አንድን አገር በዓለም የፖለቲካ መድረክ ላይ የተሻለች የሚያስብላት ዋነኛ ጉዳይ ለዓለም አቀፍ ህግጋትና መርህ መገዛቷ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳም አገራት በውጪ ፖሊሲዎቻቸው እንደየአገራቱ ፍላጎትና የዕድገት ደረጃ ቢለያይም በመርህ ደረጃ አንድ ሆነው ይሰራሉ፡፡ ከምንም በላይ ህግጋቱንና መርሁን ሲያከብሩ የሞራልና የሰብአዊነት ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነም ያምናሉ፡፡
ህግና መርሁ ሲወጣ አገራት እኩል ናቸው ከሚል አስተሳሰብ በመነሳት ነው፡፡ ሁሉንም በእኩልነት የሚያስተናግድ፣ ለዓለም አቀፍ ሰላምና መረጋጋት የሚፈጥርና ከሁሉም በላይ የሰው ልጆች ህልውናን የሚያስቀድም ተደርጎ ወጥቷል፡፡ ይህ እውነታ በተለይ ለምዕራባውያኑ የሚሰራው ብሔራዊ ጥቅም እስካልተነካ ድረስ ብቻ ነው፡፡
አገራት በኢኮኖሚ ፣ በወታደራዊና በፖለቲካው መስክ ያላቸው አቅም ከፍ ያለ ከሆነ ለጥቅማቸው ሲሉ ድሃ አገራትን በፈለጋቸው መልኩ ማዘዝና ህግን መጣስ ይችላሉ፡ ፡ በተለይም እንደ አሜሪካ ያሉ አገራት በተሳሳተ አመለካከት ጭምር ቢጓዙ የሚጠይቃቸው ማንም የለም፡፡ አቅማቸውን መሰረት በማድረግ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ሳይቀር ይገባሉ፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉ ያሉትም ይህንኑ ነው፡፡
የ ጆ ባይደን አስተዳደር በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሀገሪቱ የራስዋን ችግር በራስዋ እንዳትፈታ ተግዳሮት ሆኗል ። በዚህም ህዝቦቿን ላልተገባ መከራና ስቃይ ዳርጓል ። ከመቶ ዓመት በላይ የተሻገረውን የአገራቱን የዲፕሎማሲ ግንኙነትም አቆርፍዷል ፡፡
የባይደን አስተዳደር በኢትዮጵያ ላይ እያደረሰ ያለው ጫና ዓለም አቀፍ ህግጋቱን የጣሰ ብቻ ሳይሆን ምን ታመጣላችሁ የሚልም መንፈስ የያዘ ነው። ይህ ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ የሰየመውን ቡድን አሸባሪ ብለው እንዳይጠሩት ከማድረጉም በላይ በድብቅ እስከመደገፍ እንዲደርሱ ወኔ ሰጥቷቸዋል፡፡ ዛሬም ቢሆን ከጎንህ ነን እንደሚሉት ብዙ ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
ለዚህም አሸባሪውን ቡድን በመንግስት ከፍ ያለ ጥቃት ሲደርስበት ለቡድኑ ነፍስ ለመዝራት የሚፈጥሩት ጫና ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው ። ቡድኑ አገሪቱን የሁከትና የግጭት ማዕከል ለማድረግ በአራቱም የሀገሪቱ ክፍሎች ለአፈንጋጭ ሀይሎች ስልጠና እና የሎጀስቲክ አቅርቦቶች በስፋት ሲያቀርብ በዚህም ብዙ ንጹሀን ዜጎች ለሞትና ለስደት ሲዳርግ እንዳላየ መሆናቸው ሌላው ማሳያ ነው ።
ከዚህ አልፎም የሀገር ሉዓላዊነት መገለጫ በሆነው የመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መሰንዘሩንና አሁንም በአፋርና በአማራ ክልሎች በመስፋፋት ንጹሀንን ሲገድልና ሲያፈናቅል ዝም ማለታቸውና አለማውገዛቸው የዚሁ እውነታ አካል ነው ፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ሀገርን ህዝብን ከየትኛውም ጥቃት የመታደግ ሀላፊነቱን ለመወጣት ሲንቀሳቀስ በመንግሥት ላይ በተደራጃ መልኩ መዝመታቸው፤ የዘር ማጥፋት፣ የሰብዓዊ ጥሰት፣ የጦር ወንጀል ወዘተ እያሉ መክሰሳቸው ሌላው ለአሸባሪው ቡድን ያላቸውን አጋርነት የሚገልጹበት መንገድ ከሆነም ውሎ አድሯል፡፡
መንግሥት የህግ ማስከበር ዘመቻውን በስኬት ጨርሶ ለሰብዓዊነት ድጋፍ ቅድሚያ በመስጠት ሰራዊቱን ከክልሉ ሲያስወጣ፤ የሞተውን ቡድን አክመውና አብልተው ዳግም ጥቃት እንዲፈጽም ማበረታታቸው ሌላው ከጎኑ መሆኑን ያሳዩበት ነው ፡፡ ከሁሉም በላይ ግን ይህ ሁሉ እውነት በተጨባጭ አደባባይ በሞላበት ሁኔታ ውስጥ በሀገር ላይ ማዕቀብ እንጥላለን እያሉ የማስፈራራታቸው ነገር በእጅጉ ትዝብት ውስጥ የሚከታቸው ነው፡፡ የአሸባሪው ደጋፊዎች መሆናቸውንም በግልጽ ያሳብቅባቸዋል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሰሚነት ያለው፤ ከዛም በላይ ራሱን የዓለም የሰብዓዊ መብትና ዴሞክራሲ አስከባሪ ፖሊስ ነኝ የሚለው ይህ አካል በዚህ ደረጃ በተዛባ መንገድ፤ ፍትሀዊነት በጎደለውና ለአንድ ቡድን ለዛውም በሰራቸው ግፎች በህዝብ አመጽ ከስልጣን ለተወገደ ሀይል ወግኖ መቆም ፍላጎቱ ሌላ እንደሆነ በግልጽ መመልከት ይቻላል፡፡
በተለይም ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ደጋፊ የሆኑ ምዕራባውያንን ጭምር ያነጋገረው ሰባት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች መባረር በቂ ምክንያት እንዳለው እየታወቀ ለያዥ ለገላጋይ በማይጨበጥ መልኩ ሁንታውን አለም አቀፍ ፖለቲካ ለማድረግ የሄዱበት መንገድ አሳፋሪ ከመሆኑም በላይ ገበናቸውን አደባባ ያወጣ ነው ።
ሰራተኞቹ በተጨባጭ ከአለም አቀፉ ድርጅት መተዳደሪያ ደንብና መርህ ውጪ ሲንቀሳቀሱ ተገኝተዋል ፤ ለአሸባሪው ህወሓት በግልጽ ደግፈዋል ተብሎ በመንግስት ማረጋገጫ ቀርቦ እያለ መረጃዎችን ከማጣራት ይልቅ ውሳኔው አስደንጋጭ ነው ፤ መደረግ የለበትም ወዘተ ሲሉ እየተደመጡ ነው ፡፡
በእርግጥ ኢትዮጵያ ሉአላዊት ሀገር በመሆኗ እስከዛሬ ሌሎቹ እንዳደረጉት ሳታሳውቅ ማባረር ትችል ነበር፡፡ ሆኖም ይህንን እንዳላደረገችና በተደጋጋሚ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ለሰራተኞቹ ብቻ ሳይሆን ለድርጅታቸው መልዕክት ልካለች ፡፡ ከችግሩ በስተጀርባ ስላሉ እውነታውን መቀበል ከብዷቸዋል ። እንደ ሩስያ፣ ቻይና፣ ህንድና ቬትናም የመሳሰሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን አጋሮች ድምጻቸውን ከፍ አድርገው የማሰማታቸው ሁኔታም እውነታውን ከመረዳት የመነጨ ነው ፡፡
ክስተቱ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሀላፊዎች በማያስደነግጠው የሚደነግጡ እንደሆነ በግልጽ አሳይቷል ፡፡ መደንገጥ ቢኖርባቸው ሊደነግጡ የሚገባው ድጋፍ ጭነው ትግራይ የሄዱ መኪኖች አለመመለሳቸው ሲነገር፣ ለህዝቡ እንዲደርስና ለህጻናት እንዲውል ወደክልሉ በእርዳታ የገቡ ኃይል ሰጪ ምግቦች አሸባሪው ቡድን ሲጠቀምባቸው፣ አሸባሪው ቡድን ንጹሐንን ሲፈጅና ሲያፈናቅል ነበር፡፡
ምዕራባውያኑ አሸባሪውን የሚደግፉበት አንድምታ የተለያየ እንደሆነ ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች መረዳት ይቻላል፡፡ ዋናው ግን ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር በሚያደርጉት ግብግብ የሚፈጽሙት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ሁለት መንገዶችን አዋጭ አድርገው ይጠቀሙባቸዋል፡፡ የመጀመሪያው መንግስትን ጫና ውስጥ መክተትና ተላላኪ መንግስት መፍጠር ሲሆን፤ ሁለተኛው አሸባሪው ህወሓትን በመደገፍ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማንበርከክ ነው። ይህ ስራቸው ደግሞ አሁንም ድረስ እንደቀጠለ በብዙ መልኩ ይታያል፡፡
በእነርሱ ያልተገባ ጥቅም ፍለጋ እየተካሄዱት ባለው ጣልቃ ገብነት ንፁሃንን ብቻ ሳይሆን እንስሳትንና ሰብሎችን ሳይቀር የገፈቱ ቀማሽ ሆነዋል ፡፡ በየቀኑ ሰላም እያሉ እንዲዘምሩና ጎዳና እንዲወጡ የሆኑ ዜጎችም ተፈጥረዋል፡፡ በዚህም ህዝባችን ጠላቱ ማን እንደሆነ እየተረዳ መጥቷል።
በተለይም ከአሸባሪው ህወሓት በስተጀርባ ያሉ ሀይሎች ስለኢትዮጵያ ምን እንደሚያስቡ ለመረዳት እድል ፈጥሮላቸዋል ፡፡ የእነርሱ ጫና ለኢትዮጵያ ጥንካሬ እንደሆነም በተጨባጭ ማየት ችለዋል ፡፡
አሜሪካ እንደ ሀገር አንድም ጊዜ ከአሸባሪ ድርጅት ጋር ተደራድራ እንደማታውቅ ብዙ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡ ፡ በቅርቡ እንኳን የሆነውን ብናነሳ በሀገሪቱ ላይ የሽብር ድርጊት የፈጸመው ቢንላደን በአሜሪካ ላይ ላደረሰው ጥፋት ድርድር ሳይሆን ሞት ፈርደውበት ያንኑ ፈጽመዋል ፡፡
ችግሩ /የሽብር ጥቃቱ/ በኢትዮጵያ ላይ ሲደርስ ግን ነገሮች መልካቸውን ቀይረው ስለ ሰባዊነት አዲስ ነጠላ ዘፈን እንድትለቅ ሆናለች ፡፡ ከአሸባሪ ጋር ተደራደሩ የሚል ዋና ዜማ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ይህ የሚያሳየው ደግሞ አሸባሪነትና የአሸባሪ ጥቃት ከአሜሪካን ብሄራዊ ጥቅም አንጻር ብዙ ገጽታ ያላቸው መሆኑ ነው ፡፡
የአሜሪካ እና ተከታዮቿ ጫናና የእጅ አዙር ጦርነት የአሸባሪው ህወሓትን የባንዳነት ተልዕኮ በማስፈፀም ያልተገባ ብሔራዊ ጥቅማቸውን ማስጠበቅ ነው ፡፡ በእጅ አዙር ኢትዮጵያውያንን ለዓመታት ሲከፋፍሉ፣ ሲያጣሉና ሲያጋድሉ የቆዩት ይህንኑ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ እንደነበር የአደባባይ ሚስጥር ነው ፡፡
አሜሪካ ከዛሬ 40 አመታት በፊት አሸባሪ ያሉትን ቡድን ዛሬ ላይ የሚደግፉበት ለነሱ ተላላኪ የሆነ መንግስት ለመመስረት ቢሆንም ፣ ኢትዮጵያውያን ግን ከአሰቡት ውጪ ሆነዋል፡፡ የራሳችንን ዕድል በራሳችን በምርጫቸው ወስነዋል፡፡ ይህ ደግሞ ፍም እሳት ስለሆነባቸው ላለመረታት አገሪቱን በተላላኪያቸው በኩል በመበጥበጥ ላይ ይገኛሉ፡፡
ቡድኑ ያደረሰውን ግፍና በደል በዓለም ተገልጦ እንዳይታይና እንዳይጠየቅ የሚሸፍኑትም ለዚህ ነው፡፡ እርሱ ጠፋ ማለት በምስራቅ አፍሪካ ያላቸውን ጥቅም ማስቀጠል አይችሉም፤ ያበቃላቸዋልም፡፡ ስለሆነም የቡድኑን ህልውና የእነርሱ ህልውና ጉዳይ አድርገው እንዲንቀሳቀሱ ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት እየሄደበት ያለው የፅናት መንገድ ያኔ አፍሪካውያን ከምዕራባውያን ቅኝ አገዛዝ ነፃ እንዲወጡ ያደረገችውን እንቅስቃሴ የሚያስታውስና አፍሪካን ከተኛችበት በዘላቂነት የሚያነቃት እንደሆነ ብዙዎች ይረዱታል ፡፡ ይህም በምእራቡ አለም መደናገጥ ፈጥሯል ፡፡
ከዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ በአሸባሪው ቡድን ላይ እርምጃ መውሰድ ስትጀምር ሀይላቸውን አሰባስበው በቻሉት ሁሉ ሊያሸማቅቋት ይጥራሉ፡፡ በተቃራኒው የሽብር ቡድኑ ንጹሃንን ሲጨፈጭፍ ደግሞ ዝም ታን ይመርጣሉ፡፡
ይሁን እንጂ ሁሉም ሊገነዘቡ የሚገባው ኢትዮጵያ ዛሬም ለሰላም ያላት ቁርጠኝነት ከማንም በላይ ነው። በዚያው ልክ ሰላሟን ለማደፍረስ የሚጥሩ ሃይሎችን ፈጽሞ አትታገስም። በውጭም ሆነ በውስጥ ጠላቶች ጊዜያዊ ጩኸትም አትደናገጥም፡፡
ማንም እንደፈለገ እንዲማይጠመዝዛት ደግሞ ጣሊያኖች ምስክር ናቸው፡፡ ‹‹ማን ይናገር የነበረ ማን ያርዳ የቀበረ›› እንደሚባለው ምዕራባውያኑን ከጣልያን ተማሩ ማለት እፈልጋለሁ፡፡ ሰላም!
መንበረ ልዑል
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2014 ዓ.ም