ኢትዮጵያዊነትን ለመገንዘብ እና ለኢትዮጵያ ለመቆርቆር ኢትዮጵያዊ መሆንን ይጠይቃል።ኢትዮጵያዊ የሆነ ደግሞ ለኢትዮጵያውያን እና ለኢትዮጵያ ይሠራል።በኢትዮጵያ ላይ በግልጽም ይሁን በስውር ደባ የሚፈጽሙ ኢትዮጵያዊ ሰዎች፤ ቡድኖችም ሆኑ ድርጅቶች ኢትዮጵያዊነት የቱ ላይ እንደሆነ አይገባኝም።ከጥንተ ገናናነቷ እስከ አሁኑ ቁመናዋ አገሬ ለዜጎቿ ሁሉ ደልዳላ እና ምቹ ላትሆን ትችላለች።በዚያ ላይ የውጭ ወረራ እና የውስጥ መሻኮት ሲታከሉበት ሕይወት በኢትዮጵያ ሠማይ ስር የቱን ያህል ጉስቁልና የሚፈራረቅበት ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም።ይሁን እንጂ አገሬ የመከራ ዘመን ለማሳጠር የሚሠሩ የቁርጥ ቀን ልጆች አጥታ አታውቅም።በመንግሥት ላይ ያኮረፈ እና “ተው ጥራኝ ጫካው ተው ጥራኝ ዱሩ፤ ላንተም ይሻልሃል ብቻ ከማደሩ” ብሎ በየዘመኑ አስተዳደር ላይ የሸፈተ ሳይቀር አገሩን ከማጥ ለማውጣት ሲባል ልዩነቱን ወደ ጎን በመተው በአገሩ ጉዳይ ላይ አንድ አቋም ይዞ ለአንድ ዓላማ በጋራ ሲዋደቅ ማየቱ፤ የዘመናትን ውጣ ውረድ ተቋቁሞ አሁን እስከምንገኝበት ጊዜ ድረስ የዘለቀ እውነታ ነው።ወደ ፊትም ይህ እንደሚቀጥል አምናለሁ።
ኢትዮጵያ በብዙ መከራ እየተፈተነች፤ ፈተናዎቿንም በአሸናፊነት እየተሻገረች እዚህ የደረሰች አገር ናት።የግዛት አንድነቷ አደጋ በተጋረጠበት ጊዜ ሁሉ ትንታግ ልጆቿ ከያሉበት ተጠራርተው በድል ጎዳና ይመሯታል።በግዞት ምድር ሆነው እንኳን ሳይቀር ጀግኖቿ ለክብሯ ይዋደቁላታል።ኮሎኔል አብዲሣ አጋ እና ሳተናው ዘርዓይ ድረስ ያደረጉትም ይህንኑ ነው።
ከዚህ ታሪካችን በተጻራሪው ከቆመው አሸባሪው ህወሓት ግን ከጥንተ ልደቱ እስከ ዛሬ መጃጃቱ ድረስ ከሐሳቡ እና ከድርጊቶቹ ሁሉ ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን ፈልጌ ማግኘት አልተቻለኝም።ለዚህ ድምዳሜዬ ማሳያ እንዲሆኑኝ የሚከተሉትን አሥራ ሁለት እውነታዎች በአስረጅነት አቀርብ ዘንድ የግድ አለኝ።
1. የ1966ቱ ሕዝባዊ አብዮት፡- ምንም እንኳን ኋላ ላይ መስመሩ ተጠልፎ የተጓጓለትን ውጤት ማስገኘት ቢሳነውም፤ ኢትዮጵያን ከዘውዳዊው አገዛዝ ያላቀቀው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የምሁሩ፤ የአርሶ አደሩ፤ የወዛደሩ፤ የወታደሩ … ብቻ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይሁንታ የተቸረው እንደነበር ይታወሳል።አሸባሪው ህወሓት ግን ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ጋር በመሆን በጋራ የኢትዮጵያን መጻዒ ዕድል ለመወሰን የሚያስችለውን አጋጣሚ ገሸሽ አድርጎ አንድን የኢትዮጵያ አካል ነጥሎ ነጻ ሊያወጣ ወደ ደደቢት አቅንቷል።
