የአሸባሪው ህወሓት የጭካኔና የአረመኔነት ጥግ ላለፉት 30 አመታት እልፍ አእላፍ ጊዜ የተጻፈ ዘጋቢ ፊልም የተሰራለት ህልቆ መሳፍርት በሌላቸው የጥቃቱ ሰለባዎቹ የተነገረ ቢሆንም ባልተለመደ ሁኔታ ተዛብቶ ተጠቅሶ አሜሪካንን ሳይቀር መግለጫ እንድታወጣ እንዳስገደደው የሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት አጥንትን መገጣጠሚያንና መቅኔን ሰርስሮ እንዲገባ አድርጎ የገለጸው የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። በህወሓት የጡት አባቶች ዘንድ ባልተለመደ ሁኔታ አቧራ ያስነሳውም የዲያቆን ንግግር ዘልቆ ነርቫቸውን ስለነካው እንጂ በናዚና በጀርመን በፋሽስትና በጣሊያን ሕዝብ መካከል ልዩነት እንዳለ ሁሉ በአሸባሪው ህወሓትና በትግራዋይ መካከል ልዩነት መኖሩ ጠፍቷቸው አይደለም።
ከተለያዩ ሚዲያዎች አመራሮች ጋር በመሆን በዚያ ሰሞን በጀግናው መከላከያ ሰራዊት የአካባቢ ሚሊሽያ የአማራና የክልል ልዩ ኃይሎች ከሽብር ኃይሉ ወረራ ነጻ የወጡ አካባቢዎችንና ግንባሮችን ተዘዋውረው ከጎበኙ በኋላ አዲስ አበባ ሲመለሱ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ “ህወሓት መልካም የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ለማጥፋት የተነሳ ኃይል ነው። ኢትዮጵያን ለማጥፋት የተነሳውም ከመልካም ነገሮች አንዷ ስለሆነች ነው። ቢሆንለት በአለም ላይ ያለን መልካም ነገር ሁሉ ከማጥፋት አይመለስም። ለሰው ልጅ ህልውና አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ነው የሚያጠፋው። እስካሁን አሸባሪ ሰውን ብቻ ነው የሚረሽነው። ህወሓት ግን ሰውን እንስሳትንና እፅዋትን እረሽኗል።
ይህ በሌሎች ሀገራት የአሸባሪዎች ታሪክ ያልተፈጸመና ያልታየ ነው። ጭና መቄት እፅዋትን ከብቶችን ዶሮዎች ሳይቀሩ ረሽኗል። ቢሆንለት ኢትዮጵያን ምስራቅ አፍሪካን አለምን ከማጥፋት አይመለስም። አለም ያልተረዳው አንዱ ነገር ይህን ነው። ይህ ሀይል ተራ ተቃዋሚ ቡድን አይደለም። መልካም የሆኑ ነገሮችን ሁሉ ለማጥፋት የተነሳ እንጂ። ነሐሴ 13 የድብረታቦር ዕለት የተኮሰው መድፍ አላማ እኮ ለበዓሉ የተሰበሰቡ ሰዎችን መፍጀት ነው።
በዚህ በዓል ከምዕመኑ ከካህናቱ ከዲያቆናት መካከል እኮ የትግራይ ተወላጆች አሉ። ለእሱ ሁሉም ቢያልቁ ጉዳዩ አይደለም። ጭና ላይ ሲደመሰስ ከኋላ የነበረው አዋጊ እያዋጋቸው የነበሩትን ሳይነግር ነው ጥሎ የሸሸው። ሰው ቢያልቅ ቢኖር ባይኖር ምንም አይመስለውም። መንገድ ላይ ያየነው ያ ሁሉ የወጣት ሬሳ አያሳዝነውም። ምነው የትግራይ እናቶች፣ የትግራይ አባቶች ማየት በቻሉ። ልጆቻቸውን ምን እያደረጋቸው እንዳለ። አይራራላቸውም እኮ። ለእነዚያ ወጣቶች የማይራራ ህሌናን እንዴት አድርገን ነው የምንረዳው። በጤናማ አእምሮ እሱን ለመረዳት መሞከር በጣም አስቸጋሪ ነው።
