ለውጥ በባህሪው በብዙ ፈተናዎች የተሞላ ነው ። አሸናፊ ሆኖ ለማሻገርም ከሁሉም በላይ ራስን እንደ ግለሰብ ሆነ እንደ ማኅበረሰብ ማዘጋጀት ከፍያለ ትኩረት የሚሻ ነው ። የዝግጁነቱ መጠንም ለለውጡ ስኬት ወሳኝ አቅም እና ምዕራፍ ተደርጎ ይወሰዳል ።
በቀደሙት ዘመናት የመጣንባቸው የለውጥ መንገዶች የታሰበላቸውን ያህል ውጤታማ ከመሆን ይልቅ የከፋ ችግርና ግራ መጋባት ምንጭ የሆኑትም ለለውጦቹ የነበረን ሁለንተናዊ ዝግጅት ከፍ ያለ ክፍተት ስለነበረው እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ይህንን ክፍተት ግለሰቦችና ቡድኖች ባልተገባ መንገድም ተጠቅመውበታል።
በአንድ በኩል ስለለውጡ የጠራ ግንዛቤ ባለመያዝ ነገሮችን ደመነፍሳዊ በሆነ መንገድ ለመቀበልና ለመተግበር የተሄደበት መንገድ፤በሌላ በኩል ደግሞ ለውጡን በቡድን አሸናፊነት ለመጠቅለል የተሰላው ያልተገባ ስሌት የለውጡን አገራዊ ፋይዳ አክስሞታል።
ከዚህም በላይ ቡድናዊ አሸናፊነትን ለማፅናት የተፈጠሩ የተሳሳቱ ትርክቶችና ትርክቶቹ የፈጠሩት የአስተሳሰብ መዛነፎች ሕዝባችን ተስፋ ላደረገው ለውጥ ትርጉም የለሽ ብዙ ዋጋ እንዲከፍል ተገድዷል።
ይህንን እውነታ ከትናንት ተጨባጭ የለውጥ ተሞክሮዎች ተምረን ማረም ካልቻልን ዛሬ የጀመርነው የለውጥ ጉዞ በተግዳሮቶች ብዛት ሊቀለበስ የሚችልበት ደረጃ ላይ እንደማይደርስ ለውጡ በራሱ ማስተማመኛ ሊሆን አይችልም። ከዚህ ይልቅ ማስተማመኛ የሚሆነው የለውጥ ኃይሉም ሆነ የለውጡ ተሸካሚ የሆነው ሕዝብ ሁለንተናዊ ዝግጁነት ነው።
ከዚህ አንጻር አንዳንድ ነገሮችን በአግባቡ ጊዜ ወስደን እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ሕዝብ ልናያቸው ይገባል። ከነዚህም ውስጥ በዋነኛነት ጠላቶቻችን እነማን ናቸው? ፤ በእጃቸው ላይ ያለው የማጥመጃ መረብ ምን ይመስላል? ፤በመረቡ ላለመያዝ ምን ማድረግ ይገባናል? ለሚሉት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ያስፈልጋል ።ለነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጣቸው ምላሾች የጀመርነውን ለውጥ በስኬት ለማጠናቀቅ ወሳኝ አቅም ናቸው።
የቀደሙት የለውጥ ታሪኮቻችን ስኬት አልባ እንዲሆኑ ካደረጓቸው ተግዳሮቶች ውስጥ ትልቁና ዋነኛው በለውጥ መንፈስ አለመደማመጣችን እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ለዚህም እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ቡድን የተያዙ የለውጥ አስተሳሰቦች የሕዝብን ቀዳሚ ፍላጎት ያላስተናገዱ፤ የሕዝቡን ማኅበራዊ ስነልቦና መሰረት ያላደረጉ ስለመሆናቸውም በስፋት ይነገራል ።