የትግራይ ሕዝብ ችግር ከሌሎቹ ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ የተለየ ነበር? ቢሆንስ በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ መፍትሔ ሊፈለግለት አይችል ነበር? በርግጥ እውነቱ ግልጽ ነው፤ ጥያቄ የሚሆነው የቡድኑ ኢትዮጵያዊነት ነው።
2. የምሥራቅ ኢትዮጵያ ወረራ፡- በ1969 ዓ.ም ኢትዮጵያ በተስፋፊው የዚያድ ባሬ ጦር ተወረረች፤ ያኔ አገራችንን ወዳጆቿ ከዷት፤ አጋሮችም ፊት ነሷት።የቁርጥ ቀን ልጆቿ ግን ዘብ ቆመው ተዋደቁላት።በዚህ ጦርነት ወቅት የአሸባሪው ህወሓት መሪዎች ከወራሪው እና ተስፋፊው የሶማሊያ ጦር ጋር ሆነው ወጉን።አዎን የዚያድ ባሬ ጦር ተሳክቶለት ከአዋሽ መልስ የኢትዮጵያን ክፍል ወደ ግዛቱ ቢጠቀልል፤ ሱዳን፤ ጂቡቲ እና ኬንያም ከየአቅጣጫው ወደ ኢትዮጵያ ግዛት ቢዘልቁ ህወሓት ጥያቄያቸውን ከማጽደቅ ያለፈ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ግድ የማይሰጠው ስለመሆኑ ዛሬም ሳይቀር ከሱዳን ጋር በመናበብ የአገራችንን የግዛት አንድነት በሚጻረር ተግባር ላይ መሰማራቱ ፍንትው ያለ እውነታ ሆኗል።
ድርጅትም ይሁን ግለሰብ ከታሪካዊ ባላንጣዎቿ ጋር አብሮ አገርን የሚያጠቃ እና የሚያስጠቃ ከሆነ አገሬነቱ የቱ ላይ ነው? እስኪ እዚህ ጋር የአሸባሪው ህወሓትን ኢትዮጵያዊነት አሳዩኝ።
3. የኢትዮጵያን መከላከያ ኃይል መቅኖ መንሳት፡-
ህወሓት 17 ዓመታት በትጥቅ ትግል ላይ ነበር።በዚህ ቆይታው የአንድ እናት ሁለት ልጆች ጎራ ለይተው ተፋልመዋል።ከግራ ቀኙ አሥራ ሺህዎች ሕይወታቸውን እና አካላቸውን አጥተዋል።በሽሬ እንዳሥላሴ 6ኛ ኮር ላይ የተፈጸመው ዘግናኝ ፍጅትን ለመግለጽ ግን ቃላት አቅም ያንሳቸዋል።በግንቦት ወር 1983 ዓ.ም ህወሓት የሥልጣን መንበሩን እንደተቆናጠጠ ሳይውል ሳያድር ኢትዮጵያ ለአምሣ ዓመታት ደክማ ያደረጀችውን የምድር ጦር፤ የአየር ኃይል እና የባሕር ኃይል በተነ። በብድር የተሸመቱትን እና ዕዳቸው እንኳን ተከፍሎ ያልተገባደደውን ተዋጊ አውሮፕላኖችን፤ የጦር ጀልባዎችን እንዲሁም ሌሎች ትጥቆች ከፊሉን በችሮታ ሰጥቶ ሲወዳጅበት የተቀሩትን የት እንዳደረሳቸው እንኳን የሚያውቅ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ።ህወሓት የኢትዮጵያን የአገር መከላከያ ተቋም ማፍረስ የጀመረው ሥልጣን በያዘ ማግሥት ብሔራዊ ጦሩን በመበተን ብቻ አልነበረም።የማዕከላዊውን መንግሥት ሥልጣን ይዞ በቆየባቸው ዓመታትም ጭምር ጦሩ ከመለዮው እና ከባንዲራው ክብር ይልቅ የህወሓት አገልጋይ እንዲሆን አድርጎ አደራጀው።
ከፍተኛውንና መካከለኛውን የጦር አመራር እርከን ለአገር ሉዓላዊነት ሳይሆን ለቡድኑ የበላይነት ተግተው በሚሠሩ ሰዎች አዋቀረው።ይህም በመሆኑ ህወሓት በአኮረፈ ጊዜ ከህወሓት ከፍተኛ የጦር መኮንኖች በተዋረድ እስከ ባለ ሌላ ማዕረግ መለዮ ለባሾች የኢትዮጵያን ጦር ከድተው የክልል ጦር ኃይል ማሰልጠን፤ ማደራጀት እና ማስታጠቅ ያዙ።በማዕከል የቀሩትም ቢሆኑ በያዙት ሥልጣን ተገን የጦሩን ስንቅ፤ ትጥቅ እና መረጃ በተቃራኒው አቅጣጫ የማቀባበሉን ሥራ ይተጉበት ነበር።ኋላ ላይ ደግሞ ለለበሱት ማዕረግ ፈጽሞ በማይመጥን ወራዳ ተግባር ላይ ተሰማርተው የጦሩን የመገናኛ መስመር በጣጥሰው ከተኛበት ሳይነቃ ሰይጣናዊ ክህደት፤ ሰቆቃና ዘግናኝ ጭፍጨፋ ፈጸሙበት።ይህም ድርጊቱ ህወሓት ጥቂት ኢትዮጵያዊነት የሚባል ማገር እንደሌለው ትልቅ ማሳያ ነው።
4. በኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ላይ መዝመት፡-
የኢትዮጵያን ሀብት ወድዶ ሕዝቧን ግን ጠልቶ የሚጸና ሥልጣን ፈጽሞ አይኖርም።አሸባሪው ህወሓት ግን እርሱ በኢትዮጵያውያን ላይ ያለው ንቀት እና ጥላቻ አልበቃ ብሎት ከአራት ኪሎ ቤተመንግሥት ዕቅድ አውጥቶ እና ጥሪት በጅቶ በኢትዮጵያውያን መካከል ጥርጣሬ፤ አለመተማመንን እና እንዲያም ሲል ግጭት እንዲነግሥ ሲሠራ ለ27 ዓመታት ባጀ።ዘመን እንኳን ሲለወጥ በማይለወጠውና በአረጠ አስተሳሰቡ ደደቢት በረሃ ላይ በ1968 ዓ.ም በተጻፈ ማኒፌስቶው ላይ “አማራን ኅብረተሰብዓዊ እረፍት ለመንሳት” ታጥቆ የተነሳው ህወሓት ሥልጣን ከያዘ ማግሥት አንስቶ ለየትኛውም ኢትዮጵያዊ የሚበጅ ሆኖ አልተገኘም።ከአማራው ማኅበረሰብ የበለጠ ከስቃይና ግድያ ጽዋ የተጎነጨ ባይኖርም፤ ቡድኑ አገር ወዳድ የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ መከራ ያላዘነበበት ሕዝብ አይገኝም።የሲዳማ እናቶች አልቅሰዋል።የሸኮ ቤንች ልጆች በአረር ተቆልተዋል።የአኟዋክ ወንዶች ተመርጠው የዘር ማጥፋት ሰለባ ሆነዋል።በኦጋዴን የጅምላ ግድያ ተፈጽሟል።ከፍጅቱም ባሻገር ማቆሚያ በሌለው አፈናና እንግልት የተነሳ “እስር ቤቶች ሁሉ ኦሮምኛ ይናገራሉ” የተባለው በአሸባሪው ህወሓት አገዛዝ ዘመን መሆኑ የቅርብ ጊዜ መራር ትውስታችን ነው። እነሆ በማይካድራ(ጎንደር)፤ በጋሊኮማ (አፋር)፤ በአጋምሣ (ወሎ) እና ጭና ተክለ ኃይማኖት(ጎንደር)፤ ቆቦ(ወሎ) የተደረገውን የዘር ማጥፋት ወንጀል ስንታዘብ ደግሞ ይህን አገር የውጭ ወራሪ ቢያስገብር እንኳን እንዲህ ዓይነት ዘግናኝ ግፍ ይፈጽማል ተብሎ አይታሰብም።ይባስ ብሎ አዝመራውን ማሣ ላይ ሳለ የሚያወድም፤ ጥገት ላም እና ጥማድ በሬ እያረደ ከመብላት አልፎ የቤት እንስሳቱን እንደ ጠላት በመሣሪያ የሚፈጅ፤ የኢትዮጵያውያንን ቤት በላያቸው ላይ ከማፈራረስ አልፎ የተዋጊዎቹን እሬሳ በሰዎች መኖሪያ ቤት ውስጥ እየቀበረ አርዮሳዊ ምቀኝነቱን የሚያስረግጥ፤ ሕሊና ቢስ ተዋጊዎቹ በምጧ ዋዜማ ላይ በምትገኝ ነፍሰጡር ላይ በመንጋ የሚጎነበሱ የጉግ ማንጉግ ስብስብ ኢትዮጵያዊነቱ የቱ ላይ ይሆን? ኢትዮጵያዊነት እንኳ ይቅር ቢባል እውን በህወሓት ደም ውስጥ የሰብዓዊነት ቅንጣት አለን?
5. የኅብረ ብሔራዊነት ዓይነ ጥላ፡- ህወሓት ከውልደቱ ጀምሮ የኅብረ ብሔራዊነት ዓይነ-ጥላ የተጠናወተው ድርጅት ነው።ጎጠኝነት የአገዛዝ ዘይቤው መነሻ እና መድረሻ እንዲያም ሲል ርዕዮተ ዓለማዊ ማጠንጠኛው እንደሆነ የድርጅቱ ባሕርያት ይመሰክራሉ።አሸባሪው ሕወሓት ገና በለጋ የምሥረታ ዕድሜው ቀዳሚ የጥቃት በትሩን ያሳረፈው በኢ.ሕ.አ.ፓ እና ኢዲኅ ላይ መሆኑን ልብ ይሏል።እነ መኢአድ፤ ኢድኃቅ፤ ቅንጅት፤ አንድነት፤ ሠማያዊ እና ሌሎችንም ፓርቲዎች ህወሓት ፍዳቸውን ያስቆጥራቸው የነበረው ከፖለቲካ ፕሮግራማቸው ይልቅ ሕብረ ብሔራዊ ቅርጻቸው እንቅልፍ እየነሳ ስለሚያባንነው እንደነበር ነጋሪ የሚሻ ጉዳይ አይደለም።ሌላው ቀርቶ ህወሓትን አቅሉን ያሳተችውና ጨርቁን ያስጣለችዉ በስንብቱ ዋዜማ ላይ ከወደ ጎንደር የተደመጠች “የኦሮሞ ደም፤ የእኔ ደም ነው” የምትል ሐረግ ነበረች።በጠባብነትና ትምክህት የፈጠራ ትርክት ዓይንና ናጫ እንደሆኑ አድርጎ የቆጠራቸው ወንድማማቾች መጠራራት ሲጀምሩ የአሸባሪው ህወሓት ትኩሳት ቴርሞ ሜትሩ ማንበብ ከሚችለው አኃዝ በላይ ማሻቀቡ ከኅብረ-ብሔራዊነት ጥላቻ እና ፍራቻ ካልሆነ በስተቀር ሌላ ምንም አመክንዮ ሊኖረው አይችልም።ሌላው ቀርቶ እራሱ ህወሓት ይዘውረው በነበረ የኢሕአዴግ ምክር ቤት ተወስኖ ሲያበቃ፤ ኢሕአዴግ ፈርሶ፤ “አጋር ድርጅት” የሚለው አግላይ የእንጀራ ልጅ ስያሜም ቀርቶ፤ አንድ ሕብረ-ብሔራዊ ፓርቲ እንዲመሠረት ሲደረግ ‘ቢቀፈኝ’ ብሎ ወደ መቀሌ ካርኒ የቆረጠው ህወሓት አይደለምን? የሚጠላትን አገር ሲገዛ የነበረው ህወሓት ያልፈጠረበትን ኢትዮጵያዊነት ከየት ሊያመጣው ይችላል?
6. ኢትዮጵያን መዝረፍ፡- የህወሓት ማንነት መገለጫ ከሆኑ ባሕርያት መካከል ዘረፋ ግንባር ቀደም ተግባሩ መሆኑ አሌ የሚባል ጉዳይ አይመስለኝም።ድርጅቱ በትጥቅ ትግል ዘመኑ እግሩ ካደረሰው ስፍራ ላይ ያጋጠመውን የግልም ይሁን የመንግሥት ሀብትና ንብረት ሲበዘብዝ ኖሯል።ባንኮች ደግሞ የዘረፋው ቀዳሚ ዒላማዎች ሆነው ቆይተዋል።ወደ ሥልጣን ሲመጣ ይህን መሰሉን ድርጊት ይጠየፈው ይሆናል ተብሎም ተስፋ ተደርጎ ነበር።ግን አልሆነም።የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣንን ከተቆጣጠረ በኋላም ቢሆን ዘረፋውን በዓይነት እና በመጠን አግዝፎ ያጧጡፈው ያዘ።በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የተተከሉ ማሽነሪዎች፤ የፋብሪካ አካላት፤ ተሽከርካሪዎች፤ የኢንዱስትሪ ምርቶች እና ሌሎችም ዓይነ-ግቡ ንብረቶች በግላጭ እና በአሳቻ ሰዓትም ጭምር ተጭነው ተወሰዱ።
ሰባ ከመቶውን ሀብት በዘረፋ ካጓጓዘ በኋላ ከተቀረው ሠላሣ ከመቶው ላይ ደግሞ ሰባ ከመቶውን ለራሱ የደለደለበት የጣና በለስ ፕሮጀክት የአሸባሪው ህወሓት የዘረፋ እና የስግብግብነት ዓይነተኛ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።በየክልሉ የተተከሉ የጠጠር ማምረቻ ማሽኖች፤ ከመልጌ ወንዶ፤ ከጦላይ፤ ከወለጋ እርሻ ልማት፤ በተለይም ከመከላከያ ኮንስትራክሽን ድርጅት (መኮድ) የሸሸውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አንጡራ ሀብት በማንሳት ለቀባሪው ለማርዳት አልሞክርም።ከማሻ መዳረሻ እና ከበበቃ እርሻ ልማት ተፈትተው ስለተወሰዱት የብረት ተገጣጣሚ ድልድዮች፤ የደብረ ማርቆስ ሕዝብ ወያኔ ጥርስ ውስጥ
ስላስገባው ጠጠር ማምረቻ “እወስዳለሁ፤ አትወስድም” ውዝግብ እና ሌሎች ጥቃቅን ጉዳዮች ላወጋችሁ እምብዛም አይዳዳኝ።ኢትዮጵያን እያራቆቱ ኢትዮጵያዊነት ምን ማለት እንደሆነ ግን ከስሩ ይሰመርልኝ።
አሸባሪው ህወሓት ለንግድ ድርጅቶቹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትዕዛዝ ወስዶት ሲያበቃ “የተበላሸ ብድር” ስላስባለው በመቶ ሚሊዮኖች ስለሚቆጠረው ገንዘብም ማውራት ያለብኝ አይመስለኝም።በተደራጀ እና በተቀናጀ ዘረፋ በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሕልውና ላይ ተደቅኖ ስለለነበረው የመንኮታኮት አደጋ የአዋጁን በጆሮ ሹክ ማለት አይጠበቅብኝም።የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በምን ሁኔታ ለእነ ማን እንደተላለፉ ለማተትም ቢሆን ጊዜው ይበቃን አይመስለኝም።ከሞያሌ፤ ከሀርጌሳ፤ ከቶጎ ውጫሌ፤ ከጂቡቲ በሚሌ፤ እንዲሁም መተማን ይዘው ከሁሉም የድንበር ኬላዎች በኩል የመከላከያ ከባድ ተሽከርካሪዎችን ጭምር በመጠቀም ሲካሄድ ስለነበረው የወጭ እና ገቢ ኮንትሮባንድ ንግድ እያወራሁ ላታክታችሁ አልፈልግም።በነገራችን ላይ በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙዎች ብዙ ቢሉበትም በኢትዮጵያ ኪሳራ የመወዳጀት የጫጉላ ሽርሽር ፍቅራቸው ሲያበቃ ህወሓት ላይ የመጀመሪያውን ጥርስ ያላሳበረ እርግጫ የሰነዘረው ተስፋዬ ገብረአብ እንደነበር ልብ ይሏል።ሌባ ከሌላ መንትፎ ወደ ቤቱ ያመጣ ይሆናል እንጂ ከራሱ አይሰርቅም።አሸባሪው ህወሓት ግን ኢትዮጵያን እያራቆተ በአድራጊ ፈጣሪነት የሥልጣን ዘመኑ በውጭ አገራት ሀብትና ንብረት በማከማቸት ተግባር ተጠምዶ ከርሟል።
ይህ አልጠግብ ባይ ድርጅት በአገዛዝ ዘመኑ ከዐጼ ኃይለሥላሴም ሆነ ከደርግ የአስተዳደር ሥርዓቶች በእጅጉ የላቀ የውጭ ብድርና ዕርዳታ ማግኘት ችሎ ነበር።ነገር ግን ከውጭ ተገኘ ከተባለው የገንዘብ መጠን ጋር የሚስተካከል 31 ቢሊዮን ዶላር ከአገር በማሸሽ የሚቀጥለውን ትውልድ ሳይቀር በዕዳ ዘፍቋል።
ያዲያቆነ ሰይጣን እንዲሉ እነሆ ዛሬም ህወሓት ባንኮችን እየዘረፈ፤ ትምህርት ቤቶችን፤ የጤና እና የእምነት ተቋማትን እየመዘበረና እያወደመ ይገኛል።ከኢትዮጵያ እየዘረፉ እና ኢትዮጵያን እያወደሙ ኢትዮጵያዊነት ይኖር እንደሆነ እኔ አላውቅም።
7. ኢትዮጵያን የማፍረስ አባዜ፡- ኢትዮጵያ ከሦስት ሺህ ዓመታት የዘለገ (አንዳንድ ጸሓፍት ለምሣሌ ፍቅሬ ቶሎሣ፤ የኢትዮጵያን የሥልጣኔ እና የሥነ መንግሥት ታሪክ እስከ ዘመነ ኖሕ ያደርሱታል) የጥንታዊ ሥልጣኔ ታሪክ ባለቤት ናት።ይህን በመከራ ውስጥ የሚፋፋ እና ቢቀብሩትም የማይጠፋ የኢትዮጵያዊ ማንነትን ማኅተም ለመቅበር የህወሓትን ያህል ቀን ተሌት የደከመ ያለ አይመስለኝም።
አሸባሪው ህወሓት ተቋማትን በልኩ እየቀደደ በመስፋት ኢትዮጵያዊ ገጽታ እንዳይላበሱ አሽመድምዷቸዋል።ለሙያ፤ ለክህሎትና ልምድ ተገቢውን ዋጋ በመንፈግ ተቋማት ሁሉ እንደ በቀቀን ከተነገራቸው ውጭ እንዳያስተጋቡ በዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት ጥብቅ ጥርነፋ ስር ወድቀዋል።ከዚህም የተነሳ በሁሉም የሥልጣን እርከን የሚቀመጡ ሰዎች በዋናነት የግል ጥቅማቸውን፤ እልፍ ካሉም እንደ ጓያ ነቃይ የፊት የፊቱን ብቻ እንጂ የአገሪቱን መጻዒ ዕድል ፈንታ ራቅ እና ፈቀቅ አድርገው እንዳይመለከቱ ተደርገው ነበር የተዋቀሩት፡፡
ይህ ደግሞ ታስቦበት እንጂ በድንገት የሆነ አልነበረም።የብሔረሰቦች ጥናት ተቋም፤ የሥርዓተ ትምህርት ምርምር ተቋም፤ በየዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የታሪክ ትምህርት ክፍሎች እና ሌሎችም የሚዘጉት እና የሚታጠፉት ይሁነኝ ተብሎ እንጂ በአጋጣሚ አልነበረም።የእነርሱ ሥልጣን እስከ አምሣ ዓመት ከዘለቀ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የሚል ትውልድ እንደማይኖር በድፍረት ይነግሩን የነበረውም ቀድሞ የታሰበበት ጉዳይ ሆኖባቸው እንጂ የምላስ ወለምታ ገጥሟቸው አይደለም።
አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን በቀበኛ እጆቹ ጠፍጥፎ ያበጃት እና ሲሻውም የሚፈረካክሳት የሸክላ ዕቃ አድርጎ ይቆጥራታል።ኢትዮጵያዊነትን በማኮሰስ ኢትዮጵያ አትፈርስም።ኢትዮጵያውያንን በጎሣ እና ጎጥ በመሸንሸንም ኢትዮጵያ ሕልውናዋን አታጣም።ኢትዮጵያዊነት የሕብር መገለጫ፤ የዜግነት ክብር እና ኢትዮጵያዊ በመሆን ብቻ የሚገነዘቡት እውነት እንጂ ውኃ የማይቋጥር የቀላማጅ ተረክ አይደለም።ለዚህም ነው ለሃያ ሰባት ዓመታት ልዩነትን ብቻ እየቀለብን ያሳደግናቸው ወጣቶች ሳይቀሩ ትርክቱን ወዲያ አሽቀንጥረው ጥለው፤ ለህወሓት ክህደት ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ሲሉ ቀፎው እንደተነካበት ንብ ከአራቱም ነፋሳት አገራቸውን ለመታደግ ለዘመቻ የተመሙት።እነዚህ ወጣቶች የአገራቸውን ባንዲራ ለብሰው ስቅስቅ ብለው ሲያለቅሱ ላስተዋለ ሁሉ የኢትዮጵያ ምንነት እና ኢትዮጵያዊ ማንነት በማያሻማ መልኩ ይገለጹለታል።ህወሓት ግን ኢትዮጵያን ለማፍረስ እስከ ሲዖል ለመውረድ ይዝታል።
የአሸባሪው ህወሓት ዓላማ ኢትዮጵያን መገንባት ቢሆን ኖሮ ለሃያ ሰባት ዓመታት የማዕከላዊ መንግሥቱን ሥልጣን ያለተቀናቃኝ ተቆጣጥሮት ዘልቋል።በእነዚህ ዓመታት ሁሉ ኢትዮጵያን ጥቂት በጥቂቱ እያፈረሳት እንጂ እየገነባት አልነበረም።ይልቁንም ከአንድ ትውልድ በላይ ሥልጣን ላይ ሲቆይ በኢትዮጵያውያን መካከል አለመተማመንን እና እርስ በእርስ መጠራጠርን በማንገሥ ከጎሣ እና ጎጥ ተሻግረን ማሰብ እንዳንችል ህወሓት ያለ ዕረፍት ይታትር ነበር።የክፉ ምኞቱ አልሰመረለትም እንጂ ከማዕከላዊ መንግሥት መንበር ገሸሽ ሲደረግና አድራጊ ፈጣሪነቱ ሲከዳው፣ በየብሔረሰቡ ጉያ ውስጥ ያጠመዳቸው የጠላትነት ፈንጂዎች ከየአቅጣጫው እየተስፈነጠሩ አገሩን መያዣ መጨበጫ በነፈጉት ነበር።እንዲያው ለመሆኑ፤ ኢትዮጵያን ለሚጠላ ድርጅት ኢትዮጵያ ምኑ ናት? እርሱስ ከኢትዮጵያ ምንድን ዕድል ፈንታ አለው?
8- ኢትዮጵያን እና ብሔራዊ ጥቅሟን ለአደጋ ማጋለጥ፡- የኢትዮጵያ ታሪክ በአመዛኙ ከጦርነት ጋር ይያያዛል።የውስጡን ለጊዜው እንተወውና ከባዕዳን ጋር የገጠምናቸው ውጊያዎች ሁሉ እኛ ድንበር ተሻግረን ሄደን ሳይሆን ዳር ድንበራችንን አልፈው ከወረሩን ባላንጣዎቻችን ጋር ያደረግናቸው ጦርነቶች ናቸው።ብዙዎቹ ጦርነቶችም ቢሆኑ በእኛ አሸናፊነት የተቋጩ እንደመሆናቸው የወራሪዎቻችንን ጥያቄዎች በአዎንታ የመለሱላቸው አልነበሩም።ታዲያ እነዚያ ጦርነቶች በተመሳሳይ ይዘት፤ ነገር ግን ቅርጻቸውን ቀይረው ደግመው እንደማይከሰቱ ምንም ማስተማመኛ የለንም።
የአድዋው ድል የማይጨውን እልቂት አላስቀረልንም።ግብጽ በሐረርም፤ በምጽዋም፤ በመተማም መንገድ ከማሳሰር በቀር ኢትዮጵያን የመውረር ዓላማዋ ሁሌም ኩልል ጥርት ብሎ የሚታይ ነው።ጠላቶቿ የማይተኙላት አገር ደግሞ ተገዳዳሪዎቿን እና ታሪካዊ ተቀናቃኞቿን ተኝታ ልትጠብቃቸው አይገባትም።እንግዲያውስ፤ ኢትዮጵያ አለኝ ብላ በምትኮራበት የሰሜን ዕዝ ላይ አስነዋሪ ጥቃት መሰንዘር እና ኢትዮጵያ ተበድራና ተለቅታ ሳይቀር ያሰባሰበችውን ትጥቅ መዝረፍ ምን የሚሉት ኢትዮጵያዊነት እንደሆነ አይገባኝም።
ይህ ጥቃት የልብ ልብ የሰጣት ጎረቤት አገር ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር ተሻግራ ወረራ ስትፈጽም መስተዋሉም የአጋጣሚ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ የሚቆጠር ነገር ሊሆን አይችልም። አይደለምም። ህወሓት ከምሥረታው አንስቶ የኢትዮጵያን በጎ ማየት ከሚጓጉጣቸው የቅርብ እና ሩቅ ተገዳዳሪዎቻችን ዙሪያ መለስ ድጋፍ እያገኘ መዝለቁ እሙን ነው።ህወሓትን እና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ብረት የሚያነሳ ማንኛውንም ወገን ተገን በመስጠት፤ ትጥቅ በማቅረብ፤ ስልጠና በመስጠት ቀዳሚውን ሚና ከሚጫወቱ አገሮች መካከል ግብጽ በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች፡፡
በኢትዮ-ኤርትራ ግጭት ወቅት የግብጽ ሚና ምን እንደነበር ለህወሓት ለመንገር መሞከር ለቀባሪው ማርዳት እንዳይመስልብኝ እሰጋለሁ።በሕዳሴው ግድብ ምክንያት ግብጽ ኢትዮጵያን ያላሳቀለችበት ደብር፤ ያልከሰሰችበት ችሎት፤ ያልዛተችበትና ያላስዛተችበት የዓለም አደባባይ፤ ያላጠመደችው አሽክላ ይኖር እንደሆን እኔ አላውቅም።የቀጥታ ግብግቡን ውጤት ጥንትም ታውቀው ስለነበር አልዘለቀችበትም እንጂ ከሱዳን ጋር የጦር ልምምድ እስከማድረግ ደርሳ ነበር።ግብጽ ኢትዮጵያን ለመውረር ዛቻ ስታዥጎደጉድ ከሱዳን በተጨማሪ ህወሓትም ለሀሳቧ ታማኝነቱን አልነፈጋትም።ህወሓት ባገኛት ሽንቁር አጋጣሚ ሁሉ ከኢትዮጵያ ታሪካዊ ተቀናቃኞች ጋር ግንባር በመፍጠር የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፎ ከመስጠት እና ኢትዮጵያን ከማጥቃት የማይታቀብ ከሆነ የዚህ ድርጅት ኢትዮጵያዊነት የቱ ላይ ነው?
9. ትግራይ ከህወሓት እንጂ ከሌላ ከማን ነጻ ይወጣል? ህወሓት በትጥቅ ትግሉ ዘመን ለ17 ዓመታት፤ በፈላጭ ቆራጭነቱ ጊዜ ለ27 ዓመት፤ ወደ መቀሌ ካቀና ጀምሮ እስከ አሁን ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ፤ በጥቅሉ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ለተጠጋው ዘመን የትግራይን ሕዝብ በምርኮ ይዞት ይገኛል።በእነዚህ ለሁለት ትውልድ ለተጠጉ ዓመታት ሁሉ የትግራይ ሕዝብ ከህወሓት የተዛባ ትርክት ውጭ ሌላ ድምጽ እንዳይሰማ ተደርጎ በግዞት እንዲኖር የተፈረደበት ይመስላል።የትግራይ እናቶች የወላጅ ወጉ እንዲደርሳቸው፤ ልጆቻቸው ደርሰው እንዲጦሯቸው ያልታደሉ ይመስል ከስር ከስር ትርጉም ለሌለው ጦርነት እየተማገዱ፤ ከአንዱ ሐዘን ሳይጽናኑ ሌላ መርዶ ይደርሳቸዋል።ወላጆች የምጥ ቀናቸውን የሚረግሙት እና መካንነትን የሚመኙት እስከ መቼ ነው?
አሸባሪው ህወሓት ሕዝቡን “እኔ ከሌለሁ፤ አበቃልህ” እያለ ትግራዋይ የተቀረውን ኢትዮጵያዊ ወገኑን እንዲጠራጠር እና በስጋት እንዲኖር አድርጎታል።ወያኔ፤ የትግራይ ሕዝብ ከህወሓት በፊት የነበረ፤ ከህወሓትም በኋላ የሚኖር መሆኑን ማስታወስ አይፈልግም።ታዲያ ሕዝቢ ትግራይ ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወንድምና እህቱ በጥርጣሬ እና ጠላትነት እንዲተያይ ካደረገ፤ የህወሓት ኢትዮጵያዊነት የቱ ላይ ይሆን?
ሲጠቃለል፤ ኢትዮጵያዊው የትግራይ ሕዝብ ለታሪኩ፤ ለክብሩ እና በአስተሳሰብም ሃያ አንደኛውን ክፍለ ዘመን የሚመጥን እውነተኛ ወኪል እንጂ በስሙ የሚነግድ የህወሓት ዓይነት ሐሳዊ መሲሕ ሁሌም ከምጣድ ወደ ረመጥ እያንሸራተተ እንዲያበግነው መፍቀድ የለበትም።ህወሓትን “ይአክል” ለማለት ጊዜው አሁን ካልሆነ፤ መቼ ሊሆን ይችላል? እዚህ ላይ ቆም ብለን ማሰብ ካልቻልንስ መካረሚያችን እንዴት፤ መዳረሻችንስ የት ይሆናል?
የተቀረነው ኢትዮጵያውያንም ብንሆን ህወሓትን መጥላት ብቻውን ኢትዮጵያን መውደድ አለመሆኑን ልብ ልንል ይገባናል! የተደገሰልንን ጥፋት እጅ ለእጅ ተያይዘን፤ በእውነተኛ የወንድማማችነት መተማመን ሁላችንም የምናሸንፍበትን ዓላማ አንግበን የጋራ ወደ ሆነው አገርን ከፍ ወደ ማድረግ አቅጣጫ መትመም ይጠበቅብናል።በጥቃቅን ልዩነቶች እየተጠላለፍን እና አንዳችን ሌላውን በሾኬ እየጣልን የትም ልንደርስ እንደማንችል ትምህርት መቅሰም ካለብን ጊዜው አሁን ይመስለኛል።አገራችንን ማንም የሚገባውን የማያጣባት፤ ማንም በሌላው ጉስቁልና የማይቀናጣባት የእኩልነት ምድር ለማድረግ በየተሰማራንበት መስክ ሁሉ የየበኩላችንን ጡብ እናቀብል።በታታሪነት፤ በቅንነት እና ታማኝነት የዜግነት ግዴታችንን እንወጣ።በትናንቶች መነታረክን ትተን እና ነገን ታሳቢ አድርገን ከሠራን
ኢትዮጵያ ለሁላችንም የምትበቃ፤ ሁላችንንም የምታኮራ ለጋስ እናት ናት።
ዓለማየሁ ደበበ
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም