አፍሪካ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ እና ለሰው ልጆች ምቹ የአየር ፀባይ ያለው አህጉር ነው። ከዚህም ባሻገር ከ1 ነጥብ3 ቢሊዮን በላይ በአብዛኛውም ወጣት የሆነ የሰው ኃይል አለው። እነዚህ ሁሉ ሲደማመሩ አፍሪካን በተፈጥሮ ለሰው ልጅ ምቹ የሆነ አህጉር እንዲሆን አድርጎታል።
ይሁን እንጂ እንደአለመታደል ሆኖ አፍሪካና አፍሪካውያን ስማቸው በበጎ ሲነሳ አይታይም። ገና የሰው ልጅ ዘመናዊ የአኗኗር ዘይቤን መከተል ከጀመረባቸው እና ወደ ዕድገት የሚያደርገውን ጉዞ ባጧጧፈበት የኢንዱስትሪ አብዮት ዋዜማ ቀድመው የስልጣኔን በር ማንኳኳት በጀመሩት አውሮፓውያን ዓይን ውስጥ ገባ። ከዚያም የበለፀገውን የዚህን አህጉር የተፈጥሮ ሀብት አይተው የቋመጡት ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን ለመቀራመት ተነሱ። ከኢትዮጵያ በስተቀር ሁሉንም ተቀራመቱም።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የተነሳው የአፍሪካ የጭለማ ጉዞ ለብዙ ዓመታት ተሻግሮ ዛሬም ድረስ ዱካው አብዛኞቹን የአፍሪካ ሀገራት ሲከተል ይኖራል። እስከ 21ኛው ክፍለዘመን ድረስ የአፍሪካውያን የድህነት እና የእርስ በእርስ ጦርነት መንስኤ ይኸው የቅኝ ግዛት ዘመን ሴራና ደባ እንደሆነ ዘልቋል። በዘመኑ በርካታ ቅኝ ገዢዎች አፍሪካን በኃይል ለዘላለም ማስተዳደር ከባድ መሆኑን ሲረዱ ቢያንስ በእጅ አዙር ለመግዛት ይቻላቸው ዘንድ በኢኮኖሚ ለማዳከም የሚቻልበትን መንገድ በመቀየስ ለብዙዎቹ የቤት ሥራ ጥለው ሄዱ። ከነዚህ የቤት ሥራዎች ውስጥ አንዱ በዘመኑ የተደረጉ የድንበር ስምምነቶች እንዲሁም የብሔር ልዩነትን መሰረት ያደረጉ የልዩነት ትርክቶች ይጠቀሳሉ።
ከነዚህ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ደግሞ እንደአፍሪካ ቀንድ ደባ የደረሰበት አካባቢ አለ ማለት አይቻልም። ለዚህም ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ይነሳሉ። አንደኛ የዚህ አካባቢ መልክአምድራዊ አቀማመጥ ስትራቴጂካዊ መሆኑ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ በዚሁ ክፍል የምትገኘው የአፍሪካውያን የነፃነት ተምሳሌት የሆነች “ኢትዮጵያ” የምትባል ሀገር ለሌሎች አፍሪካውያንም የአልገዛም ባይነት አርአያ መሆኗ ናቸው።
በዚህ ሴራ የተነሳ የአፍሪካ ቀንድ የድህነት፤ የኋላቀርነት እና የጦርነት ቀጣና በመሆን በዓለም ላይ ስማቸው ከፊት ከሚመጡ ሀገራት ግንባር ቀደም መሆን ችሏል። አካባቢው እንዳይለማ በሚደረጉ ጫናዎች እና የአካባቢው ሀገራት እርስ በእርሳቸው እንዳይተማመኑና በድንበር ጉዳይ እንዲናቆሩ፣ ብሎም ሕዝቦቻቸው በብሔርና በማንነት ጥያቄዎች እርስ በእርሳቸው ተከፋፍለው ነፍጥ እንዲያነሱ የሚያነሳሱ ትርክቶችን በመስጠት ለዘመናት የእርስ በእርስ ግጭት ማዕከል እንዲሆን ተደርጓል።
በዚህ መሰረት በኢትዮጵያና በኤርትራ የነበረው ግጭት የደቡብ ሱዳን ለነጻነት የእርስ በእርስ ጦርነት ከዚህም ባሻገር ሶማሊያውያን እርስ በእርሳቸው እንዲከፋፈሉና አንድ ማዕከላዊ መንግሥት እንዳይኖራው በተሰራባቸው ውጫዊ ደባ ለብዙ ዓመታት በእርስ በእርስ ግጭት ዋጋ ከፍለዋል።
በሌላም በኩል አንዱ ሀገር ከሌላው ጋር ተስማምቶ እንደጎረቤት በጋራ ከመኖር ይልቅ መተማመን እንዳይኖር በርካታ ሴራዎች ተፈጽመዋል፤ ከነዚህም ውስጥ ኢትዮጵያና ኤርትራ ለ20 ዓመታት የቅርብ ሩቅ ሆነው እንዲኖሩ ተደርገዋል፤ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን በተባበሩት መንግሥታት የሚመራ ኃይል በመካከላቸው እንዲቆም ተደርጓል፤ ሶማሊያ የአሸባሪዎች መፈንጫ እንድትሆን በመደረጉ የሰላም አስከባሪ ኃይል የሚጠብቃት ሀገር ሆናለች። አሁን ደግሞ በሶማሊያና በኬንያ መካከል አለመተማመን እንዳይኖር እየተሰራ ነው፤ ሱዳን የኢትዮጵያን ድንበር አልፋ በመያዝ ዳግም አካባቢው የጦርነት ቀጣና እንዲሆን ለማድረግ እየጣረች ነው። ከዚህም አልፎ በውስጧ ያለው ሰላም አሁንም አንድ ቀን ሊፈነዳ የሚችል እሳተ ገሞራ እንደሆነ ይገኛል።
ከዚህም አልፎ አፍሪካ እና አፍሪካውያን ወደብልጽግና ጉዞ ማድረግ ሲጀምሩ ከጎናቸው በሚነሳባቸው ጠላት ዳግም ወደጦርነት ቀጣና ሲገቡና መልሰው ወደኋላ ሲንሸራተቱ ይስተዋላል። ለዚህም አንዱ ማሳያ ኢትዮጵያ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያየችው ፈተና ይጠቀሳል። በነዚህ ጊዜያት ኢትዮጵያ የጀመረችው የብልፅግና ጉዞ እንዳይሳካ ብዙ ተግዳሮት ተጋርጦባት ቆይቷል። ለዚህ ደግሞ የታላቁ ህዳሴ ግድብን ለማደናቀፍ ከጸጥታው ምክር ቤት ጀምሮ ሱዳንና ግብጽ እንዲሁም የዓለም የሰላም ዘብ ነኝ የምትለው አሜሪካ ምን ያህል እንደተረባረቡ ይታወቃል። ከዚህም ባሻገር ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ የማይወዳትን ሀገር የመራው ህወሓትም እንዲሁ ወደጦርነት ገብቶ የፈጠረው ሁከት እና ይህንን ቡድን በመደገፍ የተደረጉ የምዕራባውያንና አጫፋሪዎቻቸው ጫና ምን ያህል የዚህን አህጉር በተለይ የኢትዮጵያን ሰላምና መረጋጋት እንደነሳ የሚያሳይ ነው። በቅርቡ ደግሞ አሜሪካ ለአፍሪካ የሰጠችውን ነፃ የንግድ ቀጠናን እዘጋለሁ የሚለው ማስፈራሪያና ዛቻ እነዚህ ሀገራት ኢትዮጵያን ለማዳከም ምን ያህል እየሰሩ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
ያም ሆኖ ከነዚህ ችግሮች ለመውጣት ኢትዮጵያም ሆነች አፍሪካ ያላቸው አንድ አማራጭ በትብብር መስራት ብቻ ሆኗል። በተለይ በምዕራባውያን የሚደረግባቸውን ጫና በመቋቋም ለሕዝቦቻቸው ነፃነትና እድገት ለመስራት ቆርጠው የተነሱት የአፍሪካ መሪዎች ኃይላቸውን በማሰባሰብ እና ችግሮቻቸውን በጋራ ለመፍታት የጀመሩትን አጀንዳ 2063ን ማጠናከርና ከምዕራባውያን የእጅ አዙር ቅኝ ግዛት መውጣት ይ ጠበቅባቸዋል። 39ኛው የአፍሪካ የሥራ አስፈጻሚዎች ምክርቤት ስብሰባ ባካሄደው ስብሰባ የተወያየባቸውን ጉዳዮች አጠናክሮ በመሄድ በቀጣይ በመሪዎች ደረጃ በሚደረገው የጋራ ጉባኤ ላይ የጋራ አቋም በመያዝ አህጉራቸውን ከጭለማ ሊያወጡ ይገባል!
አዲስ ዘመን ጥቅምት 7 ቀን 2014 ዓ.ም