አገራዊ የነበረው የለውጥ መንፈስና ከዚሁ መንፈስ የሚቀዳውን አስተሳሰብ በሂደት በመንደርተኝነት አስተሳሰብ መጠለፉ ፤ከዛም በላይ ለመንደርተኝነቱ ሕይወት ለመስጠት የተፈበረኩ ትርክቶች ዋነኛውን የለውጥ አስተሳሰብ አኝከው ትርጉም እና ጣዕም አልባ አድርገውታል።
ይህ እውነታ የለውጥ ኃይል የሆነውን ሕዝብ ባልተገባ ሁኔታ ከመከፋፈል አልፎ ፤ በሕዝቦች መካከል ተቃርኖ በመፍጠር አጠቃላይ የሆነውን አገራዊ የለውጥ መንገድ ወዳልተገባ ሁከትና ግርግር ፤ የእርስበርስ ግጭትና የጥፋት ማዕከል አድርጎታል።
በዚህም ለውጡ በግለሰቦችና ቡድኖች ተራ ፍላጎት እንዲጠለፍ ሆኗል። እንደ አሸባሪው ህወሓት ዓይነት ፍጹም አምባገነናዊ ቡድን በንጹሓን የለውጥ ተስፋ እና የመስዋዕትነት ደም እንዲፈጠር አድርጓል።
ራሱን የለውጥ ኃይል ነኝ ብሎ በሚያምነውና የለውጡ እውነተኛ አቅም በሆነው ሕዝቡ መካከል ስለ ለውጡ የጠራ ግንዛቤ አለመፈጠሩና ፤ ከዚህ የሚመነጭ ዝግጁነት አለመኖሩ ለውጡ በራሱ አገራዊ አደጋ እንዲሆን አድርጎታል ። በዚህም አገርን እንደ አገር የቱን ያህል ከፍያለ ዋጋ እንዳስከፈለንና ዛሬም የዚሁ ችግር ጥላ ምን ያህል እየተፈታተነን እንደሆነ ለመናገር የሚከብድ አይደለም።
ይህንን እውነታ ዛሬ ላይ በአግባቡ ካልተረዳነውና ትምህርት ካልወሰድንበት ለነገዎቻችን ተስፋ አድርገን ብዙ ዋጋ እየከፈልን ያለነው የአሁኔው የለውጥ ጅማሬያችን በተመሳሳይ መልኩ ላለመጠለፉ መተማመኛ የለንም። መተማማኛ ሊሆነን የሚችለው ለውጡን ለማሻገር ያለን ሁለንተናዊ ዝግጅት ብቻ ነው።
ለዚህ ደግሞ ከሁሉም በላይ በለውጡ መንፈስ ውስጥ ሆነን መደማመጥ ያስፈልጋል። ከዚህም ባለፈ የጠላቶቻችንን አሰላለፍና የአቅማቸውን ምንጭ ማወቅና ከዚህ የሚመነጨውን ፈተና በለውጡ መንፈስ ውስጥ ሆኖ መረዳትና ከዚህ መንፈስ በሚቀዳ የተግባር ቁርጠኝነት እራስን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። ለውጡን በመንደርተኝነት ፣ በቡድነኝነት እና ማንነትን መሰረት ባደረገ መንፈስ ከመሸፈን ራስን መቆጠብንም ይጠይቃል ።
ታሪካዊ ጠላቶቻችንን ጨምሮ የነሱን አጀንዳ ተሸክመው ለውጡን እየተፈታተኑ ያሉ ኃይሎች እየቆፈሩልን ባለው ቦይ አለመፍሰሳችንን በአግባቡ ማረጋገጥ፣ ለዚህ የሚሆን በቂ ዝግጁነት እንዳለን ሁሌም ራሳችንን መፈተሽ ይጠበቅብናል። ስህተታችንን ለውድቀታችን አቅም አድርጎ በትጋት የሚሰራ ጠላት እንዳለንም መዘንጋት አይገባም።
ለዚህም የለውጡ ኃይል ያለበትን ኃላፊነት በራሱ አቅምና ቁመና እንዲወጣው እድሉን መስጠት ፣ቋንቋን ከሚደበላልቅ ስሜታዊና ደመነፍሳዊ የትግል መንገድ መውጣት፤ የለውጡን ትልቁን ኃይል /ሕዝቡን/ከሚከፋፍልና ቡድንተኝነትን ከሚፈጥር አስተሳሰብ መራቅና አስተሳሰቡን እንደ አስተሳሰብ መዋጋት ያስፈልጋል። ከዚህም በላይ ፈተናን በለውጥ የመንፈስ ጽናት መሻገር የሚያስችል ማንነት መገንባትም ወሳኝ ነው!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም