በዚህች ምድር ስንኖር እያንዳንዳችን የየራሳችን የሕይወት ፍልስፍና አለን። ኑሯችንንም የምንመራው በአሰብነውና መሆን በምንፈልገው ልክ እንደሆነ ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ አካላት የነገ እጣ ፋንታቸውን ጭምር በእጃቸው ይዘው የሚዞሩ ናቸው። ፍላጎታቸውን ለማሳካት ከጣሩበትና ወደ ተግባር ከገቡበት ነጋቸውን ብሩህ እንዳያደርጉ፣ ያሰቡት ላይ እንዳይደርሱ ማንም ሊያግዳቸው አይችልም። ምክንያቱም ዛሬ ላይ ሆነው ነገን ያልማሉና በፈተና ለመውደቅ እጅ አይሰጡም። ትናንት መሆን የፈለጉትን ዛሬ ሆነውት እንኳን ሌላ ነገን መስራት ይሻሉ፤ ለዚያም ይተጋሉ። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ለዛሬ ‹‹የሕይወት ገጽታ›› አምድ እንግዳችን ቆሞስ አባ ጌዲዮን ብርሀነ አንዱ ማሳያ ናቸው።
እርሳቸው ነገን ሲያስቡ የተማረ መነኩሴ መሆንን አቅደዋል። ለዚህ ደግሞ በከባድ ችግር ውስጥ ቢያልፉም ሁልጊዜ መማርን ያስቀድማሉ። በዚህም ዛሬ አምስት የሚሆኑ ሁለተኛ ዲግሪዎችን በ43 ዓመታቸው በተለያዩ የትምህርት መስኮች የያዙ ሆነዋል። አሁንም ነገ ሌላ ቀን ነውና ሌላ ህልምን አቅደዋል። ይህም አገራቸውንና ቤተክርስቲያንን በእውቀት ማገልገል ሲሆን፤ ለዚህ ደግሞ በእርሳቸው እምነት ትምህርት ማለቂያ ሊኖረው አይገባም ብለው እየተማሩ ይገኛሉ። ምድራዊ ህይወታቸው በትምህርትና በተማሩበት በማገልገል እንዲያልቅ ይፈልጋሉ። ሰዎችም ይህ መርሐቸው እንዲሆን ይመኛሉ። ይህ አስተሳሰብ እንዴት መጣና መሰል የሕይወት ተሞክሯቸው እንዴት ተገነባ የሚለውንም ልምዳቸውን አጋርተውናልና ለሕይወታችሁ መቀየር ትጠቀሙበት ዘንድ ተሞክሯቸውን አጋራናችሁ። መልካም ንባብ።
የእናት ልጅ
የተወለዱት ከአሰላ ትንሽ ወረድ ብላ በምትገኘው አርሲ ላይ ዴራ አማኑኤል በሚባል ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው። አስተዳደጋቸው እጅግ ፈተና የበዛበትና እራሳቸው እየሰሩ ጭምር የተማሩበት ነው። ምክንያቱም እናታቸው ብቻቸውን ነው ያሳደጓቸው። ይህ ደግሞ እርሳቸውን ማገዝ ግድ ስለሆነባቸው የሚያደርጉት እንደነበር ይናገራሉ። እናም ከትምህርት ጎን ለጎን የማይሰሩት ሥራ አልነበረም። እንዲያውም ለእርሳቸው ነብስ ማወቅ ሥራ መስራት መጀመር ነበር። በዚህም ሰባት ዓመት ላይ እናታቸውን ማገዝ ጀምረዋል። ከመቦረቁና መጫወቱ ይልቅ ወደ መሥራቱ የገቡትም በዚህ ጊዜ ነው።
በአብዛኛው የግብርና ሥራዎችን ከወንድሞቻቸው ጋር ማከናወን ዋና ተግባራቸው የሆነው ባለታሪካችን፤ ደከመኝ ሰለቸኝን አያውቁም። ምክንያቱም ለእርሳቸው እናታቸው ከምንም በላይ ናት። በእርግጥ ከሥራዎች ሁሉ የጓሮ አትክልቶችን መንከባከብና ጥሩ ምርት እንዲሰጡ ማድረግ ብዙ ልፋትን ይጠይቃቸዋል። ልፋቱ ደግሞ ውሃ ቀድቶ ማምጣት ነበር። በእነርሱ አካባቢ ውሃን በቀላሉ ማግኘት ፈጽሞ አይታሰብም። ስለዚህም ርቀት ሄዶና ወረፋ ይዞ ማምጣት ግድ ነው። በዚህም ገና ሳይነጋ ጨለማውን ተጋፍጠው የሚሄዱበት ጊዜ ቀላል አልነበረም። ይህ የማይሆንላቸው ከሆነ ደግሞ ወንዝ ዳር ማደር ግድ ይሆናል። እናም ይህንን እያደረጉ ነው ኃላፊነታቸውን የተወጡት።
ውሃ ቀድተው ከመጡ በኋላም በደከመ አዕምሮ ለተክሎቹ ማጠጣት እጅግ ይፈትናቸው ነበርም። ከዚያ በኋላ ሁለት ሰዓት ተጉዘው ለመማር መሄድም ያማርር ነበር። በተጨማሪ ለቀለብ፣ ለትምህርት ቤትና ለልብስ የሚሆኑ ተጨማሪ የገቢ ምንጮችን ማግኘትም ያስፈልጋቸዋል። ለዚህም ከትምህርት መልስ የተለያዩ የንግድ ሥራዎችን ያከናውናሉ። ይህም ሌላ ድካም እንደሆነ ግልጽ ነው። ነገር ግን ኑሮን ለማለፍና የተሻለውን ቀን ለማየት ግድ እንደሆነ ስለሚያምኑ ያደርጉታል።
በእነርሱ ቤት የእድሜ ገደብ አይሰራም። የሚችሉትን ሁሉ መሥራት ግዴታቸው እንደሆነ ይታመናል። እናም እንግዳችን ገና ጉልበታቸው ሳይጠነክር ነው በኃላፊነት ሥራዎችን የሚያከናውኑት። ትንሽ ሆነው ሳለ እርሻ ያርሳሉ፤ ወደ ገበያም ሆነ ወደ ወፍጮ ቤት የሚደርስ እህል ካለ መሸከምና ማድረስም ግዴታቸው ነው። በመሆኑም የልጅነት ጊዜያቸውን የሚያስታውሱት እጅግ ጥረትና ግረት የበዛበት እንደነበረ ነው።
እናታቸው ለእነርሱ ብላ የኖረችና የቆመች መሆናቸውን ስለሚያምኑ በሚደርስባቸው የሥራ ጫና አንድም ቀን አማረው እንደማያውቁ ያጫወቱን ባለታሪካችን፤ ሥራዎችን ሲያከናውኑ ደስተኛ ሆነው፣ በፍላጎታቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ከልጅነት ጀምሮ በፍላጎት መሥራታቸው ደግሞ አሁን ላለው ሥራ ወዳድነታቸው መሰረት እንደጣለላቸውም ያስረዳሉ። ማንም ቢሆን ጠንካራ የሚሆነው ልጅነቱ ላይ በተሰራበት ሥራ ነው የሚል እምነትም አላቸው። ምክንያቱም እናታቸው በትምህርትም፣ በሥራም፣ በሥነምግባርም ስለሰሯቸው ዛሬ ተመስጋኝ ሰው መሆን ችለዋል።
በልጅነታቸው የሥራ ወሰን ጭምር አያውቁም። በዚህም በተለምዶ ለሴት ተብለው ተለይተው የተሰጡ ሥራዎችን ጠንቅቀው ያውቁና ይሰሩም ነበር። ይህ ደግሞ ልዩ ችሎታቸውንና ፍላጎታቸውን የጠቆማቸው ሆኖላቸዋል። ከምንም በላይ ሰንበት በመጣ ቁጥር እናት ቤተክርስቲያን ተሳልመው እስኪመጡ ቡና በማፍላትና ቤት በማጽዳት የተካኑ ስለነበሩ ምርቃቱ ይጎርፍላቸዋል። ከምርቃታቸው አንዱ ደግሞ ዛሬ ላይ ያገኙት ‹‹ያሰባችሁት ይሳካላችሁ›› የሚለው የልጅነት ህልማቸው ነው። የተማረ መነኩሴ መሆን ህልማቸው ነበርና ተሳክቶላቸዋልም። በባህሪያቸውም ቢሆን ቁጥብ፤ ትንሽ ልጅ በመሆናቸው የደማ ስራ ባይሰሩም ሥራ ወዳድና ሰዎችን በመርዳት የሚያምኑ እንዲሁም እናታቸውን የሚንከባከቡ ለመሆናቸው ምስጢሩ ይህ እንደሆነም ይናገራሉ።
የማይቆመው ትምህርት
እርሳቸው ትምህርትን በምሳሌ ካልሆነ በስተቀር በቃላት ለመዘርዘር ይቸግራቸዋል። በዚህም ትምህርት በበርሜል የተሞላ ውሃን በወንፊት መቅዳት ነው ይሉታል። ውሃው ባይቀዳም ቆሻሻው ግን ይወገዳል። ትምህርትም ጥርት ያለ ሚዛናዊ አመለካከትን የሚሰጥ መሰላል ነው እንደእርሳቸው ብያኔ። ትምህርት ሂደትም ነው። በዚህ ጉዞ ውስጥ ሲኮን ደግሞ የተሻለና የጠራ አመለካከትን እየያዙ መጓዝን ያመጣል። ከዚህ በተጓዳኝ የጠፉ አመለካከቶችን ለመፈለግና ዳግም ለማምጣት ያስችላል። የተሰወሩ ነገሮችን ለመግለጥ ይረዳል። አዕምሮን የሚያበራ ነው ሲሉ ያብራሩታል።
ይህንን ማብራሪያ እንዲሰጡ ያስቻላቸውና ለትምህርት ጅማሯቸውም መሰረት የሆኗቸው ደግሞ እናታቸው ሲሆኑ፤ ለመማር ብዙ መስዋዕትነትን እንደከፈሉ ያውቃሉ። እነርሱን ለማስተማርም ቢሆን እንዲሁ ብዙ ነገራቸውን መስዋዕት አድርገዋል። በዋናነት መማራቸውን ለእነርሱ ሲሉ ትተዋል። ምክንያቱም እናት እስከ አዲስ አበባ ዘመድ ጋር ድረስ ሄደው እንዲያስተምሯቸው ጠይቀው አልተሳካላቸውም። በራሳቸው መማር ግን ይችሉ ነበር። ሆኖም የልጅ ጉዳይ ሆነባቸውና ተውት። እናትም አባትም ሆነው ብቻቸውን ‹‹በልጆቼ አየዋለሁ›› ብለው ልጆቻቸውን ወደማስተማሩም ገቡ። በዚህም ልጆቻቸው ቁርጠኛ እንዲማሩ ሆኑ።
አባ ጌዲዮን የእርሳቸው አርአያነት ያልገባው ልጅ ለመሆን አይፈልጉምና አሰቡት ላይ ለመድረስ በሚገባ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል። የትምህርት ዳዴያቸው የጀመረው በእናታቸው አማካኝነት በቀድሞው አርሲ ክፍለሀገር በአሁኑ አርሲ ዴራ አማኑኤል የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ እስከ ስድስተኛ ክፍል ትምህርታቸውን ተከታትለውበታል። ከዚያ በአቅራቢያቸው ትምህርታቸውን ሊያስቀጥል የሚችል ትምህርት ቤት አልነበረምና የእናታቸው እገዛ ሳይለያቸው ወደ አሰላ በመሄድ በቀን አራት ሰዓታትን በእግራቸው እየተጓዙ አሰላ ሁለተኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማር ጀመሩ። ሰባተኛና ስምንተኛ ክፍልን በትምህርት ቤቱ ተምረዋል።
ቀጣዩን ክፍል ያጠናቀቁትም እዚያው አሰላ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲሆን፤ የ12ኛ ክፍል ውጤታቸው ዩኒቨርስቲ የሚያስገባቸው ቢሆንም በቀጥታ አልገቡበትም። ምክንያቱም በአብነቱ ትምህርት መቀጠል ስለፈለጉ ይህ አልሆነም። ነገር ግን ቆይተው በዲፕሎማ በአልፋ ዩኒቨርስቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የትምህርት መስክ መመረቅ ችለዋል። በቲዮሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪም ጎን ለጎን ተምረዋል። ፖስት ግራጂዌት ዲፕሎማ የሚባል ነበርና በእርሱም በቲዮሎጂ ተመርቀዋል። በተመሳሳይ የአብነት ትምህርቱንም ገፍተውበታል። በደብረሊባኖስ ገዳም 11 ዓመታትን የተከታተሉ ሲሆን፤ ከንባብና ቁጥር ጀምረው ድጓ፣ ቅኔና ቅዳሴ የመሳሰሉት ትምህርቶችን ቀስመዋል።
መማር ማለቂያ የለውም ብለው የሚያምኑት ባለታሪካችን ቀጥለው በቀጥታ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ወደ መማሩ ነው የገቡት። በዚህም በቅድስት ስላሴ ዩኒቨርሲቲ በቲዮሎጂ፣ በሲስተማቲክ ቲኦሎጂ የተከታተሉት ሲሆን፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም በጥንታዊ የመዛግብት ጥናት/ፊዝዎሎጂ/፣ በካውንስሊንግ ሳይኮሎጂና በኤዱኬሽናል ፕላኒንግ ኤንድ ማኔጅመንት የትምህርት መስኮች ሁለተኛ ዲግሪያቸውን መስራት ችለዋል። አሁን ደግሞ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ለመያዝ የሦስተኛ ዓመት የሥነ ጽሁፍ ተማሪ ናቸው። ስለዚህም በቅርቡ የተመረቁበትን ጨምሮ ለሰባተኛ ጊዜ በትምህርት ምረቃን እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል።
‹‹ከምሰራው መንፈሳዊ ሥራ አንጻር ሥራ መፍታት አይፈቀድልኝም›› የሚሉት አባ ጌዲዮን፤ መማራቸውን እንዳያቆሙ የሆኑትና ወደፊትም በትምህርቱ እንዲቀጥሉ ያደረጋቸው ይህ ግዴታቸው ነው። ከአብነቱ ዘሎ መሄድንና አምስተኛውን የሁለተኛ ዲግሪ ያገኙበት መሰረታዊ ምስጢርም ይህ ሥራ አለመፍታታቸውና በአግባቡ ጊዜያቸውን መጠቀማቸው እንደሆነ አጫውተውናል።
እንደእርሳቸው እምነት መማር ብዙውን ሥራ ለማቅለል ይረዳል፤ ነገሮችን በጥንቃቄና በፍጥነት ለመከወን ያግዛል፤ ሚዛናዊ ያደርጋል፤ ለመግባባትም ቀላል የሆነ ግንኙነትን ይፈጥራል። በምክንያታዊነት ላይ የተመሠረተ ክህሎትንም ይሰጣል። ስለዚህም መማር ይህንን ሁሉ ከሰጠ ሰዎች መማርን መብት ሳይሆን ግዴታቸው ሊያደርጉት ይገባል ይላሉ። እርሳቸውም ቢሆን በ43 ዓመታቸው አምስት የሁለተኛ ዲግሪያቸውን የያዙት ይህንኑ መርህ ስለሚከተሉ ነው።
አባ ጌዲዮን ‹‹በትምህርት ራሴን አግኝቻለሁ፤ መሠረታዊ ነገሮቼን በብዙ መልኩም ቀይሬያለሁ፤ በህይወቴ ላጣው ላጎለው የማልፈልገው ነገርም አግኝቼበታለሁ። ሰዎችም ትምህርት ሁልጊዜ አዲስ ነገር ለማግኘት እንጂ ወረቀቱን ለመያዝ ብለው የሚያደርጉት እንዳይሆን እመክራለሁ›› ይላሉ። ምክንያታቸውን ሲያስረዱም ዲግሪውን ዲግሪ ወይም ዶክተሩን ዶክተር የሚያሰኘው ትምህርቱን የሚጠቀምበት መንገድ እንደሆነ በማንሳት ነው። ትምህርት ከወረቀት የሚዘለው መጀመሪያ ለእውቀት ብሎ መማር ሲጀመር ሲሆን፤ ሁለተኛ ክህሎት አድርጎ መተግበር ሲቻል ነው። ሁለቱ ተመጋግበው ሥራ ላይ ካልታዩ ስም ከመጥፋቱም በላይ አገርን ያስወቅሳል ባይ ናቸው።
‹‹ትምህርት የሚያልቅ ነገር ባለመሆኑ ገና ወደፊትም እማራለሁ። ምክንያቱም የዚህ ዓለም ምስጢር እያደር የሚደረስበት እንጂ አንድ ጊዜ የሚፈጸም አይደለም። በዚህም በመማር ይህንን አደርጋለሁ። ምሁር መሆን ከትምህርት ውጪ አይመጣምና እውነተኛ ምሁር ለመሆንም የእድሜ ልክ ተማሪ እሆናለሁ›› የሚሉት አባ ጌዲዮን፤ የሚማሩት በዓላማና ብዙ ሥራ ስለሚበዛባቸው እንደሆነ ይናገራሉ። ለምሳሌም በሥነጽሑፉ ዘርፍ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን የመማር ዓላማቸው በቃል የሰሙትን በመጽሐፍ ለመሰነድና ለአገርና ለቤተክርስቲያን አበርክቷቸውን ለማኖር እንደሆነ ያስረዳሉም።
እንደእርሳቸው እሳቤ ከ1960ዎቹ በኋላ የአውሮፓን የትምህርት ሥርዓት በአገራችን ልምድ እያደረግን የመጓዝ ሁኔታን በመፍጠራችን የራሳችንን እንድንረሳና መሠረቶቻችንን እንድንስት አድርጎናል። ይህ ደግሞ ቀጣይነት ያለው ጉዟችን እንዲገደብ አድርጎታል። በተለይም አገራዊ ትምህርት ከሌለ አገራዊ ማገልገል ሊመጣ አይችልምና ከዚህ አንጻር ያለማቋረጥ እንድማር ሆኛለሁም ብለውናል።
‹‹እኔ የእድሜ ልክ ተማሪ ነኝ›› ብለው የሚያምኑት አባ ጌዲዮን፤ መምህር የሆነ ሰው መማር ውዴታው ሳይሆን ግዴታው እንደሆነ ይናገራሉ። ምክንያታቸው መማር የማይችል መምህር ማስተማር አይችልምና ነው። ዓለምን ለማወቅ በየጊዜው መማርና መመራመር ግድ ይላል። እያደር ገንዘብ የሚደረጉት ትምህርት ሲኖር ምስጢሮች ከምስጢርነታቸው ማላቀቅ ይቻላል። ለዚህ ደግሞ ከአወቅነው መነሳት ያስፈልጋል። ይህም የአገር በቀሉ እውቀት ነው። እርሱን ትተን የምንጨምረው ነገር ራሳችንን እንድንክድ ያደርገናል። ምክንያቱም ኑሯችንም፣ ውሏችን አውሮፓዊ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይሆንም። ስለሆነም መነሻችንን ይዘን የእድሜ ልክ ተማሪ እንሁን ምክራቸው ነው።
የተማረ መነኩሴነት
ስለ ሥራ ጉዟቸው ከመናገራቸው በፊት የሥራን ዋጋ የሚያብራሩት እንግዳችን፤ እኛ የምንከተለው የመማር ማስተማር ሥርዓት አገርኛውን የተወና የውጪውን ማዕከል ያደረገ በመሆኑ አገራዊ ሁኔታውን እንዳናውቀው ተገድበናል። ይህ ደግሞ በአገሪቱ ያለውን አመለካከት መረዳት እንዳንችልና ግልጋሎታችን ማህበረሰቡን ያማከለ እንዳይሆን አድርጎናል። ማህበረሰቡ የማያውቀውን ጭምር ተግብር ማለትም የጀመርነው ከዚህ የተነሳ ነው። ሳንረዳው በግድ እንድንረዳው የሆነው የአውሮፓው የትምህርት ሥርዓት ሥራችን በእኛ ልክና ማኅበረሰቡን በያዘ መልኩ እንዳይካሄድ አድርጎታል። ስለሆነም ይህንን ማጥበብና ወደኛ መመለስ ያስፈልገናል ይላሉ።
ቀጥለውም በጥናታቸው ያዩትን ሀሳብ ያነሳሉ። ይህም አገር በቀልንና ዘመናዊውን የማስተማር ዘዴ በማነጻጸር የሰሩበት ሲሆን፤ ከተመለከቱት ውስጥ አንዱ የማስተማሪያ ዘዴ ነው። ኮንስትራክቲቭ ሜትዶሎጂ የተባለውን በመጥቀስም በ1986 ዓ.ም ጀምሮ የመጣና ሲደነቅ የቆየ የማስተማሪያ ዘዴ ቢሆንም መሰረቱ ግን 96 በመቶ የተቀዳው ከቅኔ ቤት ነው። ይህ የሚያሳየው ደግሞ መጀመሪያ ኢትዮጵያውያን ይህ ነገር እንደነበራቸውና ሲጠቀሙበት እንደቆዩ ነው። ነገር ግን ሌሎች አምጥተው አንደኛ እስኪሉን ድረስ የእኛ ነው ብለን አንቀበለውም። ስለሆነም ያለንን መመርመር ላይ ትኩረት ማድረግ አለብንም ብለዋል።
ቀድመን የራሳችንን ማየት ማንነታችንን እንድናገኘው ያግዘናል፤ ለወደፊት እንዴት መንቀሳቀስ እንዳለብንም ይመራናል፤ ያለንን እንድናውቀውም ይረዳናል የሚሉት አባ ጌዲዮን፤ ከሥራ ጋር በቅጥር የተዋወቁት በደብረሊባኖስ ገዳም ዘይነግድ የሚባለውን የአገልግሎት ሥራ በመስራት ነው። ለሦስት ዓመታት አገልግለውበታልም። በዚህ ሥራ ላይ ጸሎት ከማስጀመር እስከማሳረግ የሚደርሰውን ተግባር ፈጽመዋል።
አባ ጌዲዮን ስድስት ወር ደግሞ ከ12ቱ አርዕስተ አበው ጋር በመሆን ሰርተዋል። ከዚያ ወደ ጉዳይ አስፈጻሚነት አድገው ብዙም ሳይሰሩበት ወደ ትምህርት በማዘንበላቸው አቋርጠውታል። ይሁን እንጂ የአገልግሎትና የትምህርት ጉዳይ ከልባቸው ያለ ስለሆነ ሥራቸውን ወደ አዲስ አበባ መጥተውም ቀጥለዋል። ይህም በስብከተ ወንጌል ኃላፊነት ሲሆን፤ በአዲስ አበባ አያት ጌቴሰማኒ ኪዳነምህረት ቤተክርስቲያን ያገለገሉት ነው።
ዓመት ከአምስት ወር ከአገለገሉ በኋላ ደግሞ ወደ ቀበና ኪዳነምህረት ተዛውረው አሁንም በስብከተ ወንጌል ኃላፊነት ለዓመት ያህል ሰርተዋል። ቀጣዩ አገልግሎታቸው የሚወስደን ቁስቋም ማሪያም ቤተክርስቲያን ላይ ሲሆን፤ አሁንም በአገልግሎትም ሆነ በቦታ ቀደም ሲል ከአገለገሉባቸው ቤተክርስቲያን ጋር በሚመሳሰል ሁኔታ ሰርተዋል። ከዚያ ወደ 41 ኢየሱስ ቤተክርስቲያን ተዛውረው መሥራት ጀመሩ። በዚህም በስብከተ ወንጌል ኃላፊነት ለሰባት ዓመታት እንዲያገለግሉ ሆነዋል።
ቀጣዩ የሰሩበት ቦታ ቅዱስ ዮሴፍ ቤተክርስቲያን ሲሆን፤ ከሰባት ወር በላይ አልቆዩበትም። ምክንያቱም ወደ ሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን በአስተዳዳሪነት እንዲሰሩ በመዛወራቸው ጉዟቸውን ወደዚያ አደረጉ። በቤተክርስቲያኒቱ ሦስት ወር ብቻ ቢሰሩም ብዙ አስመስጋኝ ሥራዎችን ሰርተዋል። በተለይም ከመንፈሳዊ አገልግሎታቸው ባሻገር ማኅበረሰቡ ውስጥ በመግባት የሰሯቸው ተግባራት ከመንግስት ጭምር ምስጋና ያስቸራቸውና የምስክር ወረቀት ያሰጣቸው ነበር።
ከሐዋሳ በኋላ በቋሚነት ትምህርታቸውን እየተማሩ የሚያገለግሉት በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ ሲሆን፤ የንጽጽር ነገረ መለኮት እና የሳይኮሎጂ መምህርነት ናቸው። በተጨማሪ የማማከር ሥራም ይሰራሉ። በመንፈሳዊው በኩል ደግሞ ስብከተ ወንጌልን በመርካቶ ደብረአሚን አቡነተክለሐይማኖት ገዳም ይሰጣሉ። እነዚህን ተግባራት ሲያከናውኑ ደግሞ ሦስት መሰረታዊ ነገሮችን እንደሚጠቀሙ ይናገራሉ። የመጀመሪያው መስራት ሲሆን፤ በዩኒቨርሲቲ መምህር ሆነው በተለያየ መስክ ያስተምራሉ። ሁለተኛው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው አገልጋይ በመሆናቸው አገልጋይነትን በተግባር ማሳየት ነው። ሦስተኛው የእድሜ ልክ ተማሪ መሆንን ለሌላው በአርኣያነት ማሳየት ነውና እያደረጉት ይገኛሉ።
እንደእርሳቸው እምነት ተማሪ መሆን ቤተክርስቲያንንና አገርን በሚገባ ደረጃን በጠበቀ መልኩ ማገልገል ነው። ይህንን ደግሞ ከልጅነታቸው ጀምሮ አድርገውታል። ለዚህም ማሳያው በካውንስሊንግ ሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ ሲይዙ ማኅበረሰቡን አውቆ ለማገልገል በሚል አልመው መሆኑ ነው። ይህ የሚመጣው ደግሞ የጠራ አመለካከት እንዲኖር ሲሰራና መማር ሲቻል ብቻ እንደሆነ ያስባሉ። ወደድርጊቱም ያስገባቸው ይህ እንደሆነ ይናገራሉ።
እንግዳችን የልጅነት ህልማቸው የተማረ መነኩሴ መሆን ነው። በዚህም በጥናታቸው ሳይቀር አገራቸውን ለማገልገል አስበው በዓላማ የሚማሩ ሆነዋል። የተለያየ የትምህርት መስክ መርጠው የመማር ምስጢራቸውም ይህ ነው። ለዚህም በአብነት የሚነሳው ኢትዮጵያዊነትና ቤተክርስቲያን የተዋቀረበትን ስነዘዴ በጥናት አካተው መሥራታቸው ነው። ከጥናቱ ባለፈም በሚያስተምሩበትም ሆነ በሚማሩበት ጊዜ ላላወቀ ለማሳወቅ ቁርጠኛ ናቸው። ሆኖ በመገኘት ወደ ተሻለ ጎዳና ለማራመድ እንደሚሰሩም አጫውተውናል። በተለይም ኢትዮጵያውያን የአገር በቀል እውቀታቸውን ይዘው እንዲጓዙ በማድረግ ዙሪያ የተማሩ አባቶች ብዙ ኃላፊነት ስላለባቸው ይህንን ለማድረግ ዝግጁ እንደሆኑም አውግተውናል።
የሕይወት ፍልስፍና
የሚወሩ ነገሮች መረጃ ሊኖራቸው ይገባል፤ ማረጋገጫም መነሻችን መሆን አለበት ብለው የሚያምኑ ናቸው። በማይመለከተን ነገር መግባትና መፈትፈትም ትክክል አይደለም ብለው ያስባሉም። በዚህም ከሰዎች ጋር በመንገድ ዳር ቆሞ ማውራት ደስ አያሰኛቸውም። ለዚህ ምክንያታቸው መንገድ የተፈጠረው ለመሄጃ እንጂ ለማውሪያና ለመዝናኛ አይደለም ብለው ስለሚያስቡ ነው።
ሌላው ፍልስፍናቸው ጊዜ ከወርቅ በላይ ነው ብለው ማመናቸው ነው። ይህ ደግሞ ለንባብ የሚሰጡት ቦታና ሰዓት ከፍ እንዲል አድርጎላቸዋል። እንደውም ቴሌቪዥን ጭምር ቤታቸው እንደሌለ ይናገራሉ። ምክንያታቸውም በማያስፈልጉ ነገሮች ጊዜያቸውን ማጥፋት ስለማይፈልጉ ነው። መረጃ ከሆነ ከሚያነቡትና በየቀኑ ከትክክለኛው መገናኛ ብዙኃን ከሚያዩት ነገር ይረዳሉ። ከዚያ ባለፈ ዋና አገልግሎታቸውም ሆነ መንፈሳዊነታቸው የሚፈቅድላቸውን በገዳማት የመቆየት ሁኔታን በመጠቀም ራሳቸውን እንዲያዩም ይሆናሉ። ይህ ነውም የሕይወት መርሔ ይላሉ።
ገጠመኝ
ብዙ የማይረሱ ገጠመኞች አሏቸው። ይሁን እንጂ በልጅነታቸው የገጠማቸውን ያህል የትኛውም አይሆንም። ምክንያቱም ዛሬ ድረስ የማይረሱትን ትዝታ ፈጥሮላቸዋል። ነገሩ ምንድነው ካላችሁ ከአትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ ጋር የሆነው ነው። እርሱ ለልምምድ በሚሮጥበት ጊዜ እነርሱ እየተከተሉ በድንጋይ ያባርሩት ነበር። ያ ደግሞ ሳያስቡት ለእነርሱ ጭምር ጠንካራ ሯጭና ተራማጅ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ። ምክንያቱም እርሱ የሚሮጥባቸው ቦታዎች ከፍተኛ ተራራ ያለባቸውና የማይመቹ ቦታዎች ናቸው። እናም ለዛሬው ጥንካሬያቸው የትናንቱ የኃይሌ ሩጫ ዋጋ እንዳለው አጫውተውናል።
መልዕክተ አባ ጌዲዮን
አውሮፓውያን ኢትዮጵያን በእጅ አዙር የያዙበት ምክንያት የተበላሸና አገራዊ ያልሆነ ሥርዓትን በአገሪቱ ውስጥ በሂደት ማምጣታቸው ነው። ለዚህም ማሳያው በ1835 ዓ.ም ለእንግሊዝ ፓርላማ የቀረበው ዶክመንት ሲሆን፤ ዶክመንቱ የኢትዮጵያን አገር በቀል እውቀትን የያዘ ሥርዓተ ትምህርት በእነርሱ ሥርዓተ ትምህርት መተካትን ያትታል። ኢትዮጵያውያን በጉልበትም ሆነ በራስ መተማመን ማንም እንደማይሸረሽራቸው ገና ድሮ ተረድተዋል። ጠንካራ እምነትና ባህልን የያዘ እሴት ባለቤት በመሆናቸውም እስካሁን ቅኝ አልተገዙም ብለው ያምናሉ። በዚህም መሸርሸሪያቸው ከሚሳኤልና ቦንብ ይልቅ የትምህርት ሥርዓቱን አድርገዋል። እንግሊዘኛ አንደኛ የሚለውም ከዚህ የመነጨ ነው። ስለሆነም እንደኢትዮጵያዊነት ይህንን አስቦ መሥራት ላይ ትልቅ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የመጀመሪያው መልዕክታቸው ነው።
በአገራችን ከፍተኛ የፍልስፍና ትምህርትቤት የቅኔ ቤት እንደሆነ የሚያነሱት አባ ጌዲዮን፤ ቅኔ 500 አይነት የፍልስፍና ትምህርት ቤቶች ነበሩት። እየተሸረሸሩና የሚማርባቸው ሲጠፋ 115 ደረሱ። አሁን ደግሞ ከ15 አይበልጡም ያሉት። ከዚህ ትይዩ የሥነ ከዋክብትና ሥነመለኮት ጉዳይም እንዲሁ ትምህርቱ ጭምር እየቆመ ነው። ለዚህ ደግሞ መሰረቱ የእኛን ትተን ሌሎችን ማስቀደምና ማድነቃችን ነው። ስለሆነም ቅድሚያ ለእኛ ማለትን አሁን መጀመር ይኖርብናል ሌላው ምክራቸው ነው።
ኢትዮጵያውያን ብዙ ነገሮችን አገናዝበው የሚናገሩ ነበሩ። አሁን ግን በመሰለኝ የሚናገሯቸው ነገሮች ተበራክተዋል። ለዚህም ተጠያቂው ተማሪው ኮርጆ የሚያልፍበት ሥርዓት መኖሩ ነው። ይህ ደግሞ ኢንጅነሩ የሚሰነጠቅ ህንጻ፣ ዳኝነቱ በጉቦ እንዲፈጸም እያደረገው ይገኛል። እናም ልብ ያለው ልብ ብሎ ትምህርትን ለአገርም ለራስም መለወጫ ማድረግ ላይ መስራት ያስፈልጋልም ብለዋል።
በዓለም ላይ ከ6ሺህ በላይ ቋንቋዎች ቢኖሩም ያን ያህል የሰው ዘር ግን የለም። ቋንቋ ተቀድቶ ወይም ተፈጥሮ የመጣ ነው። ቋንቋ በየጊዜው የሚወለድ፣ የሚያድግና መናገር ስናቆመው የሚሞትም ነው። ከዚህ አንጻር ቋንቋ ከሰውነት በኋላ እንጂ በፊት የሚመጣ አይደለም። ነገር ግን አሁን በአለንበት ወቅታዊ ሁኔታ ከሰውነት ይልቅ ቋንቋ ቀድሟል። በዚህም ሰው በማይመለከተው ሁሉ እየገባ የሥላሴን ፍጥረት ያጠፋል፤ ሰብሎችንና እንስሳትን ይፈጃል። ስለሆነም አሁን ልብ ካልገዛን በስተቀር ይህንን የማናልፍበት ላይ ሆነናል። ስለዚህም ሁሉም ሰው ከሁለት ፍልስፍና አይወጣምና አንዱን ተከትሎ ከሰውነት ይልቅ ቋንቋን ማስቀደሙን አሁን ይተወው። በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ለእምነት ቅድሚያ የሚሰጡ አካላት ይህ አይመጥናቸውምና የአዳምና ሕይዋን ልጅነታቸውን ሊያስቀድሙ ይገባልም መልዕክታቸው ነው።
የዘመኑ መደማመጥ የተሸረሸረበት መናገር ግን የጎለበተበት ጊዜን ለማከም ወቅቱ አሁን ነው የሚሉት አባ ጌዲዮን፤ መደማመጥ ያለውን ዋጋ ለማሳየት ንግግሮችን በጥልቀት መመርመር ያስፈልጋል። ይህንን ማድረግና ማሰብ ስንችል ታሪክ መቀየር እንችላለን፤ መግባባትም እንችላለን፤ ራሳችንን ብቻ ሳይሆን አገራችንን እናተርፋለንና ኢትዮጵያውያን ይህ መርሐችን ይሁን ሲሉም መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ። ከሰው ይልቅ እየተኮላተፍን ለምንናገረው ቋንቋ ካደላን ግን መቼም አንግባባም፣ አንሻገርምም። ስለዚህም ዓላማ ተኮር የሕይወት እንቅስቃሴን ልንመርጥና ልንኖረው ይገባል። ሳኖረን የምንዝናና እንዳንሆን በልጠን መዝናናትን በማሰብ ጊዜያችንን መጠቀም አሁናዊ ተግባራችን መሆን አለበት የመጨረሻው መልዕክታቸው ነው።
ጽጌረዳ ጫንያለው
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2014 ዓ.ም