በጉዟችን ስድስት ተቋማትን ሲያጠፋ ተመልክተናል። አንደኛ የመንግስት ተቋማትን አውድሟል። እንግዲህ አገር ልመራ ነው ያለ ሀይል እኮ መንግስታዊ ተቋማትን አያጠፋም።አላማው ስልጣን ቢሆን ኑሮ እነዚህ ተቋማት ያስፈልጉት ነበር። አላማው እሱ አይደለም።
ሁለተኛ የሃይማኖት ተቋማትን ያጠፋል።ወሎ አፋር መስጊዶችን መዳረሻዎችን አፍርሷል። አብያተ ክርስቲያናትን ያፈርሳል። ካህናትን ከቅዳሴ ሲወጡ ገድሏል። የስልጣን ትግል ውጊያ አይደለም እያደረገ ያለው። አላማው ጥፋት ነው።
ሶስተኛ ግላዊ ተቋማትን አፍርሷል። ዳባት ላይ የገበሬውን ደሳሳ ጎጆዎች ሳይቀር በከባድ መሳሪያ አፍርሷል። ቤታቸው ገብቶ ጋን ምጣድ ድስት ይሰብራል። ከዚህ ምንድን ነው የሚያገኘው። በየደረሰበት የግል የተባለውን ነገር ሁሉ አውድሟል ዘርፏል። ይህ ቡድን እርዮተ አለሙ ምንድን ነው። አራተኛው ይህ ቡድን ማህበራዊ ተቋማትን አውድሟል። ትምህርት ቤቶችን ሆስፒታሎችን ጤና ኬላዎችን የእንስሳት ክሊኒኮችን አውድሟል። እድሮችን አፍርሷል። ዘርፏል።አምስተኛ ቤተሰባዊ ተቋማትን ያፈርሳል።ስድስተኛ ስነ ልቦናዊ ተቋማትን ያፈርሳል።
ቤቱን በልተው ጠጥተውበት አስበስለውበት መጨረሻ ላይ ያበሏቸውን ገደሉበት።የሞቱ ጓደኞቻቸውን አምጥተው ቀበሩበት። በኢትዮጵያዊ ሞራል ይሄን እንዴት እንረዳው። እዚያ አካባቢ የሚወለዱ ወጣቶች እንዴት አድርገው ይረዱታል። የገዛ አዋጊዎቻቸውን አንገት ቆርጠዋል እኮ። ጭካኔዋን እንዴት ነው የቻሉበት።ይሄ ቡድን ይሄን የክፋት አቅም ከየት አገኘው።ምንጩ ከየት ነው። ከዚህ በኋላ ስነ ምግባር የሚባለውን ነገር እንዴት ነው ማስተማር የሚችለው። እንዴት ነው ህጻናትን በመድፈር ሽማግሌዎችን በመግደል። ሆስፒታል ከተኙ ሰዎች ጉሉኮስ ነቅሎ ወስዷል።
የአካል ጉዳተኞችን ሰው ሰራሽ እግር ነቅሎ ወስዷል። በምን የቅስም/የሞራል/ልዕልና ነው መተንተን የሚቻለው። ይሄ ለሰው ልጅ የኑሮ መስተጋብር በጣም አስቸጋሪ ነው። ይሄ ቡድን መጥፋት ያለበት ለሁሉም የሰው ልጆች ሲባል ነው። ለትግራይ ሕዝብ ሲባል አሸባሪ ህወሓት መጥፋት አለበት። ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ሲባል መጥፋት አለበት። ለአለም ሕዝብ ሲባል መጥፋት አለበት።
መቼም ችግር ከአንዲት ቡድንና ከአንድ ሰው ነው የሚነሳው። ከዚያ በኋላ ነው አለምን የሚያዳርሰው።ይህ ቡድን ዝም ብለን ከፈቀድንለት አለምን ከማጥፋት አይመለስም። ሰናይ መልካም የተባለውን በሙሉ ነው ያጠፋው። ይህን ሲያደርግ መጀመሪያ ክፋትን ጽፎ ሰነድ አዘጋጅቶ አስቀምጦ ነው። ድንገት ክስተት አይደለም። አንዳንድ ሰዎች ድንገት ክስተት ይመስላቸዋል። በስምንት ወሩ ዘመቻ ወይም ከስልጣን በመውረዱ ተበሳጭቶ ወይም ተገቢውን ስልጣን አላገኘሁም ብሎ አይደለም።የስነ ልቦና ባለሙያዎችን ብንጠይቅ ድንገት እንዲህ ያለ ጥፋት አይፈጸምም። ክፋትን ጽፏል። አሰልጥኗል። በዚህ በጻፈው ክፋት ሰዎችን አሰልጥኖበታል። ክፋትን ባህሪው አድርጎታል። ጠባዩ እሱነቱ አድርጎታል። ጭና መቄትና ደቡብ ጎንደር ያደረገው ይሄን ነው። እንዲህ አድርጎ ብሎ አሰልጥኖ መመሪያ ሰጥቶ ነው ያሰማራው።”
ከዚህ ንግግሩ በተለይ”…የስነ ልቦና ባለሙያዎችን ብንጠይቅ ድንገት እንዲህ ያለ ጥፋት አይፈጸምም። ክፋትን ጽፏል። አሰልጥኗል። በዚህ በጻፈው ክፋት ሰዎችን አሰልጥኖበታል። ክፋትን ባህሪው አድርጎታል። ጠባዩ እሱነቱ አድርጎታል። ጭና መቄትና ደቡብ ጎንደር ያደረገው ይሄን ነው። እንዲህ አድርጉ ብሎ አሰልጥኖ መመሪያ ሰጥቶ ነው ያሰማራው።” የሚለው ሀሳብ በሚገርም ሁኔታ በአውሽዊትዝ ሁለት ጊዜ ተጉዞ በተአምር ከሞት ከተረፈው ከስነ አዕምሮና የፍልስፍና ዶክተሩ ቪክቶር ፍራንክል ሀሳብ ጋር ከመመሳሰሉ ባሻገር ዲያቆን ዳንኤል የስነ ልቦና ባለሙያ ብንጠይቅ ላለውም መልስ የሚሰጥና በመጨረሻ ዲያቆን ስለ አሸባሪው ህወሓት የሰጠው ድምዳሜም ትክክል መሆኑን ያረጋግጥልናል።
ነገሩ እንዲህ ነው አዶልፍ ሒትለር 6ሚሊዮን አይሁዶችን ፖላንድ በሚገኘው አውሽዊትዝና በሌሎች ማሰቃያና ማጎሪያ ካምፖች ለመስማት በሚሰቀጥጥና ለማየት በሚዘገንን ጭካኔ ሲፈጅ በግብታዊነት ተነስቶ ሳይሆን ሆን ብሎ ጽፎ አሰልጥኖ አቅዶና ተዘጋጅቶ ነው። ርዕዮተ አለሙን ጀርመኖች የተመረጡ የአርያም ዘሮች ናቸው። ለጀርመን ሽንፈት ኋላቀርነትና ደካማነት ተጠያቂዎች አይሁዶች ናቸው በሚል የተሳሳተ መነሻና መደምደሚያ ቀምሮ ለጥፋት ሲነሳ ዩኒቨርሲቲዎችና ሳይንቲስቶች ግንባር ቀደም የእኩይ አላማው ተዋናይና አራማጅ ነበሩ።
የጅምላ መጨፍጨፊያ የመርዝ አዳራሾች/ ጋዝ ቻምበርሰ/ና ሌሎች ማሰቃያዎች የእነሱ የፈጠራ ውጤቶች ነበሩ። በእነዚህ የመርዝ አዳራሾች በየቀኑ 12ሺህ አይሁዶች በግፍ ይፈጁ ነበር። ከ70 አመት በኋላም ዛሬ ድረስ ትውልድም ሆነ ታሪክም ይቅር ባላለው ዘግናኝ ግፍ የጀርመን ልሒቃን ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከላት ሚና የጎላ ነበር ይለናል ዶ/ር ፍራንክል። የሰው ልጅ ጋዝ ቻምበሩን የፈጠረ፤ በዛው ቻምበር ሲፈጅም የፈጣሪውን ምህረት ይለማመን የነበረ ወለፈንዲ ፍጡር ነው ይላል።
የስድስት ሚሊዮን አይሁዶችን ጭፍጨፋ በፊት አውራሪነት የመራው ፣ ያቀነባበረው በጭካኔው ፣ በአውሬነቱ ወደር ያልተገኘለትን የሞት መልዕክ Angel of Death የሚል ቅፅል የተሰጠውን ዶ/ር ጆሴፍ ሚንጌል መሆኑ የዘመኑ ልሒቃን በሀሊኮስቱ የነበራቸውን እኩይ ሚና ያረጋግጣል። እዚህ ላይ የትግራዋይን ልሒቃን ያስታውሷል። እነ ጌታቸውን ደብረጺዎንን ክንደያን አሉላን ሳሊኒን ወዘተረፈ ያንሰላስሏል።ኢትዮጵያዊውን ጆሴፍ ሚንጌል ጌታቸው አሰፋ ልብ ይሏል።
ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ ጥቃት እና የጥቅምት 30ን የማይካድራን፤ ከዚያ የጋሊኮማን የአጋምሳን የጭናንና የሌሎችን ትውልድና ታሪክ ይቅር የማይላቸውን የክፍለ ዘመኑን ታላላቅ ክህደቶችንና ጭፍጨፋዎችን ለመፈጸም ዝግጅቱንና ልምምዱን መጻፍ ማሰልጠንና መሰነድ የጀመረው ከደደቢት ውልደቱ ከየካቲት 11 ቀን 1967 ዓ.ም አንስቶ ነው። ለግማሽ ክፍለ ዘመን በዝግ የተዶለተበት የክህደት ደባ እና የጭካኔ ልምምድና ዝግጅት ውጤት ነው።
በ1968 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ማንፌስቶው አማራንና የኦርቶዶክስ ተዋህዶን በጠላትነት የፈረጀ ሲሆን ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላም አንዱን ጠባብ ሌላውን ትምክህተኛ እንዲሁም ሽብርተኛ እያለ ልዩነትን ጥላቻንና ጎሰኝነትን በጀት መድቦ መዋቅራዊና ተቋማዊ አድርጎ ሲጎነቁል ኖሯል። በሕዝባዊ አመጽና በለውጥ ኃይሎች የተናበበና የተቀናጀ ትግል ለ27 አመታት በበላይነት ይዞት ከነበረ አገዛዝ ገለል ሲደረግ በማኩረፍ በመማጸኛ ከተማው መቐሌ በመመሸግ ጭካኔንና አረመኔነትን ጽፎ በዚያ መሠረት አሰልጥኖና አሰማርቶ በሰሜን ዕዝ ላይ የክፍለ ዘመኑን ክህደትና ጭፍጨፋ ፈጽሟል።
ከሀዲው ትህነግ ከደርግ ጋር እየተዋጋ ለሰሞነኛው ጦርነት ይዘጋጅ ነበር። ዝግጅቱ ተደጋግሞ እንደተገለጸው የሶስት አመት ከመንፈቅ ብቻ አይደለም የ47 አመታት እንጂ። ከሀገሪቱ ሕዝብ አምስት በመቶውን ብቻ ወክሎ ሕዳጣን ሆኖ ሕዝብን እየከፋፈለና እያለያየ ፤ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ቀጥቅጦ እየገዛ ፤ እየዘረፈ ፤ በገዛ እጁ ጠላት እየቀፈቀፈ፤ ወዘተረፈ ዘላለም ስልጣን ላይ መቆየት ስለማይችል ፤ በዚህም ሕዝባዊ ተቃውሞ ሊነሳበት እንደሚችል ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ሁል ጊዜም ለጦርነት ዝግጁ ነው። የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት ተጠቅሞ በቅርብ ሊቆጣጠረውና አንድ ቀን ሊጠቀምበት ወይም ሊክደው የሚችለውን ሰሜን ዕዝ አደራጀ። ኤርትራ ትወረኛለች ብሎ ካሰብ በአሰብ መስመር አፋር የሚገኘውን የቡሬ ግንባር ለምን እንደ ሰሜን ዕዝ አላደራጀውም። መልሱ ቀላል ነው ኤርትራ እንደማትወረው ግጥም አርጎ ያውቃል።
ለዚህ ነው ሰሜን ዕዝን ለዚህ ክህደት ማስፈጸሚያነት ሲገነባው የኖረው። አበክሮ ኢኮኖሚውን በመቆጣጠር እንደ ኤፈርት ያለ ግዙፍ ኩባንያ በዘርፉ የገነባው ፤ የስነ ልቦና ዝግጅት ሲያደርግ የኖረው ይህ ቀን እንደሚመጣ ስለሚያውቅ ነው። በነገራችን ላይ በሕዝባዊ አመፅና በለውጥ ኃይሉ በኢፍትሐዊነትና አላግባብ ከያዘው ስልጣን ያለምንም ማንገራገር ጓዙን ጠቅልሎ መማፀኛ ከተማው መቐሌ የገባው ተመልሶ ስልጣን ላይ እንደሚወጣ እርግጠኛ ስለነበር እንጂ እስከመጨረሻው ህቅታው መፈራገጡ መላላጡ አይቀርም ነበር።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና በሀቀኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !
አሜን ።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2014 ዓ.ም