ውስጥ ህወሓትን የሚቃወሙ በርካታ ወጣቶች ነበሩ።እንዲህ ግን ፊትለፊት ወቶ አይደለም።ግን እንዳልኩሽ ሊወሩን ነው፤ ሊያጠፉን ነው ብለው የሰሩት ፕሮፖጋንዳ አብዛኛው ይቃወሟቸው የነበሩትን መልሶ ወደ እነሱ እንዲሳብ አርጎታል።የተለያዩ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉ የህወሓት ደጋፊዎች ፤ የትግራይ ተወላጅ የሆኑ ያልሆኑም የትግራይ ተወላጆችን ወደማሸማቀቁ እና አንዳንድ ነገሮችን ማድረስ ሲጀምሩ እየፈሩ ልክ ነው እያሉ እንዲሄዱ የተደረጉ ሰዎችም አሉ፡፡
ግን አዲስ አበባ ላይም የማውቃቸው አሉ፤ ቤተሰቦቻቸው ትግራይ ክልል ተቀምጠው ፊት ለፊት የሚሞግቱ እና የሚቃወሙ ልጆች አሉ።ሁልጊዜ የተጫነሽን ብቻ ተሸክመሽ መሄድ የለብሽም።ሲበዛ ደግሞ ይመርሻል፤ ሕዝብሽ እየተገደለ ስታይ አንዳንድ ጊዜ እውነታን መቀበል መቻል አለብሽ።ማነው ለዚህ ሁሉ ነገር የዳረገን እኔ አያድርግብኝና ቤተሰቦቼ ላይ በደል ቢደርስ፤ ጥይት እየመረጠ የሚመታው አካል የለም።ውጊያ ነው በውጊያ ሰዓት ብዙ ውድመቶች ይከሰታሉ።ስለዚህ እኔ እዛ ቤተሰቦቼ ላይ የሆነ ጉዳት ቢደርስ እኔም እዛ ሆኜ ጉዳት ቢደርስብኝ ያ እንዲከሰት ያደረገው አካል ለኔ ህወሓት ነው።ተው ሲባል ያልሰማው፤ መሸሸጊያ ያደረገኝ አካል ነው ተጠያቂው።ታናናሽ ወንድምና እህቶቼን ወደውጊያ ያሰለፈብኝ አካል ነው።ምንም በማያውቁት ሴቶች እናቶቻችን እየተደፈሩ ጦርነቱ ያደረሰውን ቀውስ ሁላችንም የምንሰማው ነው፤ ለዚህ ሁሉ ተጠየቂ ለኔ ህወሓት ነው።ስለዚህ እስከመቼ ነው ሳልቃወመው የምቀረው ለምንድነው ዝም የምለው? ዝም በማለቴ ለኔ ደጋፊነቴን ነው የምገልጸው።ዝም ስል እየደገፍኩ ነው ማለት ነው።
በኢትዮጵያ በአራቱም አቅጣጫ ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲዘምቱ መርቀው እየሸኙ ነው።ወጣቶች እንሄዳለን በማለት ሲሄዱ እና በሰላማዊ ሰልፍ ድጋፉን ሲገልጽ እያየን ነው።የትግራይ ወጣት ሆኜ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ የማላደርግ ከሆነ ደጋፊ ነኝ ማለት ነው።ዝም የምል ከሆነ በዝምታዬ ውስጥ መደገፍን ነው የማየው።በመቶ ሺዎች የምንቆጠር የትግራይ ተወላጆች ከክልሉ ውጪ እንኖራለን።ስለዚህ ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ለመከላከያ ድጋፋችንን በማሳየት፤ ደም በመለገስ፤ ሌላው ኢትዮጵያዊ እያደረገ ያለውን በማድረግ ለአገሬ አለኝታነቴን መግለጽ መቻል አለብኝ።ከኢትዮጵያ እና ከኢትዮጵያውያን ጎን መሆኔን ማሳየት መቻል አለብኝ።ዝም ብዬ እየበላሁ እየጠጣሁ እንደማንኛውም ሰው ሥራዬን እየሰራሁ ተመልሼ ቤቴ የምቀመጥ ከሆነ ግን ዝም በማለቴ ውስጥ እየደገፍኩ ነው ማለት ነው።ስለዚህ ዝም አልልም፤ ዝም የማይሉ ወጣቶችንም አበረታታለሁ።እየተንቀሳቀሱ የሚገኙትም የወጡትም ወጣቶች ከዛ አንጻር ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም በትግራይ በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው እና በመተከል ለተፈናቀሉ እርዳታ አሰባስባችሁ ነበር እና ሂደቱ ምን ይመስል ነበር?
ጋዜጠኛ ፍሬወይኒ፡- ትግራይ ላይ እኔ ከ11 ልጆች ጋር ነበረ ኤግዚቢሽን ጀርባ ጋር እርዳታ ማሰባሰብ የጀመርነው።ወገናችን እየተጎዳ ነው፤ ስለዚህ በጋራ በመሆን መንግሥትንም የእርዳታ ድርጅቶችንም እናግዝ እኛም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ በሚል ወደ አንድ ሚሊዮን አካባቢ በገንዘብ እና ወደ 300ሺ ብር የሚገመት መድኃኒት ሰብስበናል፡፡
ልክ ያንን እየሰራን ሜሮን ታደለ የምትባል ልጅ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነበር የማውቃት አሁን ጓደኛ ሆነናል፤እሷ ደግሞ ጣይቱ ጊቢ ውስጥ ለመተከል ትሰበስብ ነበር።የዚህ ጊዜ አርቲስት ታማኝ በየነ ከአሜሪካ መቶ እዚህ ነበር የሚገኘው፤ እሱም በዚህ አጋጣሚ እዚህ ባለሁበት ሰዓት ልርዳ ብሎ ተነሳስቶ ነበር።እዚህ ጋር ፍሬወይኒ እየሰበሰበች ነው እዚህ ጋር ደግሞ ሜሮን ስለዚህ በጋራ አድርገን ለትግራይና ለመተከል እንሰብስብ ክፍፍሉን በምናገኘው ዳታ መሰረት እናደርገዋለን፤ የሚል ሀሳብ ከታማኝ ሲመጣ እኛም በጣም ነው ደስ ያለን።በጋራ ስንሆን 22 ሚሊዮን ገደማ ወዲያው ነው ያገኘነው በጎፈንድሚ እና መዝጊያ ሸራተን መድረክ አዘጋጅተን።ወደ አምስት መኪና ቁሳቁስ የንጽህና መጠበቂያ እና አልባሳት ለምግብነት የሚውሉ ግብዓቶች ሰብስበናል።
በአጋርነት ከቀይ መስቀል ጋር ስለሰራን ጥሬ ገንዘቡን ሕጋዊ በሆነ መንገድ ጨረታ አውጥተው እነሱ ግዢውን ፈጸሙልን።ሜሪም እኔም ለየብቻ የሰበሰብነውን ከላክን በኋላ ነው በጋራ መሰብሰብ የጀመርነው።በሁለት ቡድን ከፍለን የተወሰኑ አካላት እርዳታውን ይዘው ወደመተከል ሄዱ።የትግራዩ እርዳታውን ይዘን ልናከፋፍል መቀሌ ከደረሰ በኋላ አንቀበልም አሉን።እኛ እርዳታውን ለመንግሥት አካል ሰተን አንመጣም፤ የቀይ መስቀል የስራ ባህሪም አስቀምጦ አይመጣም ማዳረስ አለበት።እኛ ደግሞ በፊትም ስናደርግ የነበረው በትክክል ለተቸገሩ ሰዎች እዛው ሰተን ነው የምንመለሰው።ምክንያቱም ሕዝብ አምኖ የሚሰጥሽን ነገር ታማኝ ሆነሽ ማሳየት መቻል አለብሽ።ዛሬ ላይ ለምንሰበስበው ድጋፍ ያኔ ያገኘነው ነገር መሰረት ስለሆነን ነው።ዱቄቱም ሁሉም ነገር የመጠቀሚያ ቀኑ ያለፈበት ነው ተባለ።
በወቅቱ አገራችን ውስጥ ዘይትም ዱቄትም በከፍተኛ ሁኔታ እጥረት ነበር።እነ ታማኝ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመነጋገር ይሄ አስቸኳይ ነው ረሀብ ጊዜ አይሰጥም።ስለዚህ ቅድሚያ እንዲሰጠን ተብሎ ዘይትም ዱቄትም ለእኛ ሲባል ነው ፋብሪካው ምርት አምርቶ የላክነው።ግምቴ ምናልባት ታማኝ የሰበሰበውን እኔም እዛ አካባቢ ካድሬው አይወደኝም፤ እኛ ያመጣነውን ላለመቀበል ይመስለኛል።ኅብረተሰቡ አያውቀኝም፤ ግን እንዳትቀበል ከተባለ ይፈራል፤ በጣም በስጋት ነበር አብዛኛው ማኅበረሰብ ሲኖር የነበረው።አይሆንም ተባለ ይሄ ነገር የትግራይ ሚድያ ሀውስ በሚባለው ውጪ ባለው ሚዲያ እና በድምጸ ወያኔ እንዲሁም በእነሱ ደጋፊዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ተራገበ። ኅብረተሰቡም አንቀበልም ወደማለት መጣ እህሉ ለተወሰነ ጊዜ በረንዳ ላይ ተቀመጠ።እኛም ለቀይ መስቀል ጥያቄ አቀረብን ግዢ የፈጸምከው አንተ ነህ ኃላፊነቱን ወስደህ ማከፋፈል አለብህ።ኅብረተሰብ የሰጠንን ገንዘብ ወይ ሰው አልበላው መባከኑ ነው።ደግሞ እዛ ብቻ ሳይሆን ካልተፈለገ ሌላም አካባቢ የተራበ የኅብረተሰብ ክፍል ስላለ ካልሆነ እንመልሰው ሲባል አይመለስም፤ ተበላሽቷል የተባለ ነገር ይቃጠላል ወይ ጉድጓድ ውስጥ ነው የሚቀበረው ተባልን።ነገር ግን ስለተበላሸ አይደለም፤ እኛ ስለሰበሰብነው እና ተበላሽ በሚል ሰበብ በረሀ ላሉት ለእነሱ ደጋፊዎች ለመላክ ነው፡፡
ስለዚህ አይሆንም ተብሎ ናሙና ተወስዶ የፌደራል የመድኃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ተመርምሮ ምንም ችግር እንደሌለበት የሚያሳይ ወረቀት ሄደላቸው።ነገር ግን ረዥም ጊዜ ሊከፋፈል አልቻለም።ስለዚህ ተነስቶ እዛው ክልሉ ውስጥ እንዲከፋፈል አደረግን።ይሄም የሚሄደው መቀሌና ቅርብ የሆኑ ኣካባቢዎች ነው።ሌላው አካባቢ ለመላክ ይዞ የሚሄድ ሹፌር እንኳን ማግኘት አይቻልም።ለተቸገረው ሰው እኮ እርዳታ እንዳይደርስ ሲያደርጉ የነበሩት እነሱ ናቸው።በየጫካው በየበረሀው ውጊያ እየከፈቱ ነው፤ ስለዚህ ማን እርዳታ ይዞ ይሂድ።እውነት ለመናገር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፤ ለእርዳታ እጁን የዘረጋው።ያን ይዘሽ ወደበረሀ ስትሄጂ ጦርነት ይከፈትብሻል፤ ይዘርፉሻል።ስለዚህ ያለው አማራጭ ተፈናቅለው መቀሌ እና አካባቢው መድረስ ብቻ ነው።
በየገጠሩ አካባቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል በረሀብ እየተሰቃየ ህጻናቱ እየሞቱ ነበር።ይሄ እንኳን አላሳዘናቸውም።እኛ አዲስ አበባ ተቀምጠን ሲሰማን እነሱ አጠገባቸው ያሉት፤ ይሄን አይተው እንኳን አላዘኑም።ይልቅ ለምን ይጠቀሙባቸዋል ፎቶና ቪዲዮ እያነሱ ውጪ ላሉ ሚዲያዎቻቸው እና እዚህ ላሉ አክቲቪስቶቻቸው በመስጠት መንግሥት እና ኢትዮጵያውያን ላይ ጫና ለማድረስ እና በሰው ሞት መነገድ ነው የሚፈልጉት እንጂ ሰውን ከሞት ማዳን አይደለም።የትግራይን ሕዝብም እንደዛ ነው እያደረጉ ያሉት።
አዲስ ዘመን፡- በተደጋጋሚ ለትግራይ ሕዝብ እርዳታ ሲሰበሰብ ይታያል፤ ከዚህ ቀደም የጁንታው ደጋፊዎች ከሕዝብ የተሰበሰበውን የእርዳታ ገንዘብ ለፕሮፖጋንዳ ሥራ እናውለዋለን በማለት ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል ሲያደርጉ እናንተ የላካችሁት እርዳታ ደግሞ የተበላሸ ነው ተብሎ ለትግራይ ሕዝብ እንዳይደርስ ተደርጓል።በመሐል መርዳት የሚፈልጉ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ግራ እየተጋቡ ስለሆነ እንዴት ለትክክለኛው አካል እርዳታውን ለማድረስ ምንድነው መደረግ ያለበት?
ጋዜጠኛ ፍሬወይኒ፡- መንግሥት ወጥ የሆነ ነገር ማስተካከል መቻል አለበት።መንግሥት ብቻ ለተቸገሩ አካላት የሚረዳ ከሆነ ተደራሽ ላይሆን ይችላል።በቂ አይደለም፤የተቸገሩ ወገኖች ብዙ ናቸው አንዳንድ ጊዜ ከውጪ ሁሉ የሚመጡ እርዳታዎች በቂ አይደሉም።ስለዚህ ኅብረተሰቡ በበጎ ፈቃድ በያለበት አካባቢ እርዳታ ለማሰባሰብ ሲመጣ ፈቃድ የሚሰጥ አካል ያስፈልጋል።ፈቃድ የሚሰጥ አካል እኔም አንቺም መተን ለወገኖቻችን እርዳታ ልናሰባስብ ነው ብለን ስንጠይቅ ተቀናጅተን በጋራ እንድንሰራ ማድረግ መቻል አለበት፡፡
ምክንቱም ያኔ ተጠያቂነቱ እየጠበበ ይመጣል፤ ኃላፊነቱም ደግሞ በጣም እየጠነከረ ይመጣል።ግን አሁን የተለያየ አካባቢ የተለያየ ሰው እርዳታ ሲሰበስብ ታያለሽ።መንግሥት በቻለው አቅም ጥንቃቄ ማድረግ አለበት።የተወሰኑ አክቲቪስቶች እዚህ ሲሰበስቡ ነበር፤ የት እንዳደረሱት አይታወቅም።መንግሥት አልጠየቀም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ግንኙነት አልነበራቸውም፤ ተቃዋሚዎቻቸው ስለነበሩ መቃወም መብት ነው።እኔ ደጋፊ ስለሆንኩ ምናምን አይደለም።የምናደርገው ለኅብረተሰቡ አይደል፤ እኔ ጊዜያዊ አስተዳደሩን ወይንም መንግሥትን አይደለም የረዳሁት፤ ኅብረተሰቤን ነው።ግን ካለው አካል ጋር ቀጥታ ኃላፊነት ከተሰጠው አካል ጋር የመስራት ግዴታ አለብሽ።እነሱ ግን እየሰበሰቡ በረሀ ነው ሲልኩ የነበረው።እንዲያንሰራሩ አቅም ነው የሆኗቸው።ስለዚህ እንደዚህ አይነት ነገሮች ከዚህም በኋላ ክትትል ቢደረግባቸው በሌላም አካባቢ እንዳይከሰት መሰራት አለበት፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሸባሪው ቡድን በደረሰባቸው አካባቢዎች ሁሉ ከሊጥ ጀምሮ ያገኘውን ንብረት ሲዘርፍ እንደነበር ተገልጿል፤ ከዚህም አልፎ መዝረፍ ያልቻለውን ደግሞ ሲያጠፋ ነበር፤ ለምሳሌ እንስሳትን ሲገድል ነበር፤ ይህ ድርጊቱ ከዚህ ቀደም በአማራ ላይ ሂሳብ እናወራርዳለን ያለውን የሚደግፍ በሚመስል መልኩ ነውና በዘለቄታው በብሔሮች መካከል ጠባሳ እንዳይተው ምን መደረግ አለበት?
ጋዜጠኛ ፍሬወይኒ፡- ከዚህ በፊት ሰርተዋል አማራና ኦሮሞ ላይ፤ አማራና ኦሮሞ እሳትና ጭድ ናቸው መቼም አብረው መሆን የማይችሉ ኅብረተሰብ ናቸው።እንዴት አንድ ላይ ቆሙ ሲል ቃል በቃል በሬዲዮ ጌታቸው ረዳ ተናግሮ ያውቃል፤ አባይ ፀሐዬም ከዚህ በፊት ተናግረውት ያውቃሉ።ይሄ በቪድዮም በድምፅም ያለ ነገር ነው።ይሄን ያሉት ከመሬት ተነስተው አይደለም፤ ሁለቱ ሕዝቦች ላይ የሰሩት ሥራ ስላለ ነው።ሁሉም መንግሥታት በጊዜያቸው ጥሩም መጥፎም ነገሮች ሰርተዋል።ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለፉት መንግሥታት ጥሩነታቸው ሲነሳ ሰምተን አናውቅም፤ የትላንትናው ደርግ እና ኢህአዴግ እራሱ ጥሩነታቸው አይነሳም።ሁሌ ይሄ መጥፎው ሥራ ብቻ ነው የሚነሳው፤ደግሞ የአማራ ገዢ መደብ ሲያጠቃህ ነበር የሚል ትርክት ሲነገር ነበር። በዛ ግዜ አስተዳዳሪዎቹ አማራም ይሁኑ ኦሮሞ ይሁን በዛ ጊዜ የሚታወቅ ነገር አልነበረም።ግን ለነሱ ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲመቻቸው ድሮ ኦሮሞን እንዲህ ማድረግ ነበር ብለዋችሁ ነበር እና እንዲህ ሲያደርጓችሁ ነበር እየተባል በአማራው ላይ ጥላቻ እንዲኖር ተደረገ።
ህወሓቶች ከጫካ ጀምሮ አማራ የትግራይ ሕዝብ ጠላት ነው የሚለውን ደምድመው መተው እያስተዳደሩን እናምናቸው ነበር።የአማራና የትግሬን ጠላትነት ማንፌስቶአቸው ላይ በጽሑፍ አስቀምጠው ትውልድ በዛ ውስጥ እየቀረጹ ነበር። የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ክርክር ወቅት እናንተ እኮ አማራ የትግሬ የመጨረሻ ጠላት ነው እያላችሁ ነው ተብሎ ሲነገረን አልጠየቅንም።ምን ያህል ሸፍነውን እንደነበር ማለት ነው።በተግባር የተደረገ ነገር አልነበረም፤ ትግሬና አማራ አልተጣላም ሲታኮስ አላየንም።አብሮ በመኖር ውስጥ ነው የኖርነው፤ እኔ እናቴ አማራ የሰቆጣ ሰው ናት፤ አባቴ ትግሬ ነው። ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ምዕራብ ሐረርጌ ሚኤሶ ነው ተወልጄ ያደኩት፤ ስለዚህ ምንም እንዲህ አይነት ነገር አናውቅም ነበረ።አማራና ትግሬ ጠላት ቢሆን ኖሮ እናትና አባቴ ሊወልዱኝ አይችሉም ነበር።እኔ አንድ መነሻ ልሁን እንጂ ብዙ ሚሊዮኖች አሉ፤ ከሁሉም ብሔር ብሔረሰብ የተወለዱ ልጆች አሉ።ከአንድ ብሔረሰብ ብቻ ያልተወለዱ ይሄ የሆነው ችግሩን በግልጽ ስላላየነው ነው።ግን እነሱ ሥልጣናቸውን ሲቀሙ ሲዘሯት የነበረውን ነገር ለኮሷት እና በአይናችን እንድናይ አደረጉን።የአማራ እና የትግራይ ልዩ ኃይል እንዲጋጭ ተደረገ። እኔ የእናቴ እና የአባቴ ቤተሰብ እኮ እየተዋጋ ነው ያለው፤ እየተገዳደሉ ነው።ወንድማማቾች ማለት ነው።ይሄ ይሆናል ከዛ በኋላ ያልቃል የጦርነት መጨረሻው ሰላም መጨባበጥ ነው።ያውም እንኳን አሸናፊ እና ተሸናፊ የሌለበት ጦርነት ነገ በጋራ ተቀምጠሽ የምታፍሪበት ታሪክ ነው ይሄ።ልክ በጋራ ስትቀመጪ ጦርነቱ ሁላ ይረሳል ኢትዮ-ኤርትራ እኮ ተረስቶ ኢሳያስ አዲስ አበባ ላይ መቶ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐቢይ አስመራ ሄደው ዛሬ ኤርትራውያንን ስናገኝ በደስታ እንጋብዛቸዋለን።ጓደኛ እናደርጋቸዋለን።ነገ ይሄ ነገር ነው የሚከሰተው ትግራይ እና አማራ መሐልም።በጠላትነት ተፈራርጆ ማጋጨት የተፈለገው የእነሱን እድሜ ለማራዘም ነው።ከዛ በኋላ በለስ ከቀናቸው ደግሞ ኢትዮጵያን አፍርሰው እነሱ መልሰው አገር ለመግዛት በቃ እቺ ናት የእነሱ ፍላጎት እንጂ የትግራይ እና የአማራ ሕዝብ ጠላት ሊሆን አይችልም።የሽብር ቡድኑ አመራሮች የሚያነሷቸው ጉዳዩች የአርሶአደሮቻችን ጉዳዮች አይደሉም፤ ከነጭራሹም አያውቁትም።
አዲስ ዘመን፡- ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ማለት ጎረቤት የጎረቤቱን ብሔር የማይጠይቅበት፤ በትዳር የሚጣመሩ የተለያየ ብሔር ተወላጆች በየቦታው የሚታይ ነበር።ሁሉም ኢትዮጵያን ባስቀደመ መልኩ ነበር በህወሓት የአገዛዝ ዘመን ከአገር በላይ ብሔር ከፍ ያለውን ስፍራ እየወሰደ መሄዱ ከምን የመጣ ነው?
ጋዜጠኛ ፍሬወይኒ፡- የሰሩት ነው።የሚገርምሽ መሪዎቻችን የብአዴንንም መሪዎች ካየሽ በአብዛኛው ሚስቶቻቸው የትግራይ ተወላጆች ናቸው።ጠላት ቢሆን ኖሮ ያውም ያኔ ሲመሰረት ጀምሮ የመጡ ሰዎች እንዴት ከአማራ ጋር ይጋባሉ፤ ልጆቻቸውን እንዴት ከአማራ ጋር ያፈራሉ።ጥላቻ ቢኖር ግን ይሄ እራሳቸው ሰርተውት የመጡት ነገር ስለሆነ ለልጆቻቸው የሚነግሩት ነገር ስለነበረ ልጆቻቸውም ያንን እየተገበሩት ነው የሚመጡት።ዛሬ ትውልዱ ይፈራል፤ግጭቶችን እንዲህ ሲያይ አሁን አንቺ እንዴት ነው የሌላን ብሔር አግብቼ ብኖር የሚለውን ስታስቢ እንድትሳቀቂ ትሆኛለሽ።ይሄ እንዲሆን አይደል የተፈለገው ስለዚህ ትውልዱ እንዲፈራ ይሆናል።አይደለም በጋብቻ ለመተሳሰር አብሮ ለመኖር የሚያዳግት ደረጃ ላይ እንድንደርስ አድርገውን ነው የሄዱት።ግን እንዲህ ሆኖ አይቀርም፤ ምክንያቱም እኛ ከተለያየ ብሔር የተፈጠርን ልጆች ለእንደዚህ አይነት ነገር ምቹ ልንሆን አንችልም።ህሊናሽም እሺ አይልም፤ ጭንቅላትሽ ውስጥ እንዳስቀመጥሽው ነው የሚሆነው።ይሄ ጊዜው የፈጠረው እና የሚቀረፍ ነገር ነው።
አዲስ ዘመን፡- የአገር መከላከያ ሰራዊትን ከጀርባው የወጋው የጁንታው ደጋፊዎች ኢትዮጵያን ደግፋችሁ ከጁንታው በተቃራኒ የቆማችሁ የትግራይ ብሔር አባላትን ባንዳ በማለት የማሸማቀቅ ስራ ሲሰሩ ይታያል፤ ይሄ ምን ስሜት ይፈጥርብሻል?
ጋዜጠኛ ፍሬወይኒ፡- በፊት እናደድ ነበር፤እኔ የእናቴ ሙሉ ቤተሰቦቿ ሰቆጣ አገው ላይ በጀግንነት የሚታወቁ ናቸው።አባቴም በደርግ ጊዜ የመከላከያ አባል ሆኖ ለአገር ህልውና ሲዋደቅ የነበረ ነው።ባንዳ ቤተሰብ የለኝም፤ ያ ያናድደኝ ነበር ባንዳ ስባል።ለምንድነው ባንዳ የሚሉኝ? ደግሞ የዛን ሰሞን አዲስ ነው ባንዳ የሚለው ቃል ተደጋጋሚ ያልሰማነው ነገር ስለነበር፤ ያበሳጨኝም ያሳቅቀኝም ነበር።እውነት ለመናገር አሁን የቤት ስሜ ሁሉ እየመሰለኝ ነው።ጓደኞቻችን ጋር ስንገናኝ አንቺ ባንዳ፤ አንተ ባንዳ ነው የምንባባለው፤ ምንም አይደለም ወደማለት መተናል።
ባንዳ አገሩን የሸጠ፤ አገሩን የከዳ ነው።እነሱ ናቸው ከግብጽ ጋር ከሱዳን ሌላም አካል ቢመጣ አብረው ሊወጉሽ የሚመጡት።እኔም ደግሞ ከአገር ጎን ነው የቆምኩት።ኢትዮጵያ ናት በትልቁ የምትታየኝ።እኔ እንኳን በዚህ እድሜዬ አገሬ አስተምራኛለች፤ ሥራ ይዤባታለሁ፤ ኖሬባታለሁ ገና ወደፊት አግብቼ ወልጄ እኖርባታለሁ።እነሱ ዘርፈው አጊጠውባታል፤ ልጆቻቸውን አንደላቀው አስተምረውበታል፤ እኛ የበታች እነሱ የበላይ ሆነው ብዙ ኖረውበታል።እነሱ እንኳን ባንዳ አልተባሉም፤ የእነሱ ልጆች ባንዳ አልተባሉም፤ አዲስ አበባ ውስጥ ይሽከረከራሉ ማንም አይናገራቸውም።እነሱ የባንዳነትን ተግባር ስለሚያውቁ ነው ባንዳ የሚሉት፤ እኔ ባንዳን አላውቀውም ነበረ ስሙን እራሱ ግን እነሱ ያውቁታል ስማቸው ስለነበረ።አሁን ከጓደኞቻችን ጋር መጠራሪያችን ነው ባንድሽ እየተባባልን እንዲያውም እያቆላመጥነው ነው።ምንም አይመስለንም፤ ደግሞ በአገር መሰደብ ይሻላል፤ክብር ነው።መከላከያ እየሄደ የሚሞተው ለክብር ሲል ነው።
አዲስ ዘመን፡- እምባ አባሽ በሚል ስም በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በጁንታው ጉዳት ለደረሰባቸው እና ለተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ እያሰባሰባችሁ ነው፤እንዴት ተጀመረ? ከሕዝቡ እያገኛችሁት ያለው ድጋፍስ ምን ይመስላል?
ጋዜጠኛ ፍሬወይኒ፡- እምባ አባሽ ብለን የጀመርነው አሁን ገና በጣም ጅማሬ ነው፤ ገና ይሰፋል።ያኔም እንዲህ ብለን ጀምረን ነው ከነታማኝ ከሌሎችም ሰዎች ጋር ያሰፋነው።ሕዝብ የሚያስተባብረው ሰው ይፈልጋል፤የሚያስተባብረው ሰው ከሌለ መርዳት እየፈለገ በየቤቱ ቁጭ ይላል።ስለዚህ እኛም ከሜሪ ጋር ተነጋገርንና የተወሰኑ ጓደኞቻችንን ይዘን ለምን የባለፈውን አይነት እርዳታ አናሰባስብም? በዛ ላይ ባለፈው በሰራነው ስራ ትንሽም ብትሆን ተቀባይነት አግኝተናል።ስለዚህ ለምን እንደገና ይሄን ነገር አንጀምርም ተባባልን እና ከሌሎች የማኅበራዊ ሚድያ ጓደኞቻችን ጋር የአማራ ልማት ጽ/ቤት ሥር ቦታ ሰተውን ጀምረናል።በርግጥ ቦታው አመቺ አይደለም፤ ከጀመርን ቀናቶች ሆነውናል ያልተሟሉልን የተወሰኑ ነገሮች አሉ።ጊዜያችንን ሥራችንን የቤተሰብ የጓደኛ ጊዜ ትተን ከጠዋት እስከ ማታ እዚህ ቁጭ የምንለው የምለምነው ለሕዝብ ነው።እዚህ ሲኮን ቢያንስ ድንኳን ጠረጴዛ እና ወንበር ተሟልቶልሽ ከዛ ደግሞ በጎ ፈቃደኞች አሉ እነሱም ተጨምረው ሲሰራ ኅብረተሰቡም እምነት ይኖረዋል የተደራጀ ነገር ሲኖረው። አሁን እነዚህ ነገሮች አልተሟሉም በፊት ኤግዚቢሽን ማዕከል ጣይቱ ሆቴል እነዚህን ነገሮች ተባብረውን በሞራል ነበር የምንሰራው አሁን እነዚህ ነገሮች አልተሟሉም።ቅድም ልጆቹን ያየሻቸው በረንዳ ላይ ቁጭ ብለው ነው።በርግጠኝነት በቅርቡ ወይ ቦታ እንቀይራለን ካልሆነ እዚሁ ተነጋግረን እዚህ ህንጻ ላይ ያሉት የአማራ ልማት ማህበርም ይሁን ሌሎችም አሉ በአማራ ክልል ወጣቶችም ከእነሱ ጋር ተነጋግረን ሥርዓት ባለው መልኩ ለመስራት እንቅስቃሴ እያደረግን ነው።
ለጊዜው የቅስቀሳ ስራ እየሰራን ያለነው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ብቻ ነው።ኅብረተሰባችን አንረዳም የሚል አይደለም፤ እንዳየሽው ሰሞኑን የሚያበሳጭ ነገር፤ወጣቱ ከወልዲያም መተው እዚህ እገዛ የሚፈልግ ነው።እኛ ለእነሱ አይደለም የምናሰባስበው፤ እኛ አቅመ ደካማ ለሆኑት ቀዬአቸውን ለቀው ላልወጡት ቢወጡም፤ መጠለያ ውስጥ ሆነው በትክክል እርዳታ ለሚፈልጉ ህጻናት፣ ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ አዛውንቶች ለነሱ ነው።እነሱን ከሚመለከተው አካል ጋር ከክልሎቹ ጋር አፋርን በአፋር አገውም ሰቆጣም ጎንደርም በሚመለከታቸው በትክክል ኃላፊነት ከሚሰማቸው እና ከተሰጣቸው አካላት ጋር በጋራ ሆነን እርዳታውን እናደርሳለን።ግን አሁን ገና እየጀመርን ነው የተወሰኑ አልባሳትን እና ለምግብነት የሚውሉ ግን ሰብስበናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎች ስም አመሰግናለሁ ፡፡
ጋዜጠኛ ፍሬወይኒ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
ቤዛ እሸቱ